Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየቃቄ ውርድወት ከ“ሸርመነ” እስከ ብሔራዊ ቴአትር

የቃቄ ውርድወት ከ“ሸርመነ” እስከ ብሔራዊ ቴአትር

ቀን:

  በብርሃነ ዓለሙ ገሣ

የቃቄ ውርድወትን ተውኔት ለማየት፣ ኅዳር 4 ቀን 2009 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ብሔራዊ ቴአትር ቤት ተገኘሁ፡፡ ትዕይንቱ ከቀኑ 8፡30 ጀምሮ 11፡30 ሰዓት ላይ አበቃ፡፡

ወርድወት፣ ከዳሞ ቃቄና አጅየት አሚና ከአንድ መቶ ሰባ ዓመታት በፊት በዛሬው ጉራጌ ዞን ሞህር ሸርመነ ቀበሌ የተወለደች ታሪክ ሠሪ ወይዘሮ ናት፡፡ ውርድወት ባመነችበት ጉዳይ ጠንካራ ከመሆኗ በተጨማሪ ሲበዛ ቆንጆም ነበረች፡፡ የስመ ጥሩዋ ውርድወት ታሪክ እነሆ ከአንድ መቶ ሰባ ዓመታት በኋላ ከአገር አገር ይናኝ ጀመር፡፡ በጉራጌ ብሔረሰብ ታሪክ በርካታ ዝነኛ ሴቶች ቢኖሩም የውርድወትን ያህል ዝናቸውና ስማቸው ሚዛን የደፋ ግን አልተገኙም፡፡

- Advertisement -

በብሔረሰቡ ውስጥ እንደ ልማድ ተይዞ ሲፈጸም የነበረን አንድ ወንድ፣ ሁለትና ሦስት ሚስት የማግባት መብትን በይፋ በመቃወም ጉዳዩን አደባባይ ያወጣች ጀግና ናት – የቃቄ ውርድወት፡፡ በጀግንነቱ በጉራጌ ብሔረሰብ የሚታወቀውን የኧዣ ቤተ ጉራጌውን አጋዝ ፉርችየ ላምቢየን በመሞገት፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ባህልና ወግ ሰብራ መብቷን አስከብራለች፡፡ በዚህ ድርጊቷም ጉድ አሰኝታለች፡፡ ስሟንም በታሪክ መዝገብ አስመዝግባለች፡፡

ከኧዣ አልፋ ጉዳይዋን ለየጆካ ሸንጎ ማድረሷ በራሱ አነጋጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም በማኅበረሰቡ ባህል፣ ወግና ልማድ መሠረት ሴቶች ታዛዦች እንጂ ተከራካሪዎችና ተሟጋቾች ሊሆኑ ሥርዓቱ አመቺ ወይም ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ የብሔረሰቡን የኖረ ድንጋጌ ተጋፍጣ በሴቶች ላይ የተጣለውን አንቂት (ያለ ወንዱ ፈቃድ ትዳር ያለመመሥረት ደንብ) ተነስቶ እንደ ወንዶች ሁሉ ሴቶችም የወደዱትን አማርጠው ማግባት ወይም መፍታት እንዲችሉ የመብት ጥያቄ አንስታ ለብዙዎቹ ሴቶች እንግዳ የሆነውን የጆካ ሸንጎ ድረስ ማድረስ መቻሏ ለታላቅነቷ ማረጋገጫ ነው፡፡ ውርድወት ሳትማር፣ ሳታነብና ከተማ ሳትረግጥ እልም ባለ ባላገር ውስጥ እየኖረች፤ ከብዙዎቹ መሰሎቿ ተለይታ ለሴቶች መብት ለመታገል እንዴት ድፍረቱን አገኝች?

በብሔራዊ ቴአትሩ ተውኔትም ሆነ ቀደም ሲል በተጻፉ መጻሕፍት፣ መጣጥፎችና ሌሎች ሰነዶች የቃቄ ውርድወት ዝና ለተደራስያን ያስተዋወቁ ወገኖች ያላነሱት ነገር ግን አለ፡፡ ይኸውም በዘመኑ የነበረው የብሔረሰቡ ባህል ወግና ልማድ ለሴቶች ይሰጥ የነበረውን አንፃራዊ መብትና ነፃነትን ነው፡፡ ለዚህ አባባሌ አብነት የሚሆኑኝን ባህላዊ ትውፊቶችን እዚህ ላይ ማንሳት ይኖርብኛል፡፡

የጉራጌ ብሔረሰብ፣ ለሴቶች የተለየ ክብርና ትኩረት ይሰጣል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው በየዓመቱ ይከበሩ የነበሩ አንትሮሸት (የእናቶች በዓል)፣ ነቈ (የልጃገረዶች በዓል) እንዲሁም ስምንት ልጅ ለወለደች እናት በተጨማሪነት የሚከበረው ሣምር ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

አንዲት እናት በየዓመቱ በልጆቿ፣ በልጅ ልጆቿ፣ በዘመድ አዝማድ እንዲሁም በጎረቤትና በመንደሩ ሰዎች የእናትነት የክብር በዓሏ በድምቀት ይከበርላታል፡፡ በአንትሮሸት በዓል እናት ትሾማለች፤ ትሸለማለች፡፡ ለክብሯ በቅቤ ትታጠባለች፤ ታርዶ ትጋበዛለች፡፡ ጋቢ፣ ማርና ሌሎች ቁሳቁሶች ይቀርብላታል፡፡ ለክብሯ ይዜምላታል፡፡ ለደስታዋ ልዕልና ይጨፈርላታል፡፡ ባህላዊው ዌግ ይቀኝላታል፡፡ በደምሳሳው በአንትሮሸት በዓል እናት የፈለገችውን ይቀርብላታል፡፡ ድንገት ቅር የተሰኘችበት ጉዳይ ካለም ይቅርታ እንድታደርግ ይሰገድላታል፡፡

እንደ አንትሮሸት ሁሉ በየዓመቱ ነቈ የተሰኘ ታዳጊዎችን ያካተተ የልጃገረዶች በዓልም ይከበራል፡፡ በዓላቸውን በደመቀና በፍሥሐ እንዲያከብሩም ሁኔታዎች ሁሉ ይመቻቹላቸዋል፡፡ ጥር ወር ላይ ለሚያከብሩት በዓላቸው ከመስቀል በዓል (ወኸመያ) ማግስት ጀምሮ ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ፡፡ በጉራጌ የመስቀል በዓል ማግስት መስከረም 16 ለነቈ በዓላቸው የሚሆን ሥጋ ከየአባወራውና እማወራዋ ቤት በመሄድ ይቀበላሉ፡፡ ከየቤቱ የተቀበሉትን ሥጋ ዘልዝለው ሣር ቤት ውስጥ ከቆጥ በላይ በሚገኘው ጣራ (ዘጉዊረ) ላይ ይሰቅሉታል፡፡ ቋንጣ ሆኖ ይቀመጣል፡፡ ይኼ ቋንጣ የሚበሉት በነቈ በዓላቸው ጊዜ ቀቅለው ክትፎ ሠርተው ነው፡፡ የነቈ ልጃገረዶች ነፃነት የሚጀምረው ከመስከረም 16 ቀን አንስቶ ነው፡፡ ለነቈአቸው የሚሆናቸውን ሥጋ ለመጠየቅ ሲሄዱ መንገዳቸው ላይ የሚያደናቅፏቸው ወንዶችን የመግረፍ መብት አላቸው፡፡ ልጃገረዶቹ ብቻ በሚግባቡበት ለየት ያለ ፌድወት በተባለ “ቋንቋ” ተግባብተው ተቃውሟቸውን ይገልጻሉ፤ ምስጢራቸውን ይለዋወጣሉ፡፡

ሌላው ሣምር ነው፡፡ አንዲት እናት ስምንትና ከዚያ በላይ ልጆች ስትወልድ የእሷ ወገኖችና የባሏ ዘመዶች አንድ ላይ ሆነው በየደረጃው ትልቅ ድግስ ደግሰው ይመርቋታል፡፡ መልካም ምኞታቸውን ይገልጹላታል፡፡ እነዚህ እውነታዎች፣ ከወርድወት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል በተጻፉ መጻሕፍትና ጋዜጦች እንዲሁም በሬዲዮና በቴሌቪዥን በተላለፉ ዘገባዎች የተዘነጉ መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው፡፡

የቃቄ ውርድወት ተውኔት፣ ትውፊታዊ ድራማ ብዙ እንደ ተደከመበት ከዝግጅቱ ዐውድ መረዳት አይከብድም፡፡ ተውኔቱ ለመድረክ እንዲበቃ በየደረጃው የተሳተፉ ሁሉ ከልብ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ተውኔቱ ማለፊያ ጎኖች እንዳሉት ሁሉ ግን አንዳንድ ትኩረት ሳይሰጣቸው የታለፉ ሕፀፆች እንዳሉም ለማየት ችያለሁ፡፡ ከመድረኩ ገጽታ ስንነሳ ብዙ ቦታዎች ላይ የሚደጋገመው ግድፈት እዚህም አጋጥሟል፡፡ አንድ አቅም ያለው የጉራጌ አባወራ ወይም እማወራ (በተለይ ውርድወት በተወለደችበት በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ) የሚኖራቸው ቤት ሦስት ሳይሆን አራት ነው፡፡ እነዚህም ጎየ (ትልቁ ቤት)፣ ኸራር (እልፍኝ)፣ ዘገር (ማዕድ ቤት) እና ሰቃላ (ዕቃ ማስቀመጫ) ናቸው፡፡ በብዙዎች ተማርንና ከተሜ ነን በሚሉ የብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ እንደ ዘበት የሚታለፈው ሰቃላ ሞፈርና ቀንበር እንዲሁም የከብቶችና የበጎች መኖ ማስቀመጫ ሆኖ የሚያገለግል መሠረታዊ ቤት ነው፡፡ የሴቷም አንዳንድ ቁሳቁሶች ሰቃላ ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ ማኅበረሰቡ በምሳሌያዊ አነጋገሩ ‹‹በቤት ያሰራ ሰቃላ፣ በሁጅር ያሰራ ነጠላ›› ብሎ ይተርትበታል፡፡ ወደ አማርኛ ሲመለስም፣ ደረጃውን የጠበቀ ቤት ለመሥራት ለጊዜው በሰቃላ ተኑሮ ሲሆን፤ የተሻለ ልብስ ለማግኘት ደግሞ ነጠላ ተለብሶ ታግሶ መድረስ እንደሚቻል አመላካች ነው፡፡

ሌላው በጥንቃቄ መታየት ያለበት፣ የተውኔቱ ዐቢይ መልዕክት የሆነውን አንድ ወንድ ሁለት ሦስት ሴት የሚያገባበት ምክንያት ነው፡፡ ከአንድ መቶ ሰባ ዓመታት በፊት በጉራጌ ምድር ይኖር የነበረ አንድ የጉራጌ ወንድ ሁለት ሦስት የሚያገባው አቅም ያለው፣ ባለ ብዙ መሬትና ባለ ብዙ ንብረት መሆን አለበት፡፡ በየቦታው ያለው መሬት፣ ከብት፣ ቤትና ንብረት በአግባቡ ጠብቆ ለማቆየት መሬቱና ንብረቱ ባለበት ሚስት ለማግባት ይገደድ ነበር፡፡ በእርግጥ ሁሉም ወንዶች የሚያስገድዳቸው አጋጣሚ ነበር ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ በቂ መሬትና ንብረት የሌላቸው ከአንድ ሚስት በላይ ማስተዳደር ስለማይችሉ ብዙዎች አይደፍሩትም ነበር፡፡ ሁለት ሦስት ሚስት ማግባት የሚደገፍ ባይሆንም፣ በአንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎች አማካይነት ግን ይፈጸም እንደነበር ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ አንቂት የአቅመ ደካሞችን ትዳር አቅም አለን በሚሉ ግፈኛ ወንዶች እንዳይፈርስ፣ ባለትዳር የሆነችን ሴት በጉልበትና በሥልጣን ተመክቶ መውሰድ እንዳይቻል መከላከያም ጭምር ነው፡፡ በዘመኑ የነበሩ ባለ ጊዜዎች የተራውን ወንድ ሚስት እንዳይነጥቁ፣ እንዳያስኮበልሉና ትዳርን እንዳያናጉ አንቂት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ሌላው ርዕሰ ጉዳይ ሁለት ሦስት ሚስት ማግባት ከፍተኛ የልጅ ፍላጎትን ለማሟላትና ዘር ለማብዛትም እንደሆነ ጭምር ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበሩ አባቶችና ቅድመ አያቶች ሁለትና ሦስት ሚስት ማግባት ቡና የመጠጣትን ያህል ያዘወትሩ እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ በእርግጥ የነበረው ሥርዓት ሴቶች ላይ የበለጠ ጫና ያሳድር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አንዳንድ ወንዶች ሆዳቸውን በጣም ይወዱ ስለነበር ለሚስቶቻቸው ግድ አልነበራቸውም፡፡ ሴትን እንደ ትዳር አጋር ሳይሆን እንደ አገልጋይ ይመለከቱ የነበሩ ሞልተዋል፡፡ ሴቶችን በሚመለከት ያለው የተዛባ አመለካከት ተምረን ጫፍ ላይ ደርሰናል በሚሉ ልሂቃን ዘንድ እስከዛሬም ድረስ አልተወገደም፡፡

በዚያ ኋላቀር በነበረ ሥርዓት ውስጥ የሥርዓቱን ወግና ልማድ ተቃውሞ “እምቢኝ ለመብቴ” ብሎ መነሳት አስደናቂ ነው፡፡ ውርድወት የብሔረሰቡን ባህል፣ አኗኗርና ልማድ ሳያግዳት ጉዳይዋን ወይም የመብት ጥያቄዋን ታላቁ ተከባሪውና ተፈሪው የጆካ ሸንጎ ድረስ ማድረሷ አዎ ጀግና ያሰኛታል፡፡ በዚህም ገድሏ አማካይነት በጉራጌ ውስጥ ከነበሩት ዝነኛና ስመ ጥር ሴቶች በላቀ መልኩ ስሟ ሊገንን ችሏል፡፡

በተውኔቱ ላይ ዌግ አንጎራጓሪውን ጅረ በነስየን ሆኖ የሚጫወተው ተዋናይ የሚያንጎራጉረው በድራ ነው ወይስ ዌግ? እኔ ሳዳምጠው ግን በድራ ነው የመሰለኝ፡፡ በድራ ከሆነ ደግሞ ስህተት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለቸር፣ ለጀግና፣ ተበድሎ ማጥቃት እየቻለ ለሚታገስ፣ ከክፉ ቀን ለሚያወጣ፣ ወዘተ የሚደረደረው ዌግ እንጂ በድራ አይደለምና፡፡              

የቃቄ ውርድወት በገቢር ተከፋፍሎ በዋና ዋና እና ጥላ ገጸ ባሕሪያት የተዋቀረና በምልሰት የሚተረክ ተውኔት ነው፡፡ በተውኔቱ ውስጥ የተዋቀሩት ተዋናዮች (ገጸ ባሕሪያት) አንዳንዶቹ ምንም ሚና ሳይጫወቱ ያልፋሉ፡፡ ለምሳሌ የውርድወት እናት አጅየት አሚና፣ የውርድወት አገልጋይ … በተውኔቱ ላይ ሚናቸው የጎላ አይደለም፡፡ አጅየት አሚና የዳሞ ቃቄ ባለቤትና የጀግናዋ ውርድወት እናት በተውኔቱ በድምፅ አለመሳተፍዋ ትክክል አይመስለኝም፡፡ አጋዝ ፉርችየም ቢሆን እንዲህ በቀላሉ ሚስቱን ለመፍታት ይሁንታውን ሰጠ ማለት ይከብዳል፡፡ በተውኔቱ ላይ የተዋናዮቹ (ገጸ ባሕሪያቱ) ግጭት፣ ጡዘትና ልቀት በተገቢው ልክ ተዋቅሯል ለማለት ይከብዳል፡፡ በጣም ላልቷል፡፡ የተዋናዮቹ በተለይ ደግሞ በውርድወትና በአጋዝ ፉርችየ፣ በየጆካ ሽማግሌዎችና በአጋዝ ፉርችየ፣ በየጆካ ሽማግሌዎችና በውርድወት፣ እንዲሁም በሽማግሌዎች በራሳቸውም መካከል የሚካሄደው ምልልስ (ዳያሎግ) ተመልካቹን ውጥረትና ጭንቀት ውስጥ መክተት ነበረበት፡፡ አጋዝ ፉርችየን የመሰለ የአገሩ ጀግና የሕግ ሚስቱ ረግጣው ስትወጣና ቤቱ ሲፈርስ በተውኔቱ ላይ እንደታየው በቀላሉ እጅ ይሰጣል ወይም እሺ ይላል ማለት ዘበት ነው፡፡ መላው ጉራጌን ያነጋገረ ትልቅ ጉዳይ በአንድና በሁለት ቀጠሮ እልባት ያገኛል ብሎ ማመን ይከብዳል፡፡ የተውኔቱ ዙር አልከረረም፡፡ ሤራው አልተጋጋለም፡፡ ባህሉን፣ ወጉንና ልማዱን ለሚያውቅ ሰው አሳማኝ ነው ለማለት ይቸግራል፡፡

በተውኔቱ ውስጥ በሚታየው በጉራጌ የሸንጎ ማዕከል የጆካ የሚካሄደው ትዕይንት የሚጎድለው ነገር አለ፡፡ በየትኛውም የጉራጌ ብሔረሰብ ሸንጎ፣ በጥቂት ሰዎችም ይሁን በብዙዎች ንግግር ሲጀመር በምርቃት ነው፡፡ ዝም ተብሎ ወደ ነገር ወይም ወደ ፍሬ ጉዳዩ ዘው ተብሎ አይገባም፡፡ “ያነጋውን ቀን በሰላም ያምሽልን”፣ “ሽማግሌዎች የዕድሜ ድኃ አይሁኑ”፣ “ፍትሕ ለተበደለ ይሁን”፣ “ፍትሕ አይዛባ”፣ ወዘተ ብለው ነው ባለ ጉዳዮችም ሆኑ ሽማግሌዎች ንግግር የሚጀምሩት፡፡ የጆካ ሸንጎ ላይ በሚፈለገው መልክ ይህንን ሲያደርጉ አላስተዋልኩም፡፡

መታረም የሚገባው ሌላው ጉዳይ መቼቱ ነው፡፡ ቅድም ካነሳኋቸው የጉራጌ ባህላዊ ቤቶች አንዱ በጣውላ በተሠራ አጭር በር ተዘግቶ ይታያል፡፡ በዚያ ዘመን የጣውላ በር አይታወቅም፡፡ በዚያን ወቅት ሊኖር የሚችለው በቀርከሃ የተሠራ ትንሽዬ ተብር ነው፡፡ ትልቁ በር በተብር ወይም በሐረግ (ያብታ ወዝገብ) የተሠራ ሊሆን ይችላል፡፡ ለነፋስና አንዳንድ አስፈላጊ ያልሆኑ እንስሳት እንዳይገቡ ለመከላከል ቀን ቀን አጭሩ በር ገርበብ ይደረጋል ወይም ይዘጋል፡፡ የጣውላ በር በጉራጌ ምድር መስፋፋት የጀመረው ከ1950ዎቹ መጨረሻ ወዲህ ነው፡፡

ከአንድ መቶ ሰባ ዓመታት በፊት የነበረው የጉራጌ ገጠር በተደራጀና በሚያሳምን መልኩ የተዋቀረ አልመስልህ አለኝ፡፡ በወቅቱ ብሔረሰቡ ይተዳደርባቸው የነበሩ ባህላዊ እምነቶች በተውኔቱ ውስጥ ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡ የአንድን ሕዝብ ማንነት ለመግለጽ ዛሬ ጥቂቶች በመረጧቸውና ትክክል ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን ብቻ መከተል አግባብ አይደለም፡፡ በወቅቱ ብሔረሰቡ ይከተላቸው የነበሩት ባህላዊ እምነቶች ቦዠ፣ ደሟሚትና ዋቅ የራሳቸው የሆነ አዎንታዊና አሉታዊ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ በቃቄ ውርድወት የትግል ጉዞ፣ የኑሮ ውጣውረድና እንቅስቃሴ ላይ ባህላዊ እምነቶቹ ሁነኛ ቦታ ነበራቸው፡፡

ሩቅ ሳንሄድ ውርድወት የሞተችው እኮ ዘናበናር ወደ ተባለ ቦታ ስትጓዝ በቦዠ (መብረቅ) ተመትታ ነው፡፡ ድርጊቱን ያስተዋለው ዌጋማ (አንጎራጓሪ) እንዲህ ብሎ ዌግ ደርድሮላታል፡፡

 የቃቄ ውርድወቶ

 ዘናበናር ትትወርዶ

 አደገናም በጐቶ

 ጐት መሰረናም አንጨቶ

 ሰቀረናም በወትራ

 ወትራ መሰረናም ሰገራ… እያለ ይቀጥላል፡፡ ወደ አማርኛ ሲመለስ የጉራግኛውን ያህል ስሜት ባይሰጥም የሚከተለውን ይመስላል፡፡

የቃቄ ውርድወት

ስትጓዝ ዘናበናር

አቧራ ላይ ጣላት (መብረቅ ነው የሚጥላት)

አቧራው መሰላት ቄጠማ …

በተውኔቱ ላይ ሲነሳ የሰማሁትና “ምን እያሉን ነው?” ያሰኘኝ ሌላው ነጥብ፣ ጫትን በሚመለከት የተነሳው ነው፡፡ በቃቄ ውርድወት ዘመን የጉራጌ ብሔረሰብ አባላት (ሕዝብ) ጫት ችግሩም አሳሳቢውም ጉዳይ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ከተወሰኑ የቸሃ፣ የእኖርና ኤነር አካባቢዎች ውጪ የሚያመርትም ሆነ የሚሸጥ አልነበረም፡፡ ጫት በጉራጌ ምድር የተስፋፋው ከሃምሳ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ በተለይ በጎማረ፣ በኧዣና በሞህር በውርድወት ዘመን ብዙ አይታወቅም፡፡

ተውኔቱ ከባህል፣ ከታሪክና ከሥነ ሰብ (አንትሮፖሎጂ) አንጻር ብዙ ሊያነጋግር የሚችል ቢሆንም ረዥም ውጣ ውረዶችን አልፎ፣ ጠመዝማዛውን መንገድ አሸንፎ ለእይታ በመብቃቱ በተውኔቱ ላይ ለተሳተፉ ለደራሲው፣ ለመራሔ ተውኔቱ፣ ለተዋንያኑና ለመድረክ ገጽ ሠዓሊዎች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ተውኔቱ ለሕዝብ ከመቅረቡ በፊት እንዲተቹ ተጋብዘው የተመለከቱ የብሔረሰቡ ተወላጆች፣ የታዩ ሕፀፆችን እንዲታረም አለማድረጋቸው ያሳዝናል፡፡ ከላይ ከዘረዘርኳቸው በተጨማሪ ሌሎችም ጥቃቅን ጉድለቶች ቢኖሩትም በዚህ ደረጃ ለፍሬ መብቃቱ በራሱ ትልቅ ድል ነው፡፡ ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ብሔራዊ ቴአትር ቤትንና በተውኔቱ የተካፈሉትን ሁሉ ከመቀመጫዬ በመነሳት ደጋግሜ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...