Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጤፍን ከጀሶ ጋር በመቀላቀል እንጀራ ጋግረው ያሰራጩ ግለሰቦች ተቀጡ

ጤፍን ከጀሶ ጋር በመቀላቀል እንጀራ ጋግረው ያሰራጩ ግለሰቦች ተቀጡ

ቀን:

ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ዘነብ ወርቅ ታቦት ማደሪያ አካባቢ፣ ጤፍን ከጀሶ ጋር በመቀላቀል እንጀራ ጋግረው ለጠቃሚዎች ያሰራጩ ግለሰቦች በአሥር ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ፡፡

ድርጊቱን የፈጸሙት ተከሳሾቹ አንደኛ አልማዝ ሺፈሬና ሁለተኛ ጥሩሴት ወዲያ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሐምሌ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ጤፍን ከጀሶ ጋር ቀላቅለው በመጋገር ላይ እያሉ ነበር፡፡

ተከሳሾቹ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት ሊጋገር የተዘጋጀ በተለያዩ ዕቃዎች ተቦክቶ የተቀመጠ የጤፍና የጀሶ ድብልቅ ተይዟል፡፡

ተከሳሾቹ ከጤፍና ከጀሶ ድብልቅ ቡኮ በማዘጋጀት በቀን እስከ አንድ ሺሕ እንጀራ በመጋገር በደንበኝነት ለያዟቸው ሆቴሎችና ተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡ በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ቡኮና ከተጋገረው እንጀራ የተወሰደ ናሙና በላቦራቶሪ ተመርምሮ፣ የሰው ልጅ ቢመገባቸው ከፍተኛ የሰውነት ክብደት መቀነስና እስከሞት የሚያደርስ አደጋ እንደሚያስከትል ተረጋግጧል፡፡

ተከሳሾቹ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የተበላሹ ዕቃዎች በመሥራትና በመሸጥ እንዲሁም ጥራታቸውን በማርከስ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ ችሎት ክሱን ለተከሳሾች በንባብ ያስደመጠ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም ብለው ክደው ተከራክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

የግራና ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹን ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን እንደ ቅጣት ማቅለያ በመያዝም አንደኛ ተከሳሽ በአሥር ዓመት ጽኑ እስራትና በአምስት ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽን በአሥር ዓመት ጽኑ እስራትና በአንድ ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡    

ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በተገኘ መረጃ መሠረት በከተማዋ 2,721 በዳቦ፣ ኬክ ብስኩትና እንጀራ ምርት የተሰማሩ፣ 178 የምግብ ዘይት የሚያመርቱ፣ 125 በእንስሳት እርባታና ተዋጽኦ ማምረት ላይ የተሰማሩ አሉ፡፡ ወደ 500 የሚሆኑ በባልትና ውጤቶችና በመሳሰሉት የተሰማሩ ነጋዴዎችና ድርጅቶችም ይገኛሉ፡፡ በሕገወጥ ንግድ የተሰማሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በአቋራጭ ለመክበር ሲሉ በሚያዘጋጁት ምግብ ላይ ባዕድ ነገር እየቀየጡ ለገበያ ሲያቀርቡ ይታያል፡፡

የምግብነት ይዘት የሌለውን ባዕድ ነገር ከምግብ ጋር መቀላቀል በኩላሊት፣ በጉበት፣ በጨጓራ፣ በምግብ ቱቦ ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ከማድረሱም ባለፈ በውስጡ የሚኖረው የኬሚካል ይዘት ለካንሰር በሽታ አስተዋጽኦ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት በፉድ ኤንድ ኒውትሪሽን ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ዶ/ር አብነት ተክሌ ናቸው፡፡ ምግብነት የሌለው ነገር ከምግብ ጋር ተቀላቅሎ ወደ ሰውነት በሚገባበት ጊዜ በሦስት ዓይነት መንገዶች ጉዳቶችን ያደርሳል፡፡ የመጀመሪያው አላስፈላጊ ኬሚካል ወደ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ የሚፈጠረው የጤና ቀውስ ነው፡፡ ሁለተኛው በዓይን የማይታይ ተህዋሲያን በውስጡ ሲኖር አልያም ከተህዋሲያኑ በሚመነጭ መርዛማ ንጥረ ነገር የሚፈጠረው ነው፡፡ ሌላው ተደባልቀው ወደ ሰውነት በሚገቡበት ጊዜ የሚደርሰው አካላዊ አደጋ ነው፡፡

‹‹ማንኛውም ኬሚካል ወደ ሰውነታችን ሲገባ በጉበት መጣራት ይኖርበታል፡፡ ጉበት በሰውነታችን ያልተለመዱ ኬሚካሎችን ለማጣራት በሚያደርገው ሒደትም ይጐዳል፡፡ ጨጓራም እንደዚሁ፤›› የሚሉት ዶ/ር አብነት፣ ባዕድ ነገር ወደ ሰውነት ውስጥ በሚገባበት ወቅት በማንኛውም ዓይነት መንገድ የጤና ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ከሚታዩት ችግሮች ባሻገር ከጊዜ በኋላ የሚከሰቱ መኖራቸውን፤ ባዕድ ነገርን ከምግብ ጋር ቀላቅሎ ለገበያ የማቅረቡን ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችም ይህንን ተገን በማድረግ በድፍረት እየሠሩበት እንደሚገኙ ይጠቁማሉ፡፡  

የሸማቹን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር መፈጸም ወንጀል ነው፡፡ በዚህ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉ በአንድ ዓመት ነግደው ካገኙት ገቢ ላይ 10 በመቶውን እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ እንደ ጥፋታቸው ክብደትና ቅለትም ከሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ይፈረድባቸዋል፡፡ ‹‹በቅቤ፣ በወተት፣ በማር፣ በእንጀራና በሌሎችም ለምግብነት በሚውሉ ነገሮች ላይ ባዕድ ነገር በመቀየጥ ተግባር ወደኛ የሚመጡ ኬዞች ብዙ ናቸው፤›› ያሉት በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ፀጋዬ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን አዋጅና ደንብ መሠረት የምግብ መልክን ለማሳመርና ክብደትን ለመጨመር ሲባል ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ በሕግ የተከለከለ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጤፍን ከሰጋቱራ ጋር ቀላቅሎ ለገበያ የማቅረቡ ሁኔታ በስፋት ታይቶ ነበር፡፡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማም እንደዚሁ ከሸክላ ጋር የተቀየጠ 20 ኩንታል በርበሬ እንዲወገድ፣ ድርጊቱን የፈጸሙም ለሕግ እንዲቀርቡ መደረጉን ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡

በተግባሩ የተሰማሩት ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው በቤታቸው ውስጥ ተደብቀው የሚሠሩ ናቸው፡፡ ከፈቃድ ጋር በተያያዘም ውስብስብ ነገሮች ታይተዋል፡፡ በተለይ በየካ ክፍለ ከተማ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳይኖራቸውና ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል የብቃት ማረጋገጫ ሳያገኙ ለ12 ምጣዶች የሚያገለግል የኤሌክትሪክ ኃይል ተገጥሞላቸው ሲሠሩ የቆዩ፣ በተመሳሳይ የወንጀል ተግባር የተሰማሩን በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል፡፡

 

 

 

 

                            

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...