ወይዘሮ ብሌን ሰለሞን ወደ ዲዛይነርነት ሙያ ከገባች አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ሙያ ከመሰማራቷ በፊት በመንግሥት ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ትሠራ ነበር፡፡ ጥሩ የሚባል ደመወዝም ነበራት፡፡ ይሁንና ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የግሏን ሥራ ብትሠራ የተሻለ እንደሚሆን ታስብ ነበር፡፡ ስለዚህም ሥራውን አቁማ በምትፈልገው ሥራ ለመሰማራት የሚያስችላትን የዲዛይን ትምህርት መማር ጀመረች፡፡
ትምህርቱን እንዳጠናቀቀችም የራሷን ድርጀት ከፈተች፡፡ ቀለል ብለው የሚለበሱ ባህላዊ አልባሳትን በዘመናዊ መልክ ዲዛይን አድርጋ እየሰራች ለገበያ ታቀርብ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ በሁለት እግሩ መቆም እስኪችል ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ ‹‹አሥር ብር ለታክሲ ይቸግረኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በደንብ ከሠራሁ የኔ የምለው ትልቅ ነገር እንደሚኖረኝ አስብ ስለነበር ይህ ረብሾኝ አያውቅም›› ስትል ነገሮች እስኪስተካከሉ መንፈሰ ጠንካራ ሆና በትዕግሥት መሥራቷን ትናገራለች፡፡
በአንድ ወቅት ተዘጋጅቶ በነበረ የሥራ ፈጠራ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ስትል በከተማ ልማት አማካይነት የሥራ ፈጠራ ሥልጠና ወስዳለች፡፡ ይህም በሥራዋ ውጤታማ እንድትሆን ረድቷታል፡፡ በሥራ ፈጠራ ላይ በተዘጋጁ ውድድሮች በመሳተፍ ዕውቅና እንደተሰጣት ትናገራለች፡፡
በብዙ ጥረት ለስኬት ብትበቃም አንዳንድ ችግሮች እየተፈታተኗት ነው፡፡ ‹‹ከፍተኛ የሆነ የኮፒ ራይት ችግር አለ፡፡ አንድ አዲስ ሥራ ይዘን ስንወጣ ሌሎች አስመስለው በመስራት ዝቅ ባለ ዋጋ ለገበያ ያቀርባሉ፤›› ስትል በየስድስት ወሩ ሌሎች አዳዲስ ዲዛይኖችን ለመሥራት እንደሚገደዱ ትናገራለች፡፡
አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማግኘትም ብዙ እንደሚቸገሩ ብሌን ተናግራለች፡፡ ‹‹አንድ ነገር ለማሸመን ከሸማኔ ጋር ተዋውለን ቀብድ ከከፈልን በኋላ የተሻለ ሥራ ሲያገኙ የያዙትን ቁጭ አድርገው ሌላ ይሠራሉ፡፡ በተቀጣጠርንበት ጊዜ ስንሄድ አለመሠራቱን ይነግሩናል፡፡ ጀምረው የማይጨርሱበት ሁኔታም አለ፤›› ብላለች፡፡
የኢንተርፕሩነር ልማት ማዕከል ሥራ ፈጣሪዎች በሥራቸው የሚያጋጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች እንዴት ማለፍ እንደቻሉ ለሌሎች ልምድ የሚያካፍሉበትን መድረክ ሰሞኑን በጽሕፈት ቤቱ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ብሌንም ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ከተጋበዙ ስራ ፈጣሪዎች መካከል ነበረች፡፡
በዕለቱ በጂብሰምና በፕላስቲክ ምርት ላይ የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎችም ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ተደርጓል፡፡ የውጭ አገር ድርጅቶች በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ እየተሰማሩ ዋጋ ሰብረው ምርት የሚያከፋፍሉበት ሁኔታ መኖር ጤናማ ፉክክር እንዳይኖር ማድረጉን፣ ከውጭ አገር በወረደ ዋጋ ተገዝተው ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታም ከገበያ ውጪ እያደረጋቸው እንደሚገኝና ይህም ገበያ ውስጥ ለመቆየት ፈተና እንደሆኑባቸው በውይይቱ ላይ አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም የተማረ የሰው ኃየል እጥረት፣ የፋይናንስ ችግርና ሌሎችም በስራቸው እድገት እንዳያሳዩ ማነቆ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ኢንጂነሪንግ ምሩቋ ቤተልሔም ወርቁ ከተጋባዥ እንግዶች መካከል ነች፡፡ ማንኛውንም ዓይነት የህትመትና የማስታወቂያ ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት ከፍታ መሥራት ከጀመረች ሁለት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ ባለፈው ዓመት የሥራ ፈጠራ ሥልጠና ወስዳ ነበር፡፡ ‹‹ሥልጠናውን ከወሰድኩ በኋላ ሥራዬን በደንብ እንድሠራና በሌሎች ሥራዎች እንድሰማራ ሞራል ሆኖኛል፡፡ ከሥልጠናው በኋላ ወደ ሚዲያው ኢንዱስትሪ እንድገባ የራሴን የሬዲዮ ፕሮግራም እንዳዘጋጅ አድርጎኛል›› ትላለች፡፡
ተጨማሪ የህትመት ማሽኖችን በማምጣት የድርጅቱን አቅም ከፍ የማድረግ ፍላጎት አላት፡፡ ይሁንና ባለባት የካፒታል ችግር ከፍላጎት በዘለለ ወደተግባር ማለፍ ከባድ ሆኖባታል፡፡ ያለባትን የገንዘብ ችግር ከባንክ ብድር በመውሰድ ለማስተካከል ብታስብም የሚጠይቁት መያዣ (ኮላትራል) ከእሷ አቅም በላይ ነው፡፡ አጋጣሚው ድርጅቱን በምትፈልገው መጠን ለማሳደግ እንዳትችልና ተፎካካሪ እንዳትሆን እንዳደረጋት ትገልጻለች፡፡ ‹‹በረዥም ጊዜ የምንከፍለው የብድር ዕድል ቢመቻችልን ጥሩ ነው›› ስትል የብዙዎች ሥራ ፈጣዎች ችግር የሆነውን የካፒታል ችግር በዚህ መንገድ ማስተካከል እንደሚቻል እምነቷን ትገልጻለች፡፡
የውይይት መድረኩን ሲመሩ የነበሩት በኢንተርፕሩነር ልማት ማዕከል የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ሰርቪስ ማኔጀር ወይዘሮ ሃና ፈለቀ እንዳሉት፣ ድርጅቱ ለኢንተርፕሩነሮች በአመለካከት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡትም በነፃ ሲሆን እስካሁን 33,000 ለሚሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች ሥልጠና መስጠት ተችሏል፡፡ ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ የሒሳብ አያያዝ፣ የቢዝነስ ፕላንና የገበያ ትስስርን በተመለከተ የማማከር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ይህኛው የማማከር አገልግሎት ግዴታ አይደለም፡፡ ነገር ግን ቢጠቀሙበት ትልቅ ለውጥ መፍጠር የሚቻልበት ነው፡፡ ሥልጠናውን ከወሰዱ 33,000 ሰዎች መካከል አገልግሎቱን ፈልገዉ የተጠቀሙበት 7000 ብቻ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የመነሻ ካፒታል ችግር አለባቸው፡፡ የረጅም ጊዜ የቢዝነስ ግብና የመሳሰሉት ችግሮች መኖርም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡
የኢንተርፕሩነር ልማት ማዕከሉ የተቋቋመው ከሦስት ዓመታት በፊት በዩኤንዲፒ ድጋፍ ነው፡፡ ለማእከሉ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው ዩኤንዲፒ ሲሆን፣ የሚተዳደረው ደግሞ በመንግሥት ነው፡፡ በየክልሉ ቢሮ የከፈተ ሲሆን፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም ይሠራል፡፡