Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምዶናልድ ትራምፕ የተተቹባቸው አዳዲሶቹ ሹማምንት

ዶናልድ ትራምፕ የተተቹባቸው አዳዲሶቹ ሹማምንት

ቀን:

የነጭ የበላይነት አቀንቃኝ ናቸው የሚባሉትና 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ. በ2017 ለሚጀምሩት የሥልጣን ዘመናቸው ቁልፍ ሥራ የሚመሩላቸውን ባለሥልጣናት ከወዲሁ እየሾሙ ነው፡፡ ሹመታቸው የነጭ አክራሪነት የተጠናወታቸው ላይ ማነጣጠሩ ግን፣ ትራምፕ በሌሎች ላይ ያላቸውን ጥላቻ ቁልጭ አድርጎ ያወጣ ነው አስብሏቸዋል፡፡

ሐፊንግተን ፖስት እንደሚለው፣ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ሆነ ከዚህ ቀደም ዘረኝነትንና ልዩነትን የሚያጎሉ የተለያዩ ንግግሮችን አድርገዋል፣ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፡፡

አሜሪካ ኢራቅ ውስጥ በነበራት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሕይወቱን ላጣውና የክብር ኮከብ ሜዳልያ ተሸላሚ ለሆነው ሙስሊም አሜሪካዊና ለቤተሰቦቹ ያሳዩት ክብር መንፈግ፣ ‹‹በትራምፕ ዩኒቨርሲቲ›› ላይ በነበረ ክስ ዳኛ የነበሩት ጐንዛሎ ክሩየል የሰጡትን ውሳኔ አስመልክቶ፣ ‹‹ዳኛው የሜክሲኮ ደም ስላለበት ነው፤›› ማለታቸው ከሚያስተቿቸው ንግግሮች ይጠቀሳሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1973 የቤተሰባቸውን ሪል ስቴት ሲያስተዳድሩ ቤቶችን ለጥቁር አላከራይም በማለታቸውና በቀለም ላይ ባላቸው አድልኦ መከሰሳቸው፣ በ1992 በአትላንቲክ ሲቲ በሚገኘው ‹‹ትራምፕስ ካዚኖ›› ውስጥ የሚሠሩ ጥቁር ሠራተኞችን ‹‹ሰነፍ፣ ጥቁር አይሠራም›› ብለው በመሳደባቸውና እሳቸው ወደ ካዚኖው ሲገቡ ጥቁር ሠራተኞች በሙሉ ጓዳ እንዲደበቁ የሚደረጉ መሆኑ በመረጋገጡ የኒውጀርሲ ካዚኖ ኮንትሮል ኮሚሽን 200,000 ዶላር የቀጣቸው መሆኑ፣ ትራምፕን ወግ አጥባቂና ብሔርተኛ ካስባሉ ድርጊቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ትራምፕ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት፣ ለእሳቸው ቅስቀሳ ያደርጉ የነበሩትና የኬኬኬ ወይም ‹‹ዘ ክላን›› በመባል የሚታወቀው ንቅናቄ የቀድሞ መሪ ዴቪድ ዱክ፣ ‹‹ከትራምፕ ውጪ ሌላ ፕሬዚዳንት መምረጥ የራሳችሁ ቅርስ ላይ የአገር ክህደት እንደፈጸማችሁ ይቆጠራል፤›› ማለታቸውን አለማውገዛቸው፣ ይህን አስመልክቶ ለተነሱ ትችቶችም ቦታ አለመስጠታቸው፣ ዘረኛና በጥላቻ ንግግር የተሞሉ እንዲባሉ አድርጓቸዋል፡፡

‹‹ሂስፓኒክ››፣ ‹‹ሙስሊም››፣ ‹‹ብላክ›› እንዲሁም ‹‹ሜክሲካን›› የሚሉ ልዩነትን የሚያጎሉ ንግግሮችን በማድረግ የሚተቹት ትራምፕ፣ ከወር በኋላ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚመሠርቱትን አዲስ መንግሥት ለማዋቀር፣ በእስልምና ላይ ጭፍን ፍራቻና ጥላቻ አላቸው ከሚባሉት ምሁር ፍራንክ ጋፍኒ ምክር እንደሚያገኙ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

በነጮች የበላይነት ላይ የማይደራደሩት ትራምፕ፣ የነጮች ብሔርተኝነት አቀንቃኙን ስቴፈን ባኖን ዋና የስትራቴጂ አማካሪ አድርገው ሾመዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የሪፐብሊካን ብሔራዊ ኮሚቴ መሪ የነበሩትን ሬንስ ፕሪበስን የዋይት ሐውስ የበላይ ሹም አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ሥልጣኖች የሴኔቱን ይሁኝታ ማግኘት የማይጠበቅባቸው ናቸው፡፡ የትራምፕ የሹመት አካሄድ በዴሞክራቶችም ሆነ በሪፐብሊካን እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሰላ ትችት እየገጠመው ነው፡፡ የሪፐብሊካኑ ስትራቴጂስት ጆን ዊቨር የትራምፕን የሹመት አመራረጥ ‹‹ዘረኛና ፋሽስት›› ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ማስፈራቸውን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡

በአሜሪካ ከጥላቻ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን የሚከታተለው ሳውዘርን ፖቨሪቲ ሎው ሴንተር፣ ሚስተር ባኖንን ‹‹የነጭ ብሔርተኝነት ፕሮፓጋንዳ መፍለቂያ›› ይላቸዋል፡፡

የሲአይኤ የቀድሞ ኦፕሬቲቭ ኢቫን ማክሙሊን፣ የባኖንን ሹመት ሪፐብሊካን እንዲያወግዙት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ለአሜሪካውያን በሕይወት ዘመናችን ከእኩልነትና ከነፃነት የበለጠ ወሳኝ ጉዳይ የለም፤›› ሲሉም ባኖን ለሹመቱ እንደማይመጥኑ ተናግረዋል፡፡

ባኖን አክራሪ ነጭ ናቸው ቢባልም፣ በአቋማቸው የሚደግፉዋቸውም አልጠፉም፡፡ የኬኬኬ የቀድሞ መሪ ዴቪድ ዱክ ሚስተር ባኖንን፣ ‹‹እንኳን ደህና መጣህ›› ካሉ ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹ባኖን ወዴት መሄድ እንዳለብን መሠረታዊ የፖለቲካ አቅጣጫ የሚያስቀምጥልን ነው፡፡ የፖለቲካ አቅጣጫ ደግሞ የማንኛውም መንግሥት መሠረት ነው፤›› ሲሉም ለሲኤንኤን ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ ለካቢኔያቸው ወግ አጥባቂዎችን መምረጣቸው ቢያስተቻቸውም፣ ከማድረግ አልተቆጠቡም፡፡ ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከኢራን ጋር ያደረጉትን የኑክሌር ስምምነት በመቃወም የሚታወቁትን የ52 ዓመቱ ማይክ ፖምፒዮ የሲአይኤ ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሾመዋል፡፡ የሚስተር ፖምፒዮ ሹመት የሚፀድቀው የሴኔቱን ይሁኝታ ሲያገኝ ቢሆንም፣ በእሳቸው በኩል ግን በትራምፕ ለተሰጣቸው ሹመት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ ፖምፒዮ ሒላሪ ክሊንተን የግል የኢንተርኔት ሰርቨር መጠቀማቸውን አጥብቀው የሚቃወሙና የአሜሪካን ሚስጥር ዘክዝኮ ያወጣው ኤድዋርድ ስኖውደን በሞት መቅጣት አለበት ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የጦር መሣሪያ ንግድ ስምምነት እንዳትፈርም የተደረገውን ተቃውሞ የደገፉ ሲሆን፣ ጓንታናሞ እስር ቤት እንዳይዘጋ የተሟገቱም ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በነበራቸው የሁለት ጊዜ የሥልጣን ዘመንም ቃል በገቡት መሠረት ጓንታናሞን እንዳይዘጉ ካደረጉ ተቀናቃኞች አንዱ ነበሩ፡፡

ሪፐብሊካኑ ዕጩ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ባደረጉት ቅድመ ምርጫ ፖምፒዮ የሚታወቁት ትራምፕን በመተቸት ነበር፡፡ ለፍሎሪዳው ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩት ፖምፒዮ፣ በኋላ ትራምፕን መደገፍ መጀመራቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ ፖምፒዮ በአርበኝነት ያገለገሉ የምክር ቤት አባልና የቀድሞ የጦር ሠራዊት መኮንን ሲሆኑ፣ በምክር ቤቱ የደኅንነት ኮሚቴ ውስጥም አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 በሊቢያ ቤንጋዚ በአሜሪካ ዲፕሎማቶች ላይ የደረሰውን የሽብር ጥቃት በመረመረው ኮሚቴ ውስጥ ሠርተዋል፡፡ በዚህም በእስረኞች ላይ አስከፊ የምርመራ ዘዴ ተጠቅመዋል ተብለው ይተቻሉ፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ለአሜሪካ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግነት በነጭ አክራሪነት የሚታወቁትን ሴናተር ጄፍ ሴሽንስ ሲሾሙ፣ የቀድሞውን ጡረተኛ ሌተና ጄኔራል ማይክል ፍሊን ደግሞ ለብሔራዊ ፀጥታ አማካሪነት ሾመዋቸዋል፡፡ ጄኔራሉም ነውጠኛና የነጭ አክራሪነት እንዳለባቸው ይነገራል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ቀሪዎቹን ሹመቶች በእነማን እንደሚሞሉዋቸው የበለጠ ተጠባቂ ሆኗል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...