Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናተመድ ሳዑዲ ዓረቢያና ኤምሬትስ በኤርትራ የሚያደርጉት ወታደራዊ እንቅስቃሴ አሳስቦኛል አለ

ተመድ ሳዑዲ ዓረቢያና ኤምሬትስ በኤርትራ የሚያደርጉት ወታደራዊ እንቅስቃሴ አሳስቦኛል አለ

ቀን:

ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በኤርትራ ግዛት ውስጥ ወታደራዊ ካምፕ በመመሥረት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዳሳሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አጣሪ ቡድን አስታወቀ፡፡

በኤርትራ ላይ የተጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የሚከታተለው የተመድ አጣሪ ቡድን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው የክትትል ሪፖርት ያሰጉኛል ካላቸው አራት ነጥቦች መካከል አንዱ፣ የሳዑዲ ዓረቢያና የኤምሬትስ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በዋናነት ይገኝበታል፡፡

በየመን የሚንቀሳቀሱትን የሁቲ አማፂያንን ለመደምሰስ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራው የዓረብ አገሮች ቅንጅት በኤርትራ ወታደራዊ የጦር ሠፈር በመመሥረት፣ የኤርትራን ግዛት፣ እንዲሁም የአየርና የውኃ ክልል መጠቀሙ በራሱ የተጣለውን የመሣሪያ ማዕቀብ መተላለፍ ነው ማለት እንደማይቻል ይጠቁማል፡፡

- Advertisement -

ሁለቱ አገሮች በኤርትራ የአሰብ ወደብ የገነቡት አዲስ የአየር ኃይል የጦር ሠፈርና ቋሚ የባህር ኃይል የጦር ሠፈር የኤርትራ ጦርን የሚጠቅም የውጭ ኃይሎች ድጋፍ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳለው፣ ይህም ተመድ የጣለውን የመሣሪያ ማዕቀብ የሚጥስ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የአሰብ ወደብንና የኤርትራን የአየር ክልል በመጠቀማቸው የሚፈጽሙት ክፍያ፣ ለኤርትራ ጦር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እስካለ ድረስ ይህም ማዕቀቡን መተላለፍ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ወታደራዊ ሥልጠና ለመስጠትም ሆነ ወይም የታጠቁ ወታደሮችን ወይም የጦር መሣሪያዎችን ለማስተላለፍ በኤርትራ ከተጠቀሱት የሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወታደሮች በተጨማሪ፣ የሌሎች አገሮች ወታደሮች መኖራቸውን በማስረጃ ማረጋገጡን ይገልጻል፡፡ ይህ ደግሞ በቀጥታ ተመድ በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ የሚጥስ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በመሆኑም የተመድ አባል አገሮች የሆኑት ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ሌሎች አገሮች የተጣለውን የመሣሪያ ማዕቀብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዳይተላለፉ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል የተመድ አጣሪ ቡድን ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ ኤርትራ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሸባብ በመሣሪያ መደገፍ ስለመቀጠሏ የሚያሳይ ማስረጃ የለም፡፡ ነገር ግን አሁንም የአካባቢውን መረጋጋት የማወክ ተግባር የኤርትራ መንግሥት እንደሚፈጽም ገልጿል፡፡

ለአብነት ያነሳውም በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸውን ታጣቂ ቡድኖች በመሣሪያ መርዳቱን ጠቅሷል፡፡ ኤርትራ ከጂቡቲ ጋር የጦር እስረኞችን መለዋወጥ አለመፈጸሟ፣ እንዲሁም ፍሩድ የተባለውን የጂቡቲ አማፂ ቡድን በጦር መሣሪያ እንደምትደግፍ በመረጃ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የካናዳው ማዕድን ኩባንያ ኔቨሰን ከማዕድን ገቢው ለኤርትራ የሚፈጽመው ክፍያ ለወታደራዊ ጥቅም አለመዋሉን እንዲያረጋግጥ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ይህንን ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆኑ፣ ገቢው የጦር መሣሪያ ማዕቀቡን ለመተላለፍ ያስችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳሳደረበት የተመድ አጣሪ ቡድን ጠቁሟል፡፡

ምናልባትም በቅርቡ ወደ ጣሊያን ያመራው የኤርትራ ልዑክ ለሔሊኮፕተሮች መለዋወጫ ሊገዛ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬውን ገልጿል፡፡ ሪፖርቱን ያደመጠው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ አራዝሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን በኤርትራ ግዛት ወታደራዊ የጦር ሠፈር ማቋቋም አስመልክቶ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

በሰጡት ምላሽም ሳዑዲ ዓረቢያ በኤርትራ የምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ፀጥታና ደኅንነት ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደማይኖረው ማረጋገጫ እንደተሰጣቸው አስታውቀው ነበር፡፡ በማከልም የሁለቱ አገሮች እንቅስቃሴ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን የማወክ እንቅስቃሴ የሚደግፍ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ለምትወስደው ዕርምጃ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ አስረግጠው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...