Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየትራፊክ አደጋው ጠባሳ

የትራፊክ አደጋው ጠባሳ

ቀን:

መዝጊያው ወለል ብሎ ተከፍቷል፡፡ ከበሩ ትይዩ መሬት ላይ ከተዘረጋው ፍራሽ አጠገብ የብረት አልጋ ይታያል፡፡ ከአልጋው ላይ እንቅልፍ ያልወሰዳት ወጣት ተዘርግታ ተኝታለች፡፡ ግንባሯ ላይ ሰፊ ጠባሳ ይታያል፡፡ ከፊት ለፊቷ በቆሙት ሰዎች ላይ ዓይኗን ወዲያና ወዲህ ታንከራትታለች፡፡

የ22 ዓመቷ አዜብ ዘውዴ፣ ከአንገቷ በታች መንቀሳቀስ አትችልም፡፡ ልሳኗ ከተዘጋም ሆነ ከተኛችበት አልጋ ሳትንቀሳቀስ ሁለት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በራሷ ምግብ መብላትና መጸዳዳት አትችልም፡፡ የምትተኛበት አልጋ በሽንት እንዳይበላሽ ከሥሯ ላስቲክ ይነጠፋል፡፡ በቀን አንድ ጊዜ ዳይፐር ይቀየርላታል፡፡ እሷን በየቀኑ ለማጠብና ለማጽዳት ስለማያመች በወጉ ልብስ አትለብስም፡፡ እርቃኗን አልጋው ላይ ጋደም እንዳለች ከላይ አልጋ ልብስ ጣል ይደረግላታል፡፡

አስፈላጊውን እንክብካቤ የሚያደርግላት የ19 ዓመቱ ታናሽ ወንድሟ እሸቱ ዘውዴ ነው፡፡ ነገሮች ከአቅሙ በላይ እንደሆኑበትም እምባ እየተናነቀው ‹‹አምላክ ይህንን ያህል ከሚፈትነኝ ቢገድለኝ ይሻለኛል፤›› ሲል በወጣትነቱ የገባበትን ፈተና እንዲህ ያስታውሳል፡፡

አዜብ ቤተሰቦቿ የሚመኩባት የበኩር ልጅ እንጂ እንደ ዛሬው የቤተሰብ ሸክም አልነበረችም፡፡ እንዲህ ከመሆኗ በፊት በአንድ የጫማ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥራ ትሠራ ነበር፡፡ በቂ የሚባል ደመወዝም ነበራት፡፡ ይሁንና ነሐሴ 27 ቀን 2006 ዓ.ም. ንጋት 12፡00 ሰዓት ላይ የደረሰባት የመኪና አደጋ ሕይወቷን እንዳልነበረ አደረገው፡፡

 አዜብ ከሁለት የስራ ጓደኞቿ ጋር  ማለዳ ወደ መሥሪያ ቤቷ እየሄደች ነበር፡፡ መንገድ በመሻገር ላይ ሳሉ በአንድ ሚኒባስ ተገጩ፡፡ አንዷ ጓደኛቸው ብትተርፍም አዜብና ሌላኛዋ  ተጎዱ፡፡ በአዜብ ላይ የደረሰው ጉዳት ግን ከፍተኛ ነበር፡፡ ራሷን ስታ ወደቀች፡፡ ወዲውም ወደ ሕክምና መስጫ ቦታ ተወሰደች፡፡ ከጎኗ ሌላ ሊረዳት የሚችል ባለመኖሩም፣ ደሴ ወደሚኖሩት ወላጆቿ ተደወለ፡፡ ወላጆቿ አቅመ ደካማ በመሆናቸው ሊረዳት ወደ አዲስ አበባ የመጣው እሸቱ ነበር፡፡

‹‹መተንፈስ አትችልም፡፡ ኦክስጅን ተደርጎላታል፡፡ ምግብም በአፍንጫዋ ነበር የሚሰጣት፡፡ ራሷን ስታ ቆይታ የነቃችውም ከሦስት ወራት በኋላ ነው፤›› ሲል በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል፡፡ በወቅቱ ይዟት ለመመለስ አስቦ የነበረ ቢሆንም፣ አዜብ ባለችበት የጤና ሁኔታ የማይታሰብ ሆነ፡፡ ‹‹መንቀሳቀስ አትችልም፡፡ የምትጸዳዳው በዳይፐር ስለሆነ መኪና ውስጥ እንዲሁም ትውልድ ቀያችን እንዴት እንሆናለን፤›› ሲል ቤት ተከራይቶ ሊያኖራት ወሰነ፡፡

ኮተቤ ገብርኤል 33 ማዞሪያ አካባቢ በወር 500.00 ብር ቤት ተከራይቶ መኖር ጀመሩ፡፡ የቀን ሥራ እየሠራ በሚያገኘው ገቢ የሚያስፈልጋትን ለማሟላት ይሞክራል፡፡ ሌሊት አሥር ሰዓት ከእንቅልፉ ነቅቶ አዜብን ያጥባል፣ ዳይፐር ይቀይርላታል፣ ቁርስ አብስሎ ያበላትና 12፡00 ሰዓት ሲሆን  የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት አስኮ አካባቢ ይሄዳል፡፡ ሥራውን ጨርሶ ወደ ቤት የሚመለሰው ምሽቱ ከገፋ ነው፡፡ አጣጥቧት የዋለችበትን ዳይፐር ይቀይርላትና እራት ሠርቶ ይበላሉ፡፡ ከማይወጡት መከራ ውስጥ የከተታቸው የትራፊክ አደጋ፣ አዜብን የዕድሜ ልክ እስረኛው ሲያደርግ፣ እሸቱ ደግሞ ሕይወትን እንዲያማርር አስገድዶታል፡፡

 የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሜዲካል ቦርድ በሰጣቸው ማስረጃ መሠረት፣ አዜብ ጭንቅላቷ ላይ በደረሰ ጉዳት ራሷን መግለጽም ሆነ መቆጣጠር አትችልም፡፡ ጭንቅላቷ በአራቱም አቅጣጫ ፓራላይዝድ ሆኗል፡፡ ‹‹150 በመቶ ቋሚ የሆነ የጤና ጉድለት፣ በማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓቷ ላይ 75 በመቶ ጉዳት፣ 75 በመቶ የሚሆነው የዋናው የሰውነት ሞተር ተግባር መሥራት አይችልም››፣ ይላል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የትራፊክ አደጋ የበርካቶችን ሕይወት እያመሳቀለ ይገኛል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በ2015 ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት፣ 1.25 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በየዓመቱ በትራፊክ አደጋ ይሞታሉ፡፡ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችም በየዓመቱ ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡

አብዛኛዎቹ የአደጋው ሠለባዎችም ወጣቶች ናቸው፡፡ ከወዲያ ወዲህ ብለው መሥራት በሚችሉበት በወጣትነት ዕድሜ በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ይቀጠፋል፤ ተስፋቸው ይጨልማል፡፡ 50 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ የሚደርሰው በእግረኞች እንዲሁም በብስክሌትና በሞተር ሳይክል በሚንቀሳቀሱ ሰዎች ላይ ነው፡፡

አደጋው የሁሉንም ቤት እያንኳኳ ይገኛል፡፡ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ሳይመለሱ አንደወጡ ይቀራሉ፡፡ ከአፍታ በፊት ከጓደኞቹና ከቤተሰቡ ጋር ሲስቅና ሲጫወት የነበረ ሰው፣ በደቂቃዎች ልዩነት በትራፊክ አደጋ  ሕይወቱ አለፈ የሚል ዜና መስማት ተለምዷል፡፡

ሙሉቀን ይባላል (ስሙ ተቀይሯል)፡፡ በሙያው ሹፌር ነው፡፡ ከዓመት በፊት ከፍቅረኛውና ከአንድ ጓደኛው ጋር ወደ ሐረሪ ሲጓዝ፣ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ  የሄዱት በመደበኛ ትራንስፖርት ሲሆን፣ አዳማ ከደረሱ በኋላ ወደ ሐረሪ የሚሄዱ መኪኖችን ማግኘት ባለመቻላቸው፣ ወደ ሐረሪ መስመር ከሚሠራ አንድ የጭነት መኪና ጋር ለአንድ ሰው 300 ብር ሒሳብ ተስማምተው መንገድ ይጀምራሉ፡፡ ሙሉቀን፣ ሾፌሩ መኪናውን የሚነዳበት ፍጥነት ስላሳሰበው ‹‹አትቸኩል ተረጋግተህ ንዳ ቀስ ብለን እንደርሳለን፤›› ሲል ፍጥነቱን እንዲቀንስ ጠየቀው፡፡ ሾፌሩ ጥቂት አንገራግሮ በሐሳቡ ተስማምቶ ፍጥነቱን ቀንሶ ይነዳ ጀመረ፡፡

ብዙም ሳይቆይ ተመልሶ መጀመርያ ይነዳ በነበረበት ፍጥነት ያሽከረክር ገባ፡፡ ‹‹መጨቃጨቅ ሌላ ችግር ይፈጥራል ብዬ ስለፈራሁ ዝም አልኩኝ፤›› የሚለው ሙሉቀን፣ በሕይወቱ የሚፀፀትበትን ትልቅ ስህተት መሥራቱን የተረዳው በኋላ ነው፡፡

 ጠመዝማዛ መንገድ ላይ ደርሰዋል፡፡ ሾፌሩ ፍጥነቱን አልቀነሰም፡፡ ጨለማ ስለነበርም ነገሮችን በውል ለመለየት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ድንገት ከባድ ድምጽ አስተጋባና ዙሪያ ገባው ፀጥ አለ፡፡ መኪናው መንገዱ ላይ ቆሞ ከነበረ ሌላ የጭነት መኪና ጋር ተላትሟል፡፡ ግፊቱ ከባድ ነበርና ሙሉቀን በመስኮት ተስፈንጥሮ ወደቀ፡፡

 ሙሉቀን ራሱን ሥቶ ከወደቀበት ሲነሳ፣ የፍቅረኛው የቀኝ እጅ መቆረጡን አስተዋለ፡፡ በድንጋጤ ደንዝዞ መጠነኛ ጉዳት የደረሰበት እግሩን እየጎተተ አብሯቸው ወደ ነበረው ጓደኛቸው ቢዞር፣ ጓደኛው በአደጋው ወገቡ ተቆርጦ ከእግሮቹ ተለያይቷል፡፡ በሕይወት አልነበረም፡፡ በወቅቱ በሕይወት ያሉት አዳማ ሄደው ሕክምና እንዲያገኙ በአካባቢው ሲያልፉ የነበሩ ሰዎች ረድተዋቸዋል፡፡

 በአሁኑ ወቅት ሁኔታዎች ተረጋግተው እሱ ወደ ሥራው ተመልሷል፡፡ ይሁንና ፍቅረኛው በደረሰባት አደጋ ከፍተኛ የሞራል ውድቀት ደርሶባታል፡፡ ‹‹እንደ በፊቱ ወጥታ ሥራ አትሠራም፡፡ ጓደኞቿንም አታገኝም፡፡ ሰው ሁሉ ጠልታለች፤›› በማለት ከደረሰባት አደጋ በሕክምና ብታገግምም ሕይወቷ እንዳልነበረ ሆኖ መቀየሩን ይናገራል፡፡

በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው እንዳልነበር ሆኖ ከተቀየረ በታሪክ ከማይረሱ ኢትዮጵያውያን መካከል በኦሊምፒክ ውድድር ለአፍሪካ የመጀመርያውን ወርቅ ያስገኘው አትሌት አበበ ቢቂላ ይገኝበታል፡፡ በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ አንደኛ በመውጣት ዓለምን አጀብ ያሰኘው አትሌት የመኪና አደጋ የደረሰበት በ1960ዎቹ መጀመርያ ነው፡፡ ቮልስ ዋገን መኪናውን እያሽከረከረ ሸኖ ከተማ ሲደርስ ያልተጠበቀ ነገር ተፈጠረ፡፡ መኪናው ከሌላ መኪና ጋር ተጋጭቶ ከባድ የአካል ጉዳት ደረሰበት፡፡ ወደ እንግሊዝ ሄዶ ሕክምና ቢደረግለትም፣ የደረሰበት አደጋ ከፍተኛ ስለነበር ወደ ነበረው ሙሉ ጤንነት ሊመለስ አልቻለም፡፡ ከእንብርቱ በታች ፓራላይዝድ ሆነ፡፡ ይንቀሳቀስ የነበረው በዊልቸር ነበር፡፡ አጋጣሚው ስሙ ከገነነበት የሩጫ መድረክ እንዲወርድ ያደረገና ብዙዎችን ያሳዘነ ነበር፡፡  

የበርካቶችን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ የቀጠፉ ከብዙዎች አእምሮ የማይጠፉ የትራፊክ አደጋዎች አሉ፡፡ ከማይዘነጉ መሰል ገጠመኞች መካከል በሐምሌ 2006 ዓ.ም. ኮልፌ ማዞሪያ አካባቢ ኮንቴይነር የጫነ ተሽከርካሪ ተገልብጦ በቦታው የነበሩ 26 ሰዎች የሞቱበት፣ 44 ደግሞ የቆሰሉበት ቀዳሚው ነው፡፡ ኅዳር 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዋሽ አካባቢ ፈንታሌ ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ 38 ሰዎች መሞታቸውም አይረሳም፡፡ በተለየ ጥንቃቄ በተገነባው ከአዲስ አበባ አዳማ በፍጥነት መንገዱ ላይም በ2008 ዓ.ም. ጥር ላይ በደረሰ አደጋ 11 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፣ ዘጠኝ ሲቆስሉ አምስት ደግሞ ለከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ መጋቢት 2008 ዓ.ም ሱሉልታ አካባቢ ልምምድ ሲያደርጉ በነበሩ አትሌቶች የደረሰው የሞትና ከባድ የአካል ጉዳት ከማይዘነጉት መካከል ናቸው፡፡ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በመኪና አደጋ ሳቢያ ሕይወቷ ያለፈው ተዋናይት ሰብለ ተፈራ ሞትም ብዙዎችን ያስተከዘ ነበር፡፡  

ባለፈው ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ብሔራዊ የደም ባንክ ከአለላ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመቀነስ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በኢሊሊ ሆቴል የምክክር መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በእለቱ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የትራንስፖርት ባለሥልጣን የመንገድ ትራፊክ ደኅንንት ነባራዊ ሁኔታ በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ ጥናቱ በዓለም ላይ ያለውን የትራፊክ ደኅንነት ሁኔታ ከአገሪቱ ጋር በንፅፅር አስቀምጧል፡፡

አፍሪካ ከሌሎቹ የዓለም ክፍሎች በተለየ  ለትራፊክ አደጋ ያላት ተጋላጭነት 24 በመቶ ነው፡፡ ከ90 በመቶ ያላነሰ አደጋ እየተከሰተ ያለውም በአፍሪካ ነው፡፡ በአፍሪካ የሚገኘው የተሽከርካሪ ብዛት ከአንድ በመቶ ያነሰ  ሲሆን የሚደርሰው አደጋ ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ለትራፊክ አደጋ ከሚዳረጉት 48.1 በመቶ ተሳፋሪዎች ሲሆኑ፣ 43.2 በመቶ ደግሞ እግረኞች ናቸው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ሚያዝያ 2006 ዓ.ም. ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በእንግሊዝ በ100,000 ተሽከርካሪዎች የሚደርሰው አደጋ ሁለት ብቻ ነው፡፡ በኬንያ ደግሞ በ100,000 ተሽከርካሪዎች 19 ሰዎች ላይ አደጋ ይደርሳል፡፡ ይኼ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ በአገሪቱ ያለው የተሽከርካሪ መጠን ከህዝቡ ቁጥር አንፃር፣ ከሌሎች አገሮች በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ ለ100,000 ሰዎች ያለው ድርሻ 5.6 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ውስን የመኪና ብዛት ባለበት ሁኔታ ግን እየደረሰ ያለው የትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1998 ዓ.ም. በ10,000 ተሽከርካሪዎች ብቻ 120 የትራፊክ አደጋ ደርሷል፡፡ አሁን ላይ በ10,000 ተሽከርካሪዎች እየደረሰ ያለው አደጋ ወደ 60.4 ዝቅ ብሏል፡፡

ጥናቱን ያቀረቡት በትራንስፖት ሚኒስቴር የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ትምኅርትና ግንዛቤ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ዮሐንስ ለማ እንደገለጹት፣ 68.3 በመቶ የሚሆኑት በአገሪቱ የሚከሰቱት የትራፊክ አደጋዎች ምቹ በሆኑ መንገዶች ላይ ነው፡፡ ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል 85.9 በመቶ የሚሆኑት በአሽከርካሪው ስህተት፣ 3.3 በመቶ በተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ጉድለት፣ 2.8 በመቶ በእግረኛ ችግር፣ 0.7 በመቶ በመንገድ ችግር የሚከሰቱ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የትራፊክ አደጋ የሚከሰቱባቸው ምክንያቶችም በፍጥነትና በቸልተኝነት በማሽከርከር እንዲሁም በሥልጠና መጓደልና በተያያዥ ጉዳዮች ነው፡፡ በግንባታና በተለያዩ ምክንያቶች የእግረኞች መንገድ የሚዘጉባቸው ሁኔታዎች፣ የመንገድ ዳር መብራቶችና በቂ የትራፊክ ምልክቶች አለመኖር፣ የእግረኛ መንገድ ላይ ድንኳን ተጥሎ የሚነገድበት አሠራር፣ ደህንነታቸው  ያልተጠበቀ ተሽከርካሪዎች መኖርም ለአደጋው መስፋፋት መንስኤ ናቸው፡፡

በቂ እረፍት ሳያገኙ በድካም ስሜት እንዲሁም ጠጥቶና ቅሞ ማሽከርከርም ብዙዎችን ለእልቂት እየዳረገ ይገኛል፡፡ ተሽከርካሪዎች መንገድ ስተው ድንገት ወደ መኖሪያ ቤቶች ዘው በማለት በሰዎች ላይ ያልተጠበቀ አደጋ የሚያደርሱበት አጋጣሚም ተለምዷል፡፡

ጥቂት የማይባሉት አደጋውን ካደረሱ በኋላ ፍጥነታቸውን ጨምረው ከአካባቢው ይሰወራሉ፡፡ ኃላፊነቱን ወስደው ተጎጂዎቹን አፋፍሰው ወደ ሕክምና መስጫ የሚያደርሱ ቢኖሩም፣ ተገቢውን ክትትል አያደርጉም፡፡ እዚህ ነን እዚያ ነን ሳይሉ የሚጠፉም አሉ፡፡ ይኼ ለበርካቶች ፈተና የነበረ ቢሆንም፣ የሦስተኛ ወገን የመድኅን ሽፋን መጀመር ቢያንስ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች የህክምና እንዳይቸገሩ አስችሏል፡፡ ነገር ግን ለህክምና ተብሎ የተመደበው የገንዘብ መጠን በቂ አለመሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል ጠቅላላ አስተባባሪ አቶ ሲራክ ጉግሳ እንደሚሉት፣ በቀን ከሦስት እስከ አምስት የሚሆኑ ቀላልና ከባድ የትራፊክ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ሕክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ ይሄዳሉ፡፡ ይሁንና አደጋው የደረሰባቸው ሰዎች አደጋ ያደረሰባቸውን ተሽከርካሪ መለያ ኮድ አይዙም፡፡ ብዙ ጊዜ ተጐጂዎቹን ሆስፒታል የሚወስዱት መንገደኞች ናቸው፡፡ ይህም ተገቢውን ፎርም ሞልቶ ለሚመለከተው አካል ለማስገባት ችግር ሆኗል፡፡

 ይሁንና የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ በሚፈቅደው መጠን በድንገተኛ ሕክምና 2,000 ብር፣ ተኝተው ለሚታከሙ ደግሞ እስከ 40,000 ብር በሚፈቅደው መሠረት፣ ተጎጂዎች እንደመጡ ሕክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ የተመደበው ገንዘብ በተለይም ለድንገተኛ ሕክምና የማይበቃበት አጋጣሚ እንዳለ አቶ ሲራክ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የደረሰው ጉዳት የሲቲ ስካን፣ የኤም አር አይ ምርመራ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ የተመደበው 2000 ብር እዚያ የሚያልቅበት ሁኔታ አለ፤›› ሲሉ ገንዘቡ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡  

በመድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ወንድም እንደሚሉት፣ የካሳ መጠኑ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም አገናዝቦ የተቀመጠ ቢሆንም፣ በተለይ ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸው ሕክምና ይበቃል ማለት እንዳልሆነ ግን ያምናሉ፡፡ ለአስቸኳይ  ሕክምና ተብሎ የተቀመጠው 2,000 ብር አደጋው በተከሰተበት፣ በአምቡላንስ ለሚጓጓዘውና ሐኪም ቤት ሲደርስ ለሚደረገው ነፍስ የማዳን ሕክምና መሆኑን፣ ገንዘቡ ከ2,000 እየበለጠ ሲሄድ ከ40 ሺሕ ብር በሚታሰብ መታከም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ጉዳቱ ከባድ ሆኖና ሕክምናው በካሳ ክፍያ ከተቀመጠው 40 ሺሕ ብር በላይ ሲወስድ፣ ወይም ‹‹የደረሰብኝ ጉዳት ከ40 ሺሕ ብር በላይ ካሳ ያስፈልገዋል፤›› የሚል ተጎጂ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ተከራክሮ ጉዳት ያደረሰበትን ወገን ተጨማሪ ማስከፈል እንደሚችልም አቶ ዘውዱ አክለዋል፡፡

በኢሊሊ ሆቴል ተዘጋጅቶ የነበረውን ፕሮግራም በንግግር የከፈቱት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አሚን አማን፣ የመንገድ ላይ አደጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን በአገሪቱ በትራፊክ አደጋ በየዓመቱ 3,800 ሰዎች እንደሚሞቱና የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሠረት ደግሞ በትራፊክ አደጋ በየዓመቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ23,000 እንደሚበልጥ ተናግረዋል ፡፡

‹‹የትራፊክ አደጋን እየለመድን መጥተናል፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ የአደጋው ሰለባዎች በቂ ሕክምና እንዲያገኙ ለማስቻል የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመጀመርያ የሕክምና ዕርዳታ የሚሰጡ ሰዎችን በስፋት ለማሠልጠን በዕቅድ ተይዞ እየተሠራበት እንደሚገኝና 1,500 አምቡላንሶች በመግዛት አደጋዎች ባጋጠሙባቸው ቦታዎች ፈጥኖ በመድረስ ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ተችሏልም ብለዋል፡፡

አደጋ ከደረሰና ሊመለስ የማችለው የሰው ሕይወት ከጠፋ ወይም አካል ከተጎዳ በኋላ ካሳም ሆነ ሕክምና መስጠቱ እንዳለ ሆኖ፣ አደጋው እንዲቀንስ መሥራት ወሳኝ መሆኑን አስተያየት የሰጡን ይናገራሉ፡፡ ለትራፊክ አደጋ መንስኤ አሽከርካሪው፣ ተሽከርካሪውና እግረኛው ዋነኞቹ ስለሆኑም እነዚህ ላይ መሥራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪው፣ ተሽከርካሪዎች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የቴክኒክ ምርመራ ማድረግ በሚችሉ ማሽኖች እየተፈተሹ፣ ችግር ከሌለባቸው ቦሎ የሚሰጣቸው ቢሆንም፣ ‹‹እነዚህን ዘመናዊ የመኪና የቴክኒክ መመርመሪያ ማሽኖች እንዴት አለፉ›› በሚያስብል መልኩ የማስጠንቀቂያ ምልክት መብራት፣ የእጅ ፍሬንና ሌሎችም የቴክኒክ ጉድለት ያለባቸው መኪኖች ይታያሉ፡፡ በመርካቶ፣ በአትክልት ተራ እንዲሁም በተለያዩ ሥፍራዎች የቴክኒክ ጉድለት ያለባቸው ተሽከርካሪዎች ቢታዩም፣ ከአገልግሎት ሲታገዱ አይስተዋልም፣ ይህም ችግሩን ያባብሳል፡፡  

አሽከርካሪን በተመለከተ ያለው ችግር፣ የብቃት ማነስ ብቻ ሳይሆን የሥነ ምግባር፣ የባህሪና የርህራሄ ጉድለትም ነው፡፡ የትራፊክ ሕግና ደንብ፣ እግረኛንና ሌሎች አሽከርካሪዎችን አክብረው የሚያሽከረክሩ እንዳሉ ሁሉ፣ ከሥነ ምግባር  ውጪ ሆነው ሌሎችን ለጉዳት የሚዳርጉም አሉ፡፡

የራሳቸውን ጉዳይ ብቻ በማሰብ፣ ከጎናቸው ተሽከርካሪም ሆነ ሰው ያለ የማይመስላቸው፣ የትራፊክ ፖሊስ መኖርና አለመኖሩን አይተው ሕግ የሚጥሱ፣ ሕግን ሳይሆን ትራፊክ ፖሊስን በመፍራት የሚንቀሳቀሱ መኖራው የትራፊክ አደጋውን ከሚያባብሱ እንደሚመደቡም ያክላሉ፡፡

‹‹እግረኞችም ጥፋተኞች ናችሁ፣ ሕግ አክብሩ›› ሊባሉ እንደሚገባ፣ ሁልጊዜ አሽከርካሪ ጥፋተኛ ነው ስለሚባል በዚህ ተዘናግተው ሕይወታቸውንም ሆነ አካላቸውን እንዳያጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራው መጠናከር እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ እግረኞች ላይም ይጣል የነበረው ቅጣት መዘንጋቱን በማስታወስ፣ መልሶ እንዲጠናከር ይጠይቃሉ፡፡ በሆነ ወቅት ላይ በእግረኛ መንገድ ያላቋረጠንና የመንገድ አካፋይ የዘለለን እግረኛ መቅጣት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ አሁን ቀርቷል፡፡ በመሆኑም፣ ‹‹አሽከርካሪ ቀበቶውን (ሴፍቲ ቤልት) ካላሰረ የሚቀጣው ለሕይወቱ ጥንቃቄ አላደረገም ተብሎ እንደሆነው ሁሉ፣ እግረኛውም የመንገድ አጠቃቀም ሕግ ሲጥስ ለሕይወትህ ጥንቃቄ አላደረግህም ተብሎ ሊቀጣ ይገባል፤›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...