በአዲስ አበባ ከተማ፣ ባለፈው እሑድ ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ታላቁ ሩጫ፣ ተሳታፊዎቹ ካሸበረቁባቸው ነገሮች አንዱ የአሜሪካ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምስል ነበር፡፡ ትራምፕ እየጮሁ ከሚናገሩበት ፎቷቸው ግርጌ የተጻፈው የእንግሊዝኛ መልዕክት ‹‹Make Ethiopiam Athletics Federation Great Again›› [የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ዳግመኛ ታላቅ አድርግ] የሚል ለኃይሌ ገብረሥላሴ የተላለፈ መልእክት አድርገው ሥለውታል፡፡ ከ42 ሺሕ በላይ በተሳተፉበት የ10 ኪ.ሜ ሩጫ፣ አካል ጉዳተኞች በክራንችና በተሽከርካሪም ተሳትፈውበታል፡፡
* * *
የሚሉት አያጡ
አሯሩጠው ሳያደክሙኝ
ወይ ላይጥሉ ሲጎትቱኝ
ተከላክለው ሳያስጥሉኝ
ከወጠንኩት ላያስቀሩኝ
ከፊት ቀድመው ተገትረው
ከመንገዴ ተደንቅረው
ሊያዳክሙኝ ተማምለው
ደግሞ አስወሩ ሰነፍ ብለው፡፡
ሰውነቴን ተጠራጥረው
ሙሉነቴን አውቀው ንቀው
በኔነቴ ቢሳለቁ
ቢናገሩኝ ቃል አስከፊ
እንዳልሰማ ባቀረቅር
ብለው አሉ አንገት ደፊ፡፡
በራሴ ዓለም ተወስኜ
ደግሞ ብኖር ለብቻዬ
ብለው እርፍ ይኼ አውሬ፡፡
ፍስሃ ተክሉ፤ የግዞት ዓለም፤ 2008 ዓ.ም.
* * *
የግብፅ ሴቶች የብስክሌት ግልቢያ ንቅናቄ
ግብፅ ውስጥ ብስክሌት የሚጋልቡ ሴቶች መመልከት የተለመደ አይደለም፡፡ ብስክሌት የሚጋልቡ ጥቂት ሴቶችም ከማኅበረሰቡ ቀና አቀባበል አይደረግላቸውም፡፡ እንዲያውም ወሲባዊ ትንኮሳና ስድብ ይደርስባቸዋል፡፡ ይኼንን ሁኔታ ለመቀየር ቆርጠው የተነሱ አምስት ግብፃውያን ሴቶች የብስክሌት ግልቢያ የሚያካሂዱ ሴቶችን በመሰብሰብ ተቃውሟቸውን ለማሰማት እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ‹‹ዜር ኢዝ ኖ ዲፈረንስ›› (ልዩነት የለም) በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ሴቶች፣ ማኅበረሰቡ ሴት ብስክሌት ጋላቢዎችን የሚያይበትን መንገድ እንዲያስተካክል ይሻሉ፡፡፡ የመጀመርያ ዕርምጃቸው ደግሞ በርካታ ሴቶችና ወንዶች የተሳተፉበት የብስክሌት ግልቢያ ማዘጋጀት ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት የተዘጋጀው ግልቢያ የብዙዎችን ትረኩት አግኝቷል፡፡ ሴቶቹ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው እንደሚገፉበትም እየገለጹ ነው፡፡
* * *
በሞባይል ምስል የሚሰየሙት ጎዳናዎች
ዛሬ ዛሬ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ሲላክ ከጽሑፍ ጋር የሚጣጣም ምስል (ኢሞጂ) አያይዞ መላክ የተለመደ ሆኗል፡፡ የፊንላንድ መንግሥት ይኼንን ከግምት በማስገባት በቅርቡ ግንባታቸው የተጠናቀቀ ሁለት ጎዳናዎችን ‹‹ኢሞጂ ስትሪት›› እና ‹‹ሜሜ ስትሪት›› በሚል ለመሰየም ማሰቡን አሳውቋል፡፡ ጎዳናዎቹን በዘመን አመጣሽ የሞባይል ስልክ ምስሎች መጠሪያ ለመሰየም ያሰበው የአገሪቷ መንግሥት ጉዳዩን ለሕዝብ አስተያየት ክፍት ማድረጉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የሁለቱ ጎዳናዎች አርክቴክት ጁሃ አንቲላ ‹‹ዘመናዊ የሆነ ስያሜ ለጎዳናዎቹ መስጠት እንፈልጋለን፡፡ ከስያሜዎቹ በመነሳት 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ምን እንደሚመስል ቀጣዩ ትውልድ መገንዘብም ይችላል፣›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሐሳቡን የሚደግፉ የአገሪቱ ዜጎች ዘመናዊ የጎዳና ስያሜ አስፈላጊ እንደሆነ በማኅበረሰብ ሚዲያ እየገለፁም ነው፡፡
* * *
የሠራተኞች መግቢያን ያልተጠበቀ ሰዓት ያደረገው ኩባንያ
ኩባንያው በሲልከን ቫሊ የሚገኝ ሲሆን፣ ከሌሎች መሰል ኩባንያዎች ጋርም ሆነ ሌሎች ተቋማት ጋር ሲነፃፀር የሠራተኞች የሥራ መግቢያ ብሎ ያስቀመጠው ሰዓት ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቧል፡፡ የድርጅቱ ሠራተኞች ጠዋት 3፡00 የሥራ ሰዓት መጀመርያ እንዲሆን ሲያደርግ ነፃ ቁርስም ያቀርባል፡፡ የኩባንያው መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሮብ ሚ ለቢቢሲ እንደለገጹት፣ እንደተለመደው ሁለት፣ ሁለት ተኩል እንዲህ እንዲህ እያሉ የሥራ መግቢያ ከሚደረግ ይልቅ ያስቀመጡት ሰዓት ሠራተተኞች ሰዓት አክብረው ሥራ ገበታቸው እንዲገኙ ስነ ልቦናዊ እገዛ ያደርጋል፡፡ ቁርሱም ተመሳሳይ አወንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ የተለያዩ ኩባንያዎች ሠራተኞችን ለማበረታታት የተለያዩ ነገሮችን የሚያደርጉ ሲሆን፣ ኤጀንት የተሰኘው የእንግሊዝ አገር ማርኬቲንግ ኩባንያ በመሰል የስካንዴኔቪያን ኩባንያ ዕርምጃ በመነሳሳት የሥራ ሰዓት ስምንት ሳይሆን ስድስት እንዲሆን አድርጓል፡፡
* * *
ዝ መጽሐፍ
‹‹ጣዕም ያላቸው የሕፃናት ምግቦች ለመጀመርያዎቹ አንድ ሺሕ ቀናት››
እናቶች በእርግዝናቸው ወቅት መመገብ የሚገባቸውን ምግብና ልጆቻቸው ከተወለዱ በኋላ ለሁለት ዓመት ቢመግቧቸው ተመራጭ የሆኑ ምግቦች አዘገጃጀትን የሚገልጽ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል ‹‹ጣዕም ያላቸው የሕፃናት ምግቦች ለመጀመርያዎቹ አንድ ሺሕ ቀናት›› የተሰኘው መጽሐፍ ልጆች ከተወለዱ በኋላ በተለያየ ወራት ዕድሜያቸው መመገብ የሚገባቸውን ከ50 በላይ የምግብ ዓይነቶች አካቷል፡፡ ስለምግብ ማብሰያና መመገቢያ ቁሳቁሶች እንዲሁም የምግብ ዓይነቶችና ጥቅሞቻቸው በ106 ገጽ አካቷል፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጆች ሜላት ዮሴፍና ህሊና በለጠ ሲሆኑ፣ መጽሐፉ በ150 ብር ገበያ ላይ ይገኛል፡፡
* * *
‹‹ዝረፈኝ››
በአመለወርቅ ኃይሉ የተጻፈው ‹‹ዝረፈኝ›› የተሰኘው የግጥም መድበል እሑድ ኅዳር 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡30 ጀምሮ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በዕለቱ ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችም ይቀርባሉ፡፡