አቶ በቀለ ንጉሤ፣ የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት መጠነ ሰፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ መንግሥት በየዓመቱ ቢሊዮን ብሮች በመመደብ በርካታ መንገዶች፣ የባቡር መስመሮች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ የቴሌኮም አውታሮችና አውሮፕላን ማረፊያዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሳይቋረጡ በመካሄድ ላይ የሚገኙት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አስደሳች የመሆናቸውን ያህል በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የማይጠናቀቁ በመሆናቸው በኅብረተሰቡ ቅሬታ የሚቀርብባቸውም ሆነዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በተለይ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አውታሮች ግንባታ እርስ በርሳቸው የሚናበቡ ባለመሆናቸው በተለይ በገጠርና በከተሞች ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሒደት ከፍተኛ የሀብት ብክነት እየደረሰ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ማኅበራዊ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ የመሠረተ ልማት ግንባታዎቹ በተገቢው መንገድ ፕላን እየተደረጉ የሚገነቡ እንዳልሆኑም አመላካች ክስተቶች እየታዩ ነው፡፡ ግንባታ ከሚካሄድባቸው ቦታዎች የሚነሱ ዜጎችም በተገቢው መንገድ ካሳ እያገኙ አለመሆኑም ቅሬታ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን እነዚህን ችግሮች የሚፈታ ኤጀንሲ በቅርብ አቋቁሟል፡፡ ‹‹የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ›› በሚል ስያሜ የተቋቋመውን ኤጀንሲ አቶ በቀለ ንጉሤ በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ ተሹመዋል፡፡ አቶ በቀለ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለ28 ዓመታት እስከ ምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ድረስ በተለያዩ እርከኖች ሠርተዋል፡፡ አቶ በቀለ በትምህርቱ ዓለም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከኔዘርላንድ ዩኒቨርሲቲ በፕሮጀክት ማኔጅመንት የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከፈረንሣይ ዩኒቨርሲቲ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኮምፒቲቲቭነስ የዶክትሬት ዲግሪ፣ አሜሪካ ውስጥ ባለ ሌላ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በትራንስፖርት አክሰሰቢሊቲ ሌላ የዶክትሬት ዲግሪ እየሠሩ ሲሆን፣ ቤልጂየም ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ውድነህ ዘነበ አቶ በቀለን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ላለፉት 28 ዓመታት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በፕላንና ፕሮግራም መምሪያ ኃላፊነት፣ በምክትል ዋና ዳይሬክተርነትና የተለያዩ የሥልጣን እርከኖች ድረስ ሲሠሩ ቆይተው አሁን አዲስ ወደ ተቋቋመው ኤጀንሲ መጥተዋል፡፡ አዲሱ ኤጀንሲ ሥልጣንና ኃላፊነቱ ምንድነው?
አቶ በቀለ፡- ይኼ መሥሪያ ቤት የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ይባላል፡፡ የመሥሪያ ቤቱን ዓላማ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ፕሮግራሞችን ማቀናጀት ነው፡፡ ሁለተኛው ሥራ በልማት ምክንያት የሚነሱ ዜጎች የሚከፈላቸው ካሳ አሠራሩን መለወጥ ነው፡፡ የፕሮግራም ማቀናጀቱን ካየን የአገሪቱን መሠረተ ልማቶች ማስተር ፕላን ማዘጋጀት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ አያውቅም፡፡ ምናልባት ማስተር ፕላን አለ ከተባለ የትራንስፖርት ማስተር ፕላን ነው፡፡ እሱም አላለቀም፡፡ የዚህ መሥሪያ ቤት ሥራ የአገሪቱን የመሠረተ ልማቶች ማስተር ፕላን ማዘጋጀት ይሆናል፡፡ እኛ ማስተር ፕላኑን ካዘጋጀን በኋላ መሥሪያ ቤቶች የራሳቸውን ማስተር ፕላን ያዘጋጃሉ፡፡ እንዴት ነው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚስፋፋው? አውሮፕላን ማረፊያዎች የት ነው መገንባት ያለባቸውና የመሳሰሉ ጉዳዮችን ባካተተ መንገድ በካርታ የተደገፈ ማስተር ፕላን ይዘጋጅላቸዋል፡፡ እኛ ይህን ከሠራን በኋላ መሥሪያ ቤቶች የራሳቸውን ማስተር ፕላን ከዚህ ወስደው ያዘጋጃሉ፡፡ ሌላው በአገሪቱ የሚገኙ መሠረተ ልማቶች ዳታ በማዕከል ደረጃ ይጠናቀራል፡፡ በተለያዩ መንገዶች የሚጠናቀረው መረጃ በማዕከል ደረጃ በአንድ የመረጃ ቋት ይገባል (ዳታ ዌር ሐውስ)፡፡ ሌላው የአካባቢ ደኅንነት (ኢንቫይሮመንት) ጉዳይ ነው፡፡ አስተውለህ ከሆነ የኮንስትራክሽን ሳይቶች በአብዛኛው ሥርዓት የላቸውም፡፡ የሥራ ቦታ ደኅንነትን ያገናዘበ አይደለም፡፡ እኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ (ስታንዳርድ) እናዘጋጃለን፡፡ ለኮንትራክተሮች ደረጃ እንሰጣለን፡፡ አፈጻጸማቸውን በመለካት አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ የሚሉ ደረጃዎች ይሰጣቸዋል፡፡ አካባቢንና ሠራተኞቻቸውን በሥርዓት የማይዙትን ቀይ እንሰጣቸዋለን፡፡ ውጤቱን ለአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በመላክ ዕርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል፡፡ ሌላው ከግንባታ አካባቢው ለሚነሱ ንብረቶች የሚከፈለው ካሳ ጉዳይ ነው፡፡ የካሳ አከፋፈል ቀመሩን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ አዲስ ቀመር ይዘጋጃል፡፡ የካሳ አከፋፈል አሠራሩን ማዘመን ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ግንባታዎቹ እጅግ አስፈላጊ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን እየተናበቡ የሚገነቡ ባለመሆናቸው የቅሬታ ምንጭም እየሆኑ ነው፡፡ የእርስዎ መሥሪያ ቤት አዲስ ቢሆንም የተወሰኑ ቅኝቶችን አድርጎ ሊሆን ስለሚችል፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች የተናበቡ ባለመሆናቸው ምን ታጣ? መንግሥት የመሠረተ ልማት ተቋማት እንዲናበቡ ለማድረግ አልዘገየም ወይ?
አቶ በቀለ፡- በመሠረተ ልማት ግንባታ ኢትዮጵያ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች ነው፡፡ ከተመሳሳይ አገሮች ጋር ስናወዳድርም በኢትዮጵያ በርካታ ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ መንግሥት አብዛኛውን በጀት ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች እያዋለ ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ተፅዕኖው ምንድነው የሚለውን ማየት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን፡፡ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ የመናበብ ሥራን በተመለከተ በጣም ዘግይቷል፡፡ ትልቁ ችግር ሁሉም የመሠረተ ልማት ተቋማት የተሰጣቸው ዕቅድ አለ፡፡ ይህንኑ ዕቅድ ለማሳካት በራሳቸው መንገድ ይሮጣሉ፡፡ አዎንታዊ ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሒደት የሚባክን ሀብት አለ፡፡ ፕሮጀክቶች ሲዘገዩ ከኮንትራክተር ድክመት ነው ብሎ መናገር ቀላል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደ ግብ የሚታየው ፕሮጀክት መጀመር ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን 90 በመቶ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አይጠናቀቁም፡፡ ይህ ለምን ሆነ ሲባል የቅንጅት ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ከቅንጅት ጋር በተያያዘ ተፅዕኖውን ለማየት ቢያንስ በአዲስ አበባ ከተማ በመንገዶች ግንባታ ላይ የተሠራን ጥናት እንመልከት፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት ከቅንጅት ማነስ በዓመት 300 ሚሊዮን ብር ይታጣል፡፡ ይህ እንግዲህ የአዲስ አበባ መንገድ ላይ ብቻ ነው፡፡ የፌዴራል መንገዶችን ካየህ በጣም በርካታ ነው የሚሆነው፡፡ እኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥናት እናካሂዳለን፡፡ ስለዚህ ተፅዕኖው ከፕሮጀክት መዘግየት አልፎ ውስብስብ ችግሮችን እያመጣ ነው፡፡ አንዳንዴ መሠረተ ልማትን በአሉታዊ ጎኑ እንዲታይ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የመሠረተ ልማት ተቋማቱ ተቀናጅተው መሥራት ቢችሉ ምን ያተርፉ ነበር? ከአዲስ አበባ መንገዶች ውጪ ባሉ በሌሎቹ ተቋማት ያለው ተፅዕኖ እንዴት ይገለጻል?
አቶ በቀለ፡- በገንዘብ ማስቀመጥ ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ ፕሮጀክቶች እስከ 70 በመቶ ዘግይተው ይጠናቀቃሉ፡፡ ይህን መዘግየት በግማሽ መቀነስ ብንችል ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ከቅንጅት አልፈን የካሳ ክፍያን ካየን በአግባቡ እየተሠራበት ባለመሆኑ ፕሮጀክቶቹን በአሉታዊ ጎናቸው እንዲታዩ እያደረገ ነው፡፡ መንግሥት ብዙ ካሳ እንዳይከፍል ፈልጎ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰብ ጋ እርካታ የለም፡፡ ስለዚህ የሆነ ቦታ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ይህን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ሌላው በትክክል ፕላን የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ ፕላን የለም ማለት አይደለም፡፡ በትክክል እየታቀደ አይደለም ነው ጉዳዩ፡፡ በትክክል ጊዜ ተወስዶ አልተሠራም፡፡ ሕዝቡ ጋ ሲደርስም ለምሳሌ ፕሮጀክቶች ከሚካሄድባቸው ቦታዎች የሚነሱ ሰዎች ተዘጋጁ ሳይባሉ፣ በዚያ አካባቢ ምን እንደሚሠራ ሳይነገራቸው ተነሱ የሚባሉበት አጋጣሚ አለ፡፡ ከገንዘቡ በላይ የሚሠሩት ሥራዎች የሚያስደስቱ ሳይሆኑ ሕዝቡን የሚያበሳጩ እየሆኑ ነው፡፡ በገንዘብ ማስቀመጥ ባይቻልም ትልቅ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡
ሪፖርተር፡- የመሠረተ ልማት ተቋማት ሳይናበቡ በመሥራትና በትክክል ፕላን በማድረግ በኩል ያለው አንድነትና ልዩነት ምንድነው?
አቶ በቀለ፡- የመሠረተ ልማቶች ግንባታ ፕላኒንግ ጉዳይ በሌሎች አገሮች ረዥም ዓመታት ይወስዳል፡፡ አንድን ፕሮጀክት 20 ዓመት ፕላን አድርገናል የሚሉ አገሮች አሉ፡፡ እንደኛ አገር መሠረታዊ ግንባታ ሳይሆን ለምሳሌ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት ሲታሰብ በጣም ከባድ ፕላን ነው፡፡ ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ለስንት ዓመት እንደሚያገለግል፣ ትክክለኛውን ፍላጎት ለማወቅም ረዥም ጊዜ ተወስዶ መጠናት አለበት፡፡ ሁለተኛው ያለመናበብ ጉዳይ ነው፡፡ አውሮፕላን ማረፊያ ሊሠራ ሲል ሌሎች የትራንስፖርት ዘርፎች አብረው መታሰብ አለባቸው፡፡ ባቡር አለ ወይ? መንገድ አለ ወይ? የውኃ አቅርቦት መኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡ ለይስሙላ ይታያል፡፡ ግን አውሮፕላን ማረፊያውና የሚገነባው አካል ሙሉ በሙሉ አስተሳሰቡ፣ ህልሙና ትኩረቱ የአውሮፕላን ማረፊያውን ግንባታ እንዴት እንደሚያስጀምርና እንደሚያጠናቅቅ ነው፡፡ ስለዚህ ፕላኒንጉ ችግር አለበት፡፡ የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በጣም ሰፊ ነው ተባለ፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሞላ፡፡ ቴሌኮምን ማየት ነው፡፡ ተጨናንቋል፡፡ የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድን ማየት ትችላለህ ሰፊ ነው ተባለ፣ አሁን ሞላ፡፡ የአዲስ አበባ ቀለበት መንገድ ተመልከት፣ ሲሠራ ሰፊ ነው ተብሎ ነበር፡፡ አሁን ግን ሞላ፡፡ ተጨናነቀም፡፡ በፕላኒንግ ላይ በደንብ አድርጎ የአለማየት ችግር ነው፡፡ የትኛውም መሠረተ ልማት በራሱ ምንም አይደለም፡፡ ሌሎች ነገሮችም ሊካተቱበት የግድ ነው፡፡ ኤርፖርት ሲሠራ ቴሌኮም፣ ባቡርና የመሳሰሉት በሙሉ መካተት ይኖርባቸዋል፡፡ ተናቦ አለመሥራት ችግር ነው፡፡ ለዚህ ችግሩ የተሰጠውን ሥራ ለመጨረስ መሯሯጥ ነው፡፡ ጊዜ የለንም ብሎ የራስን ኃላፊነት ብቻ ማየት ነው የችግሩ ምንጭ፡፡ ነገር ግን እኛ (ኢትዮጵያ) ሁሉንም ሥራዎች በአንዴ ነው እየሠራን ያለነው፡፡ እስካሁን የተሠራው ሥራ መጥፎ ነበር አልልም፡፡ በጣም ተማርንበት፡፡ መንገድ ይሠራል፣ ከዚያ ባቡር መጣ ሲባል መንገዱ ይቆፈራል፡፡ እንደ ትልቅ ወንጀል ሊታይ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አይደለም፡፡ በዚያ ወቅት ለባቡር ግንባታ የሚሆን ገንዘብ እንደምናገኝ እንኳ አናውቅም፡፡ ስለዚህ የአገሪቷ ሁኔታ አለ፡፡ የዕይታ ችግር አለ፡፡
ሪፖርተር፡- የውጭ ኩባንያዎች በተለይ የቻይና ኩባንያዎች ግንባታ ካጠናቀቁ በኋላ ተያያዥ ሌሎች ሥራዎችን የሚገነባው አካል በፍጥነት የሚጨርስ ባለመሆኑ አስረክበው ለመውጣት ሲቸገሩ ይታያል፡፡ ከዚህ ሌላ ለአብነት የግልገል ጊቤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ተጠናቋል፡፡ ግድቡ በቂ ውኃ መያዙም ተገልጿል፡፡ ነገር ግን በሙሉ አቅሙ ኢኮኖሚውን መደገፍ አልቻለም፡፡ የእነዚህ ችግሮች ድምር ውጤት አገሪቱን እየጎዳት ነው የሚሉ አሉ፡፡
አቶ በቀለ፡- ሁሉም መሥሪያ ቤቶች የፕላኒንግ መምርያዎች አሏቸው፡፡ አብዛኛው ሥራቸው ግን ዕቅድና ክንውን ነው፡፡ አጠቃላይ ፕላኒንግ ወይም ስትራቴጂካዊ ፕላኒንግ ደካማ ነው፡፡ አልፎ ማሰብ ይቸግራል፡፡ አንደኛ የዕውቀት ሁለተኛ የጊዜ አለመኖርና የሀብት ችግር በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በጣም የማውቀውን ልንገርህ፡፡ የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድን ስናጠና የአብዛኛው ባለሙያ የነበረውን መንገድ ማስፋት ይበጃል የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን መንገዱ በአጭር ጊዜ ይሞላል፣ ኢኮኖሚውን ይጎዳል የሚል ነገር ውስጣችን ይነግረን ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ እየሠራ ያለው መንገዶች ባለሥልጣን ብቻውን ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ላይም ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ በኃይል ዘርፍ ትልቁ ሥራ ግንባታ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ሥርጭቱ እንዲቃለል የማየት ነገር አለ፡፡ ሥርጭቱ ይደርሳል ብሎ መዘናጋት አለ፡፡ የሀብት እጥረት አለ፡፡ ወረዳዎችን በመንገድ ለማገናኘት የተጀመረው ሥራም ይኸው ችግር አጋጥሞታል፡፡ መንገድ ሲሠራ ትራንስፖርቱ ይመጣል ተባለ፡፡ የመንገዱ ጥገና እንዴት ነው የሚለው መንገዱ ከተሠራ በኋላ የሚታይ ነው ተብሎ ይዘላል፡፡ የታሰቡ ፕሮጀክቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ከባድ ችግር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በአብዛኛው የሚካሄዱት በውጭ ብድር ነው፡፡ ፕሮጀክቶቹ ተናበው የሚሠሩ ባለመሆናቸው ሥራ ሳይጀምሩ የብድር መክፈያ ጊዜ የሚደርስባቸው አሉ፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት እየተገነባ ቢሆንም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ መስመሮችና ማስፋፊያው ከተጠናቀቀ ቆየ፡፡ መስመሩ ያለሥራ መቀመጡ ብክነት አይሆንም?
አቶ በቀለ፡- ትልቅ ብክነት ነው፡፡ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ መንግሥት ተደራሽነት እፈጥራለሁ፣ ሀብት እፈጥራለሁ ካለ በኋላ የተሠሩ ሥራዎችን ወደኋላ ሲመለከት ሁሉም ሥራ የሚያሰለች፣ የሚያዳክምና ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆነ፡፡ ምን ማድረግ አለብን አለ፡፡ በኮሚቴ ይሠራ ተባለ፡፡ ኮሚቴ ደግሞ ተጠያቂነት የለበትም፡፡ ይሠራል፣ ይሰበስባል፣ ይበተናል፡፡ ጫናው የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ተፅዕኖ ጋርዶታል፡፡ አሁን ያልተቻለው ተፅዕኖውን በገንዘብ መግለጽ አለመቻሉ ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያ የምትታወቀው መሠረተ ልማት በመገንባት ቢሆንም እርካታው ግን ገና አልመጣም፡፡ ግንባታዎቹ በአሉታዊ የሚታዩ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ከእኛ መሥሪያ ቤት ብዙ ይጠበቃል፡፡
ሪፖርተር፡- የእርስዎ መሥሪያ ቤት ከዚህ በኋላ ለሚገነቡ ግንባታዎች ጥሩ መፍትሔ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን የተገነቡ ግንባታዎች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን ምን ሊሠራ አቅዷል? ለአብነት ያህል ከሰበታ እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ የተዘረጋው የባቡር መስመር በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ተብሏል፡፡ ነገር ግን ባቡሩ ሞጆ ደረቅ ውስጥ አይገባም፡፡ ጂቡቲ ከደረሰ በኋላም ወደቦቹ ውስጥ አይገባም፡፡ የነዳጅ ማራገፊያ ግንባታም አልተካሄደም፡፡ ይኼ ምንድነው የሚናገረው? እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የእርስዎ መሥሪያ ቤት ምን ሊያደርግ ይችላል?
አቶ በቀለ፡- ትክክል ነው፡፡ በአጭር ጊዜ መፍታት አለብን፡፡ የማቀናጀት ጉዳይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡ ፕሮጀክት አጓቷል የተባለው እሱ ነው፡፡ መንግሥት ይኼ ችግር መዘጋት አለበት ብሏል፡፡ ያነሳኸው መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ ሲታሰብ እነዚህ ቁም ነገሮች ለምንድነው ያልተካተቱት የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ነው የመሠረተ ልማት ማስተር ፕላን አስፈላጊ የሚሆነው፡፡ ሲሠራ ለምንድነው እነዚህን ነገሮች አሟልቶ ያልያዘው? አንድ መሠረተ ልማት በራሱ ምንም አይደለም፡፡ መንገድ በራሱ ምንም አይደለም፡፡ ጉዞውን የሚያቀላጥፍ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች አንድ ላይ የሚሆኑበት በማስተር ፕላኑ መመለስ አለበት፡፡ ዛሬ ላይ የሚያጫጩኸን ቅፅበታዊ ነው፡፡ በፍጥነት መፍታት አለበት፡፡ ምንም ምክንያት ሊሰጠው አይገባም፡፡ ባቡር በመገንባቱ ከትራንስፖርት፣ ከወደብ ጋር ሊተሳሰር ይገባል፡፡ መጀመሪያ ባቡር ብለህ ካሰብክ፣ ወይ መንገድ ብለህ ካሰብክ ችግር ነው፡፡ የሚጓጓዘው ምንድነው ካልክ ችግሩን ትፈታዋለህ፡፡ ምክንያቱም ለምን የሚል ጥያቄ ይከተላል፡፡ ነገር ግን መንገድ ብቻ ካልክ ነው ችግሩ፡፡ መንገድ ለብቻው ከሄደ በቃ መንገድ ብቻ ይገነባል፡፡ ደረቅ ወደብ ኢንተርፕራይዝም የራሱን ሥራ ብቻ ነው የሚያስበው፡፡ ስለትራንስፖርት አያስብም፡፡ እነዚህ ችግሮች መፈታት አለባቸው፡፡ በማስተር ፕላኑ የሚፈቱ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ነው፡፡ ወደነዚህ አካባቢዎች የሚዘረጉ የባቡር መስመሮች በተገቢው መንገድ እንዲገነቡ ለማድረግ ትችላላችሁ ተብሎ ይገመታል፡፡ ነገር ግን የሰበታ ጂቡቲ ባቡር መስመር በአሁኑ ጊዜ ለአገልግሎት የቀረበ ነው፡፡ ነገር ግን መካተት የነበረባቸውን ሥራዎች ባለማካተቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ምን ታስቧል?
አቶ በቀለ፡- እኛ ሥራ ስንጀምር የአምስት ዓመትና የ2009 ዓ.ም. ዕቅድ አምጡ ነው ያልነው፡፡ ያላመጡም አለ፡፡ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እናስገድዳለን፡፡ ሌላኛው የወሰን ችግር ያለባቸውን ፕሮጀክቶች አምጡ አልን፡፡ ያመጡ አሉ፡፡ ያላመጡት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ማምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን እናልፍና ከዚህ በኋላ ግን በአገሪቱ የሚካሄድ ማንኛውም የፌዴራል ፕሮጀክት ከኤጀንሲው ፈቃድ ሳይወሰድ አይገነባም፡፡ እየተካሄዱ ያሉትን ግን የማቀናጀት ሥራዎች ውስጥ እንገባለን፡፡ የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ተጀምሯል፡፡ ሥራውን አናስቆምም፡፡ ግን በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ መቶ ሜትር ስፋት አለው፡፡ ፋይበር ኦፕቲክስ ይኖረዋል፣ ቴሌኮም፣ ኤሌክትሪክ ከመጡ ይህንኑ እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ አንድ ሚሊዮን ዛፍ ይተከላል፡፡ እነዚህን ሥራዎች እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በኋላ የሚመጡ የመሠረተ ልማት ተቋማት ፈቃድ ማውጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ሐዋሳ ቅርብ ነው፡፡ ነገር ግን የአውሮፕላን ማረፊያ ተገንብቷል፡፡ የፍጥነት መንገድ ተጀምሯል፡፡ የባቡር መስመር ዝርጋታም ታስቧል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የትራንስፖርት አውታሮች ከቅርበቱ አንፃር ሊገነቡ አይገባም፣ አዋጭ አይደለም ለሚሉ ምንድነው የሚሰጡት ምላሽ?
አቶ በቀለ፡- ዛሬ ላይ ሆነን ስናይ 270 ኪሎ ሜትር ርቀት ላለው ሐዋሳ ይህ መሠረተ ልማት የበዛ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ ከአዲስ አበባ ስለምናይ ነው፡፡ ከኬንያ አላየንም፡፡ ከኬንያ አውሮላፕን ተነስቶ ሐዋሳ ያርፋል ብለን ስለማናስብ ነው፡፡ ከትግራይ አላየንም፣ ከጂቡቲ፣ ከባህር ዳር አላየንም፡፡ እነዚህ መስመሮች በቅርብ ሊከፈቱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የበዛ የሚመስለን አንደኛ ሌሎች አካባቢዎች በተነፃፃሪ በዕቅድ ደረጃ የተለያዩ የትራንስፖርት አውታሮችን ተጠቃሚ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚያና ከአዲስ አበባ አንፃር ስናየው እንጂ ከተለያየ አቅጣጫ ካየነው ግን እነዚህ አውታሮች በቂ ላይሆኑም ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ መሥሪያ ቤትዎ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀው ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ቴሌኮም፣ ኤሌክትሪክ፣ አውሮፕላን ማረፊያ፣ መንገዶች፣ ወዘተ ማስተባበር ይጠበቅባችኋል፡፡ ከዚህ አንፃር ራሳችሁን ምን ያህል ዝግጁ አድርጋችኋል? የተሰጣችሁ ሥልጣንስ ምን ያህል ያስኬዳችኋል?
አቶ በቀለ፡- በአገሪቱ ውስጥ ማንኛውም የመሠረተ ልማት ቁፋሮ ያለኛ መሥሪያ ቤት ፈቃድ አይካሄድም እያልን ነው፡፡ ሁሉም ዕቅድ ከእኛ መሥሪያ ቤት መመንጨት አለበት እያልን ነው፡፡ ሁሉም የቅንጅት ሥራ፣ ኅብረተሰቡ የሚያለቅስበት የካሳ ክፍያ ውስጥ ሁሉ እንገባለን እያልን ነው፡፡ ይኼ በጣም ከባድ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የአገር ችግር ነው፡፡ የአገርን ችግር አንድ መሥሪያ ቤት አይፈታውም፡፡ እኛ እያደረግን ያለነው 140 ሠራተኞች ቀጥረናል፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጀማሪ መሐንዲሶች ናቸው፡፡ ዕውቀት ሳይሆን የልምድ ችግር ይኖራል፡፡ እያደረግን ያለነው የቁርጠኝነት ችግር እንዳይፈጠር ነው፡፡ የተነሳሽነትና የፍላጎት ሁኔታው የተለመደው ዓይነት ሳይሆን፣ በፍላጎት የሚሠሩና ለውጥ ማምጣት የሚፈልጉ ባለሙያዎችን ነው እያደራጀን ያለነው፡፡ በዚህ በኩል ጅማሬው ጥሩ ነው፡፡ የልምድ ችግር ግን አለ፡፡ አገር ውስጥ ያለውን ልምድ እንጠቀማለን፡፡ በውጭ ያለ ልምድም እንጠቀማለን፡፡ ሀብት የመንግሥት ድጋፍ በተመለከተ ጥርጣሬ የለንም፡፡ አንደኛ መሥሪያ ቤቱ በቀጥታ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ነው፡፡ ሁለተኛ አቅም ያለው ቦርድ ይኖረናል ብለን እናስባለን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በመግባባትና በማሳመን እንሠራለን ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ጥሩ ስሜት ነው ያለኝ፡፡ ሌላው ሥልጣናችን ነው፡፡ አዋጁ በሁሉም ላይ ሥልጣን እንዲኖረን አድርጓል፡፡ እኛ እስካልደከመን ድረስ ደንብ አርቅቀን በሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፀድቀን መሥሪያ ቤታችን ጉልበት እንዲኖረው ማድረግ እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- በመሠረተ ልማት ተቋማት በኩል ያለውን ፕላን ታዘጋጃላችሁ፣ እንዲተገበርም ታስተባብራላችሁ፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚውን ደግሞ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ይሠራል፡፡ በሁለታችሁ በኩል ያለው ግንኙነት ምን መልክ ይኖረዋል? ሥራችሁ ተወራራሽነት ስላለው ነው የምጠይቅዎት?
አቶ በቀለ፡- እኛ የፕላኒንግ ኮሚሽን ትልቁ ሀብት ነን፡፡ አንደኛ ማስተር ፕላኑን ለመሥራት ከእነሱ ብዙ መረጃ እንወስዳለን፡፡ እነሱ ደግሞ ሌላ ሥራ ከመሥራት እኛ የሠራነውን ማስተር ፕላን ይወስዳሉ፡፡ የእኛን መረጃ ተጠቅመው ከማክሮ ኢኮኖሚው ጋር አዋህደው ወደ ኢንቨስትመንት ይሄዳሉ፡፡ ሌሎች የሚሳከሩና የሚጋጩ ድንጋጌዎች ተሽረዋል፡፡ የቴክኒክ ባለሙያዎች ያሉን እኛ ነን፡፡ የውኃ፣ የመንገድ፣ የትራንስፖርትና የመሳሰሉት መሐንዲሶች ያሉን እኛ ነን፡፡ አብዛኛውን ሥራ ሠርተን የምናጠናቅቀው እኛ ነን፡፡ እነሱ ደግሞ ወስደው ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገባ ያደርጋሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ፕላንና ፕሮግራም የሚባሉ መዋቅሮች አሉ፡፡ እነዚህ መዋቅሮች ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች የአቅም ማነስ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ግን ባለሙያዎቹ ሲያቅዱ ጥቅም ለማያገኙባቸው ሥራዎች ትኩረት አለማድረግ፣ ወይም በሚያስፈልገው ሳይሆን እነሱ በሚያውቁት ቦታ ላይ ያተኩራሉ ይባላል፡፡
አቶ በቀለ፡- ሥራችንን ከመጀመራችን በፊት የምናደርገው ከቅንጅት ጋር በተያያዘ ተቋማቱ ከትልቁ ፕላን ጋር ተጣጥመው እንዴት ይሠራሉ የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮም አወቃቀሩ ምን ይመስላል የሚለውን እናያለን፡፡ እንዴት ነው ፕላን የሚያደርጉት? ከሌሎቹ ጋር እንዴት ነው የሚነጋገሩት? በአዋጁ እንቅፋት ካለ የእኛ መሥሪያ ቤት ያሻሽልና አዋጁን ማስለወጥ ይቻላል፡፡ አደረጃጀቶችን ከፕላን ጋር ብቻ ሳይሆን ከቅንጅት ጋር ያላቸው አሠራርን እናያለን፡፡ ፕላኒንግ ላይ ከካሳ አከፋፈል ጋር ምንድነው ችግራቸው የሚለውን እንለያለን፣ እናስተካክላለን፣ አዋጅ ይህን እንድናደርግ ሥልጣን ይሰጠናል፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ብዙ ቆይተዋል፡፡ በባለሥልጣኑ ብዙ መንገዶች የዲዛይን ለውጥ ይበዛባቸዋል፡፡ በፕላን ላይ የሌሉ ከፍተኛ ወጪዎችም ሲያስወጡ ቆይተዋል፡፡ ሙስና እንዳለባቸውም ይነገራል፡፡ ይህን ለማስተካከል የምትሠሩት ሥራ አለ?
አቶ በቀለ፡- መፈታት ያለበት ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በአንፃራዊነት ጥሩ ፕላን የሚዘጋጅበት መሥሪያ ቤት ነው፡፡ እኔ ስለነበርኩበት አይደለም፡፡ ብዙ ቦታዎች አዳዲስ መንገዶች ስለምንሠራ ፍላጎቱ በጣም ይለዋወጣል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ያቀድነው ነገ ይለወጣል፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዛሬ አልነበረም፣ ነገ ይታሰባል፡፡ የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ስንሠራ ዲዛይን አለወጥንም፣ ማንም አልጨቀጨቀንም፣ ቅሬታ አልቀረበም፣ በጊዜው ነው ያጠናቀቅነው፡፡ ለምንድነው መንገዱ ራሱን የቻለ መንገድ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ እዚያ ውስጥ ምንም አላለም፡፡ አንድ መንገድ ስንሠራ የራሱ ችግር አለ፡፡ ፍላጎቱ በብዛት ይለዋወጣል፡፡ አንዳንድ ቦታ የጠጠር መንገድ ለመሥራት እንጀምራለን፡፡ በድንገት ትራፊኩ ይጨምራል፡፡ ልክ እንደ ኢኮኖሚው ነው የዛሬ አሥር ዓመት አምስት በመቶ ያድጋል ይባላል፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በጣም ይጨምራል፡፡ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ፕላኑን ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ ለውጡ ግን ሁሉም ሰው የሚረዳው መሆን አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ ባለሥልጣናት ዲዛይን እስከ ማስለወጥና መንገዱ በመንደራቸው፣ በከተማቸው እንዲያልፍ ጫና ያደርጋሉ፡፡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ጣልቃ የሚገቡና ፕላን የሚያስቀይሩም ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዳሉ ይነገራል፡፡
አቶ በቀለ፡- በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ የሉም ማለት ግን አይቻልም፡፡ የፌዴራል መንገድ ሲለወጥ ችግር ያመጣል፡፡ ምንድነው በዚህ መስክ ያለው አንዳንዱ ከተማ መንገድ ከነበረበት ተትቶ ወደ ውጪ እንዲወጣ ይፈልጋል፡፡ ከተማው ያድግልናል ከሚል መልካም ሐሳብ በመነሳት ማለት ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በከተማ ውስጥ ይለፍ የሚል ይኖራል፡፡ በዚህ ወቅት ግጭት ይኖራል፡፡ የቡና ቤት፣ የሆቴል ባለቤቶች መንገዱ ከከተማ ውጪ ሲሆን ገበያ ሊቀንስብን ነው የሚል ሐሳብ ያነሳሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ቅሬታ ሊነሳ ይችላል፡፡ የፌዴራል መንገዶች ትልልቅ እንደመሆናቸው በመንደሬና በከተማዬ ይለፍ የሚል ነገር ከባድ ነው፡፡ በአነስተኛ መንገዶች ሊነሳ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ ቡድኖች ፍላጎታቸው አሳኩ ማለት አይቻልም፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚያስተባብሯቸው ኮርፖሬሽኖች ግዙፍ ናቸው፡፡ የራሳቸው ትልልቅና በከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚመሩ ቦርዶች አሏቸው፡፡ የእናንተ ኤጀንሲና ቦርድ ከእነዚህ አካላት ጋር ግጭት ውስጥ ሊገባ አይችልም?
አቶ በቀለ፡- ወሳኝ ነው፡፡ እኛ ቦርዳችንን ሆን ብለን አቆይተናል፡፡ ለውጥ ሊኖር ይችላል፡፡ አዳዲስ ዴኤታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሚመሠረትልን ቦርድ በየጊዜው ይገናኛል ማለት አይደለም፡፡ በየጊዜውም ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንሄዳለን ማለት አይደለም፡፡ የተባለው ችግር ሊኖር ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ግን መሥሪያ ቤታችን የአሠራር ባህሉ ደጋፊ መሆኑና የተሻለ ሥራ ማከናወኑ በሌሎች ግንዛቤው ሲመጣ ሥራውን በትብብር መሥራት ይቻላል፡፡