Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር ታክስ ባለመክፈል ወንጀል የተከሰሱ በአዲሱ ሕግ ነፃ...

ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር ታክስ ባለመክፈል ወንጀል የተከሰሱ በአዲሱ ሕግ ነፃ ሆነናል ሲሉ ተከራከሩ

ቀን:

እነ አቶ መላኩ ፈንታ በተከሰሱበት የወንጀል መዝገብ ቁጥር 141352 ተካተው የነበሩትና ከተመሠረተባቸው ከባድ የሙስና ወንጀል በነፃ የተሰናበቱት አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔርን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች፣ እንዲከላከሉ ከተበየነባቸው ታክስ አለመክፈል ወንጀል በቅርቡ የወጣው ሕግ ነፃ እንዳደረጋቸው ተከራከሩ፡፡

እነ አቶ ነጋ ክሳቸውን እያየው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት እንዳመለከቱት፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. በፀደቀው ‹‹የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008›› መሠረት፣ ታክስ አለመክፈል በወንጀል ያስጠይቅ የነበረው ድንጋጌ ቀሪ ሆኗል፡፡ በመሆኑም እነሱ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው፣ ድርጅታቸው ኦዲት ሲደረግ በሒሳብ አሠራርና መዝገብ አያያዝ ምክንያት ታክስ አልከፈሉም ተብሎ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በአዲሱ አዋጅ እንደተገለጸው፣ ታክስ ላለመክፈል ሆን ብለውና ለመሰወር አስበው መሆኑ ያልተረጋገጠ በመሆኑ ክሱ ቀሪ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) እና በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 5(3) መሠረትም ክሱ ቀሪ ሆኖ በነፃ መሰናበት እንዳለባቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ኅዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. መዝገቡን ቀጥሮ የነበረው በእነ አቶ መላኩ ፈንታና ሌሎች ተከሳሾች ላይ በተመሳሳይ ወንጀል መዝገብ ቁጥር 141352 በቀረበው የወንጀል ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ሐምሌ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከሳሾችን እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን መሠረት፣ የተከሳሾችን የመከላከያ ዝርዝር ለመቀበል ነበር፡፡ ነገር ግን ተከሳሾቹ ከተለያዩ ሥፍራዎች እንዲቀርቡላቸው የጠየቋቸው ማስረጃዎች ተሟልተው ያልቀረቡ መሆኑን በማስረዳት፣ በድጋሚ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ያቀረቡት ጥያቄም ተቀባይነት አግኝቶ፣ ዝርዝር ማስረጃቸውን ለታኅሳስ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

- Advertisement -

የ10ኛ ተከሳሽ የአቶ ከተማ ከበደና የ18ኛ ተከሳሽ የኬኬ ኩባንያ ጠበቆች፣ ፍርድ ቤቱ አስቀድሞ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል ከመቅረፀ ድምፅ ተገልብጦ በሲዲ እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤቱ ሬጂስትራር አቤቱታ አቅርበው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ለደኅንነት ሲባል ሲዲው እንዳይሰጥ ከበላይ አካል ትዕዛዝ የተሰጠ ስለሆነ ሊሰጣችሁ አይችልም መባላቸውን በመጥቀስ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ በተጨማሪም ተከላከሉ በተባሉበት ጉዳይ ተከሳሾች በሕገ መንግሥቱ ከተሰጣቸው የቀረበባቸውን ክስ የመከላከል መሠረታዊ መብታቸው ውጪ የጠየቁት ሲዲ ሊነፈጋቸው እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል በአግባቡ እንዳልተካተተ ማመልከታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን በመቅረፀ ድምፅ ከተቀዳው ከዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል ጋር በማመሳከር የመከላከያ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው በምንም ምክንያት ሊታለፍ እንደማይገባ አስረድተው፣ ሲዲው ካልተሰጣቸው የመከላከያ ዝርዝር ለማቅረብ እንደሚቸገሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ክርክሩን ከሚያዳምጡ በችሎት ከተሰየሙ ዳኞች ውጪ በችሎት ያልተሰየሙ፣ ክርክሩን በአካል ያላዳመጡና ያልነበሩ ዳኛ ፍርድ ቤቱ በሚሰጣቸው ትዕዛዞች ላይ የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ተብለው በስም እየተጠቀሱ የሚተላለፉት ትዕዛዞች፣ በፍርድ ቤቱ ላይ እምነት እንዳይኖር ጥርጣሬን የሚፈጥርና ከዳኝነት ሥራና ሥነ ምግባር ውጪ መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ተከሳሾች የመከላከያ ዝርዝር እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዳኝነት አካሄድ ላይ በተከሳሾች የቀረበውን ተቃውሞ ተቀብሎ ስህተቱ እንደማይደገም አስታውቋል፡፡

ተከሳሾቹ በነፃ እንዲሰናበቱ ባቀረቡት አቤቱታና አልተሰጠንም ስላሉት የምስክሮች ቃል (ሲዲ) ላይ ዓቃቤ ሕግ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ምላሽ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ በመዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠት ለታኅሳስ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...