Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየከሸፉ ጋብቾች

የከሸፉ ጋብቾች

ቀን:

የተዋወቁት ተከራይታ በምትኖርበት ሰፈር የሚኖሩ ዘመዶቹ ጋር ሲመላለስ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ትውውቃቸው ውስጧ ብዙ ባይቀበለውም፣ የበለጠ እያወቀችው ስትመጣ ግብረገብነቱና ለእሷ ያለው ክብር እንድትወደው አደረጋት፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው መተማመንና ፍቅርም የጠነከረ ሆነ፡፡

በተዋወቁ በወራት ዕድሜ ውስጥም እንደሚያገባት ቃል ገባለት፡፡ ጓደኞቿ ነገሮች መፍጠናቸውን ፣ ለውሳኔ ከመፍጠኗ በፊት ረጋ ብላ ማሰብ እንዳለባት ለሄለን (ስሟ ተቀይሯል) ቢነግሯትም በጄ አላለችም፡፡ በእሱ ጠንካራ እምነትና ተጋብተው እንደሚኖሩ ተስፋ ስለነበራት፣ አባቷ ሲቀሩ ሌሎቹን የቤተሰቧ አባላት በሙሉ ከጓደኛዋ ጋራ አስተዋውቃለች፡፡

 በመስከረም ወር ለመጋባት ማቀዳቸውንና ሽማግሌ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኑን ለቤተሰቦቿ አሳወቀች፡፡ ሽማግሌ ለመላክ ቀናት ሲቀሩ ግን ጓደኛዋ ያልተለመዱ ባህሪያት ማሳየት ጀመረ፣ በኋላም ተጣላት፡፡ የተጣሉበት ምክንያት ቀላል ስለነበር ተመልሶ ይመጣል የሚል እምነት ቢኖራትም፣ ዝር ሳይል ቀረና ነገሮች ባልተጠበቀ ሁኔታ መቀየራቸውን ትናገራለች፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ ሄለን፣ ሁኔታው ጭንቀት ውስጥ ከተታትና ሥራዋን መሥራት ተቸገረች፣ የምግብ ፍላጎቷ ቀነሰ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥም አሥር ኪሎ ቀነሰች፡፡ በዙሪያ ከነበሩ ሰዎች ጋር አብዝታ ትጋጭ ጀመር፡፡ ከሥራ ገበታዋ መቅረት ስላበዛችም ከቀጣሪዎቿ ጋር ተጣልታ ከሥራ ለቀቀች፡፡ ለቤት ኪራይ የምትከፍለው ስላልነበራትም ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ተመልሳ ገባች፡፡

ከቤተሰቦቿ ጋር ሆናም ደስተኛ አልነበረችም፡፡ በንግግር የሚጋጩባቸው ቀናት በዙ፡፡ ልታገባ ካሰበችው ወጣት መለያየቷ ቤተሰቦቿን ቢያሳዝንም፣ እየዋለ እያደረ የሚለዋወጠው የልጃቸው ሁኔታ በእጅጉ ያሳስባቸው ጀመረ፡፡

እርኩስ መንፈስ ተጠናውቷት ይሆን በሚል ፀበል አስጠምቀዋታል፡፡ አዲስ የተቀየረ ነገር ግን የለም፡፡ እንደማትፈልገውና እንደጠላችው ደጋግማ ብትናገርም እንደሚያገባት ቃል ሲገባላት ያደረገላትን ቀለበት ከጣቷ ለማውለቅ አትፈልግም፡፡ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ መተከዝ ሥራዋ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

የ33 ዓመቱ መስፍንም (ስሙ ተቀይሯል) ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞት ሕይወቱ እንዳልነበር ሆኖ ተቀይሯል፡፡ የፍቅር ጓደኛ የማፍራት ፍላጎቱ ከጠፋ ቆይቷል፡፡ ‹‹ሰው መተዋወቅ፣ መግባባት ከዚያም ወደ ፍቅር ግንኙነት መለወጥ ዳገት መስሎ ይታየኛል›› ይላል፡፡ ይህ ከበፊትም ጀምሮ የነበረው ባህሪ ሳይሆን ከጊዜ በኋላ አጋጣሚዎች የቀረፁት ማንነቱ ነው፡፡ የፍቅር ሕይወቱን እንዳልነበር ያደረገው አጋጣሚ የተፈጠረው ከአራት ዓመታት በፊት እንደሆነም ያክላል፡፡

ከሚወዳት ወጣት ጋር በጓደኝነት አምስት ዓመታት ቆይተዋል፡፡ በመካከላቸው የነበረው ግንኙነትም ጠንካራ ነበር፡፡ ስለዚህም በትዳር በመጣመር አብሮነታቸውን አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ አሰቡ፡፡ መስፍንም (ስሙ ተቀይሯል) ጊዜ ሳያጠፋ ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን ሽማግሌዎች መርጦ ወደ ፍቅረኛው ቤተሰቦች ቤት ላከ፡፡ እነሱም ልጃቸውን ለመስፍን ለመዳር ፈቀዱ፡፡ በምልሻቸው ተደስቶም አብሮ ለመኖር ዕቃ መገዛዛት፣ ቤት ማሟላትና ለሠርጉ የሚያስፈልጉ ነገሮችን መግዛት ጀመረ፡፡ ነገር ግን የሕይወቱን አዲስ ምዕራፍ የሚጀምርበት አጋጣሚ የፈጠረበት ደስታ፣ ብዙም ሳይቆይ እንደ ጉም በኖ ጠፋ፡፡

‹‹የተፈጠረውን መግለፅ አልፈልግም፡፡ ያደረገችው ነገር ግን በመካከላችን ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር ነበር›› የሚለው መስፍን፣ አጋጣሚው ሕይወቱን እንዳልነበረ እንዳደረገው ያስታውሳል፡፡ የተፈጠረውን ክፍተት እንድታጠብ ብዙ ለምኗታል፡፡ አማላጅም ልኮባታል፡፡ ቤተሰቦቿ ሳይቀሩ ታረሚ ብለዋት ነበር፡፡ ይሁንና በውሳኔዋ ፀናች፡፡ ነገሮች ወደነበሩበት አንደማይመለሱ ሲገባው በአብሮነታቸው ላይ ተስፋ ቆረጠ፡፡

‹‹በሕይወቴ ፈታኙ ጊዜ ነበር›› ሲል ለውሳኔ የተቸገረበትን ወቅት ያስታውሳል፡፡ ሠርጋቸው ሳይደገስ መዘግየቱን የተመለከቱት ሽማግሌዎች ‹ሠርጉን ለመች እንዲሆን ወሰናችሁ›፣ ብለው በጥያቄ ያጣድፉት ገቡ፡፡ የተፈጠረውን ነገር የሚነግርበት ወኔ አልነበረውምና ይሸሻቸው ጀመር፡፡

ይህ ከሆነ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ጓደኛውን ከተለያት በኃላ በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳለች አያውቅም፡፡ ‹‹ትዝ አትለኝም›› ይላል፡፡ ይሁንና ነገሮች በዚያው አልተቋጩም፡፡ አጋጣሚው የፈጠረበት ጠባሳ አሁንም አልሻረለትም፡፡ ‹‹ሌላ የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር አስቤ አላውቅም፡፡ አንድ ሁለቴ ሞክሬ ነበር፡፡ ነገር ግን ዝግጁ ስላልነበርኩ መዝለቅ አልቻሉም›› ሲል ችግር ውስጥ መግባቱን ይናገራል፡፡

ወላጆች ለአቅመ አዳም የደረሱ ልጆቻቸውን በወግ ማዕረግ መዳርን የሕይወታቸው ትልቁ ስኬት አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ በማህበረሰቡም ሠርግና ሞት አንድ ነው በሚባለው ብሂል መሠረት ያላቸውን አሟጥጠውና ተበድረው ድግሱን ለማድመቅ ይሞክራሉ፡፡ የእከሌ ልጅ በትልቅ ሰርግ ተዳረች/ተዳረ ብሎ ማስወራትም ያኮራል፡፡ ልጆችም ቢሆኑ የህይወታቸው ሌላኛው ምዕራፍ የሚከፈትበትን የሠርጋቸውን ቀን በከፍተኛ ጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ነገሮች አልጋባልጋ አይሆኑም፡፡ በህመም፣ በሞት፣አልያም በሌላ ሰርጉ ሊቀር ይችላል፡፡

የታሰበ ሠርግ ሲከሽፍ፣ ለጋብቻ የታሰበ ጓደኝነት ሲፈርስ ከአንዱ የአንዱ  ቢለይም ስሜት የሚጎዳ ነው፡፡ በተለይም ጋብቻው የተሰረዘው ቀላል ተብለው በሚታሰቡ ምክንያቶች ሲሆን ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡ የሚያሳድረው የሥነ ልቦና ቀውስም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አንዳንዴም ደመኛ ያደርጋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም በሁለቱ ቤተሰቦች መካከል በነፍስ እስከመፈላለግ የሚያደርስ መዘዝ እንደሚያስከትል ይነገራል፡፡ በተለይም ትዳሩን አልፈልግም ባዩ ወንድ በሚሆንበት ወቅት በሴቷና በቤተሰቦቿ ላይ የሚያሳድረው ማኅበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው፡፡ የአደባባይ ሚስጥር የሆነውን ጉዳይ መጠቋቆሚያ ያደርጋል፣ አንገት ያስደፋል፡፡

ጋብቻ በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ወግ አጥባቂ ማኅበረሰብ በሚኖርባቸው አገሮች ጋብቻ ልዩ ቦታ አለው፡፡ አንዲት ሴት ልጃገረድነቷን እንደጠበቀች፣ ዓይነ አፋር፣ አንገት ደፊና ለባሏ ታዛዥ ሆና ለጋብቻ እንድትበቃ ለማድረግ ወላጆች የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ወንዱም ቢሆን፣ ‹‹ጥሩ ባል›› ብሎ ማኅበረሰቡ በሚቀበለው መልኩ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ዓይነግቡና ግበረገብነት ያላትን አይተውም፡፡ ልጅዎን/ልጅሽን ለልጄ ብለው ወላጆች ጥያቄ የሚያቀርቡበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ገና ያልተወለዱ ልጆች ለትዳር የሚታጩበትም ሁኔታ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ልማዶች  በሁለቱ መፈቃቀድ ላይ ተመሥርቶ በሚፈጸምበት ዘመናዊ የጋብቻ ሥርዓት ተተክተዋል፡፡

ወንዱ ባህሉ በሚፈቅደው መልኩ አክብሮ ሽማግሌ ከላከና እሺታን ካገኘ የሠርግ ዝግጅቱ ይጀመራል፡፡ ወላጆችም ልጆቻችን ለወግ ማዕረግ በቁ ብለው በስኬታቸው ይኮራሉ፡፡ ልዩ ልዩ የሠርግ ዘፈኖችን እያወረዱና እያደመጡ ወገባቸውን አስረው የሰርጉን ድግስ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ማለት ይጀምራሉ፡፡ እንዲህ በወኔ የሚያስፈልገውን በሚያሰናዱበት  ወቅት የጋብቻውን መቅረት ሲሰሙ የሞት ያህል ይከብዳቸዋል፡፡ በተለይም በሠርጉ ዕለት ወዳጅ ዘመድ ተጠርቶ የሙሽሮችን መምጣት በሚጠባበቁበት ወቅት ሲሆን የሚፈጥረው ቀውስ ከፍተኛ ነው፡፡

በከተማው ከተፈጠሩ መሰል አጋጣሚዎች መካከል አነጋጋሪ የነበሩትን እንዲህ ማስታወስ ተችሏል፡፡ ከወራት በፊት የተከሰተ ጉዳይ ነው፡፡

ወጣቷ ወላጆቿን እንዲሁም የቅርብ ጓደኞቿን አስተዋውቃዋለች፡፡ ነገር ግን በሱ በኩል ማንንም አላስተዋወቃትም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ አብረው ከቆዩ በኋላ ለመጋባት ወሰኑ፡፡ ሽማግሌ ተልኮም የሠርጉ ቀን ተቆረጠ፡፡ የድግሱ ዝግጅትም ተጀመረ፡፡ ሠርጉ ሳምንት ሲቀረው ግን ያልተጠበቀ ነገር ተፈጠረ፡፡

ሙሽራው እዚህ ነኝ እዚያ ነኝ ሳይል ተሰወረ፡፡ በተደጋጋሚ ስልክ ቢደወልለትም ስልኩ አይነሳም፡፡ ተከራይቶ ወደሚኖርበት ቤት ብትሄድ፣ ቤት መልቀቁን ሰማች፡፡ ወደ መሥሪያ ቤቱ ብትሄድም ልታገኘው አልቻለችም፡፡ ዕረፍት እንደወጣ ሰማች፡፡ ግራ ቢገባት የት ሊሄድ እንደሚችል አለቃውን ጠየቀችው፡፡ እሱም ባለትዳርና የልጆች አባት መሆኑን፣ ከባለቤቱ ጋር ተለያይቶ ይኖር እንደነበርና በቅርቡ ታርቀው አብረው መኖር መጀመራቸውን ነገራት፡፡ የሰማችውን ማመን አቃታት፡፡ ለቤተሰቦቿም ነገረቻቸው፡፡ በአጋጣሚው ክፉኛ ቢያዝኑም የሚያደርጉት አልነበራቸውም፡፡ ለሠርጉ የጥሪ ካርዶችን በትነው ነበር፡፡ መልሰው ሠርጉ መሰረዙን ከይቅርታ ጋር መልዕክት ላኩ፡፡

ሌላው በአንድ መሥሪያ ቤት አብረው በሚሠሩ ጥንዶች መካከል የተፈጠረው ነው፡፡ በጓደኝነት አብረው ዓመታት ከቆዩ በኋላ በትዳር ለመተሳሰር ተስማሙ፡፡ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ሽማግሌ ወደ ልጅቷ ቤተሰብ ተላከ፡፡ ቤተሰቦቿ የሰጡትን ፈቃድ ተከትሎም ያለፈው ዓመት ግንቦት 12 ይደገስ ለነበረው ሠርግ መዘጋጀት ጀመሩ፡፡

የሠርጉ ወቅት እየተቃረበ መጣ፡፡ ሙሽሪትም በዕለቱ ደምቃ የምትታይበትን  ቬሎ ከባህር ማዶ አስመጥታለች፡፡ ሚዜዎችም የሚያምርባቸውን ልብሶች ገዝተዋል፡፡ ለአዳራሽ ቀብድ ተከፍሏል፡፡ ለሠርጉ የሚያስፈልጉ ውድ ውድ መጠጦችና ሌሎችም ተገዝተዋል፡፡ ሠርጉን ለማድመቅ ሽር ጉድ በሚሉበት ወቅት ወንድ ጓደኛዋ  ጋብቻውን እንደማይፈልግ አሳወቀ፡፡

አጋጣሚው ያልተጠበቀና አስደንጋጭ ነበር፡፡ ሙሽሪት በተቻላት መጠን ለበጐ ነው ብላ ራሷን ለማረጋጋት ብትሞክርም፣ የወላጆቿ ቁጣ ከባድ ሆነ፡፡ ሁኔታው የሚይዙት የሚጨብጡትን እስኪያጡ አብከነከናቸው፡፡

አቶ ተስፋዬ ገብሬ ዌድንግ ፕላነር (የሠርግ ፕሮግራሞች አዘጋጅ) ሆነው ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ በስራቸው የተለያዩ ገጠመኞችንም አስተናግደዋል፡፡ ዌዲንግ ፕላነር ሆነው የሠሩበት አንድ ሠርግ ላይ ያጋጠማቸውንም እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡

በሠርጉ ዕለት እንግዶች በአዳራሹ ተገኝተው ሙሽሪትና ሙሽራን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሙሽሮቹ በሰአቱ አልተገኙም፡፡ እንግዶች ሙሽሮችን ሲጠብቁ ብዙ ቆዩ፡፡ ነገሩ ግራ ቢገባቸው ሙሽሮቹ ወደነበሩበት ሄዱ፡፡ ሙሽሮቹ ተጣልተው ነበርና ሙሽሪት ሙሽራውን ጥላ ጠፍታለች፡፡ ‹‹ሙሽሪት በሕመም ምክንያት መቅረቷን ነግረን የመጡት እንግዶች በልተው ጠጥው እንዲሄዱ አድርገናል›› ይላሉ፡፡

የሠርግ መሠረዝን ያህል የከበደ ነገር ቀርቶ፣ እንግዶች በተጠሩበት ሰዓት የሙሽሮች አለመገኘት በቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ጭንቀት ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም አቶ ተስፋዬ ያጋጠማቸው አለ፡፡

በዝግጅቱ  ከ2000 ሰዎች በላይ ተገኝተዋል፡፡ እንግዶች በተጠሩበት ሰዓት በቦታው ቢደርሱም ሙሽሮቹ ግን በአዳራሹ ውስጥ አልተገኙም፡፡ የሙሽሪት አባት በጣም ተጨንቀዋል፡፡ ሙሽሮቹ ሳይመጡ ስምንት ሰዓት አለፈ፡፡ የሙሽሪት አባት የእንግዶችን ፊት ማየት ከበዳቸው፡፡ በቁጣም ጦፉ፡፡ ራሳቸውን ስተውም ወደቁ፡፡ በዚያው የደም ግፊታቸው ጨምሮ ሕይወታቸው ማለፉን አቶ ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡

የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ እስጢፋኖስ አበራ እንደሚሉት፣ ሽማግሌ ተልኮ የሠርግ ፕሮግራም ማዘጋጀት ከተጀመረ በኋላ ጋብቻው የሚሰረዝበት ሁኔታ የሚፈጠረው በጥንዶቹ መካከል ጠንካራ ግንኙነት ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡ ጥቅምን መሠረት ያደረገና የታሰበው ጥቅም አለመኖሩ ሲታወቅ፣ ሰዎችን ለመጉዳት በበቀል፣ በሕመም፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቤተሰብ ግፊት ጋብቻ የሚሰረዝባቸውት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ‹‹ለሠርጉ ቀን በሚመረጥ ሙዚቃ የሚጣሉ የሚደባደቡና ሠርጋቸውን የሚሰርዙ አጋጥመውኛል፤›› ሲሉም፣ እዚህ ግባ በማይባል ምክንያት ጥንዶቹ ተጣልተው ሰርግ የሚሰረዝባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡

ሰርግ ወላጆች የልጆቻቸውን ስኬት የሚያዩበት ቀን ነው፡፡ ፕሮግራሙም ልዩ ትርጉም አለው፡፡ ይህ አልሆነም ማለት በወላጆችም ሆነ በጥንዶቹ ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጉዳት ያደርሳል፡፡ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ቤተሰብ ነገሩን በሚስጥር ለመያዝ ሲል፣ በሙሽራው ምትክ  ከቅርብ ቤተሰብ መካከል አንድ ወንድ ሙሽሪትን ከቤት ይዞ እንዲወጣ የሚያደርጉ አሉ፡፡ አጋጣሚውን መቋቋም አቅቷቸው ራሳቸውን የሚያጠፉም አሉ፡፡ ‹‹አለመፈለግ በራስ መተማመናችንን ይቀንሳል፡፡ ስሜት ይጎዳል፡፡ እንዲሁም ሰዎች ለእኛ የሚኖራቸውን ግምት ይቀንሳል›› የሚሉት አቶ እስጢፋኖስ፣ ጋብቻውን አልፈልግም ባዩም ከጉዳት እንደማያመልጥ ተናግረዋል፡፡

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት ሙሽራው ወይም ሙሽሪት በሠርጉ ላይ ካልተገኙ ጋብቻ እንዳልተፈጸመ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህም በዕለቱ አንዱ አካል መቅረቱ የሕግ ተጠያቂነት አያስከትልበትም የሚሉት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር ወይዘሮ ዜናዬ ታደሰ ናቸው፡፡ ይሁንና ክልሎች የየራሳቸው የሆነ የቤተሰብ ሕግ አላቸው፡፡ ስለ መተጫጨት በሚለው ድንጋጌ ስር ሙሽሪት ወይም ሙሽራው ከሠርጉ ሲቀሩ፣ የሕግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ካሳ ስለመክፈል በዝርዝር የተቀመጡ አንቀጾችም አሉ፡፡ በዚያ መሠረት ለዝግጅቱ ያወጡትን እንዲካሱ ይደረጋል፡፡ ይህ ከዚህ ቀደም በፌደራል ደረጃ በስራ ላይ በነበረው የቤተሰብ ህግም ተፈፃሚነት ነበረው፡፡ ‹‹በስራ ላይ ባለው የፌዴራሉ የተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ ግን፣ ጋብቻ ሕጋዊ ውጤት የሚኖረው ሲፈጸም ብቻ ነው ይላል፡፡ ካሳን በተመለከተም በግልፅ ያስቀመጠው ነገር የለም›› ብለዋል፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕጉ ለሠርግ ከሚወጡ ወጪዎች ያነሱ ኪሣራዎች ሲያጋጥሙ ካሣ እንዲከፈል የሚያስገድዱ ድንጋጌዎች መኖራቸውን፣ ለሠርግ የሚወጡ ወጪዎችም በድንጋጌዎቹ መሠረት ካሳ እንዲከፈልባቸው ቢጠየቅ የሚካሱበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ዳይሬክተሯ ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሰለጠነው ዓለም ጥንዶች ጋብቻ ሲያስቡ ስለጋብቻ የማማከር አገልግሎት ወደሚሰጡ ተቋማት በመሄድ የምክር አገልግሎት ይሰጣቸዋል፡፡ ወደ ጋብቻ የሚገቡትም ዝግጁ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ነው፡፡ እንደዚህም ሆኖ ብዙዎች ጋብቻቸውን ይሰርዛሉ፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ 270,000 ሠርጎች በየዓመቱ ይሰረዛሉ፡፡ በዚህ ለሚያጋጥማቸው ኪሣራ የኢንሹራንስ ሽፋን የሚሰጡ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ለሠርጉ የተዘጋጀውን ፕሮግራም በቅናሽ ዋጋ ገዝተው ለሌላ ጥንዶች የሚሸጡ ድርጅቶች አሉ፡፡ በዚህም ሊደርስባቸው የሚችልን ኪሣራ ይሸፍናሉ፡፡

በኢትዮጵያ ለአንድ ሠርግ ድግስ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አሉ፡፡ ጋብቻው ተሰረዘ ብሎ ምን ያህሉ ሰው ካሳ ሊጠይቅ እንደሚችል አጠያያቂ  ቢሆንም ፣በገንዘብ ረገድ ሊኖር የሚችል ኪሣራን በፍትሐ ብሔር ማየት ይቻላል፡፡ የሚደርሰውን የሞራል ውድቀት ግን የሚካስ አይደለም፡፡ ለዚህም ወደነበሩበት የሕይወት መስመር መመለስ ተስኗቸው ከእውነታው ጋር እንደታገሉ የሚኖሩ እንደ ሔለንና መስፍን ያሉ ወጣቶችን ማየት በቂ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...