Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በተነፉ ደረቶች ውስጥ የተነፈሱ እብሪቶች!

እነሆ መንገድ! ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ነው። ቁጭት በነበር መዝገብ እየተመዘገበ፣ ተስፋ ነጋችንን እየቀረፀው መንገድ አልሰለቸን ብሎ እንጓዛላን። ወቅት አስልቶ፣ ከጊዜ ጋር አብሮ የአረማመድ፣ የአኗኗርና የአስተሳሰብ ሥልት የሚያበጅልን የአብዛኞቻችን ጎዳና አንድ ነው። ሥሌቱን የማንደርስበት፣ ክፍልፋዩን ቆጥረን የማንጨርሰው፣ አሻራው ከባድ የሆነ የሰው ልጆች የውጣ ውረድ መድረክ ይኼው ጎዳና ነው። እግረኛው፣ ባለአውቶሞቢሉ፣ አውቶብስና ታክሲ ተጠቃሚው የሚያጣድፍ እያጣደፈው በወጣችለት ፀሐይ በበራለት የንጋት ብርሃን ነግዶ ለማትረፍ፣ ዘርቶ ለማጨድ ይጓዛል። ጉዞው ቀልብ አያውቅም። ስንክሳሩ ተራኪን ያደክማል። የግርግሩ መናኸሪያ በትዝብት ጢስ ታጥኗል። እያንዳንዱ በገዛ ራሱ የሕይወት መስመር ታቅዶ የሚጠብቀው፣ ተጀምሮ ያላላቀ አጀንዳ ባለቤት ነው። እጅግ አስገራሚው ነገር ደግሞ አቅጣጫ ይዞ እየሄደ አቅጣጫው የጠፋበት ብዛቱ ነው። ቅስም ይሰብራል ይኼን ለሚያይ።

የሚጠሉትን እንደሚያፈቅሩት አምነው፣ የሚሹትን እንደሚንቁት ቆጥረው የግፊያውን ሠልፍ ያደመቁት ነፍሶች ጥቂት አይደሉም። ከቶ ምን ቃል ይኼን ቅስም የሚሰብር ትዕይት ይገልጻል? ጥቂት ከፈት ብለው ብርሃናቸው በሚታይ ጥርሶች ጀርባ ጥቁር የሐዘን ጭስ ይንበለበላል። የሆነውን ከመሆን አልፎ ሕዝበ አዳም ራስን ፈልጎ የማግኘት ማስተዋል ፍፁም ርቆታል። ይህን መሰል አብረክራኪ እውነት ጎዳናው ላይ ያፏጫል። ቀና ብለው በሚራመዱ ሰዎች ውስጥ የጎበጠ ማንነት ድንቅር እያለ ዕይታን ያጥበረብራል። ‹‹ምድሪቷ ቂሟ ከማን ጋር እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም፤›› ይላል አንዳንድ አልፎ ሂያጅ። ስብራት የሚጠግን ጊዜ ተፈጥሮ መንፈስ የሚያድስ ብሔራዊ መግባባትን የሚያሰፍን የሕዝብ የበላይነት ያልናፈቀው የለም። ደመኝነትን ታሪክ የሚያደርግ ተግባር ያልናፈቀው ማግኘት ያዳግታል። ከመጋቢው መንገድ እስከ አውራ ጎዳናው መሀል ተዘርሮ ፀሐይ የሚሞቅ ሀቅ ይህ ነው። 

‹‹ሞልቷል ሳበው!›› አለ ወያላው  ዘሎ  እየገባ። ‹‹ምን ይሞላል ብለህ ነው የዚህ ዓለም ነገር?›› ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ አዛውንት ናቸው። ‹‹አይዞን! አንድ ቀን ዓለምም ብትሆን እንደዚች ታክሲ መሙላቷ አይቀርም፡፡ ዓለም ባትሞላ ሲኦልና ገነት ቀድመው ሞልተው ይገላግሉናል፤›› አላቸው። ‹‹ምን? ምን? ሆሆ! ስቴዲየም መሰሉህ እንዴ እንዲህ እንደምታስበው ጢም የሚሉት? መጀመሪያ እስኪ ዓለም ትሙላ። ይቀልዳል እንዴ ይኼ?! እንኳን ዓለም መቼ ሞባይላችንስ ሞላ? እንፍቃለን የለም። ኪሳችን ባዶ። ሆዳችን ባዶ። ኔትወርክ ባዶ። እኮ ዓለም ናት የምትሞላው?›› አሉት አንዴ በመስኮቱ አሻግረው ወደ ውጭ እየተመለከቱ፣ አንዴ ደግሞ ወደወያላው ዞረው ዓይን ዓይኑን እያዩ። ‹‹ታዲያ ምን ተሻለ ይላሉ?›› አላቸው ሾፌራችን። የወያላውን ተግባቢነት ለመንጠቅ ይመስላል።

‹‹የዘመኑ ሰው በውድድር ስም የማይነጣጠቀው ነገር የለም›› ይላል ከጎኔ። ‹‹ምን ይሻላል? ጊዜን ከዚህ የበለጠ ለመታዘብ ዕድሜ መለመን! አበቃ። ምንም የሚሻል ነገር የለም። ደግሞ በዚህ ጊዜ ምኑን ትቼ ምኑን እተወዋለሁ ልጄ። እንዲያው በአጠቃላይ ፖለቲካን ማመን ኢኮኖሚን ማመን አያስፈልግም። እኛም እኮ አልሰማ ብለን እንጂ ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም ተብለናል፤›› አሉት። ሳቀ ሾፌራችን። ‹‹መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያችን መሥራት እንዲጀምር ቢያንስ መፍትሔ የለዎትም?›› ቢላቸው አጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት ተራቸውን ሳቃቸውን ለቀቁት። ‹‹አንተ? ተወኝ ስል አትሰማም እንዴ? አንተስ ብትሆን አርፈህ ውሎህን ጨራርሰህ በሰላም ወደቤትህ ብትገባ አይሻልም?  . . . እ? ምነው አንተን ባደረገኝ! ያልተነካ አቤት ግልግል ሲችልበት እኮ?›› እያሉ አሽሟጠጡት። ወጣቱ ግራ ተጋብቶ አፍሮ ዝም አለ። ወያላው ነገሩን እንደገና አንስቶ፣ ‹‹‘ፋዘር’ ታዲያ ነገራችን ሁሉ መቆራረጥ በበዛበት ዘመንና ምድር ላይ ለመኖር ምን ዕድሜ አስለመንዎ?›› አላቸው። ‹‹የለም! ርስት ልለምን ኖሯል? ያውም በሊዝ የገባ መሬት? ኧረ እባካችሁ ተውኝ ብያለሁ ዛሬ። ነው ምክክር አላችሁ የሰው የማናገር?›› ብለው ቁጣ ቁጣ አላቸው። ‹‹ይቅርታ ‘ፋዘር’ አስቆጣሁዎት መሰለኝ?›› ብሎ ሳይጨርስ በድጋሚ፣ ‹‹ወይድ ቀጣፊ! ወትሮም ተደራጅተሽ ስታበቂ ሰውን ክፉ ለማናገር እሳት መጫር ሙያ መስሎሻል አዳሜ? ቆይ ግድ የለም!›› ብለው አፈጠጡበት። ወያላው ቀልቡ ተገፎ አመዱ ሲቦን ትዕይንቱ ዘና ያደረጋቸው ተሳፋሪዎች ይሳሳቃሉ። ወይ መንገድና ድዱ!

ጉዟችን ቀጥሏል። በብዛት ከተደረደሩ ጥቅሶች መሀል አንዷን አስተውሎ ያነበበ ወጣት መናገር ጀመረ። ‘ፍጥነት ዕድሜን ያሳጥራል እንጂ ጊዜን አይቆጥብም’ ትላለች። ገርሞት ፈገግ እንዳለ፣ ‹‹እኔ እኮ የማይገባኝ አሁን ይኼ ጥቅስ ለእኛ ነው መለጠፍ ያለበት? ወይስ ለሾፌሩ?›› ብሎ ጠየቀ። ‹‹ኧረ ተወኝ ወንድሜ!›› ይላል አጠገቡ የተቀመጠው ተሳፋሪ በሰለቸ ድምፀት። ወያላው ይገላምጠዋል። ለካ አላየነው ኖሮ እንጂ ጫቱን እያኘከ ነው።  ‹‹ወይ ይኼ ምርቃና? ስንቱን አጀገነው? ስንቱን አከሰረው? ስንቱን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ስንቱን ካርል ማርክስ፣ ስንቱን መንገድ ቀያሽ፣ ስንቱን ቀዶ ጠጋኝ አደረገው?›› ይላል ይኼን የሚያስተውል። ከጎኑ ያለው ተቀብሎ፣ ‹‹ስንቱን እንደሚያደርግ አርጎ እንዳይሆን አድርጎ አስቀረው ብለህ ጨምርበትማ። ስንቱ ትዳሩን ፈታ፣ ስንቱ ጥርሱ ሟሟ፣ ስንቱ መልኩ ጠፋ፣ ስንቱ ሙዱ ከፋ አትልም?›› ሲለው ወያላው ብግን ብሎ እንዳልሰማ ሆኗል። የሚስቅ ይስቃል።

ወዲያው የዋናው ርዕሰ ጉዳይ ጨዋታ ተመልሶ ተነሳ። ወጣቱ ‹‹በጣም እኮ ነው የሚገርመው። ‘ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ጠንካራ የልማት ሠራዊት እንፍጠር’ ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። ‘ለሙስና እጅ አንሰጥም’ ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። መቼ ይሆን ሁሉም የራሱን ጉድፍ ማጥራት የሚጀምረው?›› ይላል። አሁንም አጠገቡ የተቀመጠው፣ ‹‹ህም ድረቅ ቢልህ! ልፋ ቢልህ! ሰሚ ያለ መስሎሃል?›› ይለዋል፡፡ ‹‹ወሬ! ወሬ! ኧረ ወሬ ጠላሁ!›› ሲል ወያላው እንደ መወናጨፍ ይቃጣዋል። ‹‹የመጣ የሄደው ዝም ብሎ ሲቀደድ. .  . . አንተ ምን አለብህ የምቀዳው እኔ፤›› ብሎ ሾፌሩን ይተነኩሰዋል።  ሾፌሩ ግራ እንደመጋባት እያለ፣ ‹‹ታዲያ መደምሰስ ነዋ። ኮማንድ ፖስት ነህ እንዴ አንተ ምን ያስቀዳሃል ሰውስ ምን ያድርግህ? መሥራት ካልቻለ፣ መብላት ካልቻለ፣ ቢያንስ ማውራት መቻል የለበትም?›› ይለዋል በስፖኪዮ እያየው። ‹‹እውነት ነው! ስናወራ ነው የሚያምርብን፤›› አዛውንቱ ቅድም የጀመሯትን ሽሙጥ እንደማገባደድ አሉ። በዚህ መሀል ነበር አንዱ፣ ‹‹አይ እማማ ኢትዮጵያ! እስከ መቼ ይሆን የሞት ክብረወሰን ሰባሪ ሆነሽ የምትኖሪው?›› ብሎ በትራፊክ አደጋ አሳቦ ብዙ ነገር የተናገረው። ብቻ ለብቻ አንሳፈር ነገር ተደራርበንም አልተረፍን!

ወያላችን ከደም ፍላቱ ቀዝቀዝ ብሎ ሒሳብ እየተቀበለ መልስ ይመልሳል። መጨረሻ ወንበር ከሁለት ሴት ጓደኞቻቸው ጋር የተሰየሙ ወጣቶች ድንገት ወሬ ጀምረዋል። ‹‹ወንድሜ እዚህ አገር ስንዝር ለመራመድ ግንብ ማፍረስ እንደሚጠበቅብህ አልነግርህም። ቢሮክራሲው፣ ሕጉ፣ አስተዳዳሪው እኛን ማገልገል ሳይሆን ዓላማቸው የሚመስለው እኛ እንድናገለግላቸው ነው። ማን ወዶ ይሰንፋል? ማን መማር ይጠላል? ማን ማትረፍን ይንቃል? ግን ሁሉንም እንዳይሆን የሚያደርገው አጥር ነው። እና በዚህ መሀል እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት ብዬ ላስብ ወይስ እንዴት ብዬ በልቼ ልደር?›› ሲል ያኛው ብዙም ሊከራከረው አልፈለገም። ‹‹በልቶ ለማደር ማሰብ እንደ አስተዋጽኦ ይቆጠር ይሆን?›› ይላል ከጎኔ። ይኼን ሲለኝ ሰምቶት ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመ ጎልማሳ፣ ‹‹ምን ይታወቃል ጊዜው የኑሮ ውድነት ነው እኮ! የአገር ነገር ሲነሳ ሁሌም  ቢሆን ምሳጤ አይጠፋም። ሁሉም በየራሱ ህሊና ጅረት ይሆናል። ግራ ቀኝ እያየ አንዳንዴም ፊት ለፊት፣ ብቻ በዝምታ ያስባል። ኑሮ አንዳንዴ እንደሚታክተን አዕምሮን ማሰብ ቢታክተው ከተማችን የዕብድ መናኸሪያ መሆኗ ባላጠያየቀ ነበር፤›› አለው። ምኑ ከምኑ እንደሚገናኝ ሳይገባን ጎልማሳውን በጥርጣሬ ተመልክተን ደስ እንዲለው አንገታችንን በአዎንታ ነቀነቅን። ‹‹አይ አንቺ አገር መቼ ይሆን በልቶ ማደር ልጆችሽን በሐሳብ አዙሪት እየናጠ መድፋቱን የሚተዋቸው?›› እያሉ  አዛውንቱ ለብቻቸው ሲያጉተመትሙ፣ መጨረሻ ወንበር የተሰየሙት ወጣቶች ባልሰማ ሌላ ወሬ አውርተው ያሽካካሉ። አለመደማመጥ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መጨረሻ ወንበር የተሰየሙት ሴቶች የጓደኞቻቸው ደርሶ ኮስታራ መሆንና ኮስታራ ወሬ ማውራት እያስገረማቸው ይጠይቃሉ። ‹‹አንተ ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ አገሬ ኑሮዬ የምትል ልጅ የሆንከው? አርፈህ አበልህን እየበላህ አትኖርም እንዴ?›› ብላ አንደኛዋ ከት ብላ ስትስቅ ሌላይቱ ተቀብላ፣ ‹‹ኧረ በማርያም እንዲህ ስታወሩ አንዴ ቪዲዮ አንስቼ ፌስቡክ ላይ ሼር ላድርጋችሁ ፕሊስ? ኦ ለካ ፌስቡክ ብሎክ ተደርገናል። ወይኔ ግን ደስ ሲሉ እነዚህ ውብ አገር ወዳዶች፤›› እያለች ማላገጧን ቀጠለች። ይኼኔ ወንዶቹ አንበለጥም ዓይነት፣ ‹‹መቼም እንዳንቺ በዓመት አንዴ ታላቁ ሩጫ ከመሮጥ ቢረባም ባይረባም ስለአገር ስለኑሮ ማውራት ይሻላል፤›› ይሏቸዋል። ‹‹ውይ ውይ የሩጫውንስ ነገር አታንሳብኝ። ሲያቀብጠኝ በአለቀ ሰዓት እንሩጥ ልሩጥ ብዬ ሁለት ቀን ልተኛ?›› ብላ ወደ አንዱ ወዳጇ ደረት ልጥፍ ስትል፣ ‹‹እዚህ አገር እኮ ያስቸገራችሁት እናንተና እናንተን መሳዮች ናችሁ፤›› አላት ያኛው። ‹‹እነማ?›› ስትል ወዲኛው ተቀብሎ፣ ‹‹ሳታሟሙቁ የምትሮጡት፣ ሳትንደረደሩ የምትዘሉት፣ ሳትሮጡ ‘አሸንፈናል’ ‘ተሸንፋችኋል’ እያላችሁ በሜዳሊያ የምትጣሉት ናችኋ?›› ብሎ ተሳፋሪዎችን ፈገግ አሰኛቸው። ወያላው ‘መጨረሻ’ ብሎ በሩን ከፈተው። አንዱ ከጎኔ እየተራመደ፣ ‹‹ልክ ልካቸውን ነገረልኝ፡፡ አስመሳይ ሁሉ…›› ይላል፡፡ ‘በተነፉ ደረቶች ውስጥ የተነፈሱ እብሪቶች ሲሟሽሹ ማየት እንዴት ደስ ይላል?’ የሚል ጥቅስ ብናክልበት መልካም ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት