Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ለሰላምና ለመረጋጋት አስተማማኝነት አሁንም ከዴሞክራሲ የበለጠ ፍቱን መድኃኒት የለም!

  ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ወራት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት መመለሱ በመንግሥት ሰሞኑን ተገልጿል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ ከሆነ የተለያዩ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ወደ ቀድሞ ቦታው መመለሱን አረጋግጠዋል፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ፣ ለአንድ ዓመት ያህል በሁከት ውስጥ ለከረመች አገር መልካም ዜና ነው፡፡ የበርካታ ዜጎች ሕይወት የጠፋበት፣ የአካል ጉዳት የደረሰበትና መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት የወደመበት ክፉ ጊዜ አልፎ አንፃራዊ ሰላም ሲሰፍን ደስ ያሰኛል፡፡ ግን ሰላምና መረጋጋቱ ዘላቂና አስተማማኝ ሆኖ የሚቀጥለው ዴሞክራሲ በሚፈለገው መጠን ሲሰፍን ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ፍቱን መድኃኒት የለም፡፡

  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀባቸው ምክንያቶች መካከል በዋናነት የተጠቀሰው በወቅቱ የተከሰተውን ነውጥ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ማስቆም ባለመቻሉ ነው፡፡ በእርግጥም ዜጎች እየሞቱ፣ አካላቸው እየጎደለና የአገር ሀብት እየወደመ የሕዝቡና የአገር ህልውና ሥጋት ውስጥ በገባበት ወቅት፣ በመደበኛው መንገድ ሕግ ለማስከበር አለመቻሉ በሚገባ ታይቷል፡፡ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ መሆናቸውም ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል በተቃውሞው ውስጥ የነበሩ ወጣቶች ለብሶት የዳረጉዋቸው በርካታ ምክንያቶች አሉዋቸው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ጥቅምና ዕድል ተጠቃሚ ያለመሆንና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል መጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ ከዴሞክራሲና ከሰብዓዊ መብት ጋር የሚያያዙ ጥያቄዎችም ቀርበዋል፡፡ ወጣቶቹ በሰላማዊ መንገድ ብሶታቸውንና ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበት ማጣታቸው፣ በየደረጃው የተመደቡ የመንግሥት ሹማምንት ደንታ ቢስነት፣ ሙስና፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ መጥፋት፣ ወዘተ. ለሁከቱ መነሳት አቀጣጣይ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ አሁን ችግሩን ለጊዜውም ቢሆን ከማረጋጋት ባለፈ ዘለቄታዊ መፍትሔ ማፈላለግ ጠቃሚ ነው፡፡ መድኃኒቱ ዴሞክራሲ ነው፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዲፕሎማቶቹ ባደረጉት ገለጻ በተቃውሞው ወቅት 90 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ወጣቶች እንደነበሩ፣ መንግሥት በርካታ የሥራ ዕድሎችን ቢፈጥርም ካለው ፍላጎት አንፃር የተመጣጠነ እንዳልነበር አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ወጣቶች ተቃውሞአቸውን የሚያሰሙበት ምቹ ምኅዳር አለመኖሩ ደግሞ ሌላው የተቃውሞ መንስዔ መሆኑን፣ ይህም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ወጣቶች አንደበት በግልጽ መነገሩን አስታውቀዋል፡፡ ለመፍትሔው በመንግሥት በኩል የታመነበት የዴሞክራሲ ተቋማትን ማስፋፋት መሆኑንና ለዚህም መንግሥት ሥራውን እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች ዜጎች በመንግሥት ላይ ጥላቻ ወይም ተቃውሞ እንዲኖራቸው የሚያስገድደው፣ በአገሪቱ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ተግባራዊ ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ነው፡፡ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት በፍትሐዊነት መጠቀም የሚቻለውም ሆነ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የሚከበረው፣ ሕገ መንግሥቱ ባረጋገጠው መንገድ ዴሞክራሲ ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡

  የውጥረቱ ጊዜ አልፎ ሰላማዊው ድባብ ሲመለስ ችግሮች ለምን ተፈጠሩ? መፍትሔያቸውንስ እንዴት መፈለግ ይቻላል? መባል አለበት፡፡ ችግርን ማወቅ የመፍትሔው ግማሽ መንገድ ነው እንደሚባለው፣ ያጋጠሙ ችግሮችን ፈልቅቆ ማየት ተገቢ ነው፡፡ እዚህ አገር ውስጥ በጣም ከሚያስቸግሩና መፍትሔ ከታጣላቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሕግ የበላይነት አለመከበር ነው፡፡ እያንዳንዱ መንግሥታዊ ተቋም፣ ሹም፣ ሠራተኛ፣ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ዳኛ፣ ፖለቲከኛ፣ ነጋዴ፣ ወዘተ. በሕጉ መሠረት ብቻ ሥራውን ካከናወነ አገር ሰላም ይሆናል፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ዋስትና የሰጣቸው መብቶችና ነፃነቶች ያላንዳች መሸራረፍ ተግባራዊ ቢሆኑ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ይወገዳሉ፡፡ የመንግሥት ተቋማትና ሹማምንት በሕጉ መሠረት ከሠሩ፣ የፍትሕ አካላት በአግባቡ ሕጉን ካስከበሩ፣ የፖለቲካ ተዋናዮች የጨዋታውን ሕግ ካከበሩ፣ ነጋዴው በሕጋዊ መንገድ ከተንቀሳቀሰ፣ ሌሎች ዜጎችም ለሕግ የበላይነት ጥረት ካደረጉና ሰላም ከተፈጠረ ምን ይፈለጋል?

  በአገሪቱ ውስጥ ግማሽ ክፍለ ዘመን ሊያስቆጥር ምንም ያህል ያልቀረው የፖለቲካ መቆራቆስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማይመጥን፣ በጥላቻና በቂም በቀል የተመረዘ፣ ለአገር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይልቅ አውዳሚ፣ ለአዲሱ ትውልድ አርዓያነት የሌለውና እጅግ በጣም ኋላቀር ነው፡፡ ይህንን የተበላሸ የፖለቲካ ምኅዳር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በተመሠረተ ዘመናዊ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ ለመቀየር፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ የመግባቢያ መድረክ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ መጣበብ ችግር የፖለቲከኞችና በዙሪያቸው ያሉ ውስን ወገኖች ብቻ ጉዳይ ሳይሆን፣ የመላው ሕዝብን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚመለከት በመሆኑ ፈጣን የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ ከአገርና ከሕዝብ ህልውና በላይ ምንም ነገር ስለሌለ፣ ዴሞክራሲያዊው የፖለቲካ ምኅዳር እንዲፈጠርና በአገሪቱም በሕግ የበላይነት ሥር የተመሠረተ ሥርዓት እንዲገነባ መሠረታዊ የሆነ ሥር ነቀል ለውጥ መደረግ አለበት፡፡ በግራም በቀኝም ያሉ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ግድ ይላቸዋል፡፡ ሌላ አማራጭ የለም፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው በነፃነት መኖር ነው፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ በነፃነት እንዲኖር የሕግ የበላይነት መስፈን አለበት፡፡ ሕገወጥነት መቆም አለበት፡፡ ሙስና ከሥር መሠረቱ መናድ አለበት፡፡ ኢፍትሐዊነት መወገድ አለበት፡፡ አጭበርባሪነትና አድርባይነት መክሰም አለበት፡፡ ይህ ሕዝብ የአገሪቱ የሥልጣን ባለቤት በመሆኑ ሊከበር ይገባዋል፡፡ የሚወዳት አገሩም መከበር አለባት፡፡ በሥልጣን ያላግባብ መገልገልም ሆነ በቡድን ተደራጅቶ መጠቃቀም ማብቃት አለበት፡፡ ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ ድንፋታና ፉከራም መገታት አለባቸው፡፡ ለሥልጣንና ከሥልጣን ለሚገኝ ጥቅም ሲባል የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች በቃችሁ መባል አለባቸው፡፡ የአገርን ሉዑላዊነትና ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ ተግባራት በሕግም ሆነ በታሪክ ማስጠየቅ አለባቸው፡፡ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ከአገር ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው ጋር መሻረክም እንዲሁ፡፡ እነዚህ ሁሉ እኩይ ድርጊቶች ተገትተው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ዓውድ እንዲፈጠር ሁሉም ዜጎች በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ አገርን ለማፈራረስና ሕዝብን ለዕልቂት ለመዳረግ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩትን በመተው፣ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ራዕይ ያላቸውን ዜጎች በብሔራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በማሠለፍ ለለውጥ መነሳት ታላቅነት ነው፡፡ ይህ ኩሩና የተከበረ ሕዝብ መመራት ያለበት በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ ነው፡፡ ሰላሙም ሆነ መረጋጋቱ አስተማማኝ የሚሆነው የዴሞክራሲ ፍቱን መድኃኒትነት በመፍትሔነት ሲቀመጥ ብቻ ነው!   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ‹‹ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

  የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን...

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡...

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...

  መኖሪያ ሸጦ መዞሪያ!

  እነሆ ከመካኒሳ ወደ ጀሞ ልንጓዝ ነው። ቀና ሲሉት እየጎበጠ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ ከዚህ ኢፍትሐዊ ዓለም መፍትሔ ይገኛል ብሎ መጠበቅ የማይቻልበት ጊዜ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ የዓለምን ሚዛን ያስጠብቃሉ...

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...