[ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው የቤት ሠራተኛቸውን አስጠሯት]
- አንቺ ምን ሆነሻል?
- ምን ሆንኩ ጋሼ?
- ለምንድን ነው ሸሚዜን ያልተኮሽው?
- ሥራ ይዤ ነው ጋሼ?
- ማታ አይደል እንዴ እንድትተኩሽው የነገርኩሽ?
- እንጀራ ስጋግር ነበር፡፡
- እና ምን ለብሼ ልሂድ?
- አሁን እተኩስልዎታለሁ ጋሼ፡፡
- በምንድን ነው የምትተኩሽው?
- በካውያ ነዋ፡፡
- የከሰል ካውያ አለን እንዴ?
- ኧረ በኤሌክትሪክ ካውያ ነው የምተኩሰው፡፡
- መብራት እኮ የለም፡፡
- እነዚህ መብራት ኃይሎች ደግሞ ጀመራቸው፡፡
- ያልተጠየቅሽውን አትቀባጥሪ፡፡
- መቼ ነው እነሱ ግን የሚሻሻሉት?
- ስለእነሱ አይመለከተኝም፡፡
- እንዴት አይመለከትዎትም?
- እኔ ምን አገባኝ?
- እረሱት እንዴ ጋሼ?
- ምኑን?
- ሚኒስትር መሆንዎትን፡፡
- እ…
- ይኼ እኮ የመንግሥት ሥራ ነው፡፡
- ምን እያልሽ ነው?
- እኔ እኮ እርስዎ ሚኒስትር ሲሆኑ ተገላገልን ብዬ ነበር፡፡
- ከምን?
- ከዚህ መከራ ነዋ፡፡
- ከየትኛው መከራ?
- ዛሬ ፊልም ሊያመልጠኝ ነው ማለት ነው?
- የምን ፊልም?
- ዛራና ቻንድራ፡፡
- አንቺ እሱ ነው የሚያስጨንቅሽ አይደል?
- ስለሌላ ነገርማ እንዳልጨነቅ አዋጁ ከልክሎኛል፡፡
- የትኛው አዋጅ?
- ጋሼ እኔ ፖለቲካ አያስወሩኝ፡፡
- የምን ፖለቲካ ነው?
- ያመለጠኝን ፊልም በፌስቡክ እንኳን እንዳላይ እሱም ተዘግቷል፡፡
- በፌስቡክ ፊልም ታያለሽ?
- እኔማ እርስዎን ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡
- እንዴት?
- ጋሼ እርስዎ ሚኒስትር ሲሆኑ ብዙ ነገር ጠብቄ ነበር፡፡
- ማለት?
- መብራት የሚጠፋብን አልመሰለኝም ነበር፡፡
- ሌላስ?
- ውኃም እናጣለን ብዬ አላስብም፡፡
- እሺ፡፡
- ጋሼ የአክስቴ ልጅ እኮ የቀድሞ ሚኒስትር ቤት ነው የምትሠራው፡፡
- እና?
- በቃ ዓረብ አገር ያሉ ዘመዶቻችን ጋ ስልክ እንደፈለግን ነበር የምንደውለው?
- እ…
- እዚህም እንደዛ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር፡፡
- እንደዛ ብታደርጊ የሚከተልሽን ታውቂያለሽ፡፡
- ምንድን ነው የሚከተለኝ?
- ጣትሽን ነው የምቆርጠው፡፡
- ጋሼ መቼም እኔ ላይ አይጨክኑም?
- ነገርኩሽ ሴትዮ፡፡
- እና ጋሼ ሌሎቹ ሚኒስትሮች ቤት የሚገኘው ጥቅም እዚህ አይገኝም እያሉኝ ነው?
- እኔ እንደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ አልገባም፡፡
- እኔ የምለው ጋሼ፡፡
- ምንድን ነው?
- ሰዎቹ እርስዎን አልተቀበሉዎትም እንዴ?
- እንደ ምን?
- እንደ ሚኒስትር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንዳንድ ነገሮች ላይ መወያየት አለብን፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ያው እኔ ብዙ ጊዜ ምርምሩ ላይ ነው የቆየሁት፡፡
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እና እዚህ መሥሪያ ቤት ስላለው የአስተዳደር ሥራ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡
- ምን ልንገርዎት ክቡር ሚኒስትር?
- መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ያለው ዋሻ ምንድን ነው?
- የምን ዋሻ ነው?
- መሥሪያ ቤቱ በየፍሎሩ በፓርቲሽን የተሠራ ዋሻ አለው፡፡
- እ…
- ለምንድን ነው ሁሉም በፓርቲሽን ተከፋፍሎ የራሱን ቢሮ የያዘው?
- ያው…
- አውቃለሁ ለምን እንደዛ እንደሆነ፡፡
- ማለት?
- ሁሉም ጉቦ መቀባበሉ እንዲመቸው ነው፡፡
- እ…
- የመሥሪያ ቤቱ ዋና ዓላማ ሕዝቡን ማገልገል አይደል እንዴ?
- በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ ለተገልጋዮች የሚመች ቢሮ ነው ሊኖረን የሚገባው፡፡
- የሚመች ሲሉ?
- በቃ ተገልጋዮች በየቢሮው መግባት ሳይጠበቅባቸው በአንድ ፍሎር ላይ ተገልግለው መሄድ አለባቸው፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- ዋሻዎቹ መፍረስ አለባቸው፡፡
- እ…
- አዎ ሁሉም ፓርቲሽኖች ፈርሰው ልቅ ቢሮ ይሁን፡፡
- እርስዎ ካሉ እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሱ ብቻ አይደለም፡፡
- ሌላ ምን አለ?
- ካሜራ መገጠም አለበት፡፡
- እ…
- እያንዳንዱ ሠራተኛ እንዴት አገልግሎት እንደሚሰጥ በካሜራ ይታያል፡፡
- እንዳሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ ጉቦ መቀባበልም ይቀራል ማለት ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ጉቦን ለማስቀረት ስንቱ ቦታ ካሜራ ይተከላል?
- ሁሉም ቦታ፡፡
- እሱማ አይቻልም፡፡
- ለምን አይቻልም?
- አብዛኛው ድርድር የሚካሄደው እኮ በየመጠጥ ቤቱና በየሆቴሉ ነው፡፡
- እ…
- እና ከቢሮ ውጪ በርካታ ድርድር ይደረጋል፡፡
- ለእሱም ዘዴ ይፈለግለታል፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ብቻ አሁን በአስቸኳይ ፓርቲሽኑ ይፍረስ፡፡
- በአስቸኳይማ መፍረስ አይችልም፡፡
- ለምን?
- ጨረታ መውጣት አለበት፡፡
- የምን ጨረታ?
- የማፍረስ!
[የቀድሞ ክቡር ሚኒስትር አዲሱ ሚኒስትር በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ሊያመጡ ያቀዱትን ለውጥ ሰምተው ስልክ ደወሉላቸው]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሰላም ማን ልበል?
- እንዴት ነው አዲሱ ሥራ?
- ጥሩ ነው፣ ማን ልበል?
- የቀድሞ ሚኒስትር ነኝ፡፡
- እንዴት ነዎት የቀድሞ ክቡር ሚኒስትር?
- በጣም ደህና ነኝ፡፡
- ምን እያደረጉ ነው አሁን?
- እኔማ ኢንቨስተር ልሁን ወይስ አምባሳደር በሚለው ሐሳብ ግራ እየተጋባሁ ነው፡፡
- እ…
- ኢንቨስተር ብሆን ጥሩ እንደምሠራ አውቃለሁ፡፡
- እሺ፡፡
- አምባሳደርም ብሆን ሁሉ ወጪዬ በመንግሥት ተችሎ ስለምኖር ለእኔ ዕረፍት ነው፡፡
- እ…
- ግን አምባሳደር ብሆን የኢንቨስተር ሥራዬን ሊጎዳው ይችላል ብዬ ስላሰብኩ ግራ ተጋብቻለሁ፡፡
- በጣም ያሳዝናል፡፡
- ምኑ ነው የሚያሳዝነው?
- አሁንም ስለራስዎት ነው የሚያስቡት?
- ታዲያ ስለማን ላስብ?
- ከቦታዎት ያስነሳዎት እኮ ይኼ አስተሳሰብዎ ነው፡፡
- እኔ ከቦታዬ ብነሳም መውደቂያዬን አሳምሬ ነው፡፡
- እ…
- መጀመሪያዬ መቀመጫዬን አለች ስንጀሮ ሲባል አልሰሙም?
- አሁንም እንደዚህ ዓይነት የወረደ አስተሳሰብ ነው ያለዎት ማለት ነው?
- ለማንኛውም አሁን የደወልኩት ልመክርዎት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ምክር?
- መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ሊያመጡ ያሰቡትን ለውጥ ሰምቻለሁ፡፡
- እና ምን ይሁን?
- ብዙ ባይለፉ መልካም ነው፡፡
- ለምን?
- ፓርቲሽን በማፍረስ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡
- እርሱን ለእኔ ተውት፡፡
- እና እርስዎም ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡
- ምንድን ነው የማስብበት?
- ሹመትዎን ይጠቀሙበት፡፡
- የተሾምኩት ለእኔ ጥቅም አይደለም፡፡
- ታዲያ ለማን ነው?
- ለአገር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው]
- የደካከሙ ይመስላሉ ክቡር ሚኒስትር?
- አዎን ትንሽ ደክሞኛል፡፡
- ታላቁን ሩጫ ሮጡ እንዴ?
- አይ አልሮጥኩም፡፡
- ዊኬንድ ላይ ኳስ አዩ?
- እኔ እንደዚህ ዓይነት ነገር አይመቸኝም፡፡
- የቀድሞ ክቡር ሚኒስትር እኮ ኳስ ሕይወታቸው ነበር፡፡
- እንዴት?
- ስብሰባ አቋርጠው ራሱ ደውለው ውጤት ይጠይቁኝ ነበር፡፡
- ለዚህ ነዋ ቤቱን እንደዚህ ያበሰበሱት፡፡
- ለነገሩ እኔም አልወዳቸውም ነበር፡፡
- ለምን?
- ራስ ወዳድ ናቸው፡፡
- ማለት?
- ራሴ ብቻ በልቼ ልሙት ነው የሚሉት፡፡
- አልገባኝም፡፡
- ስንትና ስንት ደላላና ባለሀብት ነው ያገናኘኋቸው፡፡
- እና፡፡
- በቃ ይኼው ስንት ፎቅና ፋብሪካ ለራሳቸው ሠርተው፣ እኔ ጎጆ እንኳን የለኝም፡፡
- እ…
- መቼም ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እንደ እሳቸው አይደሉም?
- ማለት?
- እርስዎም ተጠቅመው እኔን ይጠቅሙኛል፡፡
- ምን?
- በርካታ ደላላና ባለሀብት አውቃለሁ፡፡
- እና?
- የሚኒስትር ጥቅሙ ምን ሆነና?
- እ…
- ደመወዝዎት እኮ ትታወቃለች፡፡
- ምን?
- ቶሎ ብለው ፎቅዎትን ይሥሩ ግን…
- ግን ምን?
- እኔንም ያስቡኝ፡፡
- አንተ መባረር አለብህ፡፡
- እ…
- ከእኔ ጋር መሥራት አትችልም፡፡
- ምን አደረግኩ?
- የእኔ ሾፌር መሆን አትችልም፡፡
- የእርስዎስ ካልሆንኩ የእርሳቸው መሆን እችላለሁ፡፡
- የማን?
- የቀድሞው ክቡር ሚኒስትር!