Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከህንዱ ኮንትራክተር የተነጠቀው የመንገድ ሥራ ለቻይናው ኮንትራክተር ተሰጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሲው በተባለው የህንድ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በመገንባት ላይ የነበረውና ባለፈው ዓመት ግንባታው የተቋረጠው የሐዋሳ – ጭኮ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ፣ ለቻይናው ሲኖኃይድሮ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰጠ፡፡

66 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ የነበረውን የዚህን የመንገድ ፕሮጀክት ሲገነባ የነበረው ሲው የተባለው የህንድ ኮንትራክተር ቢሆንም፣ በኮንትራት ውሉ መሠረት ግንባታውን ማካሄድ አልቻለም በማለት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኮንትራቱን ባለፈው ዓመት አቋርጦበት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የመንገድ ግንባታው ተቋርጦ ከቆየ በኋላ፣ ሥራውን በአዲስ ኮንትራክተር ለማከናወን በወጣ አዲስ ጨረታ ሲኖኃይድሮ አሸናፊ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

የህንዱ ኩባንያ የዚህን መንገድ ግንባታ ለማካሄድ በጨረታ አሸናፊ ሆኖ የተረከበው በ2005 ዓ.ም. ነበር፡፡ በውሉ መሠረት መሥራት አልቻለም ተብሎ ኮንትራቱ እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ ከጠቅላላ ግንባታው 33 በመቶ ያህሉን አጠናቆ ነበር ተብሏል፡፡

ውሉ ከተቋረጠ በኋላ ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል  በመንገድ ግንባታ የተሻለ አፈጻጸም አላቸው ተብለው የተለዩ አምስት የውጭ ኮንትራክተሮች ተጋብዘው ነበር፡፡  ከአምስቱ ኮንትራክተሮች ሲኖኃይድሮ የተሻለ ዋጋ በማቅረቡ ኮንትራቱን ተፈርሟል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ግንባታ ይገባል ተብሏል፡፡

ይህ ድጋሚ ጨረታ እንዲካሄድ የተደረገው የአፍሪካ ልማት ባንክ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ነው ተብሏል፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ በባንኩ ብድር የሚከናወን በመሆኑ፣ ጨረታው ከመደበኛ የጨረታ ሒደት ወጣ ያለና በመንገድ ግንባታ የተሻለ አፈጻጸም አላቸው የተባሉትን በመጋበዝ የተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ሲኖኃይድሮ በጅምር የቀረውን የሐዋሳ – ጭኮ መንገድ ገንብቶ ለማጠናቀቅ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 965 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

በ2005 በጀት ዓመት ሲው ኮንስትራክሽን ይህንን ፕሮጀክት ለመገንባት አሸናፊ የነበረበት ዋጋ 960 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ዋጋ ግንባታቸው የተቋረጡ መንገዶች ወደ ሌላ ኮንትራክተር ሲተላለፉ ከቀድሞው የበለጠ ዋጋ እየጠየቁ ለመሆናቸው ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች