Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዘረመል ጥጥ በሁለት ዓመት ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል ነው

የዘረመል ጥጥ በሁለት ዓመት ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል ነው

ቀን:

በቤተ ሙከራና በተከለለ ከባቢ ሁኔታ ውስጥ የመስክ ጥናት ሲካሄድበት የቆየውና የባዮቴክኖሎጂ ውጤት የሆነ የጥጥ ዝርያ፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎች መካሄዳቸውን ተመራመራዎች አስታወቁ፡፡

ጄኬ አግሪ ጄኔቲክስ ከተባለ የህንድ ኩባንያ ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት በኢትዮጵያ ሙከራ ሲደረግባቸው የቆዩ የጥጥ ዘረመል ምህንድስና ውጤቶች ለገበያ የሚለቀቁበት ደረጃ ላይ መቃረባቸውን፣ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ዶ/ር እንዳለ ገብሬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ ምርምር ሲደረግበት የቆየው የባዮቴክኖሎጂ ጥጥ ወይም ‹‹ቢቲ ኮተን›› ቢበዛ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለገበያ ሊውል እንደሚችል ይጠበቃል ተብሏል::

ጄኬ አግሪ ጄኔቲክስ ኩባንያ የቢቲ ኮተን ዘርን ጨምሮ የአትክልትና ሌሎች የአገዳ ሰብሎች ድቅል ዘር አምራች ነው፡፡ በህንድ እ.ኤ.አ. በ2006 በተሰጠው የዘረመል ምህድስና ዝርያዎችን የማምረት ፈቃድ መሠረት የጥጥ ምርት አዘጋጅቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በመስኩ እየሞከረች ያለውንና “X-Gene1” የተባለውን ድቅል የዘረመል ጥጥ ዝርያ አቅርቧል፡፡ ኩባንያው በሱዳንም ከዚህ ቀደም ይህንኑ ዘር በማስተዋወቁ በአሁኑ ወቅት ሱዳኖች የዘረመል ጥጥ በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምረዋል ተብሏል፡፡ ኩባንያው በስዋዚላንድ ይህንኑ የዘረመል ዘር በማቅረብ ወደ እርሻ ማሳያዎች እንዲገባ ለማድረግ መዘጋጀቱን፣ የጄኬ አግሪ ጄኔቲክስ ኩባንያ ፕሬዚዳንትና ዳይሬክተር ኤስ ኬ ጉፕታ ለሪፖርተር አአስረድተዋል፡፡

ኩባንያው ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ሽያጭ የሚያከናውንና እንደ ሞንሳንቶ ያሉ ኩባንያዎችን ለመቋቋምና ለመፎካከር የሚሠራ የህንድ አገር በቀል ኩባንያ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡ እስካሁን በህንድ ከሚቀርቡ የዘረመል ምህንድስና ውጤቶች ውስጥ አብዛኞቹ በሞንሳንቶና አጋሮቹ የተያዘውን የጥጥ ዝርያ የገበያ ድርሻ እየተጋራ የሚገኝና በጥጥ ዘርፍ ከሞንሳንቶና ማሂኮ ከተባለው የህንድ ኩባንያ ቀጥሎ በሦስተኛነት እንደሚሰለፍ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዝግጅት እየተደረገበት የሚገኘው “X-Gene1” የዘረመል ጥጥ፣ በሔክታር እስከ አምስት ቶን ምርት የመስጠት አቅም እንዳለው ሚስተር ጉብታ አብራርተዋል፡፡ ይህ ውጤት በአብዛኛው በመስኖ በሚለሙ ማሳያዎች ሊገኝ የሚችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዝናብ የሚለሙ እርሻዎች ላይ ግን ከ3.5 ቶን እስከ አራት ቶን የሚደርስ ምርት ሊሰጥ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ይህ ዝርያ የጥጥ ሰብሎችን የሚያጠቃውንና ቦልዎርም የተባለውን ተባይ ለመካለከል እንዲችል ሆኖ መዘጋጀቱንና የዓረም ርጭት መጠን እንዲቀንስ ማስቻሉም ተነግሮለታል፡፡ ጄኬ አግሪ ጄኔቲክስ በመላው ህንድ 27 የዘረመል ምህንድስና ውጤት የሆኑ የጥጥ ዝርያዎችን ያበለጸገ ሲሆን፣ አምስቱን ለአፍሪካ ገበያ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ ኩባንያው ከዘረመል ጥጥ በተጨማሪ በጨርቃ ጨርቅና በመኪና ጎማ ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ኩባንያው ለሙከራ በኢትዮጵያ ሲያቀርብ የነበረው የዘረመል ጥጥ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለገበያ ይቀርባል ብሎ እንደሚያስብ የኩባንያው ኃላፊዎች ቢገልጹም፣ በኢትዮጵያ ወገን እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ገበያ ውስጥ የሚቀርብ የዘረመል ጥጥ ይጠበቃል፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገር ስዋዚላንድ የዘረመል ጥጥ ወደ ገበያ ለማስገባት የሕግ ማሻሻል ሥራ እንደሚቀራትና በሦስት ወራት ውስጥ ይህ ተጠናቆ ዘሩ መዘራት እንደሚጀመር የአገሪቱ ፓርላማ ተወካዮች አስታውቀዋል፡፡ ኬንያም ሙከራ እንዲደረግ የሚያስችል ሕግ ብታወጣም፣ ወደ ገበያ ለማስገበት የሚያስችለውን ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ገና ጥናት ላይ መሆኗ ታውቋል፡፡ ዛምቢያና ማላዊም በዚሁ ደረጃ እንደሚገኙ ልዑካኖቻቸው ገልጸዋል፡፡

ህንድ የዘረመል ጥጥ ገበያ ላይ ካዋለች 15 ዓመታት ያስቆጠረች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 95 ከመቶው የአገሪቱ ጥጥ የዚሁ የዘረመል ምህንድስና ውጤት ነው፡፡ በህንድ በጥጥ ዘርፍ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ገበሬዎች መሰማራታቸው፣ ከ45 ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ እንዲሁም በዓለም ገበያ ያላትን የገበያ ድርሻ 27 በመቶ እንዲሆን ማስቻሉንና ሌሎችም ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጠቀሜታዎች እንዳገኘችበት ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳ ምንም ዓይነት የጤናና የአካባቢ ጉዳት እንደማያደርሱ፣ በተለይም እንደ ካንሰር ያሉትን በሽታዎች የዘረመል ምርቶች እንደማያስከትሉ በሳይንሳዊ መረጃዎች አስደግፈው ማቅረባቸውን ቢገልጹም፣ የዚህ ዘርፍ ተመራማሪዎችና ኩባንያዎች አሁንም ድረስ በአካባቢና በመብት ተሟጋች ተቋማት ተቃውሞ ይሰነዘርባቸዋል፡፡ ወደ ፍርድ ቤት የሚያመሩባቸው ጊዜያትም ታይተዋል፡፡

በኢትዮጵያም የጥጥ ዘረመል ምህንድስና ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ መሆኑ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ይህንን ለማከናወን የሚፈቅደው ሕግ እስከፀደቀበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ ክርክሮችና ተቃውሞዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ይሁንና መንግሥት በጥጥ ላይ የዘረመል ምህንድስና በማካሄድ ምርት የሚጨምሩ፣ በሽታ፣ ድርቅና አረም የሚቋቋሙ የጥጥ ዝርያዎችን ለማውጣት ከህንድ ኩባንያዎች በተገኘ ዘር ምርምር ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሠረት ውጤቱ እየተገባደደ እንደሚገኝና በሁለት ዓመት ውስጥ ለገበያ እንደሚቀርብ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፋንታሁን ዘውዴ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ፋንታሁን ለሪፖርተር በገለጹት መሠረት፣ ከጄኬ አግሪ ጄኔቲክስ በተገኘው ዘረመል የጥጥ ዝርያ መሠረት ኢንስቲትዩቱ ተገቢነቱን አረጋግጦ ያወጣውን ምርት የመጠቀም ድርሻው ያለው በጥጥ አምራቾች በኩል ሲሆን፣ ተገቢ ካልመሰላቸውም የመተው ድርሻው የአምራቾቹ ነው፡፡ ይሁንና መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታን ከማስፋፋቱም በላይ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስክ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በብዛት እንዲመጡ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡ እስካሁንም በዘርፉ የሚሠማሩ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ጋብዟል፡፡ በጥጥ ምርት አቅርቦት በኩል የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በምርት ጥራትና በአቅርቦት ችግር፣ እንዲሁም በዋጋ በኩል ከጥጥ አምራቾች ጋር ሲነታረኩ ከርመዋል፡፡ በአንፃሩ ጥጥ አምራቾች አይስማሙም፡፡ ይልቁንም ፋብሪካዎች በሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት፣ በምርትና በግብዓት ግዥ ዕቅድ፣ እንዲሁም በሌሎች መስኮች ችግሮች ስለሚታዩባቸው የተመረተውን የአገር ውስጥ ምርት በሙሉ እየገዙ እንዳልሆነ፣ የኢትዮጵያ ጥጥ አምራቾችና መዳመጫዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሐድሽ ግርማ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ35 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ቶን ጥጥ በአገር ውስጥ ቢመረትም፣ ይህንን ሁሉ ምርት ፋብሪካዎች በወቅቱ እንደማይገዙ አቶ ሐድሽ ጠቁመዋል፡፡ በአንፃሩ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በሚፈለገው ምርትና እየቀረበ ባለው መካከል ከ15 እስከ 20 ሺሕ ቶን የሚገመት የአቅርቦት ክፍተት ቢኖርም በምርት እጥረት ሳይሆን፣ በዕቅድ ችግርና በበጀት እጥረት ምክንያት ምርት በሚደርስበትና በሚፈለግበት ወቅት አለመነሳቱ ነው ነገሩን ያባባሰው ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በተፈጠረ አለመጣጣም የተከሰተ ሰው ሠራሽ እጥረት እንደሆነም ያምናሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሊመረት የታሰበው የዘረመል ጥጥም ቢሆን ብቸኛ አማራጭ ነው ብለው በግላቸው እንደማያምኑ፣ ይልቁንም ሌሎችም ዘዴዎች ሊታዩ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡

በባዮቴክኖሎጂ ወይም በዘረመል ምህንድስና መስክ የተሠሩ የጥጥ ዝርያዎች በሰፊው ጥቅም ላይ በዋለባት ህንድ፣ ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ልዑካን ባለፈው ሳምንት ትምህርታዊ ጉብኝት አድርጓል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የጥጥ አምራቾችና መዳመጫ ፋብሪካዎች ተወካዮች፣ ተመራማሪዎች፣ የምርምር ተቋማት ኃላፊዎችና የሕግ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከማላዊ፣ ከስዋዚላንድና ከዛምቢያ በህንድ የባዮቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ የእርሻ ማሳዎችንና ተቋማትን ጎብኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...