ፕሬዘዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዓርብ ኅዳር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. አገሪቱን በውጭ አገሮች ለሚወክሉ ስምንት ተሿሚዎች የሙሉ አምባሳደርነት ሹመት ሰጡ፡፡ ምንም እንኳ ተሿሚዎቹ የሚሄዱባቸው አገሮች ባይገለጽም፣ በቅርቡ ከያዙት የሚኒስትርነት ሥልጣን የተነሱ ይገኙበታል፡፡ በዚህ መሠረት የቀድሞው የወጣቶችና የስፖርት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ የቀድሞዋ የሴቶችና ሕፃናት ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ፣ የቀድሞው የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ቶሎሳ ሻጊ፣ የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዘዳንትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀጥታ አማካሪ አቶ ፀጋዬ በርሄ፣ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ረጋሳ ከፍአለ፣ በሶማሊያ የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ፣ እንዲሁም አቶ ግርማ ተመስገን በፕሬዘዳንቱ መሾማቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡