Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በአካባቢው የሚያልፈው የባቡር ሐዲድ በዱር እንስሳቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ...

  አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በአካባቢው የሚያልፈው የባቡር ሐዲድ በዱር እንስሳቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስታወቀ

  ቀን:

  በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ አቋርጦ የሚያልፈው አዲሱ የባቡር ሐዲድና በዙርያው የሚገኙ አርብቶ አደሮች፣ በዱር እንስሳቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የአዋሽ ፓርክ ቺፍ ዋርደን ተወካይ ገለጹ፡፡

  ተወካዩ አቶ  ሺፈራው መንግሥቴ ይህንኑ አስመልክተው ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ የባቡር ሐዲዱ የዱር እንስሳቱን አኗኗር በጠበቀ መልኩ አለመሠራቱና ለአርብቶ አደሮች ከከብቶች የግጦሽ መሬት አለመኖሩ የዱር እንስሳቱ ላይ በፈጠሩት ጫና እንስሳቱ እየተሰደዱ ነው፡፡ ለቁጥራቸው መመናመንም ምክንያት ሆኗል፡፡

  ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የሚዘልቀው የባቡር ሐዲድ መጀመሪያ ሲሠራ የዱር እንስሳት መኖሪያ አካባቢዎች በሆኑ የተለያዩ 11 ሥፍራዎች ላይ ‹‹ኦቨርና አንደር ፓሶች›› ማለትም ሐዲዱ የሚያርፍበት ቦታ ከፍ ያለ ከሆነ ከሥሩ፣ እንዲሁም ዝቅ ያለ ቦታ ከሆነ ደግሞ በላዩ ላይ መተላለፊያዎች ይሠራሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ይህ እንዳልተደረገ ተወካዩ ተናግረዋል፡፡

  አብዛኛው የባቡር ሐዲድ ከፍታ ቦታ ላይ ከመሠራቱም በላይ ዙሪያው በድንጋይ ተከቧል፡፡ የዱር እንስሳቱ አዲስ ነገር ስለሆነባቸው ይደነብራሉ፡፡ ቀድሞ ወደነበሩበት ሳይመለሱ እንደተሻገሩ ይቀራሉ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ወደ ጂቡቲ የሚያልፈው አስፋልት መንገድ ስላለ ሐዲዱንና አስፋልቱን አቋርጠው ለማለፍ ወይም ለማዘዋወር እንደሚቸገሩም ተናግረዋል፡፡

  ምናልባትም በፓርኩ የሚገኙ የዱር እንስሳት በዚህ ዓመት ቁጥራቸው የቀነሰበት ምክንያትም፣ ባለፈው ዓመት በነበረው ድርቅ ሣርና ውኃ ፍለጋ ከሐዲዱ ባሻገር ሄደው ተቆርጠው ቀርተው ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ከሐዲዱ ባሻገር ያለው ሜዳ ደግሞ እስከ 30 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም አቶ ሺፈራው ተናግረዋል፡፡

  ይህንን ችግር ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል አሳውቃችኋል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሺፈራው ሲመልሱ፣ ‹‹ይህንን የማያውቅ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል አለ ብዬ አላስብም፡፡ ለባለሥልጣኑ አሳውቀናል፤ መሥሪያ ቤቱም ‹ከሚመለከተው አካል ጋር የተቻለንን አድርገናል› ብሎናል›› ብለዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፕሬሽን የኮሚኒኬሽን ማናጀር አቶ ደረጀ ተፈራ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው፣ በዚሁ አካባቢ ቀደም ሲልም ባቡር እንደነበር፣ የአሁኑ ባቡር ደግሞ ድምፅ የሌለውና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ በመሆኑ፣ የዱር እንስሳቱን እንደማይረብሽ ተናግረዋል፡፡

  በሌላ በኩልም በብሔራዊ ፓርኩ ዙሪያ የሚገኙት አርብቶ አደሮች እርስ በእርሳቸው የሚወዳደሩት ባላቸው ግመሎች፣ ከብቶችና በጎች ብዛት ሲሆን፣ የከብቶቻቸውን ቁጥር ለማብዛት መኖ ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህንንም የሚያገኙት ከፓርኩ ሲሆን፣ ፓርኩ ሲገቡም ዘመናዊ ታጣቂውና ዘመናዊ መሣሪያ የፓርኩን የጥበቃ አካላት አባረው ነው፡፡ አንድ አርብቶ አደርም ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ ከብቶች እንዳሉት አቶ ሺፈራው ተናግረዋል፡፡

  ከብቶችን ለግጦሽ ማሰማራት ብቻ ሳይሆን ውስጥ ገብተው እንደሚሰፍሩ፣ ሲሰፍሩ ደግሞ ከብቶቻቸውን ይዝው እንደሚገቡ ተወካዩ ተናግረዋል፡፡ ከብቶቹ ወደ ፓርኩ ሲገቡ፣ ፓርቲኒየም እና ፕሮስኦፊስ የተባሉ አረሞችን ይዘው የሚገቡ በመሆናቸው በፓርኩ የሚገኝ ዕፀዋትን እያጠፋ ይገኛል፡፡ ፓርቲኒየም በጣም እየተስፋፋና በአንጻሩም ለግጦሽ የሚውለው ሳርም እየጠፋ መምጣቱንም አክለዋል፡፡

  አርብቶ አደሮቹ በፓርክ ውስጥ ሰፍረው፣ ከሰል እንደሚያከስሉ በዚህም የተነሳ የአካባቢውን ደን እየተራቆተና ይህ ዓይነቱ ተፅዕኖ ለችግሩ መባባስ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ተወካዩ አስረድተዋል፡፡

  በፓርኩ ውስጥ በ2005 ዓ.ም ወደ 700 ሳላ፣ ከ200 በላይ አምብራይሌ፣ 82 ወተርባክ፣ በርካታ ኢንሹዎችና ሌሎች የዱር እንስሳት መኖራቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ግን የሳላዎች ቁጥር ወደ 182 ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል፡፡

  በተጠቀሰው ጫና ሳቢያ የዱር እንስሳቱ በአብዛኛው በአፋር ክልል ሆኖ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች በሚያዋስኑትና ልዩ ስሙ አሊደጌ ወደሚባለው ፓርክ መሰደዳቸውን ተወካዩ ጠቁመዋል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img