ማርቆስ ገነቴ፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር አመራር አባል
የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ የአንድ ዓመት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በዋናነት ከክፍያ ጋር ተያይዞ በአትሌቶችና በማናጀሮች መካከል ሲፈጠር የቆየውን አለመግባባት መፍትሔ በማበጀት የበኩሉን ድርሻ መወጣቱ ይነገርለታል፡፡ ከሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ጀምሮ በቀድሞ አትሌቶች አማካይነት ለፌዴሬሽኑ ሲቀርቡ ለነበሩ ጥያቄዎች ዕውቅና በመስጠት በሕግ አግባብ መልስ የሚያገኙበትን መድረክ በማመቻቸት የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ የቆየ ስለመሆኑ ጭምር የማኅበሩ አመራር ማርቆስ ገነቴ ይናገራል፡፡ በቅርቡ በተከናወነው የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ወቅት ማኅበሩ እንደ ማኅበር ከባድ ፈተና ገጥሞት እንደነበርም ያስረዳል፡፡ ፈተናዎቹ ምን ነበሩ? ችግሮቹን እንዴትና በምን አግባብ ተወጣቸው? በሚሉትና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው አነጋግሮታል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ አትሌቶች ከሩጫው በተጓዳኝ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የአመራርነት ሚና ይኖራቸው ዘንድ ጽኑ አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህን የማኅበሩን አካሄድ የሚጠራጠሩ አትሌቶች ነበሩ፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
ማርቆስ፡- ቀደም ሲል እንደሚታወቀው እንዳሁኑ በማኅበር ደረጃ የተቋቋመ አልነበረም፡፡ ማኅበሩ ከአንድ ዓመት በፊት በአጋጣሚ ሁኔታዎች ተመቻችተው ነው ሊቋቋም የቻለው፡፡ አትሌቱ አሁን ያለውም ሆነ ቀደም ሲል የነበረው አትሌቲክስ ላይ ትልቁን አሻራ ጥሎ ያለፈ እኛና ከእኛ በፊት የነበሩት በከፍተኛ በደል ያለፉ ናቸው፡፡ እንደዚያም ሆኖ በአገሪቱ አትሌቲክስ ላይ ትልቁን አሻራ ጥሎ አልፏል የሚባለው ከእኛ በፊት የነበሩትና የእኛ ትውልዶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህ ትውልድ ነገሮች በነበረው ዓይነት እንዲቀጥሉ ፍላጎት አልነበረንም፡፡ በዚያም ሳያበቃ ስለ ስፖርቱና አትሌቶቹ መብት የሚቆም ማኅበር ተቋቋመ፡፡ ማኅበሩም አትሌቲክሱ የራሴ ነው የሚል አቋም ማራመድ ጀመረ፡፡ አትሌቲክሱ እንደሚታወቀው ለብዙ ዓመታት ሲመራ የቆየው የፌዴራል ሥርዓቱን መነሻ በማድረግ የክልል ውክልና ባላቸው አመራሮች ነበር፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ እንደተጠበቀ፣ ነገር ግን በስፖርቱ ሳያልፉ በስማ በለው ብቻ መሆን እንደማይገባው በተቻለ መጠን ዕውቀቱና አቅሙ ያላቸው ስፖርቱን በሚያውቁ መመራት እንደሚኖርበት በማመን ማኅበሩ አቋም ወስዶ እንዲንቀሳቀስ ምክንያት ሆኖታል፡፡
ሪፖርተር፡- የማኅበሩም ይሁን የሌሎች ታዋቂ አትሌቶች ወደዚህ አቋም መምጣት ግለሰቦች ስለተነኩ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እዚህ ላይ እንደ ማኅበርም ሆነ እንደግል ምን ትላለህ?
ማርቆስ፡- የማይወራ ነገር የለም፡፡ ብዙ ተወርቷል አሁንም እየተወራ ነው፡፡ በእኔ እምነት ሊያሳስበን የሚገባው የስፖርቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ቢሆን ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡ እውነት ነው አቶ ዱቤ ጅሎ ስለተነኩ ነው ተብሎ መወራቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአትሌቲክሱ አልፈው በአመራር ቦታ ላይ የነበሩት እሳቸው ብቻ መሆናቸው ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ቤቱን ተጠግተን ስንመለከተው እንደምናስፈልገው እንደ ማኅበር አቋም ከያዝን ሰነባብተናል፡፡ የማኅበሩ መፈጠር አትሌቱ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህን የማይቀበሉ እንደሚኖሩ ብገምትም የማኅበሩ አስፈላጊነት ግን ለአፍታም ሊያጠራጥረን አይገባም፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ የአትሌቶችን መብት በተመለከተ የሠራው ምንድነው?
ማርቆስ፡- ማኅበሩ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን የያዘውን ቅርፅ ይዞ ሲንቀሳቀስ አዲስና የመጀመርያው ነው፡፡ ከዚህ በፊት ማኅበሩን ለማቋቋም ብዙ ተሞክሮ ሳይሳካ ቆይቷል፡፡ አሁንም እንደ ማኅበር ከተቋቋመ በኋላ እንኳ ሒደቱ እንዲህ ቀላል ነው ተብሎ የሚታይ አይደለም፡፡ በጣም ብዙ ቢሮክራሲዎች ነበሩበት፣ አሉበትም፡፡ እነዚህን ውጣ ውረዶች እስከምንላመድ ድረስ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ አሁንም ሙሉ በሙሉ ነፃ ነን ብለን አናምንም፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ በአሁኑ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የሚመራ የቀድሞ አትሌቶች ስብስብ በፌዴሬሽኑ ላይ ሌላ ጥያቄ ይዘው መነሳታቸው የእኛን እንቅስቃሴ በመጠኑም እንዲጓተት ምክንያት መሆኑ አልቀረም፡፡ በዚህን ጊዜ ማኅበሩ ያለውን ሙሉ አቅም ተጠቅሞ መሄድ እንዳይችል በሁለት አካላት መካከል ማለትም በብሔራዊ ፌዴሬሽኑና በቀድሞ አትሌቶች በሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦች ተጠምዶ እንዲቆይ ተገደደ፡፡ በዚህ ምክንያትም ማኅበሩ የአትሌቶቹን መብትና ጥቅማ ጥቅም በማስከበሩ ረገድ ያሰበውን ያህል እንዲሄድ አላስቻለውም፡፡ እንደዚያም ሆኖ የሠራቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ መካድ አይቻልም፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በሁለቱ አካላት መካካል ሆኖ ምን ለማድረግ ነበር የሚያስበው?
ማርቆስ፡- ነገሮች በተረጋጋ መንገድ እንዲሄዱ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ነበር፡፡ ምክንያቱም በፌዴሬሽኑና በቀድሞ አትሌቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት አትሌቶች ለሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት የሚያደርጉበት ወቅት ስለነበር ነው፡፡ ማኅበሩ ፌደሬሽኑም ሆነ የቀድሞ አትሌቶች ሳይረበሹ ነገሮች መልክ መልክ ይዘው እንዲሄዱ ፍላጎት ስለነበረን ለዚያ የሚሆን ሥራ እንዲሠራ ግድ ብሎት ቆይቷል፡፡
ሪፖርተር፡- በወቅቱ በታላላቅ የቀድሞ አትሌቶች ሲነሱ የነበሩት ጥያቄዎች በማኅበሩ የነበረው ቅቡልነት እስከምን ድረስ ነበር?
ማርቆስ፡- የአትሌቶቹ ጥያቄ የማኅበሩም ጥያቄዎች መሆናቸው አያጠራጥርም፣ እናምንበታለን፡፡ ጥያቄው የቀረበበት ወቅት ግን መታየት እንዳለበትም እናምን ነበር፡፡ ልዩነታችንም እዚህ ላይ ነበር፡፡ በዚህ ሒደት ፌዴሬሽኑ የአትሌቶቹን ጥያቄ መቀበል እንደሚኖርበት፣ አትሌቶችም ጊዜው የዝግጅት መሆኑን አውቀው ጉዳዩን እንዲያለዝቡት የሚል አቋም ይዞ ሲንቀሳቀስ ነበር፣ ተሳክቶልናልም፡፡ የሚገርመው በዚህ ጉዳይ ከቀድሞ አትሌቶች ጋርም ሆነ ከፌዴሬሽኑ ጋር ብዙ ስብሰባዎችን አድርገናል፡፡ ተስማምተን ከወጣን በኋላ ነገሮች እንደገና ወደ አላስፈላጊ ጡዘት የሚሄዱበት አጋጣሚም ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ የሪዮ ኦሊምፒክ በሰላም እንዲጠናቀቅ እንደ ማኅበር ከፍተኛ ጥረት አድርገን ተሳክቶልናል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በፌዴሬሽኑ አመራሮች ጫና ይደረግበት እንደነበር፣ ያም በመሆኑ አንዳንድ አትሌቶች በተለይ በማኅበሩ አመራሮች እምነት እንዳልነበራቸው ሲነገር ተደምጧል፡፡
ማርቆስ፡- ሰዎች የፈለጉትን የማለት መብት አላቸው፡፡ እውነቱ ግን እኔም ሆነ ስለሺ የአትሌቶቹ ጥያቄ በትክክል መልስ እንዲያገኝ እንፈልግ ነበር፡፡ ምክንያቱም የእኛም ጥያቄ ስለሆነ፡፡ ልዩነታችን የጊዜ አጠቃቀም ላይ ብቻ ነበር፡፡ የፌዴሬሽን ጫና ስለሚባለው አልነበረብንም ብዬ መዋሸት አልፈልግም፡፡ ጫናው ግን ከነበረን አቋም ወደ ኋላ እንድናፈገፍግ ግን አላደረግንም፡፡ ነገሮች ጥናት ሳይደረግባቸው የእምቧይ ካብ እንዳይሆኑ ጽኑ እምነት ስለነበረን ተረጋግተን መመልከትን መርጠናል፡፡ እያንዳንዱ ጥያቄ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ እንዲመለስ ሙሉ ፍላጎቱም ነበረን፡፡
ሪፖርተር፡- የፌደሬሽኑስ አቋም?
ማርቆስ፡- ሁሉንም ነገር በጊዜውና በወቅቱ መልስ እንደሚሰጡ ነበር የሚነግሩን፡፡ በማኅበሩ በኩል ደግሞ በተቻለ መጠን ጊዜው እንዳይርቅ የሚል የፀና እምነት ነበረን፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ነገሩ በምንፈልገው መንገድ ሄዶልናል፣ ሳናመሰግናቸው አናልፍም፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ የአትሌቶቹን ተጠቃሚነት በተመለከተ ሠርቸዋለሁ የሚለው ምንድነው?
ማርቆስ፡- ነገሮች አሁን ላይ ሆኖ ለሚመለከት ቀላል ይመስላሉ፡፡ እውነቱን ለመናገር ከሆነ የነበረው ጫና ለማኅበሩ ሳይቀር በጣም ከባድ ነበር፡፡ በዚህ በኩል ሰዎች የፈለጉትን ቢሉም የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ስለሺ ስሕን የከፈለው መስዕዋትነት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ማኅበሩ ፌዴሬሽኑ ለሚያደርገው የአመራር ምርጫ ክልሎች ታዋቂ አትሌቶችን ዕጩ አድርገው እንዲያቀርቡ በቡድንና በተናጠል ብዙ ጥረት ሲያደርግ ነበር፡፡ ይህንኑ አንዳንዶቹ ሲቀበሉን አንዳንዶቹ ደግሞ ጭራሽ የእኛን ሐሳብ ለመቀበል ቀርቶ ጊዜ ሰጥተው ለማናገር እንኳን ፍላጎት ያልነበራቸው ገጥመውናል፡፡ ወደ ክልሎች የምንልካቸው ደብዳቤዎች በወቅቱና በጊዜው መልስ ሳያገኙ ሲቀር እንደገና ከሁለትና ሦስት ጊዜ በላይ የምንጻጻፍበት ጊዜ ሁሉ ነበር፡፡ እንደዛም ሆኖ ፈተናው ከባድ ነበር፡፡ አንወክልም ብለው እስከመጨረሻው በአቋማቸው የጸኑ ክልሎች ነበሩ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በምንፈልገው መጠን ባይሆንም ከውክልናና ምርጫ ጋር ያለው ጉዳይ ተሳክቶልናል ብለን ነው የምንወስደው፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ያህል አትሌቶችን ለማስመረጥ አስባችሁ ነበር?
ማርቆስ፡- ቢያንስ ግማሽ ያህሉን የአመራርነት ቦታ መያዝ እንፈልግ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትልቅ ተቋም ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዕውቀትም ሆነ በልምድ ትልቅ የሆኑ አመራሮች ያስፈልጋል፡፡ ተቋሙ ሙሉ ለሙሉ በአትሌቶች ይመራ ቢባል ያስኬዳል?
ማርቆስ፡- ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም አቅሙም ብቃቱም አለን ብለን ነው የምናምነው፡፡ ሆኖም ጥያቄው የመጀመርያ እንደመሆኑ ቢያንስ ግማሽ ያህሉን ኃላፊነት ማግኘትን እንጠብቅ ነበር፡፡ አሁን ባገኘነው ውክልናም ቢሆን የሚያስከፋ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ድምፅ እንዲቀነስ የሚል ነገር ገጥሟችሁ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ እውነት ነው?
ማርቆስ፡- ትክክል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ማኅበሩ ያለው ሁለት ድምፅ ነው፡፡ በመሀል አገልግሎቱን ያጠናቀቀው ሥራ አስፈጻሚው ድምፅ መስጠት የለበትም በሚል ችግሮች ተፈጥረው ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ እንደምንስማማ ተነጋግረን ችግሩ ሊፈታ በመቻሉ ዝርዝር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ከዚህ ባለፈ ለጉባዔው በአጀንዳነት እንዲያዝልን ማለትም አትሌቶች በአትሌቲክሱ ከአመራርነት ጀምሮ በየደረጃው ድርሻ እንዲኖራቸው የጠየቅናቸው ነበሩ፡፡ አጀንዳችን ውድቅ ተደርጎብናል፡፡ ለጉባኤውም ጠይቀን አጥጋቢ መልስ አልተሰጠንም፡፡ ችግሩ ምን እንደሆነ ባይገባኝም ጥያቄውን ይፈሩት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሒደቱ በጣም በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ማኅበሩ በድምፅ ብልጫ ተስማምቶ ያፀደቀውን ውሳኔ እንኳ ሳይቀር ለክርክር የቀረበበት ሁኔታ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከችግሩ ጎን ለጎን አትሌቶቹን ለማስመረጥ ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዳላደረገ የሚናገሩ ነበሩ?
ማርቆስ፡- ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ለፕሬዚዳንትነት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ለሥራ አስፈጻሚነት ደግሞ ኦሮሚያ ገዛኸኝ አበራ፣ ትግራይ ገብረ እግዚአብሔር ገብረማርያምን እንዲያቀርቡልን ብዙ ቦታ ደርሰናል፡፡ ይኼ ቅስቀሳ አይደለም ከተባለ ሊገባኝ አይችልም፡፡ የተወከሉት አትሌቶችም የበኩላቸውን እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ እልህ የተላበሰ ሒደት ነበር፡፡ እንደ ማኅበር በምርጫው ቀን ሳይቀር የመጨረሻውን ውጤት እስከምንሰማ ድረስ እምነት አልነበረንም፡፡ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ከየአቅጣጫው ስድብና ትችት ይደርስብን ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ተማራችሁ?
ማርቆስ፡- በግሌ በጣም ብዙ ነገር ተምሬበታለሁ፡፡ ምክንያቱም በሙያዬና ስፖርቱን ልርዳ የሚልን አካል አይመለከትህም ሊባል ያስገርመኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለምርጫ ያቀረባቸው አትሌቶች ቁጥር ምንም እንኳ እንዳሰበው ባይሆንም አዲስ አበባን ወክሎ የቀረበው ኃይሌ የተቋሙን ዋናውን የኃላፊነት ድርሻ አግኝቷል፡፡ ምን እንጠብቅ?
ማርቆስ፡- ማናችንም እንደምናውቀው አትሌቲክሱ ታሟል፡፡ የታመመን ነገር ለማዳንና ትክክለኛውን መድኃኒት ለማግኘት ትክክለኛውን ሐኪም ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ይህን በሕመም ውስጥ የሚገኘውን አትሌቲክስ ስፖርት ለማከም ብዙ ትግልና ሥራ ይጠይቃል፡፡ ሳይሰለቹ ጊዜ ወስዶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ተደርጓል፡፡ ሁሉንም ነገር የተመረጠው አካል ኃላፊነት ነው ብለን መቀመጥ የለብንም፡፡ የአትሌቶች ማኅበር በጣም ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቅበታል፡፡ በጣም ብዙ የተበለሻሹ ነገሮች አሉ፡፡ ችግሮቹን ተጋግዘንና ተነጋግረን ካልሆነ ለአንድ አካል ብቻ በመወርወር መፍታት አይቻልም፡፡ በርካታ አትሌቶች የየራሳቸው ጥያቄዎች አሏቸው፡፡ ሁሉንም በአግባቡና በሕጉ መሠረት መልስ እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ፌዴሬሽኑ አይደለም ማኅበሩ ራሱ የአትሌቶችን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ መልስ ሰጥቻለሁ ብሎ አያምንም፡፡ ገና ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ አትሌቶች እንዳለፉት ዓመታት መጎዳት የለባቸውም፡፡ ወደ ሥራ አስፈጻሚው ስንመጣ ደግሞ አሁን እንደ ድሮው በምክንያት ማለፍ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከኃይሌ ጀምሮ በስፖርቱ ያሳለፉ በመሆኑ ይቅርታ በስህተት ነው ተብሎ የሚታለፍ አንድም ነገር አይኖርም፡፡ ስለሆነም ብዙ ነገር ይጠበቅብናል፡፡ ሁላችንም አትሌቶች፣ አሠልጣኞች፣ ማናጀሮችና አመራሩ ተናበን መሥራት የግድ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አትሌቶች በልፋታቸው መጠን ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የሚናገሩ አሉ?
ማርቆስ፡- በጣም እስማማለሁ፡፡ ለዚህም እኮ ነው ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል የምለው፡፡ በአትሌቶችና በአትሌት ማናጀሮች መካከል የነበረው የጥቅም ግጭት በተወሰነ መልኩ እልባት ያገኘበት ሁኔታ አለ፡፡ ማኅበሩ በዚህ በኩል መሥራት ያለበትን ያህል ሠርቷል እየሠራም ይገኛል፡፡ በማናጀሮች እጅ የነበረ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የአትሌቶች ገንዘብ ክፍያ እንዲፈጸም አድርጓል፡፡ በሒደት ላይ ያሉ ነገሮችም አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- አትሌቶች በዋናነት ከሚታሙባቸው ነገሮች የአካዴሚክ ዕውቀታቸው ነው፡፡ እንዴት ታየዋለህ?
ማርቆስ፡- ያለ ዕውቀት ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ሆኖም እዚህ አገር ዕውቀት ተብሎ የሚነገረው ለምንና እንዴት የሚለው ተለይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ አንድ ሰው ዶክተር ከሆነ አትሌቲክሱን እንደሚመራ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እኛም በስፖርቱ ያሳለፍንበት የቆየንበት፣ ሀብትና ንብረት ያፈራንበት ዘርፍ እንደመሆኑ ይከብደናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ዕውቀት አያስፈልግም እያልኩኝ እንዳልሆነ ሊወሰድልኝ ይገባል፡፡ ሌላው ዕውቀት ያለ ቦታው ደግሞ ትልቅ የሀብት (ሪሶርስ) ብክነት እንዳይሆንም ሥጋት አለኝ፡፡ አትሌቶቻችን ከሩጫው ጎን ለጎን የአካዴሚክ ክህሎታቸውን ለማጎልበት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ሌላው አትሌቲክስ ቤታችን ነው ብለን እንገምታለን፡፡ አንድ ሰው ቤቱን ለማፍረስ፤ አይነሳም በመሆኑም በዚህ ረገድ እኛም የምንችለውን አድርገን የማንችለውን ደግሞ ለሚችለው አሳልፈን ክፍተቶቻችንን ለመድፈን ዝግጁ ነን፡፡
ሪፖርተር፡- ከፌዴሬሽኑ አደረጃጀት ጋር ተያይዞ ምን አስተያየት አለህ?
ማርቆስ፡- መታደስ እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በተቋሙ ውስጥ የሚያስፈልጉም የማያስፈልጉም ሰዎች አሉ፡፡ የይስሙላ ሳይሆን እውነተኛው ቢፒአር ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይኼ ከሆነ ብቻ ነው ተቋሙንና ስፖርቱን ማሳደግ የሚቻለው፡፡