ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀኔራል ኢንሹራንስ ኩባንያ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ለመቀላቀል ሲንደረደር ከሌሎች ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተለየ የራሴ የሚለውን አዲስ ነገር ይዞ ነበር፡፡
ሁሉም የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እስካሁንም ድረስ እንደሚያደርጉት ሕይወትና ሕይወት ነክ ያልሆኑ የመድን ሽፋኖችን በጣምራ የሚሠሩ ሲሆን፣ ኢትዮ ላይፍ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍን ብቻ ይዞ ለመሥራት ወስኖ ወደ ሥራ ይገባል፡፡
ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀኔራል ኢንሹራንስ ኩባንያ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ብቻ ለመስጠት የተነሳ በመሆኑ፣ ከሌሎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተለይቶ የሥራ ፍቃዱንም የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት በሚል ወሰደ፡፡ የዛሬ ስያሜውን ከመያዙም በፊት ሕይወት ኢንሹራንስ ላይ ብቻ የሚሠራ ስለነበር፣ መጠሪያው ኢትዮ ላይፍ ኢንሹራንስ የሚል ነበር፡፡ ይህንን ስያሜና የሕይወት መድን ሽፋን ሥራውን እየሠራ ለዓመታት ዘለቀ፡፡
ይሁን እንጂ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ስድስት በመቶ ባልሞላበት አገር ዘርፉ አዋጭ እንደሚሆን ታሳቢ ተደርጎ የተጀመው ሥራ ግን እንደታሰበው አልተጓዘም፡፡ ኩባንያውንም አትራፊ ማድረግ ሳይቻል ቀረ፡፡
ይህ አካሄዱ ለተከታታይ አራተኛ ዓመታት ኩባንያውን ከኪሳራ እንዲሸጋገር ባለማድረጉና በኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወት ኢንሹራንስ ብቻ ነጥሎ መሥራት ትርፋማ እንደማያደርግ በማረጋገጡ፣ እሱም እንደሌሎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለተሽከርካሪዎችና ለሌሎች ንብረቶች ዋስትና ለመስጠት ወደሚያስችለው አጠቃላይ የመድን ሽፋን አገልግሎት ፊቱን እንዲያዞር አስገድዶታል፡፡ አጠቃላይ የኢንሹራንስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ፍቃድ ለማግኘት ጥያቄውን ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ ከሦስት ዓመት በፊት አወንታዊ ምላሽ አግኝቶ ስያሜውን ለውጦ ገበያውን ተቀላቅሏል፡፡
እንደ አዲስ በጀመረው ሥራ ኩባንያው ከቀዳሚው ዓመት ጀምሮ ከኪሳራ ወጥቶ ወደ ትርፍ ሊሸጋገር እንደቻለ የኩባንያው መረጃ ያስረዳል፡፡ በቀደመው ዓመት ከኪሳራ ወጥቶ ሦስት ሚሊዮን ብር ሲያተርፍ፣ በ2008 በጀት ዓመትም ከታክስ በፊት ትርፉን ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችያለሁ ብሏል፡፡ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽመልስ ገብረ ጊዮርጊስ እንደገለጹትም፣ ይህ ትርፍ ከ60 በመቶ በላይ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ የተጣራ ትርፉም 8.1 ሚሊዮን ብር በመሆኑ ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል፡፡ በአንፃሩ ግን ኩባንያው በ2008 በጀት ዓመት ከፍተኛ የካሳ ጥያቄ ያስተናገደበት ሆኗል፡፡
እንደ ኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት በበጀት ዓመቱ የቀረበለት የካሳ ክፍያ ጥያቄ 33.4 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የካሳ ክፍያ ጥያቄ ከቀደመው ዓመት የ119 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ የካሳ ክፍያ ጥያቄ በዚህን ያህል ደረጃ ዕድገት ማሳየቱ የኩባንያውን ትርፋማነት ከመቀነሱም በላይ የቀረበለት የጉዳት ካሳ ጥያቄ የዕድገት መጠን ከፍተኛ የሚባል ሆኗል፡፡ ከሰሞኑ ሪፖርታቸውን ይፋ ያደረጉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ የከፈሉት የካሳ ክፍያ መጠን በመቶኛ ሲሰላ ከ60 በመቶ የበለጠ አይደለም፡፡
በቀደመው ዓመት 15 ሚሊዮን ብር የነበረው የካሳ ጥያቄ በበጀት ዓመቱ በዚህ ያህል ደረጃ ለመጨመሩ ዋናው ምክንያት በተደጋጋሚ የደረሱ የተሽከርካሪ አደጋዎች ናቸው፡፡
ይህም ቢሆን ግን ማትረፉን የገለጸው ኩባንያው፣ 8.1 ሚሊዮን ብር ለባለአክሲዮኖች እንደሚከፋፈልም አመልክቷል፡፡ አንድ አክሲዮንም 12.8 በመቶ ያስገኛል በማለት ጠቅሷል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያው በ2008 መጠቅለያ ላይ አሴቱ 220 ሚሊዮን ብር እንደደረሰለት አመልክቷል፡፡ ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ አረቦን ማሰባሰብ የቻለው ኢትዮ ላይፍ፣ 86.1 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዟል፡፡
የኢትዮ ላይፍ ዋና አደራጅና እስካለፈው ዓመት ድረስ የኩባንያው የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉት አቶ ተሾመ በየነ፣ የኩባንያው የዓመታት ጉዞ ፈታኝ ቢሆንም አሁን ውጤት እያገኘ በመሆኑ ቀጣይ ተስፋዎች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ በመሰናበቸ ንግግራቸውም ይህንኑ አንፀባርቀዋል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያው በአዲሱ የምርጫ ድንጋጌ አዳዲስ የቦርድ አባላትን መርጧል፡፡