Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሰው ገብተው የነበሩ 20 አውሮፕላኖች ተለቀቁ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ሲቪል አቪዬሽንና አየር ኃይል ሲከታተሏቸው እንደነበር ተጠቆመ

የኢትዮጵያን የአየር ክልል ያለፈቃድ ጥሰው የገቡ የ20 አነስተኛ አውሮፕላኖች ፓይለቶች ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ ከአገር ለቀው እንዲወጡ መደረጉን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ገለጸ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አውሮፕላኖቹን ይዘው በጋምቤላ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ፓይለቶች ጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፉ መደረጉንና የምርመራ ቡድን በፓይለቶቹ ላይ ምርመራ አድርገዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ምርመራውን አጠናቆ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ፣ በምርመራው ግኝቶች መሠረት ፓይለቶቹና አውሮፕላኖቹ ከአገር እንዲወጡ መወሰኑን ጠቁመዋል፡፡

‘ቪንቴጅ የአየር ትዕይንት’ በሚል መጠሪያ በሚታወቀው ፕሮግራም ወደተለያዩ አገሮች በረራ ሲያደርጉ የነበሩት ፓይለቶች፣ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሰው የገቡት ማክሰኞ ኅዳር 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡

ፓይለቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው አስቀድሞ ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በኢትዮጵያ አየር ክልል ለመጠቀም ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ፈቃድ እንዳልተሰጣቸው ኮሎኔል ወሰንየለህ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ለጥያቄው ፈቃድ ያልተሰጠበት ምክንያት ፓይለቶቹ ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል ለመግባት የጠየቁት በጋምቤላ በኩል በመሆኑ ነው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ሕግ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ የውጭ አውሮፕላን በመጀመሪያ ማረፍ የሚችለው ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ብቻ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

‹‹የተለየ ሁኔታ ካልገጠመና በዚህም ጉዳይ ላይ ባለሥልጣኑ ፈቃድ ካልሰጠ በስተቀር በአዲስ አበባ በኩል ብቻ ነው መግባት የሚቻለው፤›› ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ፈቃድ ሳይሰጣቸውና ይህንን ዓለም አቀፍ አሠራር ጥሰው በመግባታቸው ጋምቤላ እንዲያርፉ መታዘዛቸውንና ይህንኑ መፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አየር ክልል ከመግባታቸው በፊት ጀምሮ ክትትል እያደረግንባቸው ነበር፡፡ አነስተኛ ሲቪል አውሮፕላኖች በመሆናቸው ማስገደድ ሳያስፈልግ በትዕዛዝ ብቻ እንዲያርፉ ተደርጓል፤›› ሲሉ አቶ ወሰንየለህ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

የሪፖርተር የአየር ኃይል ምንጮች በበኩላቸው፣ አየር ኃይል አውሮፕላኖቹ ወደ ኢትዮጵያ ክልል ከመግባታቸው አንስቶ ሲከታተላቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የአየር ክልል ጥብቅ ነው፡፡ ሳይፈቀድለት ሊገባ የሚችለው አሞራ ብቻ ነው፤›› ያሉት ኮሎኔል ወሰንየለህ፣ የምርመራ ግኝቱን ተከትሎ መንግሥት በሰጠው ትዕዛዝ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ መደረጋቸውን ባለፈው ዓርብ አስታውቀዋል፡፡ ፓይለቶቹ የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች፣ የአሜሪካ፣ የደቡብ አፍሪካና የቦስትዋና ዜግነት ያላቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቀጣዩ በረራቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ፈቃድ ሳያገኙ ወደ ኢትዮጵያ አየር ክልል አምስት ሔሊኮፕተሮች ይዘው የገቡ 26 የሩሲያ ፓይለቶች ተይዘው ከሁለት ሳምንት በኋላ መለቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች