Wednesday, May 22, 2024

በደቡብ ሱዳን የሪክ ማቻር ተፅዕኖ እያበቃ ይሆን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል በአዲስ አበባ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ከቀናት በፊት ዶ/ር ሪክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ተከልክለው ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት መመለሳቸው ተስፋው ለመበላሸቱ ማሳያ ነው፡፡

ከሱዳን ለመገንጠል ከ20 ዓመታት ያላነሰ ጊዜ የተዋጉት ደቡብ ሱዳናውያን እስካሁን ድረስ ሰላም አላገኙም፡፡ ደቡብ ሱዳን በአፍሪካ ኅብረት አዲሲቷ አገር ተብላ በተመዘገበችበት በአንድ ዓመት ውስጥ የተጀመረው ሁከት፣ ኋላ ላይ ወታደራዊና የብሔር ግጭት እየያዘ ቢመጣም በሁለቱ ቁንጮ ተቀናቃኝ መሪዎች መካከል በተከሰተ አለመግባባት የተጀመረ ነበር፡፡

በነፃይቱ አገር የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና በምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ግን፣ ዛሬም ድረስ አገሪቱን ሰላም ነስቷታል፡፡

በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ኑዌሮች በመወለዳቸው ምክንያት ዶ/ር ማቻር በኢትዮጵያ ይደገፋሉ ለሚለው ወቀሳ ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቡት አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አማካይነት የማስታረቅ ሚናው በገለልተኝነት ሲወጣ መቆየቱን ያምናል፡፡

ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ሥዩም መስፍን፣ ጉዳዩን በልዩ መልዕክተኛነት ይዘውት ላለፉት አራት ዓመታት ዘልቀዋል፡፡ ሁለቱን መሪዎችና ከጀርባቸው ያሉ ወታደራዊና የፖለቲካ ኃይሎችን በገለልተኝነት የማስታረቅ ኃላፊነት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዋናነት ለኢትዮጵያ የተተወ ቢመስልም፣ የኢጋድ አባል የሆኑ ሌሎች ጎረቤት አገሮች በተለይ ኬንያና ኡጋንዳ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሽምግልናው አካል ለመሆን ሞክረዋል፡፡  

የኢጋድ ሸምጋይ ቡድንን በደባልነት የምትመራው ኬንያና እንዲሁም ኡጋንዳ በአብዛኛው ጊዜ ድጋፋቸውን የሚሰጡት ሥልጣን ላይ ላለው ለሳልቫ ኪር መንግሥት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለይ ኡጋንዳ በኢጋድ ዕውቅና ያልተሰጠው ወታደራዊ ኃይል በጁባ ማስፈሯን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከሰላም ሒደቱ ጀርባ ስሙ ገኖ የሚሰማው የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለቱም መሪዎች በሸራተን አዲስ የሰላም ስምምነት እንዲፈርሙ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ላይ ተፅዕኖ ፈጥረዋል የሚሉ አንዳንድ ሪፖርቶች ወጥተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በስምምነቱ መሠረት ከቆዩበት ሌላ አገር ወደ ጁባ የተመለሱት ሪክ ማቻር እምብዛም ሳይቆዩ ባለፈው ሳምንት ከቦሌ ኤርፖርት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተገደው እንደመለሱ መደረጋቸው እያነጋገረ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቅርቡ ጁባ በሄዱበት ወቅት ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር ለመተባበር እንደሚገደዱ፣ በተለይ ዶ/ር ማቻር ከኢትዮጵያ ግዛት ተነስተው ደቡብ ሱዳንን እንዲያጠቁ እንደማይፈቅዱ መናገራቸውን የሱዳን ትሪቡን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ዶ/ር ማቻር በፕሬዚዳንቱ የፀጥታ ኃይሎች ጥቃት እንደደረሰባቸውና በዚሁ ሳቢያ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ለሞት መዳረጋቸውን በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ሊፈጸም የታሰበው የፖለቲካና የጦር ኃይል ውህደትም ውድቅ ሆኗል፡፡

የሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች በቅርቡ በተወካዮቻቸው አማካይነት በአዲስ አበባ ያደረጉት ውይይት መጠነኛ መግባባት ፈጥሯል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬም ድረስ የታሰበው ለውጥ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ማቻርም በድጋሚ ተቃውሞአቸውን ከደቡብ ሱዳን ውጪ በመሆን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊና የፀጥታው ምክር ቤት ይህንን ጥቃት ተከትሎ በድጋሚ የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቆምና ሰላም አስከባሪ ኃይል በአካባቢው እንዲሰማራ ቢወስኑም፣ ተግባራዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ ለችግሩ ተጠያቂ ናቸው የተባሉተ የሁለቱ ጎራ መሪዎች ላይ ሊጣል የታሰበው ማዕቀብና በዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲጠየቁ በአሜሪካ የቀረበው ሐሳብም በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ግን በማቻር ላይ ማዕቀብ መጣል አለበት ብላለች፡፡

የእርስ በርስ ጦርነቱ ተባብሶ ቀጥሏል

የፀጥታው ምክር ቤት በተለይ ሐምሌ ወር በድጋሚ የተቀሰቀሰውን ጦርነት አጣሪ ቡድን በመላክ ያጣራ ቢሆንም፣ አፋጣኝ ዕርምጃ አልወሰደም ተብሎ እየተተቸ ነው፡፡ ማት ዌልስ የተባሉ የአካባቢውን ግጭት የሚከታተሉ ተመራማሪ፣ ‹‹ምክር ቤቱ ሺሕ ነገር ከሚያወራ በቀውሱ ተጠያቂዎች ላይ ማዕቀብ ቢጥል ምን አለበት?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

በድጋሚ የተቀሰቀሰውን ግጭት በማብረድ ሰላምን ወደነበረበት መመለስ ካልተቻለና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ፣ እስከ ዛሬ የተደከመበት የሰላም ሒደትና የሽግግር ፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የሚሠጉ በርካቶች ናቸው፡፡ የዛሬው ቀውስ ሲከሰት እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች አስቀድመው አስጠንቅቀው ነበር፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ከሐምሌ ወር ጀምሮ እየተከናወነ ላለው ቀውስ፣ በአካባቢው የሚገኘው የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይልን ወቅሰዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን ያለው ከጎረቤት አገር የተውጣጣ ይኸው ሰላም አስከባሪ ኃይል በኬንያ ጄኔራል ይመራ የነበረ ሲሆን፣ በጁባና በአካባቢው የተቃጣውን ጥቃት መከላከል አልቻለም በማለት ጄኔራሉን አሰናብተዋል፡፡ የኢትዮጵያን ጨምሮ የጎረቤት አገሮች የተውጣጡበት ሰላም አስከባሪ ኃይል በአግባቡ አልመሩም ተብለው ከቦታቸው ጄነራሏ የተነሱባት ኬንያ ግን፣ አንድ ሺሕ ወታደሮቿን እንደምታስወጣ አስፈራርታ ነበር፡፡ ከመካከላቸው 100 ወታደሮችን በቅርቡ ማስወጣቷም ተሰምቷል፡፡

ተመድ በፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በቅርቡ ወደ ጁባ ለመላክ ዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ሆኖም በቅርቡ በደቡብ ሱዳንና በሱዳን ድንበር አካባቢ በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት የ15 ንፁኃን ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡

ለረዥም ጊዜ የቆዩትና የተመድ ሠራተኞችንና ቁሳቁሶችን የሚጠብቁ የጃፓን ሰላም አስከባሪ ኃይሎች በመውጣታቸው ሳቢያ፣ በሌሎች 4,500 ወታደሮች ከመተካታቸው ውጪ እንደታሰበው አዲሱ ተጠባባቂ ኃይል እስከ ዛሬ አልተሰማራም፡፡ በእርግጥ ሩዋንዳ ጠንካራ የፖሊስ ኃይል ወደ ጁባ በመላክ ላይ ትገኛለች፡፡ የሰላም ዕጦቱን ምን ያህል ያረጋጋል የሚለው ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡   

ዶ/ር ማቻር ሱዳንን ጨምሮ በተለያዩ ጎረቤት አገሮች እየተዘዋወሩ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ኬንያ ወደ አገሯ እንዳይገቡ የሚያስችል ስምምነት እንድትፈራረም አድርገዋል፡፡

ዶ/ር ማቻር በቅርቡ ከደቡብ አፍሪካ ወደ አቡጃ (ናይጄሪያ) በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የገጠማቸው ጉዳይ የሚዲያዎችን ቀልብ ስቧል፡፡ ለዶ/ር ማቻር ታደላለች ተብላ የምትታማውና ብዙ ጊዜ የእሳቸው መቆያ ነበረች የምትባለው አዲስ አበባ አቋሟን ቀይራለች ብለው ብዙዎች እንዲጠራጠሩም ምክንያት ሆኗል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነጋሪ ሌንጮ ግን፣ ጉዳዩ ከፖለቲካ የሚያያዝ እንዳልሆነና ከኢሚግሬሽን ሕግ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ እንደሚሉት ማቻር አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን እንደ ትራንዚት በመጠቀም ላይ ሳሉ የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአቡጃ ቪዛቸው በመሰረዙ ምክንያት፣ ከኤርፖርቱ ወደመጡበት ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውጪ የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ቀደም ሲል ይዞት ከቆየው የገለልተኛ አስታራቂነት ሚና የተለየ አቋም እንደሌለው ዶ/ር ነገሪ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ማቻርም ሆኑ እሳቸው የሚመሩት አማፂ ኃይል ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞ እየተሰማባቸው ቢሆንም፣ የሳልቫ ኪር መንግሥትን ለመጣል ማንኛውንም ዓይነት ጥረት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ገለልተኛ ወገኖች የደቡብ ሱዳን ችግር በተቻለ መጠን ፖለቲካዊ መፍትሔ ካልተገኘለት ለአገሪቱም ሆነ ለአካባቢው ሰላም ጠንቅ ይፈጥራል እያሉ ነው፡፡

 

     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -