– በኤርትራ የተቋቋመው የሳዑዲ ወታደራዊ ጦር ሠፈር አንዱ መወያያ ነበር
በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ በመገኘት፣ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር በሁለትዮሽ ትብብርና የፀጥታ ጉዳይ ላይ መምከሩ ተገለጸ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የተመራው የባለሥልጣናት ቡድን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያመራው እሑድ ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡
የዚህ ጉዞ ዓላማ በሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ሳዑዲ ዓረቢያ በኤርትራ በመሠረተችው ወታደራዊ ጦር ላይ መነጋገር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዑክ ውስጥ የተካተቱት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ፣ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ሱፊያን አህመድና ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያመራው በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ አቶ ሲራጅ ፈጌሳና አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ከሳዑዲ ዓረቢያ አልጋ ወራሽ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ መሐመድ ቢን ናይፍ አብዱላዚዝ ጋር በፀጥታ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ውይይት የየመንን የውስጥ ቀውስ ለመቅረፍ በሳዑዲ የሚመራው የዓረብ አገሮች ጥምረት በኤርትራ ወታደራዊ ጦር ሠፈር መመሥረቱ ችግር የሌለው ቢሆንም፣ በዚህ ወታደራዊ ጦር ሠፈር አማካይነት የኤርትራ መንግሥትና መከላከያ ሠራዊት የገንዘብና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያገኘ ስለመሆኑ፣ ይህም ለኢትዮጵያ ብሎም ለአካባቢው ሥጋት እንደሆነ ማስረዳት አንደኛው ተልዕኮ እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የኤርትራና ሶማሊያ ማዕቀብ ትግበራ አጣሪ ቡድን ኅዳር 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በኤርትራ ያቋቋሙዋቸው የአየርና ኃይልና የባህር ኃይል ጦር ሠፈሮች ለኤርትራ መንግሥትና ወታደራዊ ኃይል አቅም እየፈጠሩ መሆናቸውን መረጃ እንዳለው፣ ይህም ሥጋት እንደፈጠረበት መጥቀሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ሌላው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው ልዑክ አባላት ዶ/ር አብርሃም ተከስተና አቶ ሱፊያን አህመድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን የሳዑዲ ኢንቨስተሮች በተለይ በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ፣ እንዲሁም በቆዳ ማቀነባበሪያ ዘርፎች ቢሰማሩ ሁለቱም አገሮች ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማስረዳታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡