Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት ማኮብኮቢያ ተጨናንቋል ተባለ

  የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት ማኮብኮቢያ ተጨናንቋል ተባለ

  ቀን:

  –  የዱር እንስሳትና አዕዋፋት የአደጋ ሥጋት ፈጥረዋል

  በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እያደገ የመጣውን የአየር ትራፊክ፣ ያለው አንድ የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ ለማስተናገድ በቂ ሊሆን እንዳልቻለ ተገለጸ፡፡ አዕዋፋት በአዲስ አበባ ኤርፖርት በአውሮፕላኖች እንቅስቃሴ ላይ እንከን እየፈጠሩ እንደሆነ፣ በክልል ኤርፖርቶች ደግሞ የዱር እንስሳት በአውሮፕላኖች ላይ ጉዳት በማድረስ የአደጋ ሥጋት እየፈጠሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከባለድርሻ አካላት ጋር ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በሐርመኒ ሆቴል ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ መሆኑንና የበረራ አድማሱን በማስፋት አዲስ አውሮፕላኖች በመግዛት ላይ እንደሆነ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የኤርፖርት አገልግሎት ከአየር መንገዱ ዕድገት ጋር ተያይዞ ማደግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ እያደገ የመጣውን የብሔራዊ አየር መንገዱን ፍላጎት፣ የአየር መንገዱን የበረራ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት፣ የግል አየር መንገዶች የቻርተር በረራዎችና የግል ፓይለት ማሠልጠኛ ተቋማት አነስተኛ አውሮፕላኖችን፣ በተለይ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት በሚኖርበት ወቅት በአንድ ማኮብኮቢያ ማስተናገድ ለባለሥልጣኑ ፈተና እየሆነበት እንደመጣ ተናግረዋል፡፡

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኦፕሬሽን ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ አየር መንገዱ ፓይለቶችን በአዲስ አበባ ለማሠልጠን በመቸገሩ የሥልጠና ፕሮግራሙን በከፊል ወደ ድሬዳዋና መቐለ ወስዶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

  በድሬዳዋና በመቐለ ኤርፖርት በተለያዩ ምክንያቶች እንደተፈለገው ማሠልጠን ባለመቻሉ፣ በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ በልዩ ፈቃድ በደብረዘይት አየር ኃይል ለማሠልጠን መገደዱን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ወደ ሐዋሳ ለማዛወር መታሰቡን ገልጸው፣ ይህ ጊዜያዊ መፍትሔ በመሆኑ ለዘለቄታው የአዲስ አበባ ኤርፖርትን ወደ ደረጃ ሦስት ለማሳደግ (ሁለተኛ ማኮብኮቢያ ለመገንባት) ተይዞ የነበረው ዕቅድ ምን እንደደረሰ ጠይቀዋል፡፡

  ሌላው በስብሰባው ላይ የተነሳው አሳሳቢ ችግር የአዕዋፋትና የዱር እንስሳት በኤርፖርቶች አካባቢ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ አቶ መስፍን በአዲስ አበባ አሞራዎች በአውሮፕላኖች ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ፣ በክልል ኤርፖርቶች በተለይ በድሬዳዋ፣ በመቐለና በባህር ዳር የዱር እንስሳት በመንደርደር ላይ ያሉ አውሮፕላኖችን በማቋረጥ ጉዳት እንደሚያደርሱ፣ በቅርቡም በድሬዳዋ በከርከሮዎች አማካይነት የደረሰውን የአደጋ አጋጣሚ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹እነዚህ አጋጣሚዎች አየር መንገዱን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጉት ነውና ይህን ችግር ለመፍታት ምን እየተሠራ ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

  የኢስት አፍሪካን አቪዬሽን የበረራ አገልግሎትና የፓይለት ማሠልጠኛ ኩባንያ ተወካይ ሻምበል ግርማ ገብሬ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ለመንደርደሪያ መጨናነቁ በጋራ መፍትሔ ሊፈልጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

  የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና የበረራ ማሠልጠኛ ተቋም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፣ አውሮፕላኖቻቸው ከአዲስ አበባ ኤርፖርት ለመነሳትና ለማረፍ ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ለመነሳት ለረዥም ጊዜ ቆማችሁ ተጠባበቁ እንባላለን፡፡ ሠልጣኝ ፓይለቶቻችን ለማረፍ ከ30 እስከ 40 ደቂቃ በአየር ላይ እንዲሽከረከሩ ይደረጋሉ፤›› ሲሉ ካፒቴን ሰለሞን ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በአዲስ አበባ አካባቢ መሬት ከተሰጣቸው የራሳቸውን አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

  ኮሎኔል ወሰንየለህ የተጠቀሱት ችግሮች መኖራቸውን አምነዋል፡፡ የአዲስ አበባ ኤርፖርትን ወደ ደረጃ ሦስት ለማሳደግ የቀድሞ ትራንስፖርት ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በተገኙበት መወሰኑን፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ተጨማሪ ማኮብኮቢያ ለመገንባት ጥናት በማካሄድ ላይ መሆኑን፣ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይና ዝግጅት የሚጠይቅ በመሆኑ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ሁለተኛ ማኮብኮቢያ ለመገንባት ኤርፖርቱ አካባቢ ያሉ ገደላማ ቦታዎች (የካባ ድንጋይ ሲወጣባቸው የነበሩ ቦታዎች) በአፈር የመሙላት ሥራ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

  አዕዋፋትና የዱር እንስሳት የሚፈጥሩትን የአደጋ ሥጋት በተመለከተ የተለያዩ የመከላከል ሥራዎች በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽንና በኤርፖርቶች ድርጅት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአዲስ አበባ ትልቁ ችግር ኤርፖርቱ ከተማ ውስጥ መገኘቱ ነው፡፡ በመኖሪያ ሠፈሮች የተከበበ በመሆኑ በየአካባቢው የሚካሄዱ ሕገወጥ ዕርዶች ለአሞራዎች መሰባሰብ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፤›› ብለዋል፡፡

  በክልል ከተሞች ደግሞ ኤርፖርቶቹ ከከተማ ወጣ ብለው በመገንባታቸው የዱር እንስሳት በኤርፖርቶቹ ቅጥር ግቢ ሾልከው በመግባት ችግር እንደሚፈጥሩ አምነዋል፡፡

  ከዱር እንስሳት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ክስተቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን፣ ክስተቱ እያደገ ሄዶ ከፍተኛ አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል ኮሎኔል ወሰንየለህ ተናግረዋል፡፡ በድሬዳዋ፣ በመቐለና በባህር ዳር ጥብቅ አጥር መገንባት እንደሚያስፈልግ፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በዚህ ጉዳይ የዝግጅት ሥራ በማካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ግፊት በማድረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

  ኮሎኔል ወሰንየለህ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ማብራሪያ እንዲሰጥ ዕድል ቢሰጡም፣ የድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች በስብሰባው ላይ ባለመገኘታቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በሚያዘጋጀው የምክክር መድረኮች ላይ ቢጋበዙም በአብዛኛው እንደማይገኙ፣ ይህም ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የግል አየር መንገዶች ተወካዮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

  ባለሥልጣኑ የአዕዋፋትና የዱር እንስሳት አደጋ ሥጋቶችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጀት ጋር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራበት አስታውቋል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img