ዕለተ ቅዳሜ ጠዋት የዕረፍት ቀኔ እንደመሆኑ፣ የልማዴን ቡና ለማድረስ ከመኖሪያ ቤቴ 200 ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ካፌ ታኅሣሥ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ተገኝቻለሁ፡፡ ከለመድኩት የጠዋት ቡና ጎን ለጎን የአዲስ አበባን ሳምንታዊ ጋዜጣና መጽሔቶች ይዘት ጎብኘት አድርጌ ወደ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ስመለስ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አዲስ ፎቶ መነጋገሪያ ሆኖ አገኘሁት፡፡
መነጋገሪያ የነበረው ፎቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች በአንዱ ጥግ ቆሻሻ እየጠረጉ የሚያሳየው ነው፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተጀመረው የውይይት ሐሳብ በፍፁም ትኩረቴን አልሳበውም፡፡ አንድ መሪም ከቤተ መንግሥቱ ወጥቶ በከተማዋ ጎዳናዎች ቆሻሻ በመጥረግ የፅዳት ዘመቻ መጀመሩ ተምሳሌታዊነቱ ጉልህ መሆኑን አልክድም፡፡
‹‹ነገር ግን አዲስ አበባን ፅዱ ማድረግ የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው?›› የሚል ጥያቄ በአዕምሮዬ እየተመላለሰ ወደ ቤቴ ሳቀና አንድ ክስተት ሳበኝ፡፡
ከኔ መንገድ በተቃራኒ ባለው የመንገድ ጠርዝ ‹‹ቪ8› የሚባለውና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚመደብላቸው አንዳንዴም ባለሀብቶች የሚይዙት ተሽከርካሪ ቆሟል፡፡
ተሽከርከሪው ከግል ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት በመቆሙ ባለሥልጣኑ ኮሌጅ የምትማር/የሚማር ልጁን ወይ ቤተሰቡን እየጠበቀ እንደሆነ በመገመት ዓይኔን ሳልነቅል ማንነቱን ለማወቅ ስጥር የሽንብራ እሸት እየበላ በመስኮት በኩል ወደ ውጭ አስፋልት ላይ ይጥላል፡፡ ያየሁትን ድርጊት ኮድ አራት ታርጋ ከተለጠፈበት የመንግሥት ተሽከርካሪ ባለመጠበቄ የሰውዬውን ማንነት ለማወቅ ጉጉት አደረብኝና ተጠጋሁ፡፡ የባለሥልጣን ሾፌር ይሆን? እሱስ ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ጎዳና እየጠረጉ እንዴት ቆሻሻ ይጥላል? የሚል ጥያቄ እየተመላለሰብኝ ተጠጋሁት፡፡ ያጋጠመኝ ግን ተቃራኒ ነበር፡፡
በቅርበት ባይሆንም የማውቃቸው ከፍተኛ አመራር ናቸው፡፡ ማንነቴን ከመለየታቸው በፊት ፊቴን ወደ ሌላ አቅጣጫ አዙሬ ፍጥነቴን ጨመርኩ፡፡ እሳቸው ቆሻሻ በጣሉ እኔ ለምን ደንግጬ እንዳያዩኝ ሠጋሁ? የሚል ጥያቄ በአንድ በኩል ሲሞግተኝ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎዳና ማፅዳት በጀመሩበት ቀን?›› ብለህ በማፌዝ ሰላምታ ተለዋውጠህ አታሳፍራቸውም ነበር የሚል ሐሳብም መጣብኝ፡፡
ባለሥልጣኑ በመስኮት የጣሉት ቆሻሻና አዲስ አበባን በየወሩ የማፅዳት
ከፍተኛ ባለሥልጣኑ የሕግ ምሁር እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡ በመሆኑም የንቃተ ህሊና ወይም የግንዛቤ ችግር እንደሌለባቸው ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን ቆሻሻን ከማስወገድና አዲስ አበባን ፅዱ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ማኅበረሰቡን ሰንጎ የያዘው የአመለካከት ችግር መገለጫ ይመስሉኛል፡፡ ከምሁርነታቸው ባለፈ የመንግሥት ከፍተኛ አመራር መሆናቸውና ኮድ አራት ታርጋ በለጠፈ ተሽከርካሪ ውስጥ ሆነው የሽንብራ እሸቱን ተረፈ ቆሻሻ ደጋግመው ወደ መንገዱ መጣላቸው የደረስንበትን የአመለካከት ጫፍ የሚያሳይ ነው፡፡ ኮድ አራት ታርጋ የለጠፈ ተሽከርካሪ ለዚያውም ቪ8 ለመንግሥት ባለሥልጣን የተመደበ መሆኑ የአደባባይ መረጃ ሆኖ ሳለ፣ ሳይጨነቁ ቆሻሻውን መጣላቸው ‹‹እንዴትና ለምን?›› ብሎ የመጠየቅ የሞሯል ልዕልና ያዳበረ ማኅበረሰብ አለመኖሩን ወይም የማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ድርጊት በመሆኑ እንደ ነውር አለማየታቸውን ይናገራል፡፡
ሲጠቃለልም ከፍተኛ ባለሥልጣኑ የማኅበረሰቡ አካል እንደመሆናቸው ድርጊታቸውም የዚሁ ነፀብራቅ ነው፡፡ ቆሻሻ ጎጂና አፀያፊ ስለመሆኑ የእሳቸውም ሆነ የማኅበረሰቡ ተመሳሳይ ልማዳዊ ድርጊቶች አመልካች ናቸው፡፡ እሳቸው ቆሻሻውን ከተሽከርካሪው ውስጥ አርቀው እንደጣሉት በየዕለቱ የማኅበረሰቡ ድርጊትም መኖሪያ ቤትንና ደጃፍን አፅድቶ ቆሻሻውን የማስወገድ ሳይሆን የማራቅ ተግባር ነው፡፡ ይህ ድርጊት ማኅበረሰቡ ቆሻሻን ስለመጠየፉ የሚናገር ቢሆንም ቆሻሻን ከተወሰነ ‹‹የኛ›› ከምንለው ሥፍራ በማራቅ ባለቤት እንዳይኖረው የማድረግ የቆየ ልማድ ሰለባ በመሆናችን ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል፡፡ አዲስ አበባ ባለቤት የሌለው ቆሻሻ ከተማ የሆነችው፡፡
ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኑ ከላይ የተገለጸውን ማኅበራዊ ጉድለት ፍንትው አድርገው ሲያሳዩን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ለዚህ ማኅበራዊ ችግር መፍትሔ እንደሆኑ ያመኑበትን ድርጊት ጎዳና ላይ ወጥተው በመከወን የአዲስ አበባን ማኅበረሰብ ለማነቃነቅ የተጀመረው የፅዳት ዘመቻ አካል መሆናቸውን እንረዳለን፡፡
‹‹እኔ አካባቢዬን አፀዳለሁ እናንተስ?›› በሚል መሪ ቃል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በተጀመረው አዲስ አበባን የማፅዳት ዘመቻ በየወሩ መጨረሻ ቅዳሜ እንደሚካሄድና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ዘመቻው በሚቆይበት የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በየወሩ በፅዳት ዘመቻው እንደሚሳተፉ ይፋ አድርገዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚታየውን የቆሻሻ አያያዝ ጉድለት ለመቅረፍ ሁሉም በኃላፊነት ካልሠራ ከተማዋ በዓለም በዚሁ ችግር የምትታወቀውን የህንድ ከተማ ኒውደልሂ የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አቶ ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ ከሚያደርጋቸው ጥረት ጎን አካባቢን ማፅዳት የኅብረተሰቡ ቋሚ ባህል እንዲሆን ማድረግ የዘመቻው ዓላማ መሆኑን ደግሞ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በወቅቱ ተናግረዋል፡፡
አካባቢን ማፅዳት ወይስ አዲስ አበባን ፅዱ ማድረግ?
በተጀመረው በዚህ የፅዳት ዘመቻ የአዲስ አበባ ማኅበረሰብ የመኖሪያ አካባቢውን ሊያፀዳ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚህ መንገድ አዲስ አበባን ፅዱ ማድረግ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ችግሩን ለመመለስ ቁልፍ ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ማኅበረሰቡ ቆሻሻን አስመልክቶ ያለውን አመለካከት መቀየር ተገቢ ቢሆንም፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የከተማዋ አስተዳድር ቢሮን ተቋማዊ አመለካከት መቀየር ቀዳሚው ጉዳይ ስለመሆኑ የሌሎች አገሮች ስኬታማ ተሞክሮ ምስክር ነው፡፡ ቆሻሻ መወገድ ያለበት ጉዳት ያለው አፀያፊ ቁስ ቢሆንም፣ ቆሻሻ ሀብት ነው በሚል መርህ ተኮር ተግባር የተንቀሳቀሱ አገሮች ስኬታማ ሆነዋል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ለሥራ ጉዳይ በጃፓን የተለያዩ ከተሞችን በጎበኘሁበት ወቅት ያስተዋልኩት የከተሞቹ ተሞክሮ ይህንኑ ይመሰክራል፡፡ ከጃፓን ዋና መዲና ቶኪዮ ጎረቤት የሆነችው ዮኮሃማ ከጃፓን ሰባት ግዙፍ ከተሞች መካከል አንዷ ነች፡፡
ከዮኮሃማ 3.7 ሚሊዮን ነዋሪዎች በየዓመቱ የሚመነጨውን 1.2 ሚሊዮን ቶን ቆሻሻ ማስወገድ ከሁለት አሠርታት በፊት የከተማዋ አመራሮች ፈተና፣ የማኅበረሰቡ ችግር፣ የከተማዋ ከባቢያዊ ጤንነት ሥጋትና አጠልሺ ገጽታ ነበር፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በአስተሳሰብ ደረጃ የተቀፀረው ሥራ ቆሻሻን የማስወገድ ተግባር ራሱን የቻለ አንድ ትልቅና የማይቆም ፕሮጀክት አድርጎ ከመረዳት ይጀምራል፡፡ የሕግ ማዕቀፍ፣ ተዋረድ ያለው ሥርዓት መዘርጋት የዚህ ፕሮጀክት ቀዳሚ አካል ሲሆኑ፣ ቆሻሻን በየዓይነቱ በቤተሰብ ደረጃ ከመለየት አንስቶ በተከፋፈሉ አካባቢዎች የመሰብሰብ ተግባርና መዋቅርን የማደራጀት ሥራን ያካትታል፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ የተሰበሰበው ቆሻሻ የአካባቢ ጉዳት ሳያስከትል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚሰጥ መንገድ እንዴት ይወገዳል? የሚለው ዋነኛው የፕሮጀክቱ አካል ነበር፡፡ ይህ ሒደት ቆሻሻን እንደ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ ሀብት በመቁጠር የፕሮጀክት ቀረፃ ሒደቱ ተከናውኗል፡፡
የዮኮሃማ ከተማን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር መቅረፍ ተጓዳኝ ዓላማ ያደረገው የፕሮጀክቱ ቀረፃ፣ ካንዛዋ የኃይል ማመንጫ ጣቢያን ዕውን ማድረግ ችሏል፡፡
ይህ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የከተማዋ ቆሻሻዎችን በየዓይነታቸው ተለይተው እንዲቀርቡ በማድረግ አካባቢን በማይበክል ከፍተኛ ሙቀት በማቃጠል ማስወገድ አንዱ ተግባሩ ሲሆን፣ በዚህ ሒደት የሚፈጠረውን ከፍተኛ ግፊት ያዘለ እንፋሎት በመጠቀም የጂኦ ተርማል ኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል፡፡
የዚሁ ጣቢያ ሌላኛው አካል ደግሞ መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲክና የአልሙኒየም ቆርቆሮ ቆሻሻ ዓይነቶችን በመለየት መልሶ የመፈብረክ ተግባር ይካሄድበታል፡፡ በፕላስቲክ ቆሻሻ ማቀነባሪያ ውስጥ ተወጋጅ ፕላስቲኮች አልፈው ሲያበቁ የሚገኘው የመጨረሻ ውጤት ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በግብዓትነት ይቀርባሉ፡፡ ከዚህም የጥጥ ፈር የመሰሉ የአልጋ መውረጃ ሸበጦች እንዲሁም ሙቀት የሚሰጡ አልባሳት ተፈብርከው ለገበያ ይቀርባሉ፡፡ የአልሙኒየም ምርት የነበሩ ተወጋጅ ቆሻሻዎች በተመሳሳይ ሪሳይክሊንግ ሒደት ውስጥ አልፈው ተመልሶ የቢራና ለስላሳ መጠጦች ማሸጊያ ቆርቆሮ ይፈበረክባቸዋል፡፡
በእንፋሎት ኃይል የሚሠራው የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት በዓመት 319,128 ሜጋ ዋት በሰዓት በማመንጨት ለጃፓን ኃይል አከፋፋይ ኩባንያ ያቀርባል፡፡
‹‹ካናዛዋ ፕላንት›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው የዮካሃማ ከተማ ቆሻሻ ማስወገጃ ጣቢያ ተገንብቶ የተጠናቀቀው እ.ኤ.አ. በ2002 ሲሆን፣ ጣቢያውን ለማቋቋም የወጣው አጠቃላይ ወጪ 41 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር በቆይታዬ ከኃላፊዎቹ ተረድቻለሁ፡፡
ይህ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት የሚያመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ብቻ በየዓመቱ 30.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል፡፡ በከፍተኛ የሙቀት ኃይል ከሚቃጠለው ቆሻሻ የሚገኘው የመጨረሻ ምርት ደግሞ ለመንገድ ሥራ አገልግሎት ይውላል፡፡
ከከተማዋ 3.7 ሚሊዮን ነዋሪዎች የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ መሰብሰቢያ 77,000 ቦታዎች ተለይተው የተሰናዱ ሲሆን፣ ከ30 እስከ 40 ለሚሆኑ አባወራዎች አንድ ቆሻሻ መሰብሰቢያ በሚል ሥሌት የተደራጁ ናቸው፡፡ ከየማከማቻዎቹ ቆሻሻውን ወደ ጣቢያው የሚያመላልሱ 900 ተሽከርካሪዎችና 1,000 ሠራተኞች የየዕለት ሥራቸውን ሳያቋርጡ ይተገብራሉ፡፡
አገልግሎቱ ከ15 ዓመታት በፊት ሲጀመር ከእያንዳንዱ ቤት የሚወጣውን ቆሻሻ በየዓይነታቸው ለይቶ የማሰናዳት ቸልተኝነት በማኅበረሰቡ ዘንድ መንፀባረቁ ዋነኛ ችግር የነበረ ቢሆንም፣ ቅጣትን የሚያስከትል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ መቀረፉን ገንዝቤያለሁ፡፡
የሚወገዱ ቆሻሻዎችን ለይቶ ያላሰናዳ በመጀመርያ የግንዛቤ ማብራሪያ ይሰጠዋል፡፡ በመቀጠል ማስጠንቀቂያ፣ በኋላም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ስህተቱን ወይም ቸልተኝነቱን የደገመ ሁለት ሺሕ የን ቅጣት ይጣልበታል፡፡
ስህተቱን የሚደግሙት ተቋማት ከሆኑ ግን የገንዘብ ቅጣቱ ከፍ የሚል ሲሆን፣ በተጨማሪም በሕዝብ ፊት እንዲሸማቀቁ ስህተቱን በሠሩ ቁጥር ስማቸው በይፋ ይገለጻል፡፡ በዚህ መንገድ ችግሩን በመፍታት ሥርዓት ማስያዛቸውን በቆይታዬ ተረድቻለሁ፡፡ ቆሻሻ ከየመንደሩ የሚሰበስቡ ሠራተኞች ተሽከርካሪ የሚቀርብላቸው ቢሆንም ተቀጣሪ አይደሉም፡፡ በየቀኑ ላቀረቡት የቆሻሻ መጠን ግን በቶን ክፍያ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡
ከጃፓኗ ዮኮሃማ ከተማና ከሌሎች የተሳካላቸው ከተሞች መረዳት የሚቻለው፣ ቆሻሻ የኢኮኖሚ ገቢ ምንጭ፣ ማለትም ከአንዱ ቤት የመነጨ ቆሻሻ ለሌላው የገቢ ምንጭ መሆን እንደሚችል፣ በጥቅሉ ደግሞ ለከተማዋ ወይም ለአገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ፅዱ ከተማም መፍጠር እንደሚቻል ነው፡፡
ይህንን እውነት የሚያደርጉ ተሞክሮዎች ከከተማዋ አስተዳደር ድጋፍ ውጪ የተጀመሩ መሆናቸውን በማጤን ሥርዓት ማበጀትን ይጠይቃል፡፡
የመጠጥ ውኃ የቀረበባቸው የፕላስቲክ ማሸጊያዎች በአንድ ወቅት በየአካባቢው ተዝረክርከው ያስቸግሩ እንደነበር አሁን ላይ ግን ቆሻሻ ከየቤቱ የሚሰበስቡ ወጣቶች የሰበሰቡትን ቆሻሻ በሚያከማቹበት ሥፍራ ፕላስቲኮቹን ከክምችቱ የመለየት አስቸጋሪ ሥራ አከናውነው ለፕላስቲክ ፋብሪካዎች በግብዓትነት በማቅረብ ከዋናው ቆሻሻ የመሰብሰብ ሥራ ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ ጠቃሚ የገቢ ምንጭ ሆኗቸዋል፡፡
ቤት ለቤት በመዞር ጥቅም የማይሰጡ ጫማዎችን፣ አልባሳትንና ሌሎች ቁሶችን በመግዛት ወይም በልዋጭ ዕቃ የሚያስወግዱ በተለምዶ ‹‹ቁራሌው›› እና ‹‹ልዋጭ›› ተብለው የሚጠሩ የግል ጥረት ሠራተኞች ተሞክሮ የሚያስተምረውም ቆሻሻን ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር በማያያዝ በአግባቡ ማስወገድ የሚቻል መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱን የሚመራ ተቋም ይጠይቃል፡፡
በአዲስ አበባ የተጀመረው በየወሩ አካባቢን የማፅዳት ዘመቻ በራሱ ፋይዳ የለውም ባይባልም ፅዱ አዲስ አበባን ከመፍጠር አንፃር የሚያስፈልገውን የማኅበረሰቡን አመለካከት ከመቀየር አንፃር ሲመዘን ግን መሠረታዊ እንከኖች ያሉበት በመሆኑ ዓላማውን ያሳካል ለማለት አያስደፍርም፡፡
እንከኑ የሚጀምረው የአዲስ አበባን አካባቢዎች በየወሩ ማፅዳት በሚለው ፕሮግራም ውስጥ ወሩ እስኪደርስ ቆሻሻ በየመንደሩ እንደሚከማች ትርጉም የሚሰጥ መልዕክት በመያዙ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አመለካከትን ከመቀየር ወይም ቆሻሻን በየቀኑ በሥርዓቱ ይዞ ከማስወገድ ይልቅ ‹‹ኑና የጣልነውን ቆሻሻ እናንሳ›› የሚል ዘመቻ ሥራ ያደርገዋል፡፡