Sunday, March 26, 2023

የሕገ መንግሥቱን ቀጣይነት የማረጋገጥ የቤት ሥራዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በቅርቡ ካቤኔያቸውን በድጋሚ ያዋቀሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጽሕፈት ቤታቸው የሚገኙ አማካሪዎችን በተመለከተ ከሰጡት መግለጫ ጋር በተያያዘ፣ የልዩ አማካሪዎች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል በሚል ዜጎች መጠየቃቸው አልቀረም፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአንድ ጉዳይ ማማከር ከአሁን በኋላ ይቀራል፡፡ ይልቁንም የአማካሪ ቡድኑ ወጣት ምሁራንን በሚያሳትፍ መልኩ ደግሞ ይዋቀራል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩት ዶ/ር ፋሲል ናሆምን ጨምሮ የልዩ አማካሪዎች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ተጠባቂ ሆኗል፡፡ የዶ/ር ፋሲል የመንግሥትን ከፍተኛ አመራር የማማከር ሚና ከንጉሡ ጊዜ የሚጀምር ነው፡፡ ዶ/ር ፋሲል እ.ኤ.አ. በ1968 ከያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ካገኙ በኋላ፣ በአሜሪካ ከሚገኘው የግል ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሕግ አጠናቀዋል፡፡ ዶ/ር ፋሲል የሕግ መምህር በመሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ማገልገል ጀመሩ፡፡ የሕግ ትምህርት ቤትን በዲንነት ከመሩ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል የሚመደቡም ናቸው፡፡

ዶ/ር ፋሲል ቆይተው እ.ኤ.አ. በ1974 የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ላቋቋመው የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚቴ አማካሪ ሆነዋል፡፡ እርግጥ ነው ይህ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ሳይፀድቅና ወደ ሥራ ሳይገባ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በአብዮት ለመውደቅ ተገዷል፡፡ ‹‹በወቅቱ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ንጉሣዊ ሥርዓቱ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመራ ማድረግ የተሻለው አማራጭ ነው የሚል አቋም ይዤ ነበር፤›› በማለት ዶ/ር ፋሲል የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ ከጥቅምት 28 እስከ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. መቀሌ በሚገኘው አክሱም ሆቴል ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ መክፈቻ ቀን ላይ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ያልተሳካ ሙከራ በኋላ አገሪቱ ለ13 ዓመታት ያህል ያለ ሕገ መንግሥት ነው የተዳደረችው፡፡ ይሁንና ደርግም ከመውደቁ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ በኋላ እ.ኤ.አ. 1987 የፀደቀውን የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሒደት ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ዶ/ር ፋሲል ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን የማርቀቅ ሒደቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ዶ/ር ፋሲል፣ ‹‹ኢትዮጵያ በወቅቱ ትመራበት ከነበረው ሥርዓት ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማሸጋገር መልካም ዕድል እነደሆነ ነበር የወሰድኩት፤›› ብለዋል፡፡ ዶ/ር ፋሲል የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት ርዕዮተ ዓለማዊ ጫና ቢኖርበትም፣ የሃይማኖት ነፃነትን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊና የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን ያካተተ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ረቂቁን ሕገ መንግሥት ለፖሊት ቢሮው አስረክበናል፡፡ ቢሮው በሚፈልገው ጉዳይ ላይ ለውጥ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎችን እንዳለ በሙሉ ተቀብሏል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ፋሲል በንጉሡ ጊዜም ሆነ በደርግ ዘመን በሙያቸው በሰጡት አገልግሎት እንደሚኮሩ ቢገልጹም፣ በሥራ ላይ ስላለው ሕገ መንግሥት የማርቀቅና የማስፈጸም ሒደት ላይ ስላላቸው አስተዋጽኦ ሲናገሩ ስሜታቸው ሞቅ ይላል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደተቆጣጠረ ሕገ መንግሥት የማፅደቅ ሒደቱን እንዲያማክሩ ጠይቋቸዋል፡፡ ‹‹በወቅቱ እኔ ከልቤ የምፈልገው ዓይነት ሕገ መንግሥት በመሆኑ አብሮ ለመሥራት የራስ መተማመን ነበረኝ፡፡ በማርቀቅ ሒደቱም ሆነ በአፈጻጸም ረገድ ባለኝ አስተዋጽኦ ደስተኛ ነኝ፣ ኩራትም ይሰማኛል፤›› ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ አማካሪ ከመሆናቸው በፊት መንግሥትን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡ የፍትሕና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፣ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መሥራች ፕሬዚዳንትም ነበሩ፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን ባገለገሉባቸው ዓመታት ብዛትም ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡ ዶ/ር ፋሲል ‹‹Constitution for a Nation of Nations›› በሚል ርዕስ መጽሐፍም አሳትመዋል፡፡

‹‹ከአንድ ሕገ መንግሥት ወደ ሌላ ሕገ መንግሥት ወዲያ ወዲህ ማለት ዕጣ ፈንታዬ ሆኗል፤›› በማለት በፈገግታ ታጅበው ከተለያዩ ሕገ መንግሥቶች ጋር ስላላቸውና ስለነበራቸው ቁርኝት ተርከዋል፡፡ በአደጉት አገሮች በለውጥና በአለመረጋጋት ውስጥም ቢሆን ሕገ መንግሥት ሳይለወጥ መቀጠሉ የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ልምድ እንደሚያሳየው በአደጉ አገሮች መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር ሕገ መንግሥቶች ይቀያየራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ዶ/ር ፋሲል ስላለፉት ሕገ መንግሥታት ያላቸው ቅርብ ዕውቀትና አረዳድ የተሻሉ እሴቶችን፣ መርሆዎችንና ተቋማትን ወደ አዲሱ ሥርዓት ከማሸጋገር አንፃር አንድ አዎንታዊ ጎን እንዳለው የሚገልጹ አሉ፡፡

ይሁንና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህርት የሆኑት አቶ ሰይፈ ኃይሉ ለተለያዩ ሥርዓቶች ዶ/ር ፋሲል ሳያቋርጡ አገልግሎት እንዴት ሊሰጡ እንደቻሉ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ሰይፈ፣ ‹‹ፈጽሞ የተለያዩ ፍልስፍናዎችን የሚያካትቱ ሦስት መንግሥታትን እንዴት ሊያማክሩ ቻሉ?›› ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ ‹‹ላለፉት ሥርዓቶች ሙያዊ አገልግሎት በመስጠት ኩራት ይሰማኛል፡፡ በምችለው መጠን ለማማከር ሞክሬያለሁ፡፡ ሁሌም ቢሆን የምትሠራው ባለው ተጨበጭ ሁኔታ ሥር ነው፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን እየኖርክ የ21ኛው ክፍ ለዘመን ሰው ልትሆን አትችልም፤›› ብለዋል፡፡

በመቀሌው ኮንፈረንስ የአቅራቢዎቹን ሐሳብ በመደገፍ ወይም በመንቀፍ የሚሰማቸውን ሐሳብ በነፃነት በማጋራት ረገድ አቶ ሰይፈ ብቻቸውን አልነበሩም፡፡ ኮንፈረንሱ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ትክክለኛ የአካዴሚ ከባቢ የተስተዋለበት ነበር፡፡ በመሰብሰቢያ አዳራሹ የተገኙት አቅራቢዎችና ተሳታፊዎች በንቃት ሐሳባቸውን ለማጋራት ዳተኝነት አላሳዩም፡፡ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለተገኙ ሁነቶችና እሱን ተመርኩዞ ሊፈጠር ስለሚገባው ስምምነትም ያላቸውን ታማኝነት በአብዛኛው አጋርተዋል፡፡ አንጋፋና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱት የሕገ መንግሥትና የሰብዓዊ መብት የሕግ ባለሙያዎች እነ ዶ/ር ፋሲል ናሆም፣ ዶ/ር አሰፋ ፍሰሐ፣ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋና አቶ ጌታሁን ካሳ ሲጠቀሱ ከወጣት የሕግ ባለሙያዎች እነ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ አቶ ወንድወሰን ዋኬኔ፣ አቶ የማነ ካሳና አቶ ጀቱ ኢዶሳ ጋር በመጣመር ለኮንፈረንሱና ለተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች ነፍስ ዘርተዋል፡፡

በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ቀጣይነት

የመቀሌው ኮንፈረንስ ‹‹The FDRE Constitution at 20 and Beyond: Towards an Enduring Constitution›› በሚል ርዕስ ጭብጥ የተካሄደ ነው፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተው የጥናት ውጤቶቻቸውን ያጋሩት ኤክስፐርቶች ሕገ መንግሥቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ቅቡልነት ሊኖረው እንደሚገባና ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የሆኑ ዜጎች የአብላጫውን ድምፅ መያዝ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹Legitmacy, Integrity and Vitality: Perspectives on the Endurance of the FDRE Constitution›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቱ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ፣ የሕገ መንግሥት አርቃቂዎች የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሰነድ ለረጅም ዘመናት እንዲያገለግል አስበው ቢያዘጋጁትም ቀጣይነቱ ግን በተለያዩ ተያያዥነት ባላቸው ምክንያቶች ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ጌድዮን ለሕገ መንግሥት ቀጣይነት አስፈላጊ ከሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ተቀዳሚው ቅቡልነት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ቅቡልነት ኅብረተሰቡ ሕገ መንግሥቱን ተገቢና አሳማኝ ነው ብሎ በመቀበሉ የሚገለጽ ነው፡፡ ሌላኛው ምክንያት በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎችና በተግባር መሬት ላይ ባለው ሁኔታ መካከል ያለው መናበብ ነው፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ወይም ቅድመ ሁኔታ ደግሞ የሕገ መንግሥቱ የማደግ አቅም ነው፡፡ ይህም ለአዳዲስ ተጨባጭ ሁኔታዎች በሚሰጠው ምላሽ በዋናነት የሚገለጽ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከኢሕአዴግም ባሻገር ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች እንዳሉ ዶ/ር ጌድዮን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም በቅድሚያ የጠቀሱት ከሕገ መንግሥቱ ማርቀቅ ሒደት ጋር በተያያዘ ያለውን የቅቡልነት ክፍተት ነው፡፡ በማርቀቅ ሒደቱ የኢትዮጵያዊ ማንነትን ያቀነቅን የነበረው ቡድንን ጨምሮ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ቡድኖች መገለል፣ በተወካዮች ምክር ቤትና በሕገ መንግሥታዊ ጉባዔው ኢሕአዴግ ውስጥ ሕወሓት የበላይነት አለው ተብሎ መታመኑና ዜጎች ተደራጅተው ውጤታማ ተሳትፎ ማድረግ አለመቻላቸው የዚህ የቅቡልነት ክፍተት መገለጫዎች እንደሆኑም አስገንዝበዋል፡፡

ከዶ/ር ጌድዮን በተቃራኒ ዶ/ር ፋሲል ሕገ መንግሥቱ ቅቡልነት የጎደለው አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ዶ/ር ፋሲል ቅቡልነት የሚመነጨው ከሕዝቡ ፈቃድ እንደሆነ አስረግጠዋል፡፡ በ27,000 ቀበሌዎች 15 ሚሊዮን ዜጎች በሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደቱ መሳተፋቸው የሚያረጋግጠው የቅቡልነት ችግር አለመኖሩን ነው ሲሉም ሞግተዋል፡፡ ዶ/ር ፋሲል ‹‹The Making of the FDRE Constitution: Exploring the Original Legitimacy›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ የፖለቲካ መረጋጋት ሌላኛው ቁልፍ የቅቡልነት መገለጫ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አንድ ተሳታፊ እንደ ኢሠፓ፣ መኢሶንና ኢሕአፓ ያሉ ፓርቲዎች በሒደቱ እንዳይሳተፉ ለምን ተከለከሉ ሲሉ ለዶ/ር ፋሲል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡ የታገለው እነሱን ለመጣል ነው፡፡ አባላቱ ወንጀል ፈጽመው ነበር፡፡ አመራሩም በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር፡፡ በተለይ ኢሠፓ ዕድል ካገኘ ጦርነቱን መቀጠል ነበር የሚፈልገው፡፡ እኛ ደግሞ ሰላም ነበር የምንፈልገው፡፡ እናም እነሱን አካተን ጦርነት ውስጥ እንግባ እንዲሉን ዕድል መስጠት ነበረብን?›› በማለት ዶ/ር ፋሲል መገለላቸው ተገቢ ነው ብለው ተከራክረዋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት አቶ ሙሉ በየነ ሕገ መንግሥት ካለፈው ሥርዓት የተለየ አዲስ ሥርዓት ለማምጣት ዋነኛ መሣሪያ ከመሆኑ አኳያ፣ ካለፈው ሥርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውን የተወሰነ አካል ከሒደቱ ማግለሉ የማይቀር ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ዶ/ር ጌድዮን ግን በጉዳዩ ላይ የተለየ አመለካከት ነው ያላቸው፡፡ ‹‹ካለፈው ሥርዓት ጋር ቁርኝት አለው በማለት ቁጥሩ ቀላል የማይባል ማኅበረሰብ ክፍልን ማግለል አይቻልም፡፡ ባለፈው ሥርዓት ያለውን መንገድ ለመከተል ብንመርጥ እንኳን በምን ያህል መጠን እንለወጥ? በምን አቅጣጫ እንለወጥ? የሚሉት ጉዳዮች ራሳቸው ሁሉን አቀፍ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መወሰን አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ሙሉ ፓርቲዎቹ በአካል ባይወከሉም ሐሳባቸውስ አልተስተናገደም ነበር ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ዶ/ር ጌድዮን ከኢሕአዴግ ሕገ መንግሥታዊ ራዕይና ፍላጎት የተለየ አመለካከት የነበራቸው አካላት ሐሳብም ጭምር አልተስተናገደም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ከኮንፈረንሱ ጥናት አቅራቡዎች አንዱ አቶ ምስክር ታሪኩ የቅቡልነት ዝቅተኛው መሥፈርት ምን እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ ዶ/ር ጌድዮን በጥያቄው ላይ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ቅቡልነትን በቁጥር ልትለካው አትችልም፡፡ ሕዝቡ ሕገ መንግሥቱ ባቋቋማቸው ተቋማት ላይ አመኔታ አጥቶ ቅሬታና በደሉን ለማሰማት ኢ ሕገ መንግሥታዊ አካሄድን ከመረጠ ግን የቅቡልነት ችግር እንዳለ ግልጽ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹Making constitutions Endure from Below: Issues of Constitutional Loyalty in Multinational Federal Politics›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ ወንድወሰን ዋኬኔ ሕገ መንግሥታዊ ታማኝነት የአንድ ሕገ መንግሥት ቀጣይነትን ከሚወሰኑ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ለሕገ መንግሥት ታማኝ መሆን ማለት የሕገ መንግሥቱን ሁሉንም አንቀጾች መቀበል እንዳልሆነ፣ በአፈጻጸሙ ላይም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መተቸት ከሕገ መንግሥታዊ ታማኝነት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ተከራክረዋል፡፡

አቶ ወንድወሰን በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ ሁለት ጽንፍ የያዙ አቋሞች እንዳሉ አስታውሰዋል፡፡ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱን ፍፁም አድርጎ መስበኩም ሆነ ተቃዋሚዎች የችግሮች ሁሉ ምንጭ ሕገ መንግሥቱ ነው ማለታቸው የሚያዋጣ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

ዶ/ር ጌድዮንና ሌሎች ጥናት አቅራቢዎች ከሕገ መንግሥቱ ቅቡልነት ባልተናነሰ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ጉዳዮችን የመከወን ችግር ጎልቶ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ እንደ አብነት በዶ/ር ጌድዮን የተጠቀሱት ከፌዴራል መዋቅሩ ጋር ተጻራሪ የሆነ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት፣ አገሪቱ በተግባር ወደ አንድ ፓርቲ ሥርዓት መሸጋገሯ፣ በየቀኑ የሚከሰቱ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ጥሰቶችና በሕገ መንግሥቱ ነፃና ገለልተኛ ሆነው የተቋቋሙ ተቋማት ወገንተኝነት እያደገና እየጎላ መምጣቱ ናቸው፡፡

በኮንፈረንሱ ‹‹Federalism and the Evolving Conceptions of Unity and Diversity in Ethiopia: Capturing the Emerging Issues›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ዕውቁ የፌዴራሊዝም ኤክስፐርትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራል ጥናት ተቋም ኃላፊ ዶ/ር አሰፋ ፍሰሐ፣ በቅርቡ አገሪቱ የገጠማት ችግር በሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ሐሳቦችና በተግባር መካከል ልዩነት ከመኖሩ ጋር የተያያዘ ገጽታ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር አሰፋ ሕገ መንግሥቱና የፌዴራል መዋቅሩ ለቡድኖች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማጎናፀፍ፣ የዜጎችን ሕይወትና ኑሮ ለማሻሻል፣ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም አሁንም የሚቀሩ ብዙ ነገሮች እንዳሉ አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ ከፍተኛ ትኩረትና የቅቡልነት መሣሪያ እየሆነ በመጣው የልማት ጉዳይ ላይ ዜጎችና ቡድኖች በበቂ ሁኔታ ተሳታፊ አለመደረጋቸው ችግሮችን ይዞ እየመጣ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የልማታዊ መንግሥት የዕድገት ሞዴል አውራ ፓርቲ በመፍጠሩ ኢኮኖሚው ሊጠቀም የሚችልበት ዕድል ቢኖርም፣ የሐሳብ ብዝኃነትን በመድፈቅ የራሱ የሆነ ሌላ ችግር መምዘዙንም አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ ከተቋማት ይልቅ በፖለቲካ እንደሚመራ በኦሮሚያና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ከተከሰተው አደጋ ማየት እንደሚቻልም ዶ/ር አሰፋ አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ በማሰብ በሕገ መንግሥቱ የተቋቋሙ ተቋማት ድምፃቸው አለመሰማቱ የችግሩን መጠን እንደሚያሳይም ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ጌድዮንም በተመሳሳይ ሕገ መንግሥቱ ለአዳዲስ ሁኔታዎች ምላሽ እየሰጠና እያደገ እንዳይሄድ እንደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ፍርድ ቤቶች ያሉ ተቋማት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥር ያሉ ምሁራንና የሕግ ባለሙያዎች የሚሰበቅባቸውን አለመፈጸማቸው የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከኢሕአዴግ በኋላ እንዳይቀጥል የሚያደርጉ በርካታ ክፍተቶች ያሉ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ስፖንሰሩ ኢሕአዴግ ሥልጣን ቢለቅ እንኳን መቀጠል ያለበት ስለመሆኑ ተከራክረዋል፡፡ ሦስት መሠረታዊ መከራከሪያ ነጥቦችንም ዘርዝረዋል፡፡ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥቱ ያስከተለው የፌዴራል መዋቅርና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ቀላል ቁጥር በሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው መሆኑና ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጣቸው የቤተሰብ የመብት ጥበቃ የተካተቱበት መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛ ሕገ መንግሥታዊ ባህል ለመፍጠርና ለማስፋፋት ቀጣይነት የሚፈለግ በመሆኑ ነው፡፡ ሦስተኛ አዲስ ሕገ መንግሥት ለማርቀቅ መሞከር ዋጋው እጅግ ከፍተኛ ነው፣ የመከፋፈል አደጋ ያመጣል፣ የፖለቲካ ዋጋውም ቀላል አይሆንም ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -