ኦሮሚያ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ2008 በጀት ዓመት ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት በ37 በመቶ ቀነሰ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢንሹራንስ ኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በ2008 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 33.39 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ይሁን እንጂ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ በ2007 በጀት ዓመታት አግኝቶት ከነበረው ትርፍ ጋር ሲነፃፀር በ20 ሚሊዮን ብር ወይም በ37 በመቶ ያነሰ መሆኑን የቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት አመላክቷል፡፡
በ2007 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት አትርፎት የነበረው 53.3 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚያሳየው ይኸው የኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት፣ የተጣራ ትርፉም ከቀደመው ዓመት በ27 በመቶ ቀንሶበታል፡፡ መጠባበቂያና ሌሎች ተቀናሽ ሆነው የበጀት ዓመቱ የተጣራ ትርፉ 28.55 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በ2007 በጀት ዓመት የተጣራ ትርፉ 38.46 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡
ኩባንያው በበጀት ዓመቱ የተጣራ ትርፉ መቀነሱ ደግሞ የትርፍ ክፍፍል ድርሻውን በ37 በመቶ አውርዶታል፡፡ በቀደመው ዓመት ለአንድ አክሲዮን የተከፈለው የ54.1 በመቶ ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. ግን ዓመታዊ ትርፉ በመቀነሱ ወደ 33.7 በመቶ ወርዷል፡፡
የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤልያስ ገነቲ እንደገለጹት፣ የኩባንያቸው ትርፍና የትርፍ ድርሻ ክፍፍሉ በዚህን ያህል ደረጃ ሊቀንስ የቻለው የኩባንያው አጠቃላይ አስተዳደራዊ ወጪና ለካሳ ክፍያ የዋለው ገንዘብ መጠን በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ነው፡፡
ከዚህ ሌላ ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ያሰባሰበው አረቦን መጠን ከቀደመው በጀት ዓመት ጋር በንፅፅር ሲታይ 16 በመቶ አካባቢ መቀነሱም፣ በዓመታዊ የትርፍ መጠኑ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡
ኢንሹራንስ ኩባንያው በ2008 በጀት ዓመት 333.9 ሚሊዮን ብር አረቦን ያሰባሰበ ሲሆን፣ አሰባስባለሁ ብሎ በዕቅድ ከያዘው ያነሰ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የቀረበለት የካሳ ክፍያ ጥያቄ ከታቀደው በጀት ዓመት በ48 በመቶ በልጦ 261.2 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡
በቀደመው ዓመት ለካሳ ክፍያ የዋለው 176.18 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ለካሳ ከተጠየቀው ገንዘብ ውስጥ 86 በመቶው ወይም ከተሽከርካሪ አደጋዎች ጋር ለተያያዙ የጉዳት ካሳዎች ነው፡፡
ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ በ2001 ዓ.ም. ወደ ሥራ ሲገባ በ540 ባለአክሲዮኖች 85.04 ሚሊዮን ብር ካፒታል በመያዝ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሀብት መጠኑን ወደ 597 ሚሊዮን ብር በማሳደግ ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሀብት መጠኑ ቀዳሚ ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡