Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በርካታ የግብርና ምርቶችና ሸቀጦች በሕገወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ መሆኑ ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቋመ

ቡናን ጨምሮ በአገሪቱ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች በከፍተኛ ደረጃ በኮንትሮባንድ ንግድ ከአገር እየወጡ መሆኑን መረጃዎች አመለከቱ፡፡ በተለይ ቡና፣ ጥራጥሬና የቁም እንስሳት እንዲሁም ነዳጅ ሲሚንቶና ስኳር በገፍ ከአገር እየወጡ መሆኑን ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት እንደታየው ሁሉ የቡና ግብይትን መቆጣጠር ባለመቻሉ አገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና በሕገወጥ ንግድ አማካይነት በድንበር በኩል ከአገር እየወጣ ነው፡፡ ይህ ቡና በትክክለኛው የኢትዮጵያ ንግድ ገበያ በኩል ቢያልፍ እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ድረስ አገሪቱ ገቢ ልታገኝ እንደምትችል ተጠቁሟል፡፡

የኢብራሂም ሁሴን ቡና ላኪ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢብራሂም ሁሴን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቡና በኮንትሮባንድ ከአገር እየወጣና በመርካቶም እየተሸጠ በመሆኑ አገሪቱን ከፍተኛ ገንዘብ አሳጥቷታል፡፡ አቶ ኢብራሂም ጨምረው እንደገለጹትም፣ በተለይ ከውጭ ገዥዎች ጋር ውል የገቡ ሕጋዊ ነጋዴዎች ውላቸውን ላለማፍረስ በውድ ዋጋ በመግዛት ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ከውጭ ገዥዎች ጋር ውል ገብተን በገባነው ውል መሠረት መላክ ባንችል በቀጣዩ ንግዳችን ላይ ችግር ይፈጠራል፡፡ ይህንን ለመከላከል ስንል በውድ ዋጋ በመግዛት ለኪሳራ እየተዳረግን ነው፤›› በማለት አቶ ኢብራሂም ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የቡና ምርት በየጊዜው እየጨመረ ቢሆንም የዚያኑ ያህል ግብይቱ በሕገወጥ መንገድ እየተከናወነ ነው፡፡ ግብይቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ገበያ ዕውቅና ውጭ እየተፈጸመ በመሆኑ አገሪቱ ማግኘት ያለባትን ማግኘት እንዳላስቻላት አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡

የቡና ግብይት በአስቸጋሪ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ መሆኑን የሚናገሩት ሌላኛው ቡና ነጋዴ አቶ አደም ከድር ናቸው፡፡ አቶ አደም የሆራ ትሬዲንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ አቶ አደም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቡና በከፍተኛ ደረጃ በኮንትሮባንድ ንግድ ከአገር እየወጣ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መርካቶ በከፍተኛ ደረጃ እየቀረበ ሲሆን፣ በመርካቶ ገበያ እንድ ኪሎ 100 ብር ሲሸጥ፣ በውጭ ገበያ ግን በኪሎ 52 ብር ሒሳብ እየተሸጠ ነው፡፡

የጥራጥሬ ምርትም በሕገወጥ መንገድ ከአገር እየወጣ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ለጥራጥሬ ግብይት ቅርበት ያላቸው ነጋዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቦሎቄን የመሳሰሉ ጥራጥሬዎች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውጪ ከሕገወጥ  ንግድ ተዋናዮች ጋር በመመሳጠር ከአገር እየወጣ ይገኛል፡፡

‹‹ግብይቱ በዋናነት የሚፈጸመው በአዳማ ከተማ ነው፡፡ ወደ ምርት ገበያ ሳይገባ ግብይቱ የሚፈጸም ከሆነ በርካታ ገንዘብ በትርፍ መልክ የሚገኝ በመሆኑ የአገር ሀብት እየባከነ ነው፤›› ሲሉ የሁኔታውን ውስብስብነት እኝህ ነጋዴ ይናገራሉ፡፡

ይህ የጥራጥሬ ንግድ በትክክለኛው የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ቢያለፍ አገሪቱ በዓመት እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ ልታገኝ እንደምትችል እኝህ ነጋዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገሮች የቀንድ ከብቶች እየተነዱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምርት ገበያው የሚቀርቡለትን ምርቶች ማገበያያት እንጂ ሕግ የማስክበር ኃላፊነት የለበትም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉም ተናግረዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን በኢትዮጵያ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች ከዚህ ቀደምም በሕገወጥ መንገድ በድንበር በኩል ወደ ውጭ የሚወጡ ቢሆንም፣ ከትክክለኛው የንግድ ሰንሰለት ውጪ በአገር ውስጥ ገበያም የሚቀርቡበት ዕድል ቢኖርም፣ ተባብሶ የቀጠለው ግን መንግሥት ሙሉ ትኩረቱን ሰላም ማስከበር ላይ  ባደረገበት ወቅት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

መንግሥት ይህንን ሁኔታ በመረዳት ግብረ ኃይል ማቋቋሙንና ግብረ ኃይሉም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንደሚመራ ታውቋል፡፡  በግብረ ኃይሉ ውስጥ የንግድ ሚኒስቴር፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የቡናና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ይገኙበታል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በርካታ የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች ከአገር እየወጡ ነው፡፡ ነገር ግን ሚኒስቴሩ በጥናት ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ የሚወጡትን ምርቶች በመጠን መግለጽ አልተቻለም፡፡ የሚመለከታቸው የክልል ኤጀንሲዎችም በጥናቱ ተካተውበታል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የንግድ ሚኒስቴር አስተያየት እንዲሰጥ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ግን በተለያዩ ጊዜያት ሕገወጥ ንግድን ለማስቀረት ከክልሎችና ከአዋሳኝ አገሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ መግባባት ላይም ተደርሷል፡፡ ነገር ግን ዘርፉ ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት በመሆኑ ማስቀረት ወይም መቀነስ ካለመቻሉም በላይ፣ የቁርጠኝነት አለመኖር ለችግሩ ውስብስብ መሆን ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች