Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስንቱን አስፈቅደን እንዘልቀዋለን?

ሰላም! ሰላም! መቼም አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስብላሉ። ‹አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስገርሙኛል› እንዲል ጥላሁን ገሠሠ። አንድ የሬዲዮ አድማጭ በቀደም ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው። ደወለና “ሃሎ?” አለ። “ሃሎ አስተያትዎን ይቀጥሉ፤” ሲባል፣ “አይ እኔ እንኳን ምንም የምለው የለኝም። ብቻ አንተን በጣም ስለምወድህና ስለማደንቅህ ይኼን ለመንገር ነው፤” አይለው መሰላችሁ ጋዜጠኛው? እና እኔ ምለው ካርዴን በላው ተብሎ ቴሌ ላይ ብቻ ተለቅሶ ይሆናል እንዴ? ኧረ የምር ዕድሜና ጉልበታችንን ቅርጥፍ አርገን እየበላን ያለን እኛው ራሳችን አይደለንም ወይ? እንዲያው ለነገሩ ነገሩ ሁሉ ዞሮ ዞሮ ልጅነት ላይ መላከኩ አይቀርም። አብዛኞቻችን በትምህርት ቤት ዘመናችን ነገ ትምህርት የለም ስንባል ጮቤ የረገጥን ነን። እንዲያው ይኼን ጨዋታ የማጫውታችሁ ተጠያቂው ማን ነው የሚለውን እንድታብሰለስሉት ነው። መቼም ሰው ሥረ መሠረቱ ልጅነቱም አይደል?

በቀደም ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ “የአንድ ሙሉ ሰው አባት የሥጋ አባቱ ሳይሆን ልጅነቱ ነው፤” ስላለው  ጸሐፊ ሲያጫውተኝ ነበር። እሱ ምሁራዊ አተያዩን ከማስረጃ ጋር እያቀናበረ ሲያጫውተኝ እኔ የማስበው ልጅነቴን ነበር። አንዳንዴ ዛሬያችሁ ግራ ሲያጋባችሁ እኔ እንዲህ ነኝ? ኧረ ማን ነኝ? ስትሉ ዝም ብላችሁ አስተዳደጋችሁ ላይ ሂዱ። እመኑኝ መልሱ ያለው እዚያ ብቻ ነው። ታዲያ ምነው ሥራው ላይ ከመረባረብ በግምገማ፣ በሂስና ግለ ሂስ ተጠምደን እየዋልን መፍትሔ አጣን? የሚል ጥያቄ ያላችሁ ግምገማውን ረግጣችሁ የመውጣት መብት አላችሁ። መልስ አልባ ሆኜ ብቻ ሳይሆን ዶስቶቪስኪ በሕይወት ስለሌለ ጭምር እንጂ፣ ቢያንስ እሱን ለማጠያየቅ መመኮሬ አይቀርም ነበር። እና ልጅነታችንን ስናጠና ትምህርት ቤት አርፍዶ የመግባት የአብዛኞቻችን አባዜ ትዝ ይለኝና ዛሬ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ዋና ሥራ አስኪያጁ ገና አልገቡም የሚባለው መዳኛው ይጠፋኛል።  ሠልፉና የባንዲራ ሥነ ሥርዓቱን አድምቀን ስናበቃ አንደኛው ክፍለ ጊዜ ላይ የተሰጠንን የክፍል ሥራ፣ በገዛ ስንፍናችን ወደ ሦስት ቀን የቤት ሥራነት ስንቀይረው ያደግነውን ልጆች አስብና ዛሬ ስለአገር ክብር፣ ዕድገትና ልማት ያዙኝ ልቀቁኝ ብለን ስናበቃ ከምናቃልለው ሸክም የምንቆልለው እየታየኝ ተጠያቂው ይጠፋብኛል።

ለግርግርና ሆታ ቅድሚያ ሰጥተን፣ ለሐሜትና ለአሉባልታ ትኩረት መድበን ስንጓዝ ብቻ እንጀራ እንደሚወጣልን እየነገሩ ያሳደጉንን ወላጆች የታዘዝን እኛ ለሠርግና ለድግሱ የምንጨነቀውን ያህል፣ ለፍቺው አለመብሰልሰላችን እውነት ምን ይገርማል? ተፈጥሮ ያላደለንን አብሾና የአሳ ዘይት እየጋቱ ለአንደኝነት፣ ኮሌጅ ለመበጠስ፣ ሁሉንም በልጦ ተቆጣጥሮ ለመገኘት ካሳደጉን ወላጆቻችን የተገኘን እኛ ዛሬ ከተማውን ተቆጣጥረን ኪስ አውላቂና ሙሰኛውን ብንረሳው ምን ያስተቻል? አይደለም እንዴ? “በመበላለጥ የኑሮ ብልኃት የተቃኘ ልጅነት . . . ” አለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በቀደም አንድ ቦታ ቆመን ስናወራ።

“ . . . በመበላለጥ የተቃኘ ልጅነት በጉልምስና ዘመን እያነጣጠቀ አገር ከመበጥበጥ ሌላ ውጤቱ ምን ሊሆን ኖሯል?” ሲለኝ፣ “ምን እኔን ትጠይቀኛለህ?” ስለው፣ ይኼን ጊዜ አንድ ነካ ያደረገው በጉያው ሦስት አራት የጫት እንጨት የሸጎጠ መጣና “ብርዱ ሳይጠፋ አንድ ብር ስጡኝ፤” አለን። ዝም ስንለው፣ “ብርዱ!” ብሎ ደገመው። የባሻዬ ልጅ አንድ ብር አውጥቶ ሰጠው። እያየነው ቀጥ ብሎ ሄደ። ገርሞኝ ሳፈጥበት ‘ምን ትደነቃለህ? የዘንድሮ ብርድ ታቦት አያስረሳም ልትል ነው?’ ይለኛል። እኔን የገረመኝ ግን ያ አልነበረም። ለዚህ ብርድ አንድ ብር ብቻ ይለመናል? ይኼውላችሁ ይኼን ያህል ብር  ወድቆብን ልመና ማሻሻልም እያማረን ነው!

በቀደም ታዲያ አንዱ አፋልጉኝ እያለ መጣ። ማንን ስንለው ቫይበር አውጥቶ ድመቱን አሳየን። አስቡት። ከእሱ በፊት ስለዕድሜ ከባሻዬ ጋር ያወራሁትን ላጫውታችሁ። እንዲህ በነበር ብዙ ነገር ጥለን የማለፋችንን ያህል የዕድሜ ጣሪያችን በአርባ ዙሪያ መሽከርከር አልነበረበትም። ባሻዬ አዘውትረው፣ “ሙሴ በአርባ ዓመቱ ለአገልግሎት ሲሰማራ፣ የሠለጠነው ዓለም ከአርባ ዓመቱ በኋላ የቤተሰቡንና የአገሩን አደራ በዕውቀትና በሙላት ተሸክሞ መሮጥ ሲጀምር እኛ እናሸልባለን፤” ይሉኛል። “ምን ያደርጉታል ብለው ነው? የአርባ ቀን ዕድላችን ነዋ፤” እያልኩ እኔ ደግሞ ዘመንን በቀን አጣፋላቸዋለሁ። እንዲያው ሌላ ሌላው ቢቀር የማጣፋት ‹ታለንት› ቸግሮን አያውቅማ። ልብ አርጉልኝ ታዲያ። ያፋልጉኟን ነገር አልረሳኋትም። እንዲህ ያለው ያፋልጉኝ ስላቅ ደግሞ አይመቸኝም። በቃ አይመቸኝም። ስለዚህ ለምን የባሰ አላጣፋቸውም አልኩና “ያለችበትን አውቃለሁ፤” ብዬ ጻፍኩ። አዳሜ በድብርቱ መጠን በሳቅ እስክተረትረው እየጠበቀ ነው።

“የት? ወዴት አለች?” ጥያቄ ተንጋጋ። እኔም ኮስተር ብዬ፣ “ያለችበትን ስጠቁምና ስታገኙዋት ይህችን ትመስላለች። የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤትነት ተመዝግባ ትቆጥባለች። ዕድሜዋን በአግባቡ ለመጠቀም ትጥራለች። ለህዳሴው አንድ ጋትም ቢሆን አስተዋፅኦ ታደርጋለች። በረባ ባረባው አፋልጉኝ እያለች ሥራ አትፈታም፤›› ብዬ ፌስቡክ ላይ ጻፍኩለት፡፡ ሳልጨርስ የፍረጃና የስድብ ውርጅብኝ አስተናገድኩ። በካድሬነት ታማሁ ያልኳችሁም ይኼን ጊዜ ነው። ቆይ ግን እኔ ምለው የአገር ካድሬ መሆንም ያጠቋቁራል እንዴ? የምሬን እኮ ነው። ይኼ ‘ቫይበርና ፌስቡክ’ በቃ በተቀባባ ማንነት መረብ ለመረብ እያደራጀ አገልግሎቱ ሥራ ለማስፈታት ሆኗል ማለት ነው? የኢትዮ ቻይና የኢኮኖሚና የ‘አይዲዮሎጂ’ ልምድ ልውውጥ ‘እውነተኛ የልማት አጋር ከማኅበራዊ ድረ ገጾች የታቀበ ነው’ ቢለን ምን ልንሆን ነው? እንደ ፈረደብን ‘ኮሙዩኒዝም ይውደም!’ እያልን በየሰርጡ ፖስት ማድረጋችን ይቀራል ያን ጊዜ? በበኩሌ ኮብልስቶን ሳይሰማኝ ‘ታጥቦ ጭቃ’ ብያለሁ!

እናላችሁ ሥራዬን ትቼ በዚያው ‘ላይክና ኮሜንት’ ሳደርግ ሰዓታት አለፉኝ። ድንገት አንድ ሰው የሌለው ዳያስፖራ፣ “እባካችሁ ከሰላሳ እስከ አርባ ሺሕ ብር የሚከራይ መኖሪያ ቤት ካወቃችሁ አሳውቁኝ፤” ብሎ ስልኩን ቁልጭ አርጎ ጽፎ ለጠፈ። የዛሬ ጊዜ እንጀራ ከቀኝ ይጀምር ከግራ በየት በየት አድርጎ ዞሮ እንደሚቀባ አታውቁትም። “ያልተቀባ ሲጀምር ምኑን ያውቀዋል?” የሚሉኝ ባሻዬ ትዝ አሉኝ። ባሻዬ ደግሞ ሰሞኑን መለኮታዊ ፍቺና እሳቤዎቻቸው ጨምረዋል። ለነገሩ ወደው አይመስለኝም። እንደ እሳቸው አገላለጽ ከቅዱሱ መጽሐፍ ሌላ የማይዋሽና የማይዘላብድ አዋጅና ራዕይ አጣሁ ስለሚሉ ነው። የዕምነት ነፃነትና እኩልነት በተከበረባት አገር ይኼን በተመለከተ ምንም ወግ መቀመር የሚቻል አይመስለኝም። ብቻ ምሁሩ ልጃቸው ይኼን አባባላቸውን ሲሰማ፣ “ለማወቅ አለማወቅን ማመንና መቀበል እንጂ መቀባትን ምን አመጣው?” እያለ ይሟገታቸዋል።

አባትና ልጅን እዚህ ተወት እናደርጋቸዋለን። በበኩሌ ግን አላውቅምን ካለማወቃችን የተነሳ ፖስታ ቤት ሲጠይቁን ፖሊስ ጣቢያ እየጠቆምን፣ ስንቱን ‘ነገር ባይኖርህ ምን አቅለብልቦ አመጣህ’ እያስባልን አስላጭተነው ይሆን እያልኩ አስባለሁ። ይኼን እያሰብኩ ወዲያው ወደ ዳያስፖራው የፌስቡክ ደንበኛዬ ደወልኩ። እጄ ላይ ሁለት ቤቶች ነበሩ። አሳየሁት፣ ሳያገነግን ተስማማ። “ቤቱን ግን በደንብ አይተኸዋል?” አልኩት በችኮላ የወሰነ ስለመሰለኝ ደግሞ ነገ ዞሮ በፌስቡክ ስሜን እንዳያጠፋው ሰግቼ። “ምን ምርጫ አለኝ? ነገ ትመጣለች፣ ቀን የለኝም።” አለኝ፤ “ማን ናት?” እንደ ዘበት የወረወርኩት ጥያቄ ነው። “ሚስቴ ናታ! በስንት ጭንቅ ስንት ወጪ አውጥተን የሰው ማህፀን ተከራይተን ልጅ ስናገኝ ሆቴል ላሳርፋት ደግሞ?” ሲለኝ ደግ የለ ክፉ የለ ዲዳ ሆኜ ዋልኩ። ‘ኖ ኮሜንት!’ ብዬ ፖስት ሳደርግ ላይክ አርጉልኝ እሺ!

በሉ እንሰነባበት። ኮሚሽኔን ተቀብዬ ወደ ቤቴ ስጓዝ መንገድ ተዘጋ። ወዲያው ሁለት ፖሊሶች የእግረኛ መንገዱን ዘግተው “ባላችሁበት!” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡ። “ምን ገዶን?” ብለን በተለመደው ጨዋነትና እንግዳ አክባሪ ባህላችን መሠረት ትዕዛዝ ተቀብለን ቆምን። አንዳንዱ ሳይታዘዝ አለመቆሙም ሲያበሳጨው አይቻለሁ። የሆነ ግንብ ነገር ተደግፌ ዙሪያዬን መቃኘት ጀመርኩ። ከማየው አንዱ፣ “ለእንግዶቻችን በትዕዛዝ ምርጥ በለጬ ያሉበት ድረስ እናደርሳለን” የሚል ጽሑፍ ነው። አጠገቤ የቆሙትም አንብበውት ኖሮ፣ “ጭራሽ! ሳይቅሙ አርባ ሃምሳ ዓመት እየገዙ መርቅነውማ ሁለት መቶ ዓመትስ ይለቁልናል?” ይላል አንዱ።

“ኧረ ደንበኞችን የተመለከት ማስታወቂያ እንጂ ገዥዎቻችንን አይመስለኝም?” ይላል ሌላው። “በቃ አገሩ ጫት ቤት ብቻ ሆኖ ቀረ?” ስትል ወዲያ ግድም፣ “ምክር ቤቱም፣ መሥሪያ ቤቱም፣ ከፍተኛ ትምህርት ቤቱም እንቅልፍ እንቅልፍ ሲል በማን ይፈረዳል?” ይላታል አጠገቧ የቆመ። ደግሞ ዘወር ስል ጠባብ በረንዳ ያለው ካፌ ጢም ብሎ የተሰበሰበ ደንበኛ ሰብሰቦ ሻይ ቡና ሲጋብዝ አስተውላለሁ። “የምር ግን ቤታችን ሻይ ማፍላት እያቃተን ነው ካፌ እየተሰበሰብን በትኩስ ነገር የዛልነው?” ይላል አንዱ። “የመሰብሰብ መብታችንን የሚጋፋ ጥያቄ ይመስላል፤” ትለዋለች ዘንካታ ወጣት ፈገግ ብላ። “ከሥራ ሰዓታችን የሻይ ሰዓታችን ከበዛስ?” ይላል ሌላው። “አይ አፍሪካ! በመሰብሰብና በመቀመጥ ቢሆን ይኼኔ ማን እንደ እኛ!” ሲል ቆንጂት ተቀብላ፣ “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነዋ!” አለችው። መንገድ ተለቆ መጓዝ ተፈቀደልን።  የሆነስ ሆነና ስንቱን አስፈቅደን እንዘልቀዋለን? መልካም ሰንበት!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት