Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የግብርና ግብአቶች ግብይትና አሳሳቢው ሸመታ

በእርሻ ወይም ግብርና ላይ የተመሠረተው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወደፊትም የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ ሆኖ ይቀጥላል ተብሎ ይታመናል፡፡ የቱንም ያህል ኢንዱስትሪ ቢስፋፋ የግብርና ምርቱ የአገሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው የሚባልበት በርካታ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፣ በተለይ አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ከግብርና ጋር ያለውን ትስስር ልብ ይሏል፡፡ ከዚህ አንፃር ከየትኛውም ዘርፍ በተለየ ይህ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ያሻል፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት ከተፈለገም የግብርናው ዘርፍ መዘመን የበለጠ ምርታማ መሆንን ይጠይቃል፡፡ በአጭሩ ያለግብርና ዕድገት ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡

ግብርናውን ለማሳደግ ደግሞ ሊተገበሩ ይገባቸዋል ተብለው ከሚታመኑ ቁልፍ ክንውኖች ውስጥ አርሶ አደሩ የተሻለ አምራች እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ የተሻለ አምራች ለመሆን ደግሞ አርሶ አደሩ ዘመናዊ የአመራረት ዘዴን እንዲጠቀም ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ምርቱን ለማሳደግ የሚያስችሉ የግብርና ግብዓቶችን እንዲጠቀም ማበረታታትና ለዚህም እገዛ በማድረግ ዘመናዊ አሠራሮችን ማስረጽና በዘመናዊ መሣሪያዎች ማስታጠቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ አርሶ አደሩን ምርታማነት ለመጨመር በባለሙያዎች ጭምር እንዲታገዙ ማድረግንም ይጠይቃል፡፡ እንደ ማዳበሪያና ፀረ አረምና የሌሎች በሽታ ማጥፊያ መድኃኒቶች አጠቃቀም ቢሆን ከዚሁ ጋር ይያያዛል፡፡ እንደ ቀድሞ በፍግና በሌሎች በባህላዊ ማዳበሪያዎች ብቻ በመጠቀም ምርታማ አይኮንምና ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ የአመራረት ዘዴ ለመተግበር ከተፈለገ የግብርና ግብዓቶች አጠቃቀም ጉልህ ሥፍራ ይኖረዋል፡፡ የባለሙያዎች ያላሰለሰ ጥረት ይጠበቃል፡፡ 

ከዚህ አንፃር የመንግሥት የግብርና ባለሙያዎች አደርሶ አደሩን እየደገፉ ነው ተብሎ ቢታመንም፣ ከተለያዩ የግብርና ግብዓቶች ጋር በተያያዘ ያለው የግብይት ሥርዓት ግን ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው እየሆነ ነው፡፡

ለተለያዩ ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች በተለያየ ደረጃ ለሚያጋጥማቸው በሽታ ወይም በምርት ወቅት የግድ የሚሉ ፀረ አረምና ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ትክክለኛነት በወጉ ቁጥጥር የሚደረግባቸው አይመስልም፡፡ ለዚህም ነው በአገሪቱ ሕግ ያልተመዘገቡ ከግብርና ግብአት ጋር የተያያዙ ‹‹መድኃኒቶች›› ገበያ ላይ የሚታዩት ማለት ይቻላል፡፡

አርሶ አደሩም ቢሆን በትክክል በሰብሉ ላይ ለተከሰተው በሽታ የሚሆን መድኃኒት ሸመታ ላይ ክፍተት ያለበት ስለመሆኑ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በተጨባጭ ያልተፈቀዱ ‹‹መድኃኒቶች›› ገበያው ላይ መኖራቸውና አርሶ አደሩም እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡ ለአትክልትና ፍራፍሬ ይውላሉ ተብለው በሕገወጥ መንገድ ገብተዋል የሚባሉ ፀረ አረም ወይም ለሰብልና ለአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ለሚያጋጥማቸው በሽታ ይሆናሉ የተባሉ መድኃኒቶች ጉዳይ ቁጥጥር የማይደረግባቸው ከሆነ ደግሞ፣ አደጋቸው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡  

ከጥቂት ዓመታት በፊት በቲማቲም አምራችነታቸው በሚታወቁ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረ አንድ በሽታ የቲማቲም ምርቱን በከፍተኛ ደረጃ ማውደሙን እናስታውሳለን፡፡ በወቅቱ በሽታውን ለመከላከል አምራቾች መድኃኒት ነው የተባለን ነገር ሲጠቀሙ ነበር፡፡ ከእነዚህ መድኃኒቶች የበዙት በሕገወጥ መንገድ የገቡና አንዳንዶቹ የመድኃኒት ባህሪ የሌላቸው እንደሆኑም ማስታወስ ይቻላል፡፡ ችግር ነውና ምርቱን ለማዳን ሲባል መፍትሔ የተባለውን ሁሉ የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ግን ገንዘባቸውን አፈሰሱ እንጂ ቲማቲማቸውን ከጥፋት ማዳን አልቻሉም፡፡ መፍትሔ ያገኙት ቆይቶ ነበር፡፡ ያ ወቅት ግን ብዙ ትምህርት ሰጥቶ አልፏል፡፡

ቲማቲሙ እርሻ ላይ በተከሰተው በሽታ ሳቢያ አርሶ አደሩ የተለያዩ ኬሚካሎችንና መድኃኒቶችን ይጠቀም ስለነበር በኬሚካል የጠገበውና ከበሽታ ካመለጠው ውስጥ የቲማቲም ምርት ለገበያ ቀርቦ ሲቸበቸብ ነበር፡፡ ያውም በውድ ዋጋ፡፡ ይህ ለሸማቹ የቀረበው ቲማቲም ይዘት ቢመረመር ጉዳቱ ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ በቻልን ነበር፡፡

ከሰሞኑም በተመሳሳይ ለገበያ ከቀረቡና ከአንዳንድ የምርት ቦታዎች የሚመጣው የቲማቲም ምርት በበሽታ የተመታ ስለመሆኑ ምልክት ይታያል፡፡ የቀድሞ ዓይነት በሽታ በአንዳንድ የቲማቲም አምራች አካባቢዎች በመግባቱ የተፈጠረ መሆኑንም የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ ገበያ ላይ የሚቀርበውን ቲማቲም ልብ ብለን ከተመለከትን በቀላሉ የምናረጋግጥበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ ለበሽታው ማጥፊያ ተስማሚ መድኃኒት አልቀረበም ወይ? የሚለውን ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከበሽታው መከሰት ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ አሁንም እየተጠቀመባቸው ነው የሚባሉ መድኃኒቶች ትክክል ናቸው ወይ? ማለቱ ተገቢ ነው፡፡

ዋናው ጥያቄ የሚመጣውም እዚህ ላይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት በሽታዎች ሲከሰቱ ተስማሚ የሆነ መድኃኒት የቱ እንደሆነ ለይቶ ማቅረቡ ላይ ችግር አለ፡፡

በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ መድኃኒቶች ገበያ ውስጥ ሾልከው መግባታቸው ጉዳይም ችግሩን ለመቅረፍ እንቅፋት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩም የቀነሰ ዋጋ አገኘሁ ብሎ የሚፈጽመው ግብይት ራሱን ሊጎዳ ይችላል፡፡ እየጎዳም ነው፡፡ ችግሩ በአርሶ አደሩ ጉዳት ብቻ የሚያቆም ሳይሆን የምርት ግብዓቶችን በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ውድመት አርሶ አደሩን ብቻ በመደቆስ የሚቆም አይደለም፡፡ በውድመቱ በሚፈጠር የምርት እጥረት ሸማቹ ላይ የሚጫን መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

እንዲያውም በሕጋዊ መንገድ ያልገቡ መንገዶች በርካሽ ሲቸበቸቡም ይታያሉ፡፡ የቸገረው መድኃኒት ነው የተባለውን ይገዛል፡፡ ጉዳቱ ግን ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ቁጥጥር ያሻቸዋል፡፡ ለሰው ልጆች እንደሚገቡ መድኃኒቶች ሁሉ ለግብርናው ግብዓት የሆኑ የመቆጣጠሪያ ስልቱን አገልግሎት ላይ ከመዋላቸውም በፊት አርሶ አደሩ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ በግብርና ባለሙያዎች ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡ ምርቶችን እንዳይጠቀሙ ያልተቋረጠ ግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት እስካልተቻለ ድረስ አደጋው የበለጠ ይሆናልና፡፡ ለግብርና ግብዓት ሆነው የሚሆኑ ማንኛውም ዓይነት ምርቶች ጉዳይ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር አሁን አለ ከሚባለው በላይ ሊሆን ይገባል፡፡ በመስክ ፍተሻም ሕገወጥ መሆናቸው የተረጋገጡ ምርቶችን የማስወገድ አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡   

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት