Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አሰላ ብቅል ፋብሪካና ሐይኒከን የተስማሙበትን ውል በማሻሻል የተጠረጠሩ ሥራ አስኪያጅ በሙስና ተከሰሱ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– መንግሥት ከ17.5 ሚሊዮን ብር በላይ ማጣቱ ተጠቁሟል

ሐይኒከን ቢራ አክሲዮን ማኅበር የብቅል ገብስ ለማቅረብ፣ አሰላ ብቅል ፋብሪካ ደግሞ የቀረበለትን ገብስ አብቅሎ ለማስረከብ የተዋዋሉበትን ሰነድ በማሻሻል፣ መንግሥት ከ17.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያጣ በማድረግ የተጠረጠሩት የአሰላ ብቅል ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ የሙስና ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኅዳር 5 ቀን 2009 ዓ.ም. የመንግሥትን ወይም ሕዝባዊ ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው፣ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ ዋቅጅራ ናቸው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ሐይኒከን ቢራ አክሲዮን ማኅበርና አሰላ ብቅል ፋብሪካ የስምምነት ውል ፈጽመዋል፡፡ ሐይኒከን 160,000 ኩንታል የብቅል ገብስ ሲያቀርብለት፣ አሰላ ብቅል ፋብሪካ ደግሞ በአንድ ኩንታል 817 ብር ሒሳብ ብቅል አብቅሎ ለማስረከብ መዋዋላቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ተከሳሹ የውሉን አፈጻጸም በመከታተል የተቋሙን ጥቅም ማስጠበቅ ሲገባቸው የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ፣ ሐይኒከን ቢራ ፋብሪካ በውሉ መሠረት ማቅረብ ከነበረበት 160,000 ኩንታል ውስጥ 67,122.56 ኩንታል አቅርቦ፣ 92,877.4 ኩንታል ማቅረብ እንደማይችል ለፋብሪካው መግለጹንም ጠቁሟል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ድርጊቱን ከመቃወም ይልቅ በስምምነት ውሉ ላይ ስለካሳ የሚገልጸውን የውል ክፍል ማሻሻላቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በውሉ መሠረት ሐይኒከን ቢራ አክሲዮን ማኅበር መክፈል የነበረበትን 17,527,830 ብር ባለመክፈሉ፣ በመንግሥት ላይ ጉዳት መድረሱን ክሱ ያብራራል፡፡

ተከሳሹ የክስ ቻርጁ ተሰጥቷቸው ከተነበበላቸው በኋላ፣ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው እንዲመጡ ጊዜ እንዲሰጣቸውና ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እሥራት ሊያስቀጣቸው ስለሚችል ዋስትና እንደማይፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱ ነግሯቸው፣ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች