Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰየመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ አቶ አስፋው በንቲ ሲልጋን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ሾመ፡፡

ከኢንሹራንስ ኩባንያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአቶ አስፋውን ሹመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መስከረም 21 ቀን 2016 በቁጥር ISD/1199/2016 በጻፈው ደብዳቤ አፅድቋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በተፈረመ ፊርማ የአቶ አስፋው ሹመት የፀደቀበት ደብዳቤ የደረሰው መሆኑን የሚገልጸው የኢንሹራንስ ኩባንያው መረጃ፣ እ.ኤ.አ. ከኖቬምበር 10 ቀን 2016 ጀምሮ ሥራቸውን እንደጀመሩም ይገልጻል፡፡

የአቶ አስፋው ሹመት ከፀደቀ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ሥራ ጀመሩ እስከተባለት ቀን ድረስ ኩባንያው በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመራ የቆየበት ጉዳይ ግልጽ ባይሆንም፣ አቶ አስፋው ከኢትዮጵያ ውጪ በመቆየታቸው ሳቢያ ምናልባት የዜግነት ጉዳይ ማጣራት በመፈለጉ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ሆኖም ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ላለ ሹመት አዎንታዊ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ያሉ ማጣራቶችን አድርጎ በመሆኑ፣ ሹመታቸው ከፀደቀ በኋላ ዘግይተው መጀመራቸው ሌላ ምክንያት ሊኖረው ይችላል ተብሏል፡፡   

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከግንቦት 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት በተሾሙት አቶ ትዕግሥቱ ሽፈራው ሲመራ የነበረው፣ ኩባንያውን ለስድስት ዓመታት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ተስፋዬ ለሜሳ ከኃላፊነታቸው በመልቀቃቸው ነው ተብሏል፡፡  

አቶ አስፋው በተለያዩ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ በማገልገል ጠለቅ ያለ የኢንሹራንስ ልምድ ያካበቱ መሆናቸውን ኩባንያው አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ መድን ድርጅት በነበራቸው የረዥም ጊዜ ቆይታ ማለትም ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች የሠሩ መሆናቸውን፣ እስከ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ኃላፊነቶች ላይ ተመድበው ማገልገላቸውን ኩባንያው በላከው መግለጫ አስረድቷል፡፡

አቶ አስፋው እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 2004 እስከ ጥር 2006 ዓ.ም. በናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ ከኦፕሬሽን መምርያ ሥራ አስፈጻሚነት እስከ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ማገልገላቸው ታውቋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ እ.ኤ.አ. በ1983 ዓ.ም. ያገኙ መሆናቸውን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ እንግሊዝ ከሚገኘው ኦፕን ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. በ1998 ማግኘታቸውንና እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. ከቻርተርድ ኢንሹራንስ ኢንስቲትዩት በኢንሹራንስ ዲፕሎማ መቀበላቸው ተገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያን እስከ ተቀላቀሉበት ጊዜ ድረስ፣ በአሜሪካ በተለያዩ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በመሥራት ሙያቸውን ያዳበሩ መሆናቸውን ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ አስታውቋል፡፡ 

‹‹አቶ አስፋው በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ካላቸው ጥልቅ እውቀት በተጨማሪ በመሪነት፣ በሙያ ፍቅር፣ በሥነ ምግባራቸውና በሥራ ወዳድነታቸው በበርካቶች ዘንድ አንቱታን አትርፈዋል፡፡  በኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን የዳይሬክተሮች ቦርድና የማኔጅመንት አባላት ከወዲሁ ተመኝቷል፤›› ሲል ኩባንያው ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች