የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል መሆናቸውና በአምቦ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ኃላፊንና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትን ለመግደል ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ፡፡
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦ የኦሕዴድ ኃላፊ አቶ ያሬድ ተሾመንና የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ምትኩ ቴሶን በቦምብ ለመግደል ሲከታተሏቸው ነበር የተባሉት ተከሳሾች፣ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማና በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል፡፡
ባቲ ሙለታ ዋቅጅራ፣ መስፍን መኮንን መርጋ፣ ታፈሰ ደበሌ፣ ተፈራ ሙለታ፣ ሸንተማ ቀንአ፣ አስፋው አበራ፣ ጉቱ ሶሪ፣ እንደገና በቀለ፣ ፈይሳ ለማና አስማረ በላይ የተባሉ ተከሳሾች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ጫካዎችን ለተለያዩ ዝግጅቶች ማድረጊያ ማጥናታቸውን፣ ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ በጨጫመነ ኤርጋ ቀበሌ፣ ልዩ ቦታው ሳቃ ጮጴ ወይም ሺሾ የተባለውን ጫካም መምረጣቸውን አክሏል፡፡
በተለይ አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ባቲ ሙለታ ዋቅጅራ የተባለው ተከሳሽ፣ በተመረጠው ጫካ ውስጥ ካምፕ በመመሥረት አባላትን በሴል በማደራጀትና ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት፣ ሌሎቹ ተከሳሾች የሽብር ተግባር ወንጀል እንዲፈጽሙ አመራር በመስጠት ከኦነግ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡ ተከሳሹ በሁለቱ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዲያደርስ እንደገና በቀለ የተባለውን ሌላኛውን ተከሳሽ ከማሰማራቱም በተጨማሪ፣ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ለመለመላቸው የኦነግ አባላት ያስገዛ እንደነበር በክሱ ተገልጿል፡፡ እሱን የመለመለው በውጭ አገር የሚገኝ አባገርቡ የተባለ የኦነግ አባል መሆኑን፣ እሱም በአጭር ጊዜ 20 ሰዎችን መመልመል በመቻሉ ጫካ ገብተው ሥልጠና በመውሰድ መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለማስወገድ ተጨማሪ ዝግጅት ማድረጊያ 6,700 ብር በባንክ እንደላከለት ክሱ ያስረዳል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የኦነግን ተልዕኮ ለማስፈጸም በመዘጋጀትና በመንቀሳቀሳቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 35፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4ን በመተላለፍ የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ክሱ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ለተከሳሾቹ ክሱ እንዲደርሳቸው ካደረገ በኋላ በክሱ ላይ ተቃውሞ ካላቸው ለኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቶ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡