Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የብሶት ማመልከቻ በዛሳ?

እነሆ መንገድ ከመገናኛ ወደ ስድስት ኪሎ። የጎዳናው ጭብጥ ተደጋጋሚ ነው። ሕይወት ቀለም ያለቀባት ትመስላለች። በመንጋ ቅርፅ አሠልፋ የምትነዳው እልፍ ነው። ሲቃችን ተያያዥ ነው። ውክቢያው ዓይን ያጥበረብራል። ደምቆ ካማረበት ይልቅ ገርጥቶ ያስቀየመው ልቋል። ወጣት አዛውንቱ፣ ጎበዙና ሰነፉ፣ ልማታዊና ፀረ ልማታዊው ተፋጠዋል። በዚህች ምድር ለሆድ መኖር ዕውቅና የተቸረው ከዛሬ ሦስት ሺሕ ዓመት በፊት ይመስላል። አብሲቱን ተሸከሞ፣ ቅሉን አንጠልጥሎ፣ ምጣዱን አስሟሽቶ አይታይም እንጂ ለወጪ ወራጁ የዕለት እንጀራ ጋጋሪነት የነፍሱ ጥሪ ይመስላል። ሐሳብና ሐሳበኞች ሲቀበሩ ትንሳዔያቸውም አብሮ ሳይቀበር አልቀረም መሰል። እዚያ ድንፋታሙ ለዘብተኛው ላይ ይጮሃል። ዝምታ በአቅም ማጣት የተመሰለበት ደግሞ አንገቱን እንደ ደፋ መሽቶ ይነጋል። ጊዜ ሄዶ ሄዶ ማለቂያ የሌለው የከንቱነት አጥር ይመስለናል። ነገር ሁሉ ባለበት ላይዘልቅ ውክቢያችን ከማከማቸትና ከመጠውለግ ጋር የተያያዘ ነው።

ፀሐይ በተንጠለጠለችበት እንደቀረች ኳስ ቁልቁል ድምቀቷን ስትረጭ እዚህ ወሩ ኅዳር ነውና ውርጭ ያርገፈግፈናል። ‹‹ወይኔ ብርዱ?›› ስትል አንዷ፣ ‹‹ላሙቅሽ፤›› ብሎ ከጎኗ ጠጋ ይላል። ሳቅ ይቀጣጠላል። መለካከፍና አጉል ጠጋ ጠጋ ያፋቀረን ይመስል በደቦ የሚወገዘውን በደቦ እናሞግሳለን። ያቺ ፀሐይ ይኼን ስትታዘብ ጭምር ሳትውል አትቀርም።  ስለሰው ልጆች ብዙ ታዝባ ቋንቋዋ ቋንቋችን ስላልሆነ ብቻ ቁጣዋን በግለቷ የምትለካው ይመስላል። አጠገባችን ከደጅ ታክሲያችን በራፍ ላይ የቆመ ገርጀፍ ያለ ሙር፣ ‹‹ፀሐይን እዚያ የሰቀላት ማን ነው? እውነትን አብርቶ አልጋ ሥር የከተታትን ሰው ፈልጉኝማ?›› እያለ ይጮሃል። ታክሲ ጠባቂው ሠልፈኛ እርስ በርሱ ለመተያየት እንኳ አፍሮ ከንፈሩን ይመጣል። በጠዋቱ መርዶ ነጋሪ እንደተላከበት በሰሞኑ ንፋስ የደረቀ ከንፈሩን ሲመጥ እውነት በቅርፊት መልክ እየተላጠች የምትተፋ ይመስላል። ሕይወትና አብስትራክት ማለት ይኼ አይደል!

ጉዟችን ተጀምሯል። የታክሲያችን ፍጥነት እየጨመረ ሲሄድ ጆሮ የሚያደምጠው ዓይን የሚታዘበው ነገር አብሮ ጨምሯል። ሁለት ሴቶች እየተንሾካሾኩ እየተመካከሩ የደወለላቸውን ደንበኛ ያስለፈልፋሉ። ‹‹እኔ ምለው የካርድ ጣቢያው የአባትህ ነው ወይስ የእናትህ? ምነው በገንዘብህ ባትጫወት?›› ትለዋለች አንዷ። የሚላትን አንሰማም። ‹‹እኛ በቀላሉ አንገኝማ ልማት ላይ ነን በይውማ፤›› ትላታለች ጓደኛዋ። ስለብቸኝነት አነሳባቸው መሰል፣ ‹‹ገንዘብ የሌለው ነው ብቸኛ ወንድሜ። ገንዘብ ካለህ ምንም ብቸኝነት ብሎ ነገር የለም። ይዞ መገኘት ነው . . .  እውነቴን ነው። እያሾፍኩብህ ከመሰለህ ኔትወርኩን ለሠርቶ አዳሪዎች ለቀቅ አድርግላቸው፤›› ትለዋለች። ተሳፋሪው  ጭውውት እንደሚያዳምጥ አንዴ ልጆቹን ዘወር ብሎ እየጋለመጠ፣ ዘና እያለ፣ እያዘነ ቀልቡን ጥሎ ይከታተላቸዋል።

ጥቂት እንደተጓዝን ኔትወርክ ተቋረጠና ስልኩ ተዘጋ። ‹‹አሁን የኔትወርክ መቆራረጥ ባይኖር ምን ይወጠን ነበር? ሥራ ፈት…›› ብላ አነጋጋሪዋ ተቆናጠረች። ጓደኛዋ ተቀበለቻት ‹‹ቆይ ግን እሱን የሚያህል ሰውዬ በዚህ ዕድሜው ነውር አይደለም? ትንሽ እፎይ ብንል ነገር ተረሳና ንስሐም ያስታዋሽ ያለህ ማለት ጀመረ? ሆሆ!›› ብላ አንባረቀች። ‹‹አይገርምሽም? ደግሞ ብቸኝነት አሰቃየኝ ይለኛል። በኅብረት መኖር እንደሚያውቅ ሁሉ። በዛሬ ጊዜ ያውም ኮንዶሚኒየምና ልማታዊነት የሚባል ነገር ከመጣ ወዲህ ማን ማንን ከቦ? እኔና አንቺ እንኳ የተገናኘነው መቼ ነበር?›› ሲሉ ወደ ግል ጨዋታቸው ዞሩ። የኮንዶሚኒየም ነገር ሲነሳ ምድረ ቆጣቢ እየተጠቃቀሰ ‘ስለቤታችን የሰማችሁ እስኪ እንያችሁ’ መባባል ያዘ። ነገር ወደ ምሽት ትዝ የሚለን መቼም እልፍ ነን!

ጉዟችን ቀጥሏል። ሰዓቱ የሥራ መግቢያ ነው። የታክሲ ተጠቃሚው ባተሌ ሠልፍ ለዓይን ይታክታል። ትርክቱ አንዳንዴ ከቃላት አቅም በላይ ነው። ትራንስፖርት ተቸግሮ በተሠለፈው ምስኪን ነዋሪ ትይዩ የኑሮ ዳና ተሳክሮበት ልመናን መተዳደሪያው ያደረገው ሕዝብ ሌላ ሠልፍ ሠርቷል። ከቁጣና ከግልምጫ ጋር ‘ታመጣለህ? አታመጣም?’ በሚል ቃና ሰውን መድረሻ አሳጥተውታል። ‹‹ወይ ጉድ! መድረሻ አጣን እኮ እናንተ!›› ይላሉ አንዲት ወይዘሮ። በእጃቸው ያንጠለጠሉት ፌስታል ውስጥ ለማምሻ ሆድ የማይበቃ የቲማቲምና የሽንኩርት ስፍር ይታያል። ‹‹በቃ እኮ የእኛ ኑሮ . . . ከእጅ ወደ አፍ ታውቃለህ?›› እያለ ከወይዘሮዋ ራቅ ብሎ ወደ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ጎልማሳ ፌስታላቸውን ለጓደኛው ይጠቁመዋል። ወይዘሮዋ ደግሞ፣ ‹‹ከሁሉ ብሶ ለምኖ የሚያድረው ብዛት? እነሱ ተሻሉ ከእኛ ልበል?›› ብለው መነጫነጭ ጀመሩ። ‹‹እንግዲህ ምን ይደረጋል? ዓይነቱ ነው እንጂ እዚህ አገር ሁሉም ለማኝ ነው። የሳንቲም ምፅዋት አለመጠየቃችን እንጂ ሁላችን በደረጃችን የማንለምነው የለም፤›› አላቸው አመዛዛኝ ነኝ ባዩ ጎልማሳ።

ከጎልማሳው አጠገብ የተሰየመ ወጣት ሳያስበው ንዴት አንዘረዘረው። ‹‹ታዲያ እኛ እኮ የምንለምነው የራሳችን የሆነውን ነገር መልሱልን ብለን ነው። ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ዴሞክራሲን ነው የምንማጠነው፤›› ብሎ ሲነጫነጭ፣ ‹‹ሁሉን በአንድ ሙቀጫ የሚወቅጠው አይደል አገር እያጠፋ ያስቸገረን? ንገረውማ ደህና አርገህ፤›› ይላል ሌላው። በዚህ መሀል ታክሲያችን ልትጭን ቆመች። ተረኞች ያለ ግርግር ገብተው ትርፍ ተቀመጡ። ቀረት ቀረት ያሉ ሠልፋቸውን ጠብቀው ወደኋላ ቀሩ። ይኼኔ ‹‹አይገርምም? በሠልፍ ተወልደን በሠልፍ አድገን ሳያልፍልን ማለፋችን? በዚህ ሳምንት ብቻ አራት አብሮ አደጎቼን ስቀብር!…›› እያለ ተንገበገበ። ‹‹ግፊያና አቋራጭ ናፋቂ ሆነን እንጂ እንደ እኛ ያለ የሥነ ሥርዓት ተገዢ እንኳ አልነበረም፤›› የምትለው ደግሞ ወደ ጥግ በኩል ተወሽቃ የተሰየመች ደመ ግቡ ናት። ንግግሯ በግልባጭ ማድረስ የፈለገው ማመልከቻ የቆጠረ ይመስላል። ዘመኑ የብሶት ማመልከቻ ሆኗላ!

ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ ሾፌሩን፣ ‹‹ኧረ ነዳ ነዳ አድርገው ኳስ ይጀምራል እኮ?›› ይለዋል። ጠና ያሉ አዛውንት፣ ‹‹እንዴ የማታው አልበቃ ብሏችሁ፣ ቅዳሜና እሑድ ሥራ መፍታት አልበቃ ብሏችሁ በዚህ ማለዳ የምን ኳስ ነው ደግሞ ኧረ እናንተ ልጆች ተው አታዋክቡን?›› ሲሉ ወያላው፣ ‹‹ፋዘር ትናንትና ያመለጠኝ ግጥሚያ አሁን ስለሚደገም ነው፤›› ብሎ ሲያበቃ ወደ ሾፌሩ ዞሮ ስም እየጠራ፣ ‹‹ልክ ይኼን እንዳራገፍን እሱን እተካልህና እኔና አንተ ኳሱ ሲያልቅ እንገናኝ። አይሻልም?›› ይለዋል። ሾፌሩ፣ ‹‹እንዳልክ፤›› ብሎ ዝም ይላል። አንዱ ተሳፋሪ በበኩሉ ተገርሞ የወያላውን ሁናቴ ሲታዘብ ቆየና፣ ‹‹ዘንድሮ ለሥራ የሚቸኩል ሰው እንዲህ ከአገር ምድሩ ይጥፋ?›› እያለ የነገር ወቀጣ አስተባባሪ። ይኼኔ ሾፌራችን ከልክ በላይ ታክሲያዋን በፍጥነት ማካለብ ጀምሯል። ‹‹ቀስ በል ሾፌር። ሪፕሌይ ለማየት ሪያሊቲያችንን ልታጨልሙት ነው አንዴ እናንተ ሰዎች? ከነፍስና ከኳስ የቱ ይበልጣል?›› ብለው ከዚያም ከዚህም ወያላውን የሚያፈጡ ዓይኖች በዙ።

ወያላው፣ ‹‹አይ አባት። ማን በዚህ ጊዜ ለነፍሱ ይኖራል ብለው ነው?›› ቢላቸው አዛውንቱ ነገሩ እንቆቅልሽ ሆነባቸውና፣ ‹‹እንዴት? እንዴት?›› አሉት። ‹‹አቤት የዘንድሮ ልጅና ንግግሩ፡፡ ምንም አያውቁም ትባላላችሁ ግን ውስጠ ወይራ ንግግራችሁ ውስጡ ለቄስ ነው፤›› ብለው ወይዘሮዋ አዛውንቱን አሽሟጠጡ። አዛውንቱ ሽሙጡን ችላ ብለው ነገሩን እንዲያብራራላቸው ወያላውን ተማጠኑት። ‹‹ያው በቃ ኑሮ ከላይ ከላይ ነው የሚያስጋልበን ለማለት ነው። ለሚታየው፣ ለሥጋ፣ ለቁስ፣ ወዘተ እንጂ ነፍስን መቼ አስበናት? የመፈጠርን ዓላማ መቼ አገናዝበነው ነው ብለው ነው? ለነፍስ እንኑር ብንልማ ስንቱ መሰለዎት ዕድሜው ወደ ኋላ እንደ ሰዓት ሊሞላለት ግድ የሚለው፤›› አላቸው፡፡ ከመጨረሻ ወንበር የሰጡትን አሥር ብር ዘርዝሮ መልስ ቢላቸው ቅብጥብጥነቱና አስተሳሰቡ አልገጥም ብሏቸው ተደንቀው ተመለከቱት። ወዲያውኑ  ስለነፍሳችን ጥሪ፣ ስለሞራል፣ ስለእሴት በማሰብ መወዛወዝ ጀመርን። ጀምረን ባንተወው ኑሮና ጎዳናው በሩጫ ሲያዋክበን ታጥበን የማንጨቀይ ቢሆን እያደርን ቁልቁል እናይ ነበር ጎበዝ?!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ሰው እንደጫነ ለአፍታ ማሰብ የተሳነው ሾፌራችን እያክለፈለፈ አስጠግቶናል። ከፍጥነት እልቂት ብቻ ማትረፍ የመረረው ተሳፋሪ ዘግይቶም ቢሆን፣ ‹‹ኧረ ባክህ ቀስ በል…›› ይላል። ጎልማሳው፣ ‹‹ምን ይደረግ በፍጥነት ተለክፈን እኮ ነው?›› ይላል። ‹‹ቴሌቭዢንና ሬዲዮው እኮ ነው የሚያስበላን። ማስታወቂያውና ማስጠንቀቂያው ሁሉ ከመኪና አደጋ ጋር የተያያዘ ሆኗል፤›› ሲል አንዱ ሁሉም ግር ብሎት አየው። ‹‹ታዲያ ጥሩ ነው እንጂ ምኑ ነው ክፋቱ?›› ሲሉት ወይዘሮዋ፣ ‹‹ይኼው አያዩም እንዴ? የእኛ ሰው እኔ አውቃለሁ ካለ አለ ነው። መቼ ሲነገረን እንወዳለን? መቼ ሲነገረን እንሰማለን? ምክር አንወድም እኮ ያ አይደለም እንዴ ወስዶ ወስዶ ከዓለም መጨረሻ የወረወረን?›› ብሎ ዝም አለ። ነገሩን የሚያሰፋለት ሰው ቢያጣ ራሱ ቀጠለ። ‹‹ስክነት የማይበጀን ሕዝቦች። ሥራችን ሁሉ የዕለት። ፖለቲካው የዕለት፣ ዴሞክራሲው የዕለት (እሱም የይምሰል ለምርጫ ሰሞን ነው)፣ ፀሎታችን የዕለት፣ ዕቅዳችን የዕለት . . .  አናሳዝንም? አርቆ ማየትና አርቆ ማሰብ ያልፈጠረብን እኮ ነው የምሰመስለው፤›› ሲል ተረተረው። 

ድንገት ወያላው ‹‹ውረዱ!›› አለ በሩን ከፍቶ። ታክሲዋም ወዲያው ቆመች። ወይዘሮዋ ወያላውን ትኩር ብለው አይተው፣ ‹‹የመብራት፣ የውኃ፣ ‘የኔትወርክ’ መጥፋት አንሶን ትህትናም ድራሹ ሊጠፋ?›› አሉ። ዝብርቅርቁ ኑሯችን የሰለቸው ወጣት፣ ‹‹እሱ መልካም አስተዳደርን፣ መብራትን፣ ውኃን፣ ፍትሕን ቀድሟቸው ጠፍቶ መስሎኝ እኛና መሻሻል ጀርባና ሆድ ሆነን መቅረታችን፤›› አላቸው። አዳምጠውት ሳቁ። አጠገቤ ተቀምጦ የነበረ ተሳፋሪ እንደሚያውቀኝ ሁሉ እየሮጠ ተከትሎኝ፣ ‹‹እኔ የምልህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነሳ እንዴ? ምንድነው ሰው እንዲህ ቅልቅል ቅልቅል ያለው?›› ሲለኝ አዛውንቱ አጠገባችን ኖረው፣ ‹‹እህ ምን ይደረግ ታዲያ? ሲያንቀለቅሉን እንዴት አንንቀለቀል? ዘጠኝ ነፍስ የለን። ከነፍስ ወዲያ ምን አለና?›› ብለውት መንገዳቸውን ቀጠሉ። እኛ በየፊናችን ተበታተንን። ምነው የብሶት ማመልከቻ በዛሳ? መልካም ጉዞ!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት