– ፋብሪካው ኢትዮጵያን በማዳበሪያ ራሷን ያስችላታል ተብሏል
ሞሮኮ በኢትዮጵያ በጠቅላላ የ3.7 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚገመት የማዳበሪያ ፋብሪካ በድሬዳዋ ለመገንባት ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ፈጸመች፡፡
የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ በኢትዮጵያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት፣ ቅዳሜ ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር የ3.7 ቢሊዮን ዶላር የማዳበሪያ ፋብሪካና ሌሎች በርካታ ስምምነቶች ተፈራርመዋል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ 44 አባላት የያዘው የሞሮኮ ቢዝነስ ቡድን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ እንዲሁም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ኃላፊዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡ የሞሮኮ ባለሀብቶች የራሳቸው ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲገነቡ የኢትዮጵያ መንግሥት መሬት በነፃ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡
የማዳበሪያው ፋብሪካውን የሚገነባው ድርጅት (ኦሲፒ አፍሪካ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙስጠፋ ቴራፕ ከስምምነቱ መፈረም በፊት እንደተናገሩት፣ በድሬዳዋ አካባቢ ለመገንባት የታሰበው ይኼው ፋብሪካ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ 2.4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ በ2022 ግንባታው ሲጠናቀቅም ፋብሪካው በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ለማምረት ይችላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ራሷን በማዳበሪያ ያስችላታል ተብሎ የተገመተው ይኼው ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፋብሪካ፤ እ.ኤ.አ በ2025 የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ሲደረግበት በአጠቃላይ በዓመት 3.8 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፋብሪካው ኢትዮጵያ በማዳበሪያ ራሷን እንድትችል ከማስቻል አልፎ ወደ ውጭ መላክ እንደሚያስችላት በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ያደርጋል ተብሎ የታመነበት ይኼው ፕሮጀክት ወጪው ሙሉ ለሙሉ በሞሮኮ የሚሸፈን ሲሆን፣ የፕሮጀክት ግንባታው ከኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ እንደሚከናወን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ በተገኙበት በታላቁ ቤተ መንግሥቱ የተፈጸመው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ሁለቱ አገሮች ሌሎች አምስት ስምምነቶችና የጋራ መግባባቶችም ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በምግብ ምርት፣ እንዲሁም በኢነርጂና በማዕድን ፍለጋ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
ሞሮኮ ማዳበሪያና ሌሎች ተያያዥ ምርቶች በማምረት በአፍሪካ ግንባር ቀደም አገር ስትሆን፣ ኩባንያው በውጭ አገሮች ካከናወናቸው ግንባታዎች ትልቁ ፕሮጀክት መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡