Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹ኢትዮጵያ ላንድ ኦፍ ኦሪጂንስ››

‹‹ኢትዮጵያ ላንድ ኦፍ ኦሪጂንስ››

ቀን:

ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የተከናወነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተሳታፊዎች ከያዟቸው ማድመቂያዎች አንዱ፣ አዲሱ የኢትዮጵያ ቱሪዝም መለያ (ብራንድ) ‹‹ኢትዮጵያ ላንድ ኦፍ ኦሪጂንስ›› ነበር፡፡ እሑድ ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ውድድሩ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቀጥታ ሲተላለፍ ካስተላለፉት ጋዜጠኞች ጋር፣ የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ባለወርቋ መሠረት ደፋርና ስለሺ ስህንም ተባባሪ ሆነዋል፡፡ (ፎቶ በናሆም ተስፋዬ)

*************

እግዜር

      ኖሬያለሁ እስከ ዛሬ ስለፋ

‹‹ሊያልፍ ነው ያለፋኝ›› በሚል ተስፋ

ግና ዛሬ አንተ ፈጣሪ ልቤን ስለገባው እፋ ጥርጣሪ

ዕጣ ፈንታችንን ስትለይ ስትወስን

የአዳምን ለአዳም የሄዋንን ለሄዋን

ለፍጥረት በሞላ ያኔ ስትፅፍልን

‹‹ጥረህ ግረህ ብላ!!››

ያልከውን በሙሉ ሳሰላ

ጥረህ … ጥረህ … ጥረህ …

ግረህ … ግረህ … ግረህ …

ብላ ለማለት የረሳኸን

እኔ እንዲያ ነው የመሰለኝ

ባክህ እግዜር መልስ ስጠኝ

  • ታሪኩ ከበደ ‹‹ምክረ ሰይጣን›› (2008)

***********

‹‹ድንኳ ፕላኔት››

‹‹ዓለም ዘጠኝ›› የሚለው ብሂል የመጣው ከዘጠኙ ፕላኔቶች ጋር ተያይዞ እንደሆነ የሚገምቱ አሉ፡፡ በፀሐይ ዙርያ የሚሽከረከሩት ፕላኔቶች በቅደም ተከተላቸው ሲዘረዘሩ መነሻቸው ሜርኩሪ ሆና መድረሻው ፕሉቶ ነው፡፡ ሁሉም በተመሳሳይ ዘመን የተገኙም አይደሉም፡፡ በቅድመ ታሪክ ከተገኙት ስድስቱ የመጀመሪያ ፕላኔቶች በኋላ፣ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሦስቱ ዑራኑስ፣ ኔፕትዮንና ፕሉቶ ተገኝተዋል፡፡ የመጨረሻው ፕላኔት ፕሉቶን በተመለከተ በየዘመኑ የተለያዩ ግኝቶች መውጣታቸውም አልቀረም፡፡ ዶቼ ቬሌ በድረ ገጹ በቅርቡ እንደዘገበው፣ ፕሉቶ ለአቅመ ፕላኔት እንደማትበቃ ነው ያመለተው፡፡

 እንደ ሥነ ፈለክ እና ጠፈር ተመራማሪዎች ከሆነ ፕሉቶ ከፀሐይ 5.9 ቢሊዮን ኪሎ ሜትር ትርቃለች። እ.ኤ.አ. በ1930 ዓመት መገኘቷ ይፋ ከተደረገ ወዲህ መጠኗ ብዙ ሲያጨቃጭቅ ቆይቷል። ፕሉቶ ‹‹ፕላኔት ናት›› አልያስ ‹‹ድንክ ፕላኔት›› ሲሉም ሳይንቲስቱ ሞግተዋል። እ.ኤ.አ. በ2006 ዓለም አቀፉ ሥነ ፈለክ ኅብረት ፕሉቶን ‹‹ድንክ ፕላኔት›› ብሎ ሲሰይም ሦስት መስፈርቶችን በመዘርዘር ነበር።

ዶቼቬል ያነጋገራቸው በደቡብ አፍሪካ የኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር ጌትነት እንደገለጹት፣ «አንደኛው መስፈርት ፕላኔቷ በፀሐይ ዙሪያ መሽከርከር አለባት፣ ሁለተኛ የራሷ የሆነ ጠንከር ያለ ስበት ያስፈልጋታል፤ ሦስተኛ በዙሪያው በቅርብ የሚሽከረከሩ ነገሮች መኖር የለባቸውም፡፡» ሁለቱን መስፈርቶች የምታሟላው ፕሉቶ ሦስተኛውን መስፈርት ስለማታሟላ ከ10 ዓመት በፊት ፕሉቶ «ፕላኔት መሆኗ ቀርቶ ድንክ ፕላኔት መሆን አለባት ብለው ወሰኑ» ሲሉም አክለዋል። 

የድንኳ ፕላኔት ፕሉቶ  ከርሥ ለሕይወት አመቺ በሆነ የበረዶ ቅይጥ የውቅያኖስ ውኃ የተሞላ መሆኑን የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያመለክታሉ። አዲስ አድማስ (New horizone) የተሰኘችው ኅዋ ቃኝ መንኲራኲር እፕሉቶ ጥግ ደርሳ ድንኪቱን ፕላኔት እየመረመረች ሲሆን በበረዶ ግግር በተሞላው ከርሰ ምድሯ ፕሉቶ ከምድር የማይተናነስ የበረዶ ቅይጥ የውቅያኖስ ውኃ ሸሽጋ መኖሯን ደርሳበታለች። ቋጥኞች፣ የበረዶ ግግሮች፤ አሁን ደግሞ የበረዶ ቅይጥ ውኃዋ ተደርሶባታል በማለትም ዶቼ ቬሌ ዘግቧል፡፡

***************

‹‹ፉዞ! ፉዞ!››

በሃያ አምስት ዓመት ዕድሜው ሽበት ወሮታል፡፡ ወጣት እንጂ አዛውንት አለመሆኑ ግን ከፊቱ ወዝ ይታወቃል፡፡ አይናገርም፤ አይጋገርም፡፡ ብቻውን መንገድ ለመንገድ ሲንከራተት ይውላል፡፡ ሲደክመው ካገኘው ሻይ ቤት ገብቶ ሻይ ያዛል፡፡ እስኪመጣለት ድረስ ፊቱን በመዳፉ ያሻሸዋል፡፡ ዓይኖቹን በጣቶቹ ጫፍ ጫን ጫን ይላቸዋል፤ እንቅልፉ መጥቶ ለመንቃት እንደፈለገ ሁሉ፡፡ በእውነቱ ከሆነ ሁልጊዜም ቢሆን በእንቅልፍ መሰል ሰመመን ውስጥ የሚኖር ይመስላል፡፡ ዓይኖቹ ውጫዊ ነገር የሚያዩ ቢመስሉም ውጫዊ ነገር አያዩም፡፡ ዘወትር የሚመለከቱት ወደ ውስጥ ነው፤ ወደ አእምሮው ውስጥ፤ ወደ ሕሊናው ውስጥ፤ በአጠቃላይ ወደ ሕይወቱ ውስጥ፡፡

በሰው መሐል ቢሆንም እንኳ ዘወትር ብቸኛ ነው፡፡ ሻይ ቤት በሚገባበት ጊዜ አሳላፊው ወይም አሳላፊዋ ሲመጡ ‹‹ሻይ›› ከማለት በስተቀር ሌላ ቃል አይተነፍስም፤ በውስጣዊ ሕይወቱ ሰምጦ ስለሚቀር፡፡

ሻይ ቤት ውስጥ ያገኙትና ከሱ ራቅ ብለው የተቀመጡት ሁለት ሰዎች ስለሱ ያወሩ ጀመር፤ አንድ ቀን፤

‹‹ታውቀው የለም?››

‹‹ማንን?››

‹‹ያን ወጣት አዛውንት…. ወይንስ አዛውንቱ ወጣት ልበለው? ለወሬ የማያመች አሳዛኝ ሰው! አሁን ማን ይሙት በሃያ አምስት ዓመት ዕድሜው ሽበት ያበቀለ ሌላ ሰው ታውቃለህ?››

‹‹ኦ! እሱን ማለትህ ነው! ለመሆኑ ስለሱ የሚወራው እውነት ነው እንዴ?››

‹‹ስለሱኮ ብዙ ነገር ይወራል፡፡ የትኛውን ማለትህ ነው?››

‹‹ከዚህ ያደረሰው የሴት ፍቅር ነው የሚባለው፡፡››

‹‹እውነት ነው እንጂ! እኔኮ ደህና አድርጌ አውቀዋለሁ፡፡ መምህር ነበር፡፡ እንዴት ያለ ደስተኛ ሰው ነበር መሰለህ ሳቂታ… ተጫዋች! በዚያ ላይ ለሴት የማይንበረከክ ኩሩ ወጣት ነበር፡፡ በኋላ ጣለበትና አንዷን ተማሪ ወድዶ ቁጭ! እሷ ደሞ የሰይጣን ቁራጭ ነች…. ክልፍልፍ፡፡ አልፈልግህም አለችው፡፡ የወንድ ልጅ ኩራቱን ሰበረችበት፡፡ ከዚያ ወዲያ ሰው ለመሆን አልቻለም፡፡ እምቢ አልፈልግህም ስትለው የዓለም ፍጻሜ የደረሰ መሰለው፡፡››

‹‹ደካማ ሰው መሆን አለበት!››

‹‹እንዴት?››

‹‹አንዲት ሴት ልጅ አልፈልግህም ብትለው ሌላ ሴት ልጅ አይፈልግም ኖሯል? እንዴት የዓለም ፍጻሜ የደረሰ ይመስለዋል? በጣም ደካማ ሰው መሆን አለበት፡፡››

‹‹ኧረ አይጣል በል! ከጣለኮ ይኸው ነው! ፉዞ ሆኖ መቅረት!››

‹‹ፉዞ! ፉዞ!››

ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም ‹‹ሽኩቻ›› (1987)

*************

 

ከሰማያዊው ‹‹ግመል›› ገበታ

ድሮ ድሮ በሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ ጠቃሚ መረጃና ግንዛቤን የሚያስጨብጡ ማሳሰቢያዎችም በብዛት ይገኙ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡-‹‹ባለማጨስዎ እናመሰግናለን!››፣ ‹‹ለመውረድ ሃያ ሜትር ሲቀርዎ ይንገሩ!›› ‹‹ሾፌሩን ማነጋገር ፈጽሞ የተከለከለ ነው!›› ወዘተ!

ዛሬ ዛሬ የጥንቶቹን ዓይነት አዝናኝ ሥዕሎችና ጠቃሚ ማሳሰቢያዎችን የሚያስነብብ መኪና እምብዛም ነው!.. ጥንት የምናውቃቸው አንዳንድ ማሳሰቢያዎች ደግሞ ፌዝ አዘል ይሆኑ ዘንድ በመጠኑ ጠመም ተደርገዋል!…

ለምሳሌ ያህል ድሮ ድሮ ‹‹ሾፌሩን ማነጋገር አጥብቆ የተከለከለ ነው!›› ይል የነበረው ማሳሰቢያ አሁን አሁን በአንዳንድ ሚኒባስ ታክሲዎች ውስጥ ‹‹ሾፌሩን መጥበስ አጥብቆ የተከለከለ ነው!…›› በሚል ቀልድ አዘል ጽሑፍ ተተክቶ ይገኛል!.. ሌላም አለ!… ‹‹ሾፌሩን ለጠበሰ አንድ ባለ 15 ብር የሞባይል ካርድ እንሞላለን!›› የሚል፡፡

  • ብሩክ ወርቁ ቆቴ ‹‹ታክሲ አዲ’ሳባ ሰማያዊው ግመል›› (2006) 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...