የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በ300 ሚሊዮን ዶላር ዘመናዊ የባቡር አካዴሚ ሊገነባ ነው፡፡
የባቡር አካዴሚው የሚገነባው ከአዲስ አበባ ውጪ ሆኖ በአዲስ አበባ-ጂቡቲ ምድር ባቡር መስመር አቅራቢያ እንደሚያርፍ፣ የኮርፖሬሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር እስካሁን የለያቸው ቦታዎች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ደረጀ፣ ለካሳ ክፍያ የሚያስፈልገው ወጪ ላይ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ ቦታው እንደሚወሰን ገልጸዋል፡፡
የባቡር አካዴሚው ሲጠናቀቅ ዘመናዊ የባቡር ምሥለ በረራ (ሲሙሌተር) እና የመገናኛ መሣሪያዎች የሚሟሉለት እንደሚሆን የጠቆሙት አቶ ደረጀ፣ እስከ አንድ ዓመት ጊዜ የሚፈጁ የተለያዩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የባቡር ማስተር (ሾፌር)፣ የመገናኛና የባቡር ትራፊክ ማኔጅመንት፣ የጥገና ቴክኒሺያንነትና ተያያዥ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ ይህም ባቡር ኮርፖሬሽኑ ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት አንቀሳቃሾችን ለማሠልጠን የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስቀርለት ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎትን ወደ ሥራ ለማስገባት ሁለት የቻይና ኩባንያዎች የባቡር ትራንስፖርትና ጥገና አገልግሎቶችን ለሦስት ዓመታት ለማከናወን መቀጠራቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በጋራ 110 ሚሊዮን ዶላር የሚከፈላቸው ሲሆን፣ በቻይና የአንድ ዓመት ሥልጠና የወሰዱ ኢትዮጵያውያንን የሥራ ላይ ሥልጠና በመስጠት የማብቃት ኃላፊነትም ተጥሎባቸዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ 252 ኢትዮጵያውያንን ለአንድ ዓመት በቻይና ለማሠልጠን 250 ሚሊዮን ዶላር ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
በቅርቡ የሙከራ አገልግሎት የጀመረው 760 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ከሁለት ሺሕ በላይ የሠለጠኑ ሠራተኞችን እንደሚፈልግ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
‹‹አካዴሚው በዋናነት ትኩረት የሚሰጠው ለአገር ውስጥ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሠራተኞችን ማቅረብ ነው፤›› ያሉት አቶ ደረጀ፣ ወደፊት አኅጉራዊ ተቋም እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
አካዴሚውን ለመንባት ከሚያስፈልገው ወጪ ውስጥ 14.5 ሚሊዮን ዶላር (100 ሚሊዮን ዩዋን) በብድር ከቻይና ተገኝቷል፡፡ የዚህ ብድር ስምምነት የቻይና ምክትል ፕሬዚዳንት ሊ ዮዎንቻኦ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባን በጎበኙበት ወቅት ተፈጽሟል፡፡ የቻይና መንግሥት ተጨማሪ ብድር ለመስጠት መስማማቱን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡