Wednesday, November 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርየአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ይመለከታል?

  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ይመለከታል?

  ቀን:

  በደጀኔ አሰፋ ዳምጠው

  እንደምን ሰንብታችኋል? በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ይህን መጣጥፍ እንድጭር ገፊ ምክንያት የሆነኝ በጥቅምት 12 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ማስታወቂያን መመልከቴ ነው፡፡ በእርግጥ ይህን ጽሑፍ ካዘጋጀሁ በኋላ ማስታወቂያው በሪፖርተር ጋዜጣም እንደወጣ አስተውያለሁ፡፡ ማስታወቂያው “ዲቪ 2018”ን ይመለከታል፡፡ በትልቁ! ከትልቅነቱ የተነሳም ስንት ፎንት እንደሆነ እንኳን ለመገመት ይከብዳል፡፡ የፊደላቱ መተለቅ ወይም መጥቆር (መወፈር) ደግሞ በሥነ ጽሑፍ ዓይን ሲታይ ለዚያ ጉዳይ የተሰጠውን አፅንኦት የሚገልጽ ይመስለኛል፡፡ ዲቪ የሚለው ምህፃረ ቃል ‘ዳይቨርሲቲ ቪዛ’ ማለትና የአሜሪካ አገር እንደሆነ ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ እስከማውቀው ድረስ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖስታ የመንግሥት እንደነበረ ነው፡፡ የተለወጠ ነገር እንዳለ አላውቅም፡፡ ደግሞም አይመስለኝም፡፡ ይህንን የምለው በማስታወቂያው ውስጥ የተገለጹትን ፍሬ ነገሮች በመመዘን እንጂ “ዲቪ 2018”ን ለምን አስተዋወቀ በማለት አይደለም፡፡ ፍሬ ጉዳዮቹ ከትዝብቴ ጋር እነሆ፡፡

  “ዲቪ 2018 በኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ለአንድ ወር ብቻ” ይላል፡፡ በነፃ የሚሰጥ ይመስል! ለዚያውም የእኛው ፖስታ ድርጅት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በሼር የዲቪ ዕድልን ፈጥሮ የሚያስተዋውቅ ይመስላል፡፡ ከዚያም “ዲቪ 2018 ከመስከረም 24 እስከ… ስለሆነ በመላው አገሪቱ በሚገኙ የአገልግሎት መስጪያ ጣቢያዎች አገልግሎቱን ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እየገለጸ፣ ተሳታፊ እንድትሆኑ በአክብሮት ተጋብዛችኋል፤“ ይላል፡፡ እስቲ ያሳያችሁ የዲቪ 2018ን ዕድል የአሜሪካ መንግሥትና ሕዝብ እንጂ የኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ያዘጋጀው ዕድል እንዳልሆነ እየታወቀ አፉን ሞልቶ “ተሳታፊ እንድትሆኑ በአክብሮት ይጋብዛል’’ ሲል የልጁ ሠርግ አሊያም የልጁ ልደት ይመስል “…ማን በሠረገው ማን ይጋብዛል’’ አያስብልም? ለነገሩ አሁን አሁን የምናየው ነገር እኮ “…እከሌ ሊያገባ እከሌ ገገባ…“ ወይም “…የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ…“ ዓይነት የሚመስል ከሆነ እኮ ሰነባብቷል! በማያገባን መግባት፣ የሰውን ጩኸት መቀማት፣ የሌላ ሰው ጉዳይን ማራገብ፣ ከባለቤቱ/ባለጉዳዩ በላይ ማቀንቀንን እንደ የሕይወታችን ፍልስፍና ስንከተል የጣድነው የራሳችን ዋና ጉዳይ እያረረ ተቸገርን ለማለት ነው፡፡

  ወረድ ብሎ ደግሞ በትልቁ “ያስታውሱ“ ይለናል፡፡ የረሳችሁ እንደሆነ ወዮላችሁ! እንደ ማለት፡፡ ከዚያም በጣም አበክሮ “የዲቪ ፎርም የሚቆየው ለአንድ ወር ጊዜ ብቻ በመሆኑ በአስቸኳይ ፎርሙን በመሙላት ይላኩልን፤ …“ ይላል፡፡“ ጥድፊያው! ይህ አባባሉ ደግሞ አንድ ከአገር ስለመሰደድ አስቦ ለማያውቅ ዜጋ (እኔን ጨምሮ) በሕይወቱ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር እያለፈው እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርግ የሚችል ሲሆን፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ አገሪቱ ላይ በጣም መጥፎ አደጋ ስላለ “ከዚህ ለማምለጥ ዲቪ 2018”ን አሪፍ አጋጣሚ እንደሆነ የሚጠቁም ያስመስለዋል፡፡ ይባስ ብሎ “…እኛ በኢንተርኔት እናስተላልፋለን’’ ይላል፡፡  በእርግጥ እንደሚታወቀው በአገሪቱ ላይ ያንዣበበውን አደጋ ከማስቀረት አንፃር መንግሥት የማኅበራዊ ድረ ገጾችና ሞባይል ዳታን ላልተወሰነ ጊዜ ዘግቷል፡፡ በዚህ ውሳኔ ደግሞ አይደለም ተጠቃሚው ማኅበረሰብ መንግሥት ራሱ ደስተኛ እንዳልሆነ ይገመታል፡፡ አንገብጋቢ የአገር ጉዳይ ስለሆነበት እንጂ፡፡ ታዲያ ይህንን ደስ የማይል ሁኔታ እንደገና በማስታወቂያ መልክ ለማስታወስ ይሆን? ወይስ እናንተ ኢንተርኔት ቢቋረጥባችሁም እኛ ግን እንጠቀማለን ብሎ “እንቁልልጬ” ለማለትና ለማብሸቅ? አልገባኝም፡፡ በመጨረሻም በማስታወቂያው ግርጌ “መልካም ዕድል!’’ ይላል፡፡ ይህን ሲል በዚህ አገር መኖር መጥፎ ስለሆነ ‘ለጫማው በኋላ ይታሰባል ዋናው ማምለጡ ነው’ ለማለት ይሆን? ይህም አልገባኝም፡፡

  ምንም እንኳን አብዛኞቻችን አሜሪካ ስለሚባለው አማላይ አገር፣ ብዙ ዕድሎች ስላሉበት አገር፣ ያደገና የበለፀገ አገር የምናውቅ አሊያም በስማ በለው የሰማን ወይም ለማየት የጓጓን ልንሆን እንችላለን፡፡ በአንፃሩ የእኛ አገር ድህነት ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የሥራ ዕድሎች ጠባብ የሆኑባት፣ ኢፍትሐዊነት በሀብት ክፍፍልም ሆነ በብዙ ረገድ የሚታይባት፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የመረጃ እጥረት፣ የዋናተኛ እጥረት፣… ብቻ እንደ ኩዋሻኮር ብዙ ዕጦትና እጥረት ያሉባት አገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ እነዚህንና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመቅረፍም እንደ አገር ብዙ ሠርተናል፣ ተጨባጭ ለውጦችም ተመዝግበዋል፣ ብዙም ይቀረናል፡፡ ይህንንም ሕዝቡ ያውቃል፣ መንግሥትም ያምናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጽሑፉ በዋናነት የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ ሳለ ከአገር እንድንሰደድ ለምን ያበረታታል የሚለውን ለመጠየቅና እንዲህ ዓይነቱ የስደት መልዕክት በመንግሥት አፍ ሲራገብ “የአፋጣኝ ጊዜ የስደት አዋጅ’’ አይመስልምን? የሚለውን ለመጠቆም ይፈልጋል፡፡

  በእርግጥ በድህነትና መሰል አገራዊ ችግሮች (Pushing Factors) እና በውጭ ባሉ ሳቢ ምክንያቶች (Pulling Factors) ሳቢያ ብዙ ወገኖቻችን እንደተሰደዱ እናውቃለን፡፡ በስደትም የብዙ ዜጎቻችን ሕይወት ጠፍቷል፣ ጉልበታቸው ተበዝብዟል፣ ሰብዕናቸው ተዋርዷል፣ ለአካላዊና ለአዕምሯዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ መንግሥትም ስደትን (በተለይ ሕገወጥ ስደትን) እንደ ዋና አሳሳቢ ችግር ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ዘርፈ ብዙ ምላሾችን ለመስጠት እየጣረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው በማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሚመራና ሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴርን፣ የፌደራል ፖሊስን፣ የፍትሕ አካላትንና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ሕገወጥ ደላሎችን አሳዶ በመያዝ ለሕግ ያቀርባል፡፡ ውስን ቢሆኑም የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ይሞክራል፤ በስደት አስከፊነት ዙሪያ የዜጎችን ንቃተ ህሊና የማሳደግ ሥራዎችን ያከናውናል… ወዘተ፡፡ በአንፃሩ በሕጋዊ ይሁን ሕገወጥ መንገድ ከአገር የተሰደዱ ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው እንዲገቡና (ከቻሉ) እንዲያለሙ ካልሆነ ግን በነፃነት መኖር እንደሚችሉ እያበረታታ ይገኛል፡፡  

  ይህ በእንዲህ እንዳለ የፖስታ ድርጅቱ እንዲህ ዓይነቱን ማስታወቂያ ለመሥራት የተነሳሳው በምን ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚለውን ለመመለስ የተለያዩ መላ ምቶችን መዳሰስ ተገቢ ይመስላል፡፡ ቀዳሚ መላ ምት የሚሆነው ድርጅቱ ይህን ማስታወቂያ ሲሠራ በእንዲህ ዓይነት መንገድ ሊታይ ይችላል ብሎ ስላልገመተ ይሆናል የሚል ነው፡፡ ይህ መላ ምት ትክክል ነው ካልን ደግሞ በማስታወቂያ ዙሪያ በሚሠሩ የዘርፉ ምሁራን ዘንድ እንደ ተራ ስህተት የሚታይ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ማስታወቂያ (Promotion/Advertisement) እንደ አንድ ሳይንሳዊ የሙያ ዘርፍ የራሱ የሆኑ አሠራሮች፣ ሥልቶችና ሥነ ምግባሮች ያሉት በመሆኑ አንድ ማስታወቂያ ሲሠራ በጥናት የተደገፈ፣ ከብዙ አቅጣጫ የተመዘነና ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ… ወዘተ ሊሆን ይገባዋል ከሚሉት መርሆች አንፃር ማለት ነው፡፡ ይህም ያስፈለገበት ምክንያት ደግሞ ምንም እንኳን በማስታወቂያው ማስተላለፍ የተፈለገው ጉዳይ (ከሠራው አንፃር) ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም፣ በሌላ መልክ ሊተረጎም አሊያም ያልታቀደበትን አሉታዊ መልዕክት ሊያስተላልፍ የሚችልበት አጋጣሚ በመኖሩ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፖስታ ድርጅቱ ከተጠያቂነት የሚድን አይመስልም፡፡

  ሌላኛው መላ ምት በወቅቱ ካለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መንግሥት ፌስቡክና መሰል ማኅበራዊ ድረ ገጾችን መዝጋቱን ተከትሎ የኢትዮ ቴሌኮም ገቢ ከመቀነሱ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ነጥብ ነው፡፡ ሆኖም ግን በዚህ መልኩ የመንግሥት ገቢን ለማሳደግ በሚል ከሆነ ገቢን ማሳደግ ከዜጎች ሕይወት የሚቀድም አይሆንም፡፡ በመንግሥትም ደረጃ እንዲህ ይታሰባል ብዬ ጭራሽ አልገምትም፡፡ ከሆነ ግን ማስታወቂያው በእንዲህ ዓይነት መልኩ ሊሠራ አይገባም ነበር እላለሁ፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ ይኼኛው የዲቪ ማስታወቂያ ስለአሜሪካ ስለሆነ “ስደት”ን አይመለከትም ወይም “ስደት” የሚባለው ጉዳይ ለዓረብ አገር ብቻ ነው የሚል እሳቤ ሊኖረን ይችላል፡፡ በእርግጥ “ሕጋዊ” ስደት አለ፡፡ “ሕገወጥ” ስደት አለ፡፡ እዚህ ላይ ግን “ሕጋዊ” ወይም “ሕገወጥ” ስደት ስንል ከአገር የሚወጣበት ሁኔታ በሕጋዊ ወይስ በሕገወጥ መንገድ የሚለውን ለመጠቆም እንጂ፣ በሕጋዊም ይሁን በሕገወጥ መንገድ የሚደረግ ስደት ሁሉም ስደት ነው፡፡ እንኳንስ ዜግነትን ጭምር የሚያስቀይረው በዲቪ የሚደረገው ስደት፡፡ አለቀ!

  ገሚሶቻችን ደግሞ የእኛ ፖስታ አገልግሎት የዲቪ ማስታወቂያውን የሠራው እንደ ህንድ ባሉ አገሮች የሚከናወን የአዕምሮ ፍልሰት (Braindrain) ተብሎ የሚታወቀውን ፍልሰት እንጂ ተራ ስደትን ለማበረታታት አይደለም እንል ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የአዕምሮ ፍልሰትም ቢሆን ስደት እንጂ ሌላ ስም የለውም፡፡ የእኛ ዜጎች ወደ አሜሪካ የሚሄዱት በዚህኛው ምክንያት ነው ተብሎ ከታመነ ደግሞ፣ በዚህ ጊዜ የእኛ አገር ዘርፈ ብዙ እውቀቶችን፣ ብዙ አዋቂዎችን፣ ተመራማሪዎችንና የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን… እየፈለገች ያለችበት ሁኔታ ስላለ ከሌሎች ይልቅ የተማሩ ሰዎች ፍልሰትን እጅግ አጥብቃ ትቃወማለች እንጂ ታበረታታለች የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዚህ አግባብ ከታየ የአዕምሮ ፍልሰት የሚባለው መከራከሪያ ነጥብም አዋጭ አይሆንም ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ወደ ዓረብ አገር (በአውሮፕላን፣ በባህር፣ በኮንቴይነር፣ በእግር…) መሄድ ስሙ ስደት ከሆነ ወደ አሜሪካ (በአውሮፕላን፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣…) የሚደረግ ጉዞ ከስደት ውጪ ሌላ ስያሜ ሊኖረው አይችልም፡፡ በሱዳን፣ በኬንያ፣… ስል ግን ከላይ እንደተጠቀሱት የመጓጓዣ ዓይነቶች እንዳልሆኑ ይታወቅልኝ፡፡

  “ስደት” በሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ አንድ ሌላ መከራከሪያ ነጥብ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህም “ስደት” የሚባለው ኩነት በደሃ አገሮችም ሆነ በበለፀጉ አገሮች ከጥንት ጀምሮ የነበረ፣ አሁንም ያለና ወደፊትም የሚኖር ዓለም አቀፋዊ መስተጋብር መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም የእኛ አገር ዜጎች ቢሰደዱ ምን ነውር አለው የሚል ተጠይቅ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ከታየ የእኛ አገር ዜጎች መሰደዳቸው ምንም ነውር ላይኖረው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን አገራችን ካሏት ዋና ዋና ሀብቶችና የወደፊት የዕድገት ዓምዶች መካከል በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው የሰው ሀብቷ ነው፡፡ በተለይም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ብዛት ከ40 እስከ 45 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር የሚይዘው የአገሪቱ ወጣት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ በዚህ አግባብም ይመስላል መንግሥት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጣቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ለማሻሻልና ወጣቱ የልማት ተዋናይ እንዲሆን የሚያስችሉ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ያለው፡፡ ለምሳሌ በድኅረ ምርጫ 2007 በተደረገው የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች አወቃቀር ከሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ተገንጥሎ “ወጣቶች እና ስፖርት“ የተሰኘ ተቋም ከጠፋበት ተመልሶ እንደ አዲስ መዋቀሩን ልብ ይሏል፡፡ ይህም በወጣቶች ዙሪያ ተገቢውን ኢንቨስትመንት ለማድረግና አበክሮ ለመሥራት በመንግሥት ዘንድ የተያዘውን አቅጣጫና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የዚህ ተቋም መደራጀትም በአገሪቱ ያለውን ሰፊ የወጣት ቁጥር ተደራሽ ለማድረግም ሆነ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶቹን ለመቅረፍ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይሆንም፡፡ ይህ ውሳኔም በብዙ የወጣት አደረጃጀቶች፣ የወጣት ሲቪክ ማኅበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ዘንድ “ወጣቶች በቂ ትኩረት ያገኛሉ” የሚል ተስፋን ከመጫሩም በላይ ለመንግሥትም አድናቆትን አትርፎለታል፡፡ የወጣቱ መሻት ተሳክቶ ማየት ውስጤ ነው!

  አሁን ባለንበት የበጀት ዓመት ደግሞ በዚህ ችግር (ስደት) ዓይነተኛ ገፈት ቀማሽ ለሆነው የአገሪቱ ወጣት “የተሻለ“ የሚባል በጀት (10 ቢሊዮን ብር) በመመደብ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የኢኮኖሚ ደረጃውን ለማሻሻል መታቀዱ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን በዚህ በጀት ሁሉንም የወጣት ጉዳዮች ይመልሳል የሚል እምነት በመንግሥትም ዘንድ ባይኖርም እንደ መልካም ጅማሮ ግን ይበል፣ እሰይ የሚያስብል ነው፡፡ እነዚህ ጅምሮች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ ደግሞ ከየትኛውም ዕርምጃ በፊት የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ወጣትም ሆነ በየደረጃው ካሉ የወጣት አደረጃጀቶች፣ ሲቪክ ማኅበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር መምከር ፋይዳው አያጠያይቅም፡፡ በዚህም ወጣቱ የእኔ የሚለው ዕቅድ እንዲኖረውና የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠርበት ከማድረጉም በላይ፣ የበጀት ሥርዓቱም ግልጽና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን ያግዛል፡፡ በሒደቱም ሁሉም አካል ተሳታፊ ስለሚሆን የወጣውን የጋራ ዕቅድ የመሳካት ዕድል ከፍ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች ተቋማት ሊያገለግሉዋቸው የቆሙላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎችና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በዕቅድና በጀት ዝግጅት፣ በትግበራ፣ በክትትልና ግምገማ ሒደቶች በማሳተፍና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን በማሳደግ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑ (እግረ መንገዴን) ለማመልከት ነው፡፡ ካልሆነ ግን “እኔ አውቅልሃለሁ” በሚል እሳቤ የሚወጡ ዕቅዶች ማጣፊያ ያጠራቸው መዘዞችን ወልደው ምን ዓይነት የችግር ብፌ እንዳስነሱብን ማስታወስ አያሻኝም፡፡ 

  ብቻ ወደ ተነሳንበት ዋና ጉዳይ እንመለስ፡፡ ስደት! መንግሥት ስደትንም ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ ነው “ወጣቱ በአገሩ ሠርቶ፣ በአገሩ መለወጥ ይችላል”፣ “ከሠራን መለወጥ እንችላለን” በሚሉ መፈክሮች አገራዊ ንቅናቄን ለመፍጠር እየሞከረ ያለው፡፡ በዚህ ርብርብም ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ ለጋሽ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኝነታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ከጥቂት ወራት በፊት በአገራችን ለሚገኙ ስደተኞች ሥራ ፈጠራና ተያያዥ ጉዳዮች ማከናወኛ የሚሆን ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በአውሮፓ ኅብረት የተለገሰውን 500 ሚሊዮን ዶላር መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ብቻ ከላይ በተዘረዘሩት አመክንዮችና በተጨባጭ ካለው የአገሪቱ ሁኔታ መረዳት የሚቻለው አገራችን እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደ መንግሥት በዚህ ጊዜ ስደትን በተለይም የወጣቱን ፍልሰት ማበረታታት እንደሌለብን ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ጥረትና ቁርጠኝነት ባለበት ሁኔታ ፖስታ ድርጅት የዲቪ 2018ን ማስታወቂያ በተጋነነ ወይም ስደትን በሚያበረታታ መልክ መሥራቱ አንደምታው ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የዚህ መጣጥፍ ዓላማ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትን በሕገወጥ ደላላነትም ሆነ በሕጋዊ አስኮብላይነት ለማስፈረጅ ወይም ደግሞ ዲቪን ለመቃወም ሳይሆን፣ በተቋማት ዘንድ የሚታዩ ክፍተቶችን፣ ጠቃሚ ያልሆኑ አመለካከቶችንና የታዳጊውን ወጣት ትውልድ የማያንፁ አካሄዶች ልብ እንዲባሉ ለመጠቆም ነው፡፡

  ለምሳሌ ይህ የተጠቀስው የፖስታ ድርጅቱ ማስታወቂያ በተገቢ ትኩረትና በውል ታስቦበት የተሠራ እንዳልሆነ መገመት አይከብድም፡፡ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያዎች፣ ከመልዕክታቸው አንፃር በግሉ ሴክተርም ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ተቋማዊ ቸልተኝነት (Institutional Recklessness) ተደርጎ ብቻ የሚወሰድ ሳይሆን፣ በተቋማቶቻቸን መካከል አለመናበብ እንዳለ በተወሰነ ደረጃ አመላካች ነው፡፡ ይህንን የኢትዮጵያ ፖስታን ማስታወቂያ የፌደራል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ወጣቶችና ስፖርት ወይም ሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ቢመለከቱት ምን ዓይነት ግብረ መልስ ሊሰጡት ይችላሉ የሚለውን ሳስብ በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችል አልጠራጠርም፡፡ ስደትን ለመዋጋትና ወጣቱን በአገሩ ለማብቃት የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ያሉ ሌሎች መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትና የወጣት ማኅበራትም ቢሆኑ ደስተኛ አይሆኑም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ስህተቶች እንደ ተራ ግድፈት ሳይታለፉ ትምህርት ቢወሰድባቸው ጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ምክንያቱም አለመናበብ ካለ በየተቋማቶቻችን የምናወጣቸውን ዕቅዶች በተገቢው መልኩ ፈጽመን ተጨባጭ ለውጥ እንዳናመጣ ጋሬጣ ከመሆን አልፎ፣ አንዱ የሚሠራውን ሌላኛው የሚያፈርስበትን አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ጥረታችንንም …ጠብ ሲል ስደፍን… እንደሚባለው ዓይነት ያደርግብናል፡፡ በመሆኑም በሁሉም ረገድ “መናበብ” የጊዜው ጥያቄ (Demand) ይመስላል፡፡

  ብቻ በአገራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ሆኖ በዋናነት ደግሞ “ተጠርጣሪ” ወይም “ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ” ተብለው የሚታሰቡ አካላት ላይ አተኩሮ እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን አዋጁ/አስፈጻሚው ከዚህ በዘለለ እንዲህ በውል ሳይታሰብበት እንደተለቀቀው የ“ዲቪ 2018” ዓይነት ማስታወቂያ (የግድ ማስታወቂያ መሆን አይጠበቀበትም፤ ስለዚህኛው ድርጅት ብቻም አይደለም) የወጣቱን ልብ የሚያሸፍት፣ በአገር ሠርቶ መለወጥ እንደማይቻል የሚያስተጋባ፣ በአገር ውስጥ ጉዳይ ጨለምተኛ እንድንሆን የሚጋብዝ፣ ውጭ ናፋቂ እንድንሆን የሚያበረታታ፣ አሊያም በራስ መተማመናችንን የሚገዳደር አመለካከትም ሆነ አተገባበርን የሚያራምዱ ተቋማትን ሃይ እንዲልልን እንጠይቃለን፡፡ ተቋማትም እርስ በርስ እንዲናበቡና አሳታፊ እንዲሆኑ ተገቢውን አቅጣጫ እንዲሰጥልን እንሻለን፡፡ ይህም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ አዋጁ የወጣበትን ግብ ለማሳካት ይረዳልና ነው፡፡

  ቸር እንሰንብት!

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...