Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ማመልከቻ ቀረበ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ግንባታውን በ2007 ዓ.ም. አጠናቆ ምርቱን ለገበያ እንደሚያቀርብ ያስነገረውን ማስታወቂያ በማመን አክሲዮን ገዝተው ሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበርን የተቀላቀሉ ከሰባት በላይ ባለድርሻዎች፣ ማኅበሩ እንዲፈርስና የተመሰከረለት የሒሳብ አጣሪ እንዲሾም ለፍርድ ቤት ኅዳር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. አቤቱታ አቀረቡ፡፡

  ሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር በአማራ ክልል በምሥራቅ ጐጃም ዞን፣ ጃዊ ወረዳ ውስጥ በሊዝ በገዛው ከ6,000 ሔክታር በላይ መሬት ላይ የስኳር ፋብሪካ ገንብቶ ስኳር ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ ከአክሲዮን ሽያጭና ከባንክ ብድር የሚያገኘውን ገንዘብ የተማመነ ቢሆንም፣ እንዳልተሳካለት ባለድርሻዎቹ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ያስረዳል፡፡

  ማኅበሩ ከባንክ ብድር ለማግኘት የ1.5 ቢሊዮን ብር አክሲዮኖችን መሸጥ የነበረበት ቢሆንም፣ ማኅበሩ መሸጥ የቻለው ከ100 ሚሊዮን ብር የማይበልጥና የሚፈልገውን የባንክ ብድር ማግኘት እንዳልቻለ በአቤቱታው ተካቷል፡፡

  ማኅበሩ ባስነገረውና ባሠራጨው መግለጫ መሠረት ፋብሪካውን ገንብቶ ማምረት ባለመጀመሩ ሊፈርስ እንደሚገባ ያመለከቱት ባለድርሻዎች፣ በሕግ የተጣለበትን አስገዳጅና ጥብቅ ግዴታ መተላለፉን ጠቁመዋል፡፡ ማኅበሩ የተላለፈው ወይም የጣሰው የሕግ ግዴታ፣ የመመሥረቻ ጽሑፉንና መተዳደርያ ደንቡን ሳያሻሽል፣ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ለፋብሪካ ግንባታ ከክልሉ በሊዝ በተረከበው ሰፊ የእርሻ መሬት ላይ ሩዝ በመዝራት፣ በአክሲዮን ማኅበሩ የፋይናንስ አቅም ላይ ከባድ ኪሳራ ማስከተሉንም ገልጸዋል፡፡

  ማኅበሩ ፋብሪካውን ለማስተከል ከኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ተስማምቶ 25 ሚሊዮን ብር ቢከፍልም፣ በቦታው ላይ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ከሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ምንም ዓይነት ግንባታ አለማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

   ባለድርሻዎች በተለይ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስለተገባው ውል አጥብቀው ሲጠይቁ፣ የተከፈለው ገንዘብ ያለምንም ወለድና የኪሳራ ማሻሻያ ለማኅበሩ እንደተመለሰ ከሥራ ኃላፊዎቹ ቀጥታ ባልሆነ መንገድ እንደተነገራቸው ጠቁመው፣ የተወሰኑ የማኅበሩ ባለድርሻዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አቤቱታ አቅርበው እንደነበርም በክስ አቤቱታው ተጠቅሷል፡፡

  በመሆኑም ባለድርሻዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ አክሲዮን ማኅበሩ ፈርሶ የተጣራ ሀብትና ንብረቱ ለአባላት እንዲከፋፈል የቀረበውን ሐሳብ፣ ፍርድ ቤቱ ዓይቶ ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚገባ በማመልከቻው አብራርተዋል፡፡

  ሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር በ2008 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ያስተላለፈው ጥሪ ምልአተ ጉባዔ ባለመሙላቱ ሊካሄድ አለመቻሉን የጠቆሙት ባለድርሻዎቹ፣ በንግድ ሕግ ቁጥር 394 መሠረት በአንድ ሳምንት ልዩነት ሁለት ማስታወቂያዎችን በማውጣት ጠቅላላ ስብሰባውን ማድረግ ሲገባው፣ ሳያደርግ የበጀት ዓመቱ መጠናቀቁንና የማኅበሩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የሥልጣን ዘመን እንዳበቃ በማመልከቻው አስፍረዋል፡፡

  በባንክ የተቀመጠ የባለድርሻዎች ገንዘብ የሥልጣን ጊዜያቸው ባለፈና ሥልጣን በሌላቸው ግለሰቦች፣ ከሕግ ውጪ እየተንቀሳቀሰና ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን በክስ ማመልከቻው ገልጸዋል፡፡

  ማኅበሩ ከተቋቋመ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ በየጊዜው ለሚቀያየሩ የቦርድ ዳይሬክተሮች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ የማኔጅመንት አባላት ለደመወዝ፣ ለአበል፣ ለሥራ ማስኬጃና ሌሎች ጉዳዮች ከፍተኛ ወጪ መውጣቱን የገለጹት አመልካቾቹ፣ መቆሚያ በሌለው ወጪ የአባላቱ መብትና ጥቅም ላልተጠበቀ ኪሳራ በመጋለጡ ፍርድ ቤቱ ማኅበሩን በአስቸኳይ እንዲፈርስ ፍርድ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

    

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች