Thursday, September 21, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት አሁንም ውስጡን ያፅዳ!

ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ከሚቀያየምባቸውና ጥላቻ ውስጥ ከሚከቱት ምክንያቶች መካከል አንደኛ የአስመሳይነትና የአድርባይነት መግነን ነው፡፡ መንግሥት በውስጡ የተሰገሰጉ መርህ አልባዎችን ማፅዳት ካልቻለ ችግሩ ይቀጥላል፡፡ አስመሳይነትና አድርባይነት የመርህ አልባነት መገለጫ በመሆኑ፣ ለሕገወጥ ድርጊቶችና ሕዝብ ለሚጠላቸው ተግባራት ምቹ ሜዳ ነው፡፡ በራሳቸው የማይተማመኑና በፅናት የሚቆሙለት ሕዝባዊ ዓላማ የሌላቸው ራስ ወዳዶች፣ ሕዝብን በማስከፋትና ሕይወቱን በማመሰቃቀል በየቦታው ችግር ሲፈጥሩ ይታያሉ፡፡ መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከላይ እስከ ታች ጥልቅ ተሃድሶ እያደረግኩ ነው በሚልበት በዚህ ወቅት እንኳ፣ ከራሳቸውና ከቢጤዎቻቸው ጥቅም በላይ የአገር ጉዳይ ግድ የማይሰጣቸው  በየሥፍራው ሕዝቡን ያማርራሉ፡፡ መንግሥት በእውነት ዕድሳት ላይ ከሆነ እነዚህን በወረንጦ ለቅሞ ማራገፍ አለበት፡፡

በመላ አገሪቱ በመንግሥታዊ ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት፣ በጤና ተቋማት፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግንባታ ፈቃድ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በወረዳና በክፍላተ ከተሞች፣ በንግድ ፈቃድና ምዝገባ፣ በትራንስፖርት፣ በግዥና ጨረታ፣ በፋይናንስ ተቋማት፣ በፍትሕ አካላት፣ ወዘተ ውስጥ ለመልካም አስተዳደር መጥፋትና ለሙስና መስፋፋት አሉታዊ ሚና የሚጫወቱት አስመሳዮችና አድርባዮች ናቸው፡፡ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ሕገወጥ ተግባራት እንዲበራከቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያበረታታሉ፡፡ ሀቀኛ ሠራተኞችን በማሸማቀቅ አንገት ያስደፋሉ፡፡ የሐሰት ሪፖርቶችን በመፈብረክ ያልተሠራውን እንደተሠራ ያቀርባሉ፡፡ ብልሹ አሠራሮችን በማንገሥ ሕገወጥነትን ያስፋፋሉ፡፡ ለመውቀስ፣ ለመተቸት፣ ለማረምና ለማስተካከል የሚፈልጉ ዜጎችን በአሉባልታ እንዲጠፉ ያደርጋሉ፡፡ የመንግሥት ሚዲያዎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመቆጣጠር መደናገር ይፈጥራሉ፡፡

መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ እያደረግኩ ነው ሲል፣ እነሱ በለመዱት ብልጣ ብልጥነት በመቅረብ ‹ትግሉ የሚቀጥለው ሳይበረዝና ሳይከለስ ነው› በማለት ለሰሚ ግራ የሚያጋ ሐሳብ ይዘው ይቀርባሉ፡፡ የሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ሚና ሳይኖራቸው፣ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን የሚያከናውኑ ወገኖችን ያብጠለጥላሉ፡፡ ከአገር አጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ብቻ ስለሚያስቀድሙ፣ ለእነሱ ሕዝብ ማለት ምንም አይደለም፡፡ ሕዝብን በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት፣ በዳበረ ዕውቀትና ክህሎት ለማገልገል አሁንም ብቃቱ ያላቸው በርካታ ዜጎች እያሉ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ አስመሳዮችና አድርባዮች መንግሥትን መፈናፈኛ ያሳጡታል፡፡ መንግሥት አሁንም በቁርጠኝነት ውስጡን ማፅዳት ካልቻለ፣ አገሪቱን ችግር ውስጥ እንድትገባ ምክንያት የነበሩ ክስተቶች ዳግም መመለሳቸው እያጠራጥርም፡፡

ጥልቅ ተሃድሶው እየተድበሰበሰ ተራ ግምገማ እንዳይሆን በጠራ ሁኔታ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ የፈለገውን ያህል ግምገማ ይደረግ ወይም ሹም ሽር ይፈጸም፣ እስካሁን የነበረውን የሕዝብ ቅሬታና ብሶት መነሻ ያላደረገ ከሆነ ሥር ነቀል ለውጥ አይገኝም፡፡ ለዚህ የሚረዳው ደግሞ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱም ያዛል፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ደግሞ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የመገናኛ ብዙኃን  የሕዝብ አገልጋይ መሆን አለባቸው፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ‹‹ኔትወርክ›› በሚባሉ ኃይሎች እየተጠለፉ የአስመሳዮችና የአድርባዮች መጫወቻ መሆን የለባቸውም፡፡ ይልቁንም መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ሙስና እንዲወገድ፣ ፍትሕ እንዳይጓደል፣ ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ፣ የሕዝብ ድምፅ እንዲሰማ፣ ወዘተ መሥራት ይገባቸዋል፡፡ የመንግሥት ጠንካራ ጎኖች እንደሚወደሱ ሁሉ ድክመቶቹም በሚገባ እንዲተቹ መደረግ አለበት፡፡ ይኼ አንዱ የፅዳት መገለጫ ነው፡፡

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተዓማኒነት የሌላቸውና ልፍስፍስ እንዲሆኑ በመደረጋቸው መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለው ዓመኔታ በጣም ወርዷል፡፡ የሕዝብ አቤቱታና እሮሮ በማፈን፣ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በማድበስበስና የአድርባዮች መጫወቻ በመሆን የደረሰው ኪሳራ ይበቃል፡፡ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ እንዲኮሰምንና ሙስና እንዲስፋፋ በማድረግ፣ ሕዝብ የደረሰበት ቦታ ሁሉ ምሬት እየተፈጠረበት አገሩን እንዲጠላ የተደረገው መገናኛ ብዙኃኑ በተገቢው መንገድ እንዲሠሩ ባለመደረጉ ነው፡፡ መንግሥት ዘንድ ያለ መረጃ በቅጡ ተደራጅቶ ለዜጎች እንዳይደርስ የሚደረገው ከብቃት ማነስ በተጨማሪ ማናለብኝነት በመንገሡ ነው፡፡ በጥልቅ የመታደስ እንቅስቃሴው እነዚህን ችግሮች ማየት ካልቻለ ውጤቱ ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው፡፡ መንግሥት ውስጡን ለማፅዳት ከፈለገ ይህንን መስክ በሚገባ ይየው፡፡

ሰላም፤ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን የሚሆኑት ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው በሚገባ እየተናበቡ ሥራቸውን ሲያከናውኑና የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠበቅ ያለ ሲሆን ነው፡፡ የሲቪክና የዴሞክራሲ ተቋማት ተጠናክረው ሥራቸውን በነፃነት ሲያከናውኑ ነው፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በተግባር ሲረጋገጥ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሀብትና የሥራ ዕድል ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ከግልና ከቡድን ይልቅ የሕዝብና የአገር ጥቅም ሲቀድም ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ሲሰፍን ነው፡፡ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት በተግባር ሲረጋገጥ ነው፡፡ አድርባዮችና አስመሳዮች ይብቃችሁ ሲባሉ ነው፡፡ በአጠቃላይ መንግሥት ራሱን ለማደስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የአገሪቱንና የሕዝቡን ዕጣ ፈንታ በጥልቀት ማሰብ አለበት፡፡ ይህቺ ታሪካዊ አገርና ይህ የተከበረ ሕዝብ ከድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የሚያስፈልጋቸው ልማት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳይ ግን ለነገ የሚባል መሆን የለበትም፡፡ ልማት ያለ ዴሞክራሲ ቀልድ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህና መሰል እሳቤዎች ላይ በመመርኮዝ መንግሥት አሁንም ውስጡን ያፅዳ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...