Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅኃይሌ ገብረሥላሴ ለመጨረሻ ጊዜ በባዶ እግሩ የተወዳደረበት የዓምናው ታላቁ ሩጫ

ኃይሌ ገብረሥላሴ ለመጨረሻ ጊዜ በባዶ እግሩ የተወዳደረበት የዓምናው ታላቁ ሩጫ

ቀን:

የሚሄድ በርጋታ

የሚሄድ በርጋታ ድምጹ ሳይሰማ

የሚኖር ይመስላል ከሁሉ እየተስማማ

ራሱን ሰውሮ

ከሰዎች አዕምሮ

ቀርበነዋል ሲሉት የሚገኘው ርቆ

በጥርሱ እየሣቀ ሕይወቱን ደብቆ

ባልተጠበቀ ቀን ድንገት የሚመጣ

የቅጽበት ፈገግታው ከልብ የማይወጣ

አንስተው ጥለውት ገድለነዋል ብለው

ተነስቶ የሚገኝ ከመካከላቸው

ቢቀርቡት ቢርቁት የማይለወጠው

ሰላም ፍቅር እንጂ ጥላቻ የማይገዛው

ድምጹ ሳይሰማ የሚኖር በርጋታ

ዓይኖቹ ቀዝቃዛ ግንባሩ ማይፈታ

ምን? ይሆን ምስጢሩ የሚደበቅበት

ፍቅሩ ወይ ጥላቻው የማይታወቅበት

ምንድነው? ከሰው ልጅ እሱ የሚፈልገው

ቢጥሉት ቢያፈርጡት የማይለወጠው፡፡

ንጉሤ ካሣዬ ወልደ ሚካኤል፣ ቅጠሎች ነን፣ (2010)

********************

74 ሚሊዮን ዶላር የፈጀው የህንዳውያኑ ሰርግ

ህንዳውያኑ በዓለም በጣም ውድ የተባለውን ሰርጋቸውን በህንድ ካርናታካ ሰሜናዊ ክፍል አክብረዋል፡፡ ለአምስት ቀናት በተከናወነው የሰርግ ሥነ ሥርዓት አምስት ቢሊዮን ሩጲ ወይም 74 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ከተከናወኑ አነጋጋሪና ውድ ሰርጐች ከቀዳሚዎቹ ይመደባል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህንዳውያን ከገንዘብ ቀውሱ ለመውጣት በሚታገሉበት ወቅት፣ የ23 ዓመቱ ነጋዴ ራጅቭ ሬዲ እና የፖለቲከኛው ጂ ጃናርድሃና ልጅ ብርሃሚኒ፣ ይህን ያህል ገንዘብ ለሰርጋቸው ማዋላቸው አስተችቷቸዋል፡፡

የሙሽራዋ ብርሃሚኒ ልብስ ብቻ 2.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ጌጣጌጦቿ ደግሞ 13 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶባቸዋል፡፡ በሃይደርባድ ባለው የቤተሰብ ንግድ ተሳታፊ የሆነው ሙሽራው ራጂቭ፣ ለሰርግ የሚውሉ ክፍያዎችን በሙሉ ከስድስት ወራት በፊት መክፈሉን ዘገባው ያሳያል፡፡

በወርቅ የተለበጠ የጥሪ ካርድ በታደለበትና የጥንት የህንድ ቤተ አምልኮ በሚመስል ዲዛይን በተሠራው የሰርግ ስፍራ ለመታደም፣ ከ50 ሺሕ ሰዎች በላይ የተጠሩ ሲሆን፣ እንግዶችን የሚያመላልሱ ሁለት ሺሕ ታክሲዎችም ተሰማርተው ነበር፡፡ 15 ሄሊኮፕተሮች ደግሞ የክብር እንግዶችን አመላልሰዋል፡፡

የብራዚል ሳምባ ዳንስ ሰርጉን ካደመቁ ትዕይንቶች አንዱ ሲሆን፣ የቦሊውድ ኮከቦችም በሰርጉ ትዕይንት አቅርበዋል፡፡

********************

የጌም ሱሰኛዋ አሮጊት

በቻይና ኢንተርኔት ካፌዎች ከ18 ዓመት በታች ያሉ ልጆችን እንዳያስተናግዱ በሕግ የተከለከለ ቢሆንም፣ ይህንን ሕግ በመተላለፍ በድብቅ የሚሠሩ ይገኛሉ፡፡ የ73 ዓመቷ አሮጊትም የልጅ ልጆቻቸው የሆኑትን ሁለት ታዳጊ ሕፃናት ይዘው ሕግ በሚጥሰው ኢንተርኔት ካፌ በመግባት፣ በቻይና ታዋቂ የሆነውን ‹‹ሌጀንድ ኦፍ ሌጉ›› የተባለውን ጌም ሲጫወቱ በካሜራ ዕይታ ሥር ወድቀዋል፡፡

የጌም ሱስ ያደረባቸው አሮጊት፣ ጌም እየተጫወቱ፣ ቢራቸውን ሲጐነጩና በተደጋጋሚ ሲጋራ ሲያጨሱም ታይተዋል፡፡ የሴትዮዋ ድርጊት የመሰጠው የኢንተርኔት ካፌው ተገልጋልይ፣ በሞባይሉ የቀረጸውን፣ የአሮጊቷን በሱስ መጠመድና ግዴለሽነት የሚያሳየውን ምስል፣ በማኅበራዊ ድረ ገጽ በመልቀቁ ጉዳዩ አነጋጋሪ መሆኑን ሚረር ዮኬ ዘግቧል፡፡  

********************

ቻይና ስለ ሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ከኢንተርኔት መረጃ ማውጣትን አገደች

ቻይና የሰሜን ኮሪያውን ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡን ‹‹Fatty Kim The Third›› በሚል ርዕስ መረጃዎችን በኢንተርኔት ማውጣትን አገደች፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው፣ በቻይና በማንኛውም ድረ ገጽ ስለ ኪም ጆን ኡን መረጃ ለማግኘት ከዚህ ቀደም በስፋት ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ‹‹Fatty Kim The Third›› ቅጽል ስም ያገደችው፣ ቻይና የማንንም አገር መሪ እንደማትሰድብና በቅጽል መጥራትን እንደማትደግፍ ለማሳየት መሆኑን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጂንግ ሽዋንግ ተናግረዋል፡፡

********************

ወጣቱን የሬሳ ሳጥን ውስጥ ከተው ያስፈራሩ ተከሰሱ

ሁለት የደቡብ አፍሪካ ነዋሪዎች አንድን ወጣት የሬሳ ሳጥን ውስጥ በመክተትና በእሳት እናቃጥልሃለን ብለው በማስፈራራት ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

ሁለቱ ነጮች ጥቁሩ ወጣት ላይ በፈጸሙት ድርጊት ፍርድ ቤት ሲቆሙ፣ የዋስትና መብታቸው እንዳይከበር ራሳቸው ጠይቀዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ድርጊታቸው በጥቁሩ ማኅበረሰብ ዘንድ ቁጣን ስለቀሰቀሰና ከእስር ቢፈቱ ሊገደሉ እንደሚችሉ በመፍራት መሆኑን ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ነጮቹ ወጣቱን በሬሳ ሳጥን ውስጥ ከተው ያስፈራሩት በጆሃንስበርግ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘው ትልቅ የኢንዱስትሪና የእርሻ ስፍራ በእግሩ ሲጓዝ ‹‹የእኛ ንብረት ባለበት ስፍራ አልፈሃል›› ብለው እንደሆነ ዘገባው ያሳያለ፡፡

ነጮቹ ቲዮ ጃክሰንና ዊሊም ኦስሽዋዜን፣ ጥቁሩን ቪክቶር ሞልሽዋ በሬሳ ሳጥን ሲከቱት የተቀረጸ የ20 ደቂቃ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ድረ ገጽ የተለቀቀው ከወር በፊት ነበር፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...