– የታሰሩ ግብፃውያን ከኤምባሲያቸው ጋር እንዲገናኙ ተጠየቀ
የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቃል በላኩት መልዕክት፣ የታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ግብፅ ለሱዳንና ለኢትዮጵያ የገባችውን የሦስትዮሽ ትብብር ቃል እንደምታከብር ገለጹ፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ኮሚቴ ማክሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሊቢያ ጉዳይ ላይ ስብሰባ አድርጎ ነበር፡፡ ከዚህ ስብሰባ ጎን ለጎን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳምህ ሽኩርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አማካሪ አህመድ አቡዜድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚህ የጎንዮሽ ስብሰባ ስለኢትዮጵያና ግብፅ ግንኙነት፣ በሁለቱ አገሮች በትብብርና በመተማመን ሊሠሯቸው የሚገቡአቸው የኢኮኖሚያዊ፣ የንግድና የባህል ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናቱ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቃል የተላኩትን መልዕክት አቅርበዋል፡፡
ግብፅ በሁለቱ አገሮች ያለው ትስስር ከዳር ለማድረስ የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ፕሬዚዳንት አልሲሲ መናገራቸውን፣ ባለሥልጣናቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ገልጸውላቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ግብፅ ለሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ጥቅምና መተማመን ለሚደረገው ጥረት ዋስትና እንደምትሰጥ፣ ፕሬዚዳንት አልሲሲ መናገራቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የታላቁን ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ግብፅ ሱዳንና ኢትዮጵያ ያደረጉትን የሦስትዮሽ ትብብር ቃል ግብፅ እንደምታከብርም ፕሬዚዳንት አልሲሲ መናገራቸውን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም ኢትዮጵያ የሁለቱ አገሮች ጥቅሞች እንደሚጠበቁ መግለጻቸውን በኢትዮጵያ የግብፅ ኤምባሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ኤምባሲው በላከው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለሥልጣናት፣ ‹‹በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የጋራ ትብብር በውኃ፣ በህዳሴ ግድብና በቴክኒክ ትብብር ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ ትብብሩን በማስፋት ለግብፅና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የጥቅም ማሳኪያ መሆን አለበት፤›› ማለታቸውን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ስለታሰሩ ሁለት ግብፃውያን ጉዳይ አንስተዋል፡፡ ኤምባሲው በላከው መግለጫ፣ ‹‹የግብፅ ዜጎች በኢትዮጵያ ታስረዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የታሰሩት ግብፃውያን የመፈታታቸው ጉዳይ እንዲታይላቸው፣ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መብታቸው እንዲጠበቅላቸውና የግብፅ ኤምባሲ ከታሳሪዎቹ ጋር ግንኙነት እንዲያደርግና ስለሁኔታቸው እንዲያረጋግጥ ዕድሉ እንዲሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፤›› ብለዋል፡፡
ኤምባሲው በመግለጫው ጨምሮ እንዳብራራው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለዚህ ጉዳይ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይኼ ጉዳይ እንዲታይ መመርያ እንደሚሰጥና ለግብፅ ኤምባሲም እንደሚያሳውቅ ቃል ገብተዋል፤›› ሲል ገልጿል፡፡
በቅርቡ ሁለት የግብፅ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የመዋላቸው ዜና መዘገቡ አይዘነጋም፡፡