Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ ሳይንቲስት የሚሆኑ ታዳጊዎች አሏት››

ዶ/ር ኮሎኔል ዓለማየሁ ገ/እግዚአብሔር፣ የእስቴም ሲነርጂ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር

ዶ/ር ኮሎኔል ዓለማየሁ ገ/እግዚአብሔር የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባል ነበሩ፡፡ ከሕንድ በሲስተምስ ኤንድ ኮንትሮልንግ ኢንጅነሪንግ የፒኤችዲ ዲግሪ አላቸው፡፡ ከ30 ዓመታት በላይ የሠራ ዘመናቸውን በመከላከያ ያሳለፉት ኮሎኔል ዓለማየሁ የመከላከያ ኢንጀነሪንግ ኮሌጅ ሲደራጅ በመምህርነት፣ በዲቪዥን ኃላፊነትና ዲንነት አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም በተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ሆነው ዳርፉር በማቅናት ግዴታቸውን መወጣት ችለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የእስቴም ሲነርጂ (Stem Synergy) አገር አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ድርጅት ዳይሬክተር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ እስቴም ሲነርጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያሉ ተማሪዎችን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ማቲማቲክስ በማሠልጠን በኢትዮጵያ የሳይንስ ማዕከል ለማቋቋም በማቀድ የተነሳ ድርጅት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበርና የሳይንስ ማዕከላትን በመክፈት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቹና በሳይንስ ማዕከላቱ ያለውን የተማሪዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት እንቅስቃሴ በተመለከተ ዳዊት ቶሎሳ ከዶ/ር ኮሎኔል ዓለማየሁ ገ/እግዚአብሔር ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የእስቴም ሲነርጂ የሳይንስ ፕሮግራም እንዴት ተጀመረ?

ዶ/ር ዓለማየሁ፡- የእስቴም ሲነርጂና የድጋፍ አድራጊው ዋና ዓላማ ሳይንስና ቴክኖሎጂን የሚሠሩ ሥራዎች ለወጣቶች በማስተማር ኢንጂነሮችና ሳይንቲስቶች መፍጠር ነው፡፡ የእስቴም ሲነርጂ ፕሮግራም የጀመረው ሚስተር ማርክ ግልፈንድ የተባለ አሜሪካዊ በሌላ የሥራ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት አጋጣሚ ነው፡፡ በአገሪቷ ውስጥ ያሉትን ወጣቶች የሳይንስ ክህሎት በመመልከት የተለየ ድጋፍ ቢደረግላቸው ከፍተኛ ውጤት ሊመጣ እንደሚችል በማመን ፕሮግራሙ ተጀምሯል፡፡ ቀደም ብሎ ግን መነሻ የነበረው ከጐንደርና ከትግራይ አካባቢ ወደ እስራኤል አምርተው የሚኖሩ ወጣት ልጆች በሳይንስ ላይ ያላቸውን ችሎታ ሲመለከት በኢትዮጵያም ድጋፍ ከተደረገላቸው የተሻለ ነገር መሠራት የሚችሉ ወጣቶች እንደሚገኙ በማመኑ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ መጥቶ የቢሾፍቱ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅን ተመልክቶ ከእኔ ጋር በመወያየት፣ በኢትዮጵያ የሳይንስ ማዕከል መክፈት እንደሚፈልግ ገለጸልኝ፡፡ ከዛም በመከላከያ ኮሌጅ ውስጥ ያሉትን ላብራቶሪዎች ከተመለከተ በኋላ በቢሾፍቱ የሳይንስ ማዕከል ለማቋቋም ወሰነ፡፡ በተጨማሪም ከሌሎች አካላት ጋር በመነጋገር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በቢሾፍቱ ከተማ የፎቃ የሳይንስ ትምህርት ማዕከል እንዲመሠረት አደረገ፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ከተመሠረተ በኋላ በሥሩ የሚሠለጥኑ ተማሪዎችን ለማስተማር መምህራን እንዴት ማግኘት ተቻለ? የናንተስ ድጋፍ ምን ይመስል ነበር?

ዶ/ር ዓለማየሁ፡- ከዚህ ቀደም በመከላከያ ኮሌጅ ለረጅም ዓመታት ልምድ ያላቸው ግን የጡረታ ጊዜያቸው የደረሰ አስተማሪዎች ነበሩ፡፡ እነሱን ቀጥታ ወደ ሥራው ማስገባት ተቻለ፡፡ እኔም በሐሳብ ደረጃ ድጋፍ ሳደርግ ነበር፡፡ የላብራቶሪ መምህር የሆኑትም እንዲሁ በሌሎችም የሳይንስ ማዕከላት የነበሩ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የእስቴም ሲነርጂ የሳይንስ ማዕከላትንና ችሎታ ያላቸውን ወጣት ተማሪዎችን ከማፍራት አንጻር ከቢሾፍቱ ውጪ በሌሎች ክልሎች ለማስፋፋት የተከናወነ እንቅስቃሴ አለ?

ዶ/ር ዓለማየሁ፡- ቢሾፍቱ ከሚገኘው የፎቃ የሳይንስ ማዕከል በተጨማሪ በተለያዩ ክልሎች መስፋፋት አለበት በሚል መነሻ ቁጥራቸው 13 ማድረስ ተችሏል፡፡ ባህርዳር፣ አክሱም፣ ሐዋሳ፣ ጐንደርና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚዎች ሲሆኑ፣ በወለጋ፣ ሰመራ ጅግጅጋና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎችም በሰፊው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቹ አማካይነት ክረምት ላይ በፊዚክስ፣ ሒሳብ፣ አይቲ፣ ኬሚስትሪና በባዮሎጂ የአንደኛ ደረጃና ከዛ በላይ ያሉ ተማሪዎችን በመቀበልና የዩኒቨርሲቲ ላብራቶሪዎችንና መምህራንን በመጠቀም ወጣቶች እንዲሠለጥኑ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡና ከፍተኛ ክህሎት ያላቸው ተማሪዎች በየአካባቢው በየደረጃቸው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች የመማር ዕድሉን እኩል እንዲያገኙ ምን ዓይነት ዘዴ ነው የተቀመጠው?

ዶ/ር ዓለማየሁ፡- ቀደም ብሎ ታቅዶ የነበረው አካባቢያቸው ባለው የሳይንስ ክበብ ላይ የተደራጁ ልጆችን መርጦ መውሰድ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር ተወያይተን የተለያዩ ድጋፎች ማለትም የመኝታ፣ የምግብ እንዲሁም የአይቲ አቅርቦት ከተሟላላቸው ለምን በተወሰኑ ክልሎች ብቻ ይሰጣል? በሚል ሐሳብ ከትግራይና ከአፋር እንዲሁም ከሌሎች ክልሎች ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ተማሪዎችን መልምለው ቦታው ድረስ በራሳቸው ትራንስፖርት በማጓጓዝ ዕድሉን እንዲያገኙ ተደረገ፡፡

ሪፖርተር፡- በሳይንስ ማዕከሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከማስተማር ባሻገር በተጨማሪ የተሠራ ነገር አለ?

ዶ/ር ዓለማየሁ፡- ከሳይንስ ማዕከላቱ በተጨማሪ የሳይንስ ሙዚየሞችን መክፈት ሌላኛው ዕቅድ ነው፡፡ ለዚህም በአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ሙዚየም አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በቀጣይ ግን ከዕርዳታ አድራጊው አካል ጋር በመሆን ወደፊት ለማስፋፋት ታስቧል፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎች ተምረው ብቻ ራሳቸውን የሚመዝኑበት ዕድል ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡ ለዚህም መንግሥት ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ የሳይንስ ማዕከል እንዲስፋፋ ዕርዳታ እያደረገ የሚገኘው ሚስተር ማርክ ገልፋንድ፣ የተለያዩ ገንዘቦችን በማሰባሰብ ለአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በቀጣይ ሙዚየሞችን ለማስፋፋት እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ያሉትን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በቀጣይ የታሰቡ ነገሮች አሉ?

ዶ/ር ዓለማየሁ፡- ባለፉት ስድስት ዓመታት ለተማሪዎቹ የተለያዩ መንገዶች ተመቻችቶላቸው በተወሰነ ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ የሳይንስ፣ የፊዚክስ፣ የኬሚስትሪና የሒሳብ ሕጎችን እንዲቀስሙ ተደርገዋል፡፡ በተቃራኒው ግን ምንም እንኳ የሳይንስ ማዕከሎች ቢስፋፉም፣ እነዛን በአግባቡ ያልተጠቀሙ አሉ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች እንዲያውም በመገልገያ ዕቃዎቹ ላይ ሲቆለፍባቸው ተስተውሏል፡፡ የተሻለ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እንደ ቢሾፍቱ፣ ሐዋሳ፣ ባህርዳርና መቐለ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቀሪዎቹ ግን መሥራት ያለባቸውን ያክል ሲሠሩ አይስተዋልም፡፡

ለዚህም መፍትሔ ይሆን ዘንድ የእስራኤልና ሩሲያ ልምድ በመቀመር የሳይንስ ተማሪዎችን ብቻ መልምለን ማስተማር የሚለው ሐሳብ ላይ ደርሰናል፡፡ የሳይንስ ማዕከል ካላቸውና በጥሩ ላብራቶሪና መምህር ማስተማርና በመካከላቸው ፉክክር እንዲፈጠር በማድረግ ውድድር ማዘጋጀት አንደኛው መንገድ ነው፡፡

ሁለተኛ መፍትሔ ደግሞ ከሩሲያ የወሰድነው በኮምፒተር የላቀ ደረጃ የደረሱ ልጆችን በመምረጥ በዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ዕውቀት ባላቸው መምህራን ማስተማር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከትምህርት ቢሮና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመነጋገርና ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመተባበር በ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ (Science Sherd Campus) በሚል ስያሜ ተማሪዎችን በመሰብሰብ በወንድይራድ ትምህርት ቤትና ኮተቤ እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡ ይህም በማርክ ግልፈንድ ለላብራቶሪና ለመምህራን ወጪ የሚሆን የ65 ሺሕ ዶላር ድጋፍ በማድረግ ተጀምሯል፡፡ በመጀመሪያ ዓመትም ብዙ ተማሪዎች ለመማር ተመዝግበው 90 ያህሉ ሥልጠናቸውን ጀምረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን በተጓዛችሁበት መንገድ ውስጥ እንደ ችግር የሚነሳው ምንድነው?

ዶ/ር ዓለማየሁ፡- ምንም እንኳ የእስቴም ሲነርጂ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መሥረት ቢጀምርም የተለያዩ ክፍተቶች አሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎቹ ትኩረት በመስጠትና ተማሪዎችን በውጤታቸው መዝኖ በአግባቡ ሥልጠና ያለመስጠት አንዱ ክፍተት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከታች ካሉት ትምህርት ቤቶች ጋር ተቆራኝተው ያለመሥራት ችግርም አለ፡፡ በትምህርት ቢሮዎችም ሆነ በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም በአሠራር ግን መደገፍ አለበት፡፡ ምክንያቱም አንድ ዩኒቨርሲቲ በአግባቡ ከሠራ ሌላውም በዛው መንገድ መጓዝ አለበት፡፡ ቢያንስ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ኮተቤው ትኩረት በመስጠት የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ዓይነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዲሁም የሥርዓተ ትምህርቱ (ካሪኩለም) ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም የሳይንስ ትምህርት አሰጣጥ በሁሉም ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ያላችሁ ግንኙነት እምን ድረስ ነው?

ዶ/ር፡- ቀደም ብለን ስለሥራችን ነግረናቸው ነበር፡፡ እስቴም ሲነርጂ ራሱ በሳይንስ ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር እንዲሆን ጥያቄም ብናቀርብም አልተሳካም፡፡ ሚኒስቴሩ በቀጣይ ተማሪዎች የሚማሩበትና ሙዚየምም ለመገንባት እንዳቀደ ሰምተናል፡፡ ቀደም ብሎ ባደረግነው ውድድርም 54 ላፕቶፖችን ለሽልማት አቅርቦልናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከሳይንስ ማዕከላትና ከተለያዩ ሥፍራዎች የተወጣጡ ወጣቶችን ያሳተፈ ውድድር አካሂዳችሁ ነበር፡፡ ምን ይመስል ነበር?

ዶ/ር ዓለማየሁ፡- ውድድሩ በአብዛኛው ከእስቴም ማዕከላትና ከሁሉም ክልሎች በተውጣጡ መካከል ሲደረግ ከ60 በላይ ፈጠራ ይዘው ቀርበውበታል፡፡ ይዘው ከቀረቡት ፕሮጄክቶች አንጻር ሁሉም መሸለም ይገባቸው የነበረ ቢሆንም ካሳዩት ብቃት አኳያ 15 ልጆችን ብቻ 15 ላፕቶፕ መሸለም ችለናል፡፡ ግን ዋናው በዚህ ትንሽ ድጋፍ 60 የፈጠራ ልጆችን ማግኘት ከተቻለ፣ የበለጠ መሠረት እንደሚቻል ያሳየን ውድድር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ሳይንቲስት የሚሆኑ ታዳጊዎች አሏት ማለትም ይቻላል፡፡    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...