Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርየበላይነት! ሆይ አገርህ ወዴት ነው?

  የበላይነት! ሆይ አገርህ ወዴት ነው?

  ቀን:

  የአቶ ልደቱ አያሌውን የመጀመሪያውን ክፍል ጽሑፍ አነበብኩት፡፡ የሰነዘሩት ሐሳብ ለበለጠ ውይይት ስለሚጋብዝ ሳላመሰግናቸው አላልፍም፡፡ በስሜት ሳይሆን በምክንያታዊነት ችግሮችን ለማየት እንደጣሩም ነግረውናል፡፡ በጽሑፋቸው በርካታ ነገሮችን ዳስሰዋል፡፡ ለእኔ የበለጠ ትኩረቴን የሳበው ግን ‹‹የሕወሓት የበላይነት›› እና ‹‹የመንግሥት ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች›› የሚለው ነው፡፡

  ምክንያቱም አቶ ልደቱ ምክንያታዊ በሆነና በመረጃ ብሎም ከተራ ፕሮፓጋንዳ በዘለለ ‹‹ቀን ኢትዮጵያ ትቅደም ማታ የእኔ ብሔር ይቅደም፤›› ከሚሉት የመንግሥት ነቃፊዎች በተለየ በአኃዝ አስደግፈው ይተነትኑታል ብዬ ተስፋ ስላደረኩ፡፡

  በአንድ ወቅት አቶ ተፈራ ዋልዋ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው ‹‹ተቃዋሚዎች ቁልፍ የመንግሥት ሥልጣን ብለው የሚጠሩት የሕውሓት ሰው የተሾመበትን ቦታ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህን መልሳቸውን ትክክል የሚያደርገው ከዚህ በፊት ቁልፍ ተብለው የሚጠሩት የሥልጣን ቦታዎች እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትርና ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አሁን በተቃዋሚዎች ‘ቁልፍነታቸውን’ ተነፍገዋል፡፡ ሕውሓት የረገጠው ቦታ የተቀመጠበት ወንበር ግን በተዓምር ወደ ‘ቁልፍ ቦታነት’ ይቀየራል እያሉን ነው፤ የጥበቃም ሥራም ቢሆን?!

  አቶ ልደቱ በጽሑፋቸው አንድ ቦታ ላይ ‹‹በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የእነሱ (የትግራይ ማለታቸው ነው) ቋንቋ ጎልቶ የሚነገርበት መንደርና ጓደኛ እስከመፍጠር ደርሰዋል፣›› በማለት የሕውሓት የበላይነት ማሳያ አድርገው የጠቀሱት ትንሽ ፈገግ የሚያሰኝና ግርምትን የሚጭር ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

  በተመሳሳይ አተያይ አዲስ አበባ የሚገኙት እንደ ጎጃም በረንዳ፣ ጎንደር በረንዳ፣ ወሎ ሰፈር፣ ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ምኒሊክ አደባባይ የሚሉ የቦታ ስያሜዎች በቀድሞ መንግሥታት የአማራ የበላይነት እንደነበር ማሳያ አድርገን መውሰድ እንችላለን?

  በሰሜን አሜሪካ የተወሰኑ ግዛቶች ላይ አማርኛ የሚናገሩ ስደተኞች በቁጥር በዝተው ይታያል፡፡ አሜሪካኖች ይህን እንደ ሥጋት ወይም የበላይነት አላዩትም፡፡ ይልቁንስ መንገድ እንደተሰየመ ከሰማን ሰነበትን፡፡ ለኢትዮጵያውያን አማርኛም የሥራ ቋንቋ እንዲሆንና በተጨማሪነት እንዲካተት ከተወሰነ ከረመ፡፡

  በባዕድ አገር እንደዚህ ዓይነት መብት (Privilege) ሲሰጥ በገዛ አገሩ አንድ ማኅበረሰብ በአንድ አካባቢ በጋራ ቢኖር ብሎም በቋንቋው ቢጠቀም ምንድነው ችግሩ? የሚከላከል ሕግስ ይኖር ይሆን?

  ሶማሊኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ጉራገኛና ዶርዘኛ ቋንቋዎች የሚነገርባቸው ቦታዎች አዲስ አበባ ውስጥ ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ትግረኛ አንድ ቦታ ሲነገር ስንሰማው በአንዴ ወደ ‘የበላይነት’ ዲስኩር የሚቀይረው? አደሬ ሰፈርና ስልጤ ሰፈር ተብለው የሚጠሩ ቦታዎች ብሎም መስጅዶች እንዳሉስ አቶ ልደቱ ያውቃሉ? ትግራይ ሰፈርም ይሁን በረንዳ፣ ቤተ ክርስቲያንም ይሁን መስጅድ አዲስ አበባ ውስጥ አልተሰየሙለትም፡፡

  በከተማችን የቻይና ዜጎች አዘውትረው የሚሸምቱበት አንድ የገበያ ቦታ ነጋዴዎች ሱቃቸውን በቻይንኛ ጽሑፍ ማስታወቂያ አጥለቅልቀውታል፡፡ ነገር ግን በክፉም በደጉ ምንም ሲባል አልሰማንም፡፡

  ለምሳሌ ከተወሰነ ዓመታት በኋላ የኦሮሞ ቋንቋ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የበላይነት ከሌላው ከፍ ቢልና ቢጎላ ከተሜው ‘እኛና እነሱ’ የሚል መከፋፈል (Dichotomy) አይፈጥርም፡፡ ይልቁንስ ቋንቋውን ኢኮኖሚውንና የፖለቲካ የበላይነቱን ሳይቀር ከራሱ ማንነት ጋር ለመቀየጥ ይታትራል፡፡

  ‘የሕወሓት የበላይነት’ የሚለውን መጫወቻ ካርድ የኦሕዴድና የብአዴን ካድሬዎች ሕዝቡን በመንግሥት ላይ የሚያነሳሱበት አጀንዳ እንደሆነ አቶ ልደቱ፣ ነግረውናል፡፡ የኦሕዴድን እርግጠኛ ባልሆነም ጎንደር ላይ የበርካታ ሰዎችን ቅስቀሳ በቅርበት ላስተዋለ ግን ነገሩ ደቡብ አፍሪካ ላይ ከሆነው እጅግ ተመሳሳይነት አለው፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቀሙት እ.ኤ.አ በ2008 በቀስተ ዳመነዋ አገር ደቡብ አፍሪካ በስደተኞች ላይ የጥላቻ ቅስቀሳ፣ አሉታዊና ብሔርተኝነት እንዲባባሱ ከኤኤንሲ ቀበሌ አደራጆች እስከ የታውገሺፕ ፖለቲካና ማኅበራዊ መዋቅር እንቅስቃሴዎች የመዋቅሩ መሪዎች ድጋፍና ተደማጭነት እያሽቆለቆለ ሲመጣ ስደተኞች ላይ የሚያደርጉት አሉታዊ ቅስቀሳ ያይላል፡፡

  ‘የደኸያችሁትና ከችግራችሁ ልትወጡ ያልቻላችሁት ሥራችሁን በስደተኞች ስለምትነጠቁ ነው፡፡ ገብያችሁም ከስደተኞች በሚመጣ ፉክክር ይቀንሳል፤’ በማለት ስደተኛ ጠል ጥቃቶች እንዲጀምሩና በቀላሉ እንዲባባሱ ምክንያት ሆነዋል፡፡

  በመጨረሻም የሕውሓት የበላይነት ያለቅጥ ተንሰራፍቷል ያሉን አቶ ልደቱን መገኛውም ከታክሲ ውስጥ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እንደሚያካልል ነግረውናል፡፡ ይህን መንፈስ እንዲታገል ጥሪ ለትግራይ ሕዝብ እንዲህ በማለት አስተላልፋለሁ፡፡ ‹‹ከማንም በላይ ጉዳት እየደረሰበት የሚገኘው የትግራይ ሕዝብ በመሆኑ፣ ይህንን ፍትሐዊ ያልሆነ የሕውሓት የበላይነት የትግራይ ሕዝብ ከማንም ባላነሰ መቃወምና መታገል ይኖርበታል፡፡››

  የታላቋ አገር ጀርመን መሥራች አባት ቢስማርክ ‘ፖለቲካ የሚቻለውን ብቻ ማድረግ ማለት ነው፤’ ብሎ ነበር፡፡ የእኛ አገር የፖለቲካ ልዒቃን ግን ለግማሽ ክፍለ ዘመን ሊሆን በማይችለው ላይ ሲናቆሩ ኖረዋል፡፡ እንደኔ አስተያየት የትግራይ ሕዝብ መታገልና መቃወም ያለበት ያልተጨበጠውን፣ ምንም ያልፈየደለትንና የጽንፈኛ ፖለቲከኞች ኪስ ማደለቢያ የሆነውን ‘የበላይነት’ ዲስኩር ሳይሆን፣ በተግባር እየታየ ያለውንና እንደዜጋ ያስመረረውን ብሎም ለውጥ ሊያመጣበት የሚያስችለውን መሆን አለበት፡፡

  ለምሳሌ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ትምህርታቸውን ጨርሰው ተስፋ በማጣት አገር አቋርጠው እንዲሰደዱ፣ የተረፉትም በሱስ እንዲደነዝዙ የፈቀደውን የክልሉን አስተዳደር ነው፡፡

       በክልሉ የተሾሙ ወጣት የቢሮ ኃላፊዎች ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታን የመገንዘብና የአቅም ውስንነት ችግር የመሳሰሉትን ጊዜ የማይሰጡ የክልሉ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት እርምጃ ሲጀመር ነው፡፡ ትልቁን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ስንክሳሮች ለመፍታት ግን መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡

    በመጨረሻም ‘የበላይነት’ ማሳያ ተደርገው የሚቀርቡ ምክንያቶች በአብዛኛው ሆን ተብለው ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ሕገ መንግሥታዊ መብቱን እንዳይጠቀም ለማሸማቀቅ ብሎም እኛ ብቻ ነገ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ጎልተው መታየት ያለብን ከሚል ብልጣብልጥ አስተሳሰብ የመጣ  ይመስለኛል፡፡ በግሌ በግለሰቦች የተፈጠረ የበታችነት ስሜት አድርጌ ነው የምወስደው፡፡

  (ኤፍሬም ኃይለ ሥላሴ፣ ከአዲስ አበባ)

    

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...