Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየወተት መሰብሰቢያ ማዕከል ሊቋቋም ነው

የወተት መሰብሰቢያ ማዕከል ሊቋቋም ነው

ቀን:

በኒውዚላንድ ሚልክ ፕሮዳክትስና በኢትዮጵያ የጥሬ ወተት አቅራቢዎች ማኅበር መካከል፣ የወተት መሰብሰቢያ ማዕከል ለማቋቋም የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በተከናወነው በዚሁ ስምምነት መሠረት፣ በጫንጮ ልዩ ልዩ የመገልገያ ዕቃዎችን ያካተተ አንድ የወተት መሰብሰቢያ ማዕከል ይቋቋማል፡፡

ማዕከሉ ከሚያካትታቸው ዕቃዎች መካከል ከማይዝግ ብረት የተሠሩ የወተት መያዥያ ባልዲዎች፣ ቀዝቃዛ የወተት ማጠራቀሚያ ጋን፣ ማቀዝቀዣ የመሳሰሉ ይገኙበታል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ማዕከል የሚያቋቁመውና ዘመናዊ የሆኑ ዕቃዎችን የሚያቀርበው ኒውዚላንድ ሚልክ ፕሮዳክትስ ነው፡፡

ማኅበሩም ከወተት አምራች ገበሬዎች የሚቀበለውን ጥሬ ወተት በማዕከሉ እያጠራቀመ ለሚያቀነባብሩ ኢንዱስትሪዎች የማከፋፈል ሥራውን የሚያከናውን ይሆናል፡፡

‹‹አንከር›› በሚል መጠሪያ ዱቄት ወተት ከውጭ እያስመጣና እያቀነባበረ ለገበያ በማቅረብ ላይ ያለው ይኸው ኩባንያ፣ ማዕከሉን ለማቋቋምና ዕቃዎቹንም ለማቅረብ ያቀደው፡፡ ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ካለው የዱቄት ወተት በተጨማሪ ከማኅበሩ ጥሬ ወተት ገዝቶ በማቀነባበር ለአገር ውስጥና ለጎረቤት አገሮችም ጭምር ለማቅረብ አልሟል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት መሆኑን በስምምነቱ ወቅት ተናግሯል፡፡

አቶ ዘኩ ቃሲም፣ የኒውዚላንድ ሚልክ ፕሮዳክትስ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ስምምነቱን ከፈረሙ በኋላ፣ ኩባንያው ለማኅበሩ በሚሰጠው ድጋፍ በአሁኑ ጊዜ በወተት ሥርጭት ላይ የሚታየውን ማነቆ ለመፍታት፣ የአገር ውስጥ የወተት ፍጆታን ከፍ ለማድረግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የገበሬዎችን ገቢ ለማሳደግና ጥራቱ የተጠበቀ ወተት ለማግኘት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡

አቶ ሰሎሞን መኰንን የማኅበሩ ሊቀመንበር እንደሚሉት፣ ማኅበሩ ከ40 በላይ አባላት ያሉት ሲሆን፣ 21 ሺሕ ከሚጠጉ የወተት አምራች ገበሬዎች በየዕለቱ እስከ 120 ሺሕ ሊትር ወተት እየሰበሰበ በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚገኙ የወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ያከፋፍላል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ ከስድስት ዓመት በፊት በቀን የሚያቀነባብሩት ከ70 ሺሕ ሊትር ያልበለጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እስከ 200 ሺሕ ሊትር ወተት ያቀነባብራሉ፡፡ የማኅበሩም ዓላማ ወተት አምራች ገበሬዎችን ከገበያ ጋር ማስተሳሰርና ጥራቱን የጠበቀ ወተት ከገበሬዎቹ እየሰበሰበ ለኢንዱስትሪዎች ማቅረብ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በሚያካሂደው እንቅስቃሴ 500 ለሚጠጉ የገበሬ ልጆች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

ድጋፍ ከተገኘ ማኅበሩ የአቅርቦቱን መጠን ከፍ እንደሚያደርግ፣ በበጋ ወራት አልፎ አልፎ የወተት እጥረት እንደሚከሰትና ይህም በመኖ እጥረት ምክንያት እንደሆነ አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

ከነሐሴ እስከ ኅዳር የሚኖረውን  የወተት ምርት በመጠባበቂያ የሚይዝ ኢንዱስትሪ ቢቋቋም፣ በበጋ እጥረት ላይከሰት እንደሚችል፣ በወተት ላሞች ዘር ላይ ማሻሻያ ቢደረግና ባለሙያዎች ታች ወርደው ለአምራች ገበሬዎች ሥልጠና ቢሰጡ፣ ለምርቱ ዕድገትና ጥራት አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ፣ ዶ/ር መብርሃቱ መለሰ ወተትን ጨምሮ ብዙዎቹ የግብርና ምርቶች ከእርሻው ተጠቃሚ እስከሚደርሱ ድረስ በየደረጃው ብዙ ማነቆዎች እንዳሉ ገልጸው፣ እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንዲት ላም በቀን ከ12 እስከ 30 ሊትር ወተት ሲገኝ፣ ባደጉ አገሮች አንድ የወተት ላም በቀን በአማካይ እስከ 120 ሊትር ወተት ትሰጣለች፡፡ ከዚህ አንፃር የአገሪቱን የወተት ምርትን ከፍ ለማድረግ የሚረዳ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...