Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርየመልካም አስተዳደር ዕጦትና የሕግ የበላይነት ጥሰት በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር

  የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የሕግ የበላይነት ጥሰት በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር

  ቀን:

  በመፍትሔ አፈላላጊ ስብስብ

  ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከካፍ በፊት በጀግኖች አባቶቻችን የተመሠረተው አንጋፋ ክለባችን፣ ከዕድሜ ጠገብነቱና ካለው ወርቃማ የሰው ኃይል ብዛት ጋር ሲገመገም በቅርብ ከተቋቋሙ ወጣት ክለቦች በአደረጃጀትና በመልካም አስተዳደር ብዙ ተበልጦ ይገኛል፡፡

  የተዋደቁለትና የተደፉለት መሥራች አባላቱ ቀና ብለው ሊያዩ ቢችሉ ኖሮ ልባቸው በሐዘን በተሰበረ ነበር፡፡ ክለቡ በየመርሐ ግብሩ ዋንጫ ቢሰበስብም ዛሬም እንደ ትናንቱ በዳረጎት እየተደጎመ መጓዙ የተጣለበት ግዴታ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ እንደ ዕድሜ ጠገብነቱ በፋይናንስ አቋሙ በራሱ ገቢ መተዳደር ሲገባው በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ላይ ተንጠልጥሎ እንዲኖር በመገደዱ፣ ከእነዚህ ግለሰቦች በኋላ ከመፍረስ ሊታደጉት የሚችሉ በፍቅሩ ያበዱ ቁርጠኛ አባላቱ ብቻ ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ ቆመን ግራና ቀኝ ብናስተውል የኢትዮጵያ ቡና፣ የደደቢት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የወልዲያ ከነማ ክለቦች ራሳቸውን በራሳቸው ገቢ ችለው እንዲገኙ ለማስቻል አኩሪና ደስ የሚያሰኝ ተግባራትን ደረጀ በደረጃ እየገነቡ ይገኛሉ፡፡

  ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ቦርዱ ከሕገ ደንብ ውጪ የቀጠረው ኦዲተር እንኳን ሳይቀር ያለው ተንቀሳቃሽ ገንዘብ  315,000.00 ብር (ሦስት መቶ አሥራ አምስት ሺሕ ብር) እንደሆነ በአደባባይ ሲገለጽ፣ የአባላት መሰብሰቢያና መገናኛ ክለባቸው ከሳሪ ሆኗል ተብሎ ለውጭ ግለሰብ በኪራይ ሲሰጥና መሰብሰቢያ አጥተን በሜዳ ላይ ስንጣል ይኼ የአገር ቅርስ ክለባችን በአደገኛ የህልውና ጥያቄ ላይ ስለመገኘቱ የማይጠረጥር አባል ካለ አባል ነው ለማለት አያስችልም፡፡ ትናንት የተቋቋመው ወጣቱ ወላይታ ዲቻ ክለብ እንኳን 35,000 ከፋይና ተመዝጋቢ አባላት አፈራ ሲባል በ80 ዓመታችን 850 የማይደርሱ አባላት ምልዓተ ጉባዔ (50 በመቶ) ናቸው ስንባል የማያስደነግጠን አባላት ካለን ቆም ብለን በጥልቅ ልናስብ ይገባል፡፡

  ከላይ የሚስተዋለው አሳሳቢ ሁኔታ ለምን ተከሰተ? ቢባል በአጭሩ ብልሹ አሠራር የፈጠራቸው በክለቡ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የሕግ የበላይነት መጣስ ዓይነተኛና ቁልፍ ክስተቶች ናቸው፡፡ ከመልካም አስተዳደርና ከሕግ የበላይነት መጣሶች እጅግ ጥቂቱን ለአብነት ለመጥቀስ ያህል በየዓመቱ መጠራት የነበረበት ጠቅላላ ጉባዔ ለአራት ተከታታይ ዓመታት አለመጠራት፣ ቦርዱ የሥልጣን ዘመኑ ካለፈ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ቢሆንም ራሱን ከሕግ በላይ አድርጎ በሥልጣን ማቆየቱ፣ በየዓመቱ አባላት ዓመታዊ ዕቅድና የሒሳብ ሪፖርት ሰምተው በጠቅላላ ጉባዔ ማፅደቅና ውሳኔ መስጠት አለመቻላቸው፣ የክለቡን ኦዲተር የመሾም፣ የሥልጣን ጊዜ የመወሰን፣ አበል የመወሰን ሥልጣን የጠቅላላ ጉባዔው አባላት የሥልጣን ኃላፊነት ቢሆንም፣ በፕሬዚዳንቱና በቦርዱ ይኼ ሕግ ተጥሶ በራሳቸው ፈቃድ ኦዲተር መሾማቸው፣ ክለቡን ከ18 የማያንሱ ስፖንሰሮች ላለፉት 16 ዓመታት በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ቢለግሱትም ገንዘቡን ለማን እንደተሰጠ፣ ምን ያህል እንደተሰጠ፣ ምን ላይ እንደዋለ ከአባላት መደበቁ፣ ቦርዱ ክለቡ ራሱን በራሱ ገቢ እንዲተዳደር እንዲያደርግ ሕገ ደንቡ ቢደነገግም ተግባራዊ አለማድረጉ፣ የአሠልጣኞችና የተጨዋቾች ግዢና ክፍያ ለአባላት ድብቅ ሚስጥር መደረጉ፣ አባላት ዕምነት አጥተውበት በጠቅላላ ጉባዔ የተባረረ ሥራ አስኪያጅ ከሦስት ዓመት በኋላ እንዲመለስ መደረጉ፣ ክቡር ዶ/ር ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ለስታዲየም ግንባታ 70 ሚሊዮን ብር ለፕሬዚዳንቱ ቢሰጡም የሜዳው አፈር ተቆፍሮ ከ12 ዓመት በላይ ተገትሮ መገኘቱ ዓይነተኛዎቹ ናቸው፡፡

  በእዚህ አጭር ማብራሪያ በሙሉ ሊዘረዘሩ በማይችሉ አያሌ ምክንያቶች የክለቡ ህልውና በአደጋ ላይ መሆኑን በመገንዘባችን፣ ስድስት ነባር የክለቡ አባላት ቦርዱ እንዲያነጋግረን ብንጠይቅም ሰሚ በማጣታችን ሕገ መንግሥታችን በአጎናፀፈን የመጻፍና የመናገር መብት ተጠቅመን በተለያዩ ሚዲያዎች በክለቡ ያለውን የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለማሳወቅ ተገደድን፡፡ አልፎ ተርፎም ከ160 በላይ አባላት በክለቡ ዙሪያ የተከሰቱትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ አጀንዳዎች ቀርፀን ቦርዱ ለስብሰባ አቅርቦ እንዲያወያየን ጠይቀን፣ ጉዳዩንም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሳወቅን፡፡ በክለባችን የተንሠራፋውን ብልሹ አሠራርና መልካም አስተዳደር ዕጦት በመቅረፍ ክለባችን ዘመናዊ አደረጃጀት፣ አወቃቀርና ሲስተም ተላብሶ በራሱ ገቢ የሚተዳደር ክለብ እንዲሆን ለማድረግ አሁንም እየታገልን እንገኛለን፡፡

  የክለባችን ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረ መስቀል ይኼንን የአባላት ጥያቄ ላለመቀበል ወስነው ተደፈርኩ በሚያስመስል ሁኔታ ኢትዮጵያ ጨዋነትን ድባቅ በመታ ቋንቋ በብሥራት 101.1 ሬድዮ ጣቢያ በግንቦት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ዘለፋ፣ ስድብና ማንቋሸሽ ፈጽመውብናል፡፡ የተጠቀሙበትን ቋንቋ ከአንድ ታላቅ ክለብ መሪ የማይጠበቅ አሳፋሪ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ምንም እንኳን እርሳቸውም ሆኑ የቦርዱ አባላት የሥልጣን ዘመናቸው ቢያልፍም ራሳቸውን በሥልጣን ሰይመው አቆይተዋል፡፡ እንዲሁም ፕሬዚዳንቱ በግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ስብሰባ ጠርተው ሲዘልፉን ውለዋል፡፡ የእነዚህንም አስገራሚ ትዕይንት በዕለቱ የብዙ ሚዲያ ጋዜጠኞች በስብሰባው ተገኝተው ምስክር ሆነው ተመልክተውታል፣ አይተውም ዘግበውታል፡፡፡ በመሠረቱ የሥልጣን ዘመኑ ያለፈበት ፕሬዚዳንት ይኼንን ስብሰባ የመጥራትም ሆነ የመምራት ሕጋዊነት የለውም፡፡ ሌላው አስገራሚው ነገር ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ስብሰባ ላይ ራሳቸውን ከአባላትና ከሕግ በላይ በማስቀመጥ፣ ‹‹እኔ ኢንተርናሽናል ነኝ፣ ዩሮ አለኝ፣ ምንም ልታመጡ አትችሉም፤›› በማለት በስብሰባው ላይ በድፍረት መናገራቸው ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በተደጋጋሚ ላደረሱብን ስድብና ዘለፋ ይቅርታ እንዲጠይቁን ብንጠይቃቸውም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ከውስጣችንም አራቱን በማገዳቸው እግዱን እንዲያነሱ በጽሑፍ ብንጠይቃቸውም እንቢታን በመምረጣቸው ማንም ሰው ከሕግ በላይ ስላልሆነ ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን ለማስከበር ሳንወድ በግድ ጉዳዩን ለሕግ አቅርበናል፡፡

  በቅርቡም በክለቡ ውስጥ የተከሰተውን አምባገነንነትንና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለማስወገድ ጉዳዩን ለሕግ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ በክለቡ ውስጥ የተከሰተውን የሕግ ጥሰትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት በተመለከተ ላለፉት ስምንት ወራት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም ውሳኔ እንዲሰጡበት አመልክተን ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንገኛለን፡፡ ሁኔዎችንም በግልባጭ ውሳኔ እንዲሰጡበት አመልክተን ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንገኛለን፡፡ ሁኔታዎችንም በግልባጭ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተደጋጋሚ አሳውቀናል፡፡

  ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ላደረሱብን ስድብና ማዋረድ ብሥራት 101.1 ሬድዮ ጣቢያ ተባባሪ ሆኖ በመገኘቱ ይቅርታ እንዲጠይቀን ፣በበኩላችንም ለተከበሩ የክለቡ አባላት ፕሬዚዳንቱ በእኛ ላይ ያቀረቡት መሠረተ ቢስ የሐሰት ውንጀላን ለማስተባበል በተላለፈው ፕሮግራም ላይ የበኩላችንን እንድናሰማ ብንጠይቅም ዝምታን በመምረጡ፣ ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ከነካሴቱ አቅርበን አቤቱታችንን መርምሮ ሬድዮ ጣቢያው ጥያቄያችንን እንዲያስተናገድ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ ሬድዮ ጣቢያው ምክንያቶችን በመደርደር ተግባራዊ ባያደርግም ሕግ የበላይ ነውና ዕውን መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

  በመጨረሻም በእኛ በኩል መላው የክለቡ አባላትና ደጋፊዎች እንዲያውቁልን አጥብቀን የምናሳስበው፣

  1ኛ በክለባችን ተንሠራፍቶ የሚገኘውን የሕግ ጥሰትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለማስወገድና የክለባችን ህልውና ለማስጠበቅ በምናደርገው ሕጋዊ ትግል በሬዲዮ ፕሮግራሙም ሆነ በሌሎች የሕግ መድረኮች ክለቡን የሚጎዱ ሁኔታዎች ቢከሰቱ፣ ተጠያቂው ራሱን ከሕግ በላይ ያደረገው ፕሬዚዳንቱና ቦርዱ ብቻ እንደሚሆኑ፣

  2ኛ የክለቡ የዓመታት ገቢና ወጪ በውጭ ኦዲተር ተመርምሮ እውነቱ እንዲወጣ እንደምንታገል፣  

  3ኛ የሥልጣን ዘመናቸው ያለፋባቸው የቦርድ አባላትና ፕሬዚዳንቱ ሕገ ደንባችንን በጣሰ መንገድ ራሳቸውን በሥልጣን ላይ መሰየማቸው ተቀባይነት እንደሌለው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አቤቱታችንን በተደጋጋሚ ያሳወቅን እንደመሆኑ ግቡን እስኪመታ እንደምንታገል፣

  4ኛ የክለባችን ባለቤትና ዋናው የሥልጣን አካል አባላትና ጠቅላላ ጉባዔ ስለሆኑ፣ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ በመምራት አባላት በክለቡ ችግሮች ዙሪያ ሐሳባቸውን በነፃነት አንሸራሽረው መፍትሔ እንዲሰጡበት በኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን እስከ ካፍና ፊፋ ድረስ ለተፈጻሚነቱ እንደምንታገል፣

  5ኛ በሚጠራውና በገለልተኛ አካል በሚመራው ስብሰባ ምርጫ አስፈጻሚ ተሰይሞ በሕገ ደንቡ መሠረት ሠርተው የሚያሠሩ፣ የክለቡን ሕገ ደንብ የሚያከብሩ የቦርድ አባላት ምርጫ እንዲካሄድ፣ ክለባችን ዘመናዊ አደረጃጀት ኖሮት ራሱን በራሱ ገቢ የሚያስተዳደር ክለብ እንዲሆን የበኩላችንን ጥረትና ትግል እያደረግን ስለሆነ፣ አባላትም ችግሮችን በጥሞና መርምረው የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ ጥሪያችንን በትህትና እናስተላልፋለን፡፡

  ግለሰቦች ያልፋሉ! ክለባችን ለዘለዓለም ተከብሮ ይኖራል!

  የመፍትሔ አፈላላጊ ስብስብ

  1. ተስፋዬ ነጋሽ                      4. አንተነህ ፈለቀ
  2. ታደሰ መሸሻ                       5. ሥዩም ተፈሪ
  3. ዳንኤል ካሣ                        6. ማሙዬ ነጋ

  ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊዎቹን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...