የአሜሪካ 45ኛ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ዓለምን ሊያናጓት እንደሚችሉ ከመንበረ ሥልጣናቸው ርክክብ ቀድሞ እየተነገረ ነው፡፡ ተመራጩ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በስደተኞች፣ በአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና በውጭ አገሮች ጣልቃ ገብነት፣ ከሩሲያ ጋር በሚኖራቸው መልካም ግንኙነትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲናገሩዋቸው የነበሩትን፣ ወደፊት ተግባራዊ እንደሚያደርጓቸው እየተናገሩ ነው፡፡
ከተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር የተወያዩት ትራምፕ ከኦባማ ምክርና እገዛ እንደሚፈልጉ የተናገሩ ቢሆንም፣ አሁን እያነሱዋቸው ያሉ ጉዳዮች ግን በኦባማ እገዛ ሊቀለበሱ የሚችሉ አይደሉም፡፡
ትራምፕ የሚያነሱዋቸው አጀንዳዎች የአሜሪካን የውጭ ግንኙነት ያላላሉ የሚሉ አስተያየቶች ቢሰሙም፣ አንዳንዶች ደግሞ የአሜሪካን ጥቅም የሚያስጠብቅና ከተቆርቋሪነት የመነጨ ነው ብለውታል፡፡ ቢቢሲ እንደሚለው ደግሞ የትራምፕ ዕርምጃ አሜሪካ ከውጭው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ይጎዳዋል፡፡
ትራምፕ ስደተኞች ላይ ያላቸው አቋም
አሜሪካውያንንና አሜሪካን ማስቀደም በሚል አቋማቸው የሚታወቁት ትራምፕ፣ ለስደተኞች ያላቸው አመለካከት የወረደ ነው፡፡ በተለይ አሜሪካ የምትጠቃው በአሜሪካውያን ሳይሆን ከውጭ ገብተው ዜግነት ባገኙ ወይም በመኖሪያ ፈቃድ በሚኖሩ የሌሎች አገሮች ዜጎች ነው ይላሉ፡፡ በሙስሊሞች ላይም አሜሪካ ለተወሰነ ጊዜ በሯን ዝግ እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው እሑድ ከሲቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ለ60 ደቂቃ በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ደግሞ፣ ከምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ በሜክሲኮ ዜጎችና በሙስሊሞች ላይ የነበራቸውን አሉታዊ አቋም በማጠናከር፣ በአሜሪካ የሚገኙ ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ አገር ነዋሪዎች/ስደተኞችን ከአሜሪካ እንደሚያስወጡ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ እንደሚሉት፣ ከአሜሪካ የሚባረሩ የሌላ አገር ዜጎች በአሜሪካ በሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚኖሩና ከዚህ ቀደም ወንጀል የፈጸሙና ወንጀለኛ የሆኑ ናቸው፡፡ ‹‹የወንጀል ሪከርድ ያለባቸውንና ወንጀለኞችን እንይዛለን፡፡ በአሜሪካ የተደራጁ የዱርዬ ቡድኖች፣ ዕፅ አዘዋዋሪዎችና በብዙ ወንጀል የተሰማሩ ስደተኞች አሉ፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ሚሊዮን ይደርሳሉ፡፡ እነዚህን ከአሜሪካ እናስወጣለን፣ ወይም እስር ቤት እንከታለን፡፡ ግን ሕገወጥ ስለሆኑ ከአገራችን እናባርራለን፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የትራምፕ እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ስደተኞችን ከአሜሪካ የማስወጣት ፈተና የሚጀምረው፣ ስደተኞቹን ለመልቀም ከሚደረግ ዕርምጃ ነው፡፡ በኒውዮርክ የስደተኞች ጥናት ማዕከል የዓለም አቀፍ ስደተኞች ፖሊሲ ከፍተኛ ዳይሬክተር ኬቨን አፕሊባይ፣ ‹‹ትራምፕ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ስደተኞችን ለማስወጣት ከፈለገ በመላ አገሪቱ ማኅበረሰቡን መከፋፈልና ፍርኃት ማንገሥ ይጠበቅበታል፡፡ እነሱ ያሉባቸውን አካባቢዎች መውረርና መጠራረግ አልያም ደግሞ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን በስፋት የሚለቃቅም የፖሊስ መንግሥት መፍጠር ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በአሜሪካ የድንበር አጥር እንደሚገነቡና በሕገወጥ መንገድ አሜሪካ የገቡትን ወደ አገራቸው እንደሚመልሱ የተናገሩት ትራምፕ፣ ይህንን እንደሚፈጽሙት ከተመረጡ በኋላም አረጋግጠዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ደግሞ ትራምፕ በስደተኞች ላይ ያላቸው አቋም አሜሪካን ወዳልተፈለገ ችግር እንዳያመራት ይሠጋሉ፡፡ በተለይ የአሜሪካ ድንበር ተጋሪዎች ወደ አሜሪካ በሕገወጥ መንገድ ሲገቡ ሕፃናት ልጆቻቸውን ይዘው መሆኑና ስደተኞቹ በገቡበት ጊዜ ሕፃናት የነበሩ ዛሬ ምናልባትም ብዙዎቹ በትምህርትና በሥራ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው፣ እነዚህን በሕጋዊ መንገድ አልገባችሁም ብሎ ማፈናቀሉ ከባድ ይሆናል ይላሉ፡፡ ትራምፕም ይህንን አቋማቸውን ቆም ብለው እንዲፈትሹ መክረዋቸዋል፡፡ በየዩኒቨርሲቲው ያሉ ተማሪዎችን ጨምሮ ብዙ ስደተኞችም ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው፡፡
በኦባማ የሥልጣን ዘመን የተሠሩ ጥናቶች በአሜሪካ ወደ 1.9 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ከወንጀል ጋር ንክኪ እንዳላቸው ታውቋል ይላሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ የመኖሪያ ፈቃድና ጊዜያዊ ቪዛ ያላቸው፣ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት የማያደርሱ እንደ ስርቆት የመሰለውን የፈጸሙ፣ ጥፋት ፈጽመው ማስረጃ ያልተገኘባቸው ወይም በቡድን ተደራጅተው ወንጀል የሚፈጽሙ ይገኙባቸዋል፡፡ ትራምፕ የሚጠቅሱት ቁጥር በኦባማ ጊዜ ከተገመተው በእጅጉ የበለጠ ከመሆኑ አንፃር፣ ወንጀል ፈጽመዋል ተብሎ ከአገር ማስወጣት አልጋ በአልጋ አይሆንም፡፡ ምናልባትም የትራምፕ አስተዳደር የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸምና የስደተኛ መብት አቀንቃኞችን ማፈን ይኖርበታል፡፡
ትራምፕና የኔቶ ህልውና
የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለማስፈጸም ላለፉት 60 ዓመታት የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለገለው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በትራምፕ እየተወቀሰ ነው፡፡ ‹‹የኔቶ አባል አገሮች ከአሜሪካ በትልቁ እያተረፉ የሚኖሩ ናቸው፣ ድርጅቱም አልፎበታል፤›› የሚሉት ትራምፕ፣ አሜሪካ በኔቶ ስም ሌሎች የአውሮፓና የእስያ አገሮችን እየደጎመች እንደማትኖር፣ አባል አገሮችም ለድርጅቱ የሚከፍሉትን መዋጮ ካላሳደጉ አሜሪካ ከአባልነቷ እንደምትወጣ ገልጸዋል፡፡
ከኔቶ አባል አገሮች አብዛኞቹ ለመከላከያ ካላቸው በጀት ሁለት በመቶ ያህሉን አያዋጡም፡፡ አሜሪካ ከመከላከያ በጀቷ 3.6 በመቶ ያህል ለኔቶ ስታዋጣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ ቱርክና ካናዳን ጨምሮ 22 አባል አገሮች ከሁለት በመቶ በታች የሚያዋጡ ናቸው፡፡ ፖላንድ፣ ኢስቶኒያ፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ ግሪክ ከሁለት በመቶ እስከ 2.4 በመቶ ድረስ ሲያዋጡ፣ የአሜሪካ 3.6 በመቶ በመሆን ከሁሉም ልቆ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ በትራምፕ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አብዛኞቹ አገሮች የተጣለባቸውን ግዴታ ካልተወጡ አሜሪካ ከኔቶ ትሰናበታለች ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ትራምፕ በኔቶ ላይ ያላቸው አቋም ድርጅቱ በሩሲያ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ተፅዕኖም የሚፈትን ነው፡፡ አብዛኞቹ አባል አገሮች መዋጮውን መክፈል ካልቻሉና አሜሪካ ራሷን ካገለለች ለሩሲያ መልካም አጋጣሚ ይሆናል፡፡ ምናልባትም አሜሪካና አውሮፓ የጣሉባት ማዕቀብ ይነሳል፡፡ በሩሲያ እየተቀዛቀዘ የመጣው የንግድ ልውውጥም ያንሰራራል፡፡
ትራምፕ ለሩሲያ ያላቸው ምልከታ
ኦባማ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን ሲጀምሩ የአሜሪካ የረጅም ጊዜ ተቀናቃኝ ከሆነችው ሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መልሰው እንደሚቃኙት ተናግረው ነበር፡፡ በእሳቸው ዘመን ቀድሞውንም የሻከረው ግንኙነት የበለጠ ውጥረት ውስጥ የገባ ሲሆን፣ በሥልጣን ማብቂያቸውም አሜሪካና ሩሲያ በሶሪያ ጉዳይ ጽንፍ ሆነው አገሪቷን የጦር አውድማ አድርገዋታል፡፡
የትራምፕ ምልከታ ደግሞ ከኦባማ የተለየ ነው፡፡ ትራምፕ ለሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያላቸው አመለካከት መልካም ነው፡፡ ከሩሲያ ጋር ያለውን የሻከረ ግንኙነት እንደሚለውጡት፣ ውጥረቱንም እንደሚያረግቡት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፑቲን ጠንካራ መሪ ነው፡፡ ከእሱ ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ከአሜሪካ ጋር በቀዝቃዛው ጦርነት ስትፋለም የኖረችው ሩሲያ፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላም ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት መልካም አይደለም፡፡ ትራምፕ በመመረጣቸው ምክንያት ግን የሩሲያው ፑቲን፣ ትራምፕ ለእሳቸው ያላቸውን አክብሮት ያህል እንደሚያከብሩዋቸው ገልጸው፣ አብረው እንደሚሠሩም ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡
ነፃ የንግድ ልውውጥን መሰረዝ
ትራምፕ በተመረጡ ማግሥት አሜሪካ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን ነፃ የንግድ ልውውጥ እንደሚሰርዙና ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ግብር እንደሚጭኑ አሳውቀዋል፡፡ ይህ አውሮፓንና ከአሜሪካ ጋር ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ ያላትን ቻይና ያስደነገጠ ቢሆንም፣ ትራምፕ ግን ወደ አሜሪካ የሚገቡ ዕቃዎች ከቻይና 45 በመቶ፣ ከሜክሲኮ 35 በመቶ ታክስ እንደሚጥሉ ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ ከዓለም የንግድ ድርጅት እንድትወጣ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በአሜሪካ፣ በካናዳና በሜክሲኮ መካከል ያለውን የሰሜን አሜሪካ ነፃ የንግድ ስምምነት ጨምሮ የተለያዩ የነፃ ታሪፍ የንግድ ስምምነቶችን እንደሚሰርዙ ተናግረዋል፡፡ ሐሳባቸው ተቃውሞ የገጠመው ቢሆንም፣ አሜሪካን ለመጥቀምና ብዙ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከታክስ ነፃ ለመጠቀም ሲሉ ወደ ሌሎች አገሮች መኮብለላቸውን ለማስቀረት ነው ብለዋል፡፡
የኢራን ኑክሌር ስምምነት
ትራምፕ ‹‹በሕይወት ዘመኔ አጋጥሞኝ የማያውቅ አስቀያሚ ስምምነት›› ሲሉ ኢራን የምታበለጽገውን ኑክሌር ያወግዙታል፡፡ ለጦር መሣሪያ ሳይሆን ለኃይል ማመንጫና ለሌሎች ሥራዎች መጠቀም የምትችልበትን አግባብም ይነቅፋሉ፡፡ ‹‹የኑክሌር ጣቢያውን ማፈራረስ›› ቀዳሚ ሥራቸው እንደሚሆንም ይናገራሉ፡፡ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ በበኩላቸው፣ የትራምፕን ችኩልነት ተችተው አሜሪካ ስምምነቱን እንድታከብር ጠይቀዋል፡፡
እስያና የኑክሌር ጦር መሣሪያ
የትራምፕ አስተዳደር በእስያ የኑክሌር ጦር መሣሪያ እንዲንሰራፋ ያደርጋል የሚል አስተያየትም እየተሰነዘረ ነው፡፡ ቻይና የአሜሪካ አግላይ የውጭ ፖሊሲ ይቀየራል ስትል፣ በአሜሪካ ላይ በእጅጉ የተጣበቁት ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ግን ሥጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሆኖም ትራምፕ አገሮቹ ከራሳቸው ኑክሌር ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ቀድሞውንም ኑክሌር ለታጠቀችው ሰሜን ኮሪያ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ግን፣ ትራምፕ ኑክሌርን በተመለከተ በእስያ ላይ ያላቸው አቋም አኅጉሪቷን ብሎም ዓለምን ያናጋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ
ትራምፕ ዕጩ ፕሬዚዳንት እያሉ ሥልጣን በያዙ በ100 ቀናት ውስጥ ፕሬዚዳንት ኦባማ ያስቀመጧቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር መመርያዎች እንደሚቀለብሱ አስታውቀው ነበር፡፡ አሜሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የምታደርገውን ድጎማና ማበረታቻ በሙሉ እንደሚያስቆሙም ተናግረዋል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የትራምፕ ግዴለሽ አቋም ሌሎች አገሮች ዓለምን እያሳሰበ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ቦታ እንዳይሰጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም ዓለም የባሰ ሙቀትና ድርቅ እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎችን እንድታስተናግድ ያደርጋታል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን የዋይት ሐውስ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዲሆኑ ሌይንስ ፕሪባስን ሲሾሙ፣ በነጭ አክራሪነት የሚታወቁትን ስቲቭ ባነንን ደግሞ ዋና ስትራቴጂስትና አማካሪያቸው አድርገው ሾመዋል፡፡ በተለይ የስቲቭ ባነን በዚህ ደረጃ ለከፍተኛ አማካሪነት መሾማቸው የዶናልድ ትራምፕን መጪዎቹን አራት ዓመታት አሳሳቢ አድርጓቸዋል፡፡