የመጀመሪያው ተሽከርካሪ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ19ኛው መቶ ዘመን ነበር፡፡ መጓጓዣ ሲባል ከፈረስና ከበቅሎ ውጪ የማያውቁት ኢትዮጵያውያን መኪናው አዲስ አበባ ደርሶ ቢያዩት ተዓምር ሆነባቸው፡፡ አደባባይ ወጥተው ይመለከቱትም ገቡ፡፡ ሁለቱ ነጮች መኪናውን በጂቡቲ በኩል እያሽከረከሩ አዲስ አበባ ሲደርሱ ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ ወጣ፡፡ ብዙዎቹም ‹‹ያመጡት ነብሰ በላ ማሽን ነው›› በማለት ፍርሃት ተሰምቷቸው ነበር፡፡ የመልእክተኞቹ አመጣጥም ምኒልክን ለመግደል እንደሆነ ንጉሡ ሣይቀሩ ጥርጣሬ አድሮባቸው ነበር፡፡ በመሆኑም አፄ ምኒልክና ሕዝቡ ከአሁን አሁን ምን ይፈጠር ይሆን በሚል ሁኔታዎችን በአንክሮ ይከታተሉ ነበር፡፡
ከነጮቹ መካከል አንደኛው ስለመኪናው አጠር ያለ ገለፃ ይሰጥ ጀመረ፡፡ ገለፃውን በንቃት ሲከታተሉ የቆዩት አፄ ምኒልክም እንዲህ አሉ፡፡ ‹‹አዎ እኔን ለመግደል ፈልጎ የመጣ ጋጠወጥ አይመስልም፡፡ ያመጣው ማሽንም ቢሆን እንደተባለለት አደገኛ አይደለም፡፡ እንደተነገረኝ ከሆነ ማሽኑ ላይ ከመውጣቴ እንደምፈነዳ ነበር፤›› አሉ፡፡ ከዚያም ከጠባቂዎቻቸው ጋር ሆነው በመኪናው ተንሸራሸሩ፡፡ ሕዝቡም ጥግጥጉን ይዞ በአግራሞት ይመለከታቸው ገባ ሲል ክሊፎርድ ሃሌ በ1913 “To Menelek in A Motor-car” በሚለው መጽሐፉ አስፍሯል፡፡
በ1900 ዓ.ም. ቴክኖሎጂው ወደ ኢትዮጵያ የገባ ቢሆንም ለዘመናት ከቅንጦት ይቆጠር ስለነበር እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ከአንዳንድ ሹማምንትና ባለፀጎች በስተቀር የሚገለገልበት አልነበረም፡፡ በ1930ዎቹ ለሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው አንበሳ ባስ ሲቋቋም ግን ነገሮች ተለወጡ፡፡ ሰፊው ህዝብ መኪና ተሳፍሮ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ቻለ፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመድረስ ሰዓታት ይፈጅ የነበረው ጉዞ በደቂቃዎች ማለቁ ብዙዎችን አስደሰተ፡፡ ተፈላጊነቱም እየጨመረ ሄደ፡፡ ተቋሙም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሽከርካሪዎቹን ቁጥር በመጨመር የትራንስፖርት አገልግሎቱን በስፋት መስጠቱን ቀጠለ፡፡
ይሁንና በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር አንፃር በቂ አልነበረም፡፡ በመሆኑም የተለያዩ እንደ ታክሲ ያሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ሥራው ገቡ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ፍላጎትና አቅርቦቱን ለማጣጣም ሌሎች ጥቂት የማይባሉ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በአገሪቱ 708,000 ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትም የሚገኙት በአዲስ አበባ ነው፡፡ የቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎትም በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡ ይሁንና ካለው ሰፊ ፍላጎት አንፃር ይህ በቂ አይደለም፡፡ በከተማዋ ውስጥ ያለው የትራንስፖርት ችግርም አንገብጋቢ ነው፡፡ ለዚህም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓታት ላይ በታክሲ ማቆሚያ ሥፍራዎች የሚታየውን አሰልቺ ሠልፍ መመልከት በቂ ነው፡፡ ታክሲን ለሰዓታት መንገድ ላይ ቆሞ መጠበቅም ተለምዷል፡፡ በትራንስፖርት ምክንያት ከሥራ መግቢያ ሰዓትና ከትምህርት ማርፈድ እንዲሁም በተቀጣጠሩበት ሰዓት አለመገኘት የብዙዎች ችግር ሆኗል፡፡
እንደ አንበሳ ባስ፣ ሃይገር ባስ፣ ሸገር ባስና የመሳሰሉት በአንዴ በርካታ ተሳፋሪዎችን መያዝ የሚችሉና ከሰማያዊ ታክሲዎች ጎን ለጎን የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ቢሆንም፣ ካለው ችግር አንፃር እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ መፍጠር አልተቻለም፡፡ ባለው የትራንስፖርት ችግር የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያበቃ ለዓይን የሚከብዱ ታክሲዎች ሳይቀሩ የሚሰሩበት ሁኔታ አለ፡፡
አሰልቺ የሆነውን የታክሲ ጥበቃ ታግሶ ለማለፍ የማይችሉና አጣዳፊ ጉዳይ ያለባቸው አልያም አቅም ያላቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች፣ ላዳ ታክሲዎችን መኮናተር ይመርጣሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ ታክሲዎች የሚጠይቁት ዋጋ የሕዝቡን የመክፈል አቅም ያላገናዘበና የተጋነነ በመሆኑ እንደ አንድ አማራጭ ለመውሰድ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ እነሱም የሚታጡባቸው ጊዜያት አሉ፡፡
ያለውን ችግር በተወሰነ መጠን ለማቅለልም በቅርቡ ባሉት 7000 የላዳ ታክሲዎች ላይ 1163 ሜትር ታክሲዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ታክሲዎች በኪሎ ሜትር ታሪፍ ወጥቶላቸው የሚሠሩበት ዜና እንደተሰማም ለብዙዎች እፎይታ ሰጥቶ ነበር፡፡ ታሪፉ ከመውጣቱ አስቀድሞ መደበኛዎቹ ላዳ ታክሲዎች ከሚያስከፍሉት ዋጋ መጠነኛ ቅናሽ አድርገው ሲሠሩም ነበር፡፡
ዕድሉ የተሰጠው በአክሲዮን ለተደራጁ የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ነው፡፡ 513,000 ብር በላይ የነበረውን የአንድ መኪና ዋጋ ከቀረጥ ነፃ በ228,000 ብር እንዲገዙ በመደረጉ በወቅቱ የነበራቸው ደስታ ወደር አልነበረውም፡፡ ታሪፉ ባለፉት ሳምንታት እንደወጣ ግን ነገሮች እንዳልነበሩ ሆኑ፡፡ ማኅበራቱ አንድ ላይ በመሆን በኪሎ ሜትር አሥር ብር ተብሎ የወጣው ታሪፍ ልዩ ልዩ ወጪዎችን ከግምት ያላስገባ ነው ብለው አቤቱታ ለሚመለከተው አካል አስገቡ፡፡ ሥራ የማቆም አድማ ያደረጉም አሉ፡፡
አቶ ጥጋቡ (ስማቸው ተቀይሯል) ከቀረጥ ነፃ በተገኘው ዕድል ከተካተቱት መካከል ናቸው፡፡ የአክሲዮኑ ባለድርሻ ከመሆናቸው አስቀድሞ ላዳ ታክሲ ነበራቸው፡፡ ከዓመታት በፊት የገዙት በ65,000 ብር ነበር፡፡ በቀን እስከ 500 ብር ድረስ ይሠሩበት እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ በሚያገኙት ገንዘብም ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ማድረግ ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡
ከዓመት በፊት የነበራቸውን ታክሲ በአዲስ ለመቀየር ሲሉ ከቀረጥ ነፃ በተመቻቸው ዕድል ይመዘገባሉ፡፡ ‹‹ሊብሬ ኮፒ አድርጌ ሰጥቼ ነው የተመዘገብኩት›› የሚሉት አቶ ጥጋቡ፣ የመኪናውን 30 በመቶ ክፍያ ቀድመው እንዲፈጽሙ በተጠየቁት መሠረት የነበራቸውን ላዳ ታክሲ በ35,000 ብር ሸጠውና የቀረውን ተበድረው መክፈላቸውን፣ ከዓመት በኋላም ተሽከርካሪው በእጃቸው በመግባቱ ተደስተው እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ቀሪውን 70 በመቶ የገንዘብ ብድር የሰጣቸው ብርሃን ባንክ ሲሆን፣ ዕዳውን ከፍሎ ለመጨረስ የሦስት ዓመት የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በየወሩም 5,818 ብር ለባንኩ ዕዳ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ይህ ከሌሎች ልዩ ልዩ ወጪዎች ጋር ሲደመር በወሩ ከ7000 ብር በላይ ገቢ ማድረግ ግድ ይላቸዋል፡፡ ነገር ግን ‹‹የወጣው ታሪፍ ደግሞ ይህንን ያገናዘበ አይደለም፡፡ በቀን ሠርተን ከምናገኘው ዕዳውን ከፍሎ የሚቀር አይኖርም፤›› በማለት፣ ከዚህ ቀደም በተለመደው አሠራር መነሻ 50 ብር እንደነበር፣ ነገር ግን አሁን በወጣው ታሪፍ ውስጥ ይህ አለመካተቱን፣ በፊት ለአሥር ኪሎ ሜትር ጉዞ 250 ብር ድረስ ያስከፍሉ የነበረውን ወደ 100 ብር ዝቅ ማድረጉን፣ በቀን የሚያገኙት ዕዳቸውን ከፍሎ ለመተዳደሪያነት እንደማይበቃ ተናገረዋል፡፡
የትጋት አውቶሞቢል ታክሲ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሥራ አመራሩ አቶ ረታ ነግሬው እንደሚሉት፣ በእነሱ ማኅበር ስር 39 ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ፡፡ አባላቱም የነበራቸውን አሮጌ ታክሲዎች ሸጠው የአክሲዮኑ ባለቤት ሆነዋል፡፡ ‹‹የባንክ ብድር ለመክፈል ስንል በ120,000 ብር፣ በ110,000 ብር የገዛነውን ታክሲ በ40,000 ብር ሸጠናል፡፡ ተበድረንና የምንሸጠውን ሸጠን ነው የገዛነው›› ሲሉ ተደራራቢ ዕዳ እየከፈሉ ባሉበት ወቅት የወጣው ታሪፍ አነስተኛ መሆኑ ለኪሳራ እንደሚዳርጋቸው ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ያወጣው ታሪፍ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን ከግምት ያስገባ አይደለም፡፡ ታሪፉ ሲወጣ ታሳቢ ያደረገው ተሽከርካሪዎቹ በቀን 160 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ፣ ከብዛት ያተርፋሉ በሚል ቢሆንም፣ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ባለው የትራፊክ መጨናነቅ ቀኑን ሙሉ ይሠራሉ የሚባሉ ሚኒባሶች እንኳን፣ በቀን የሚጓዙት ከ90 ኪሎ ሜትር ያልበለጠ መሆኑን ጥናት አድርገን አውቀናል፡፡ የእኛ ደግሞ ከዚህ በታች ነው፡፡ በዚያ ላይ የጎማ፣ የቅባት፣ የተለያዩ አስተዳደራዊ ወጪዎች አሉብን፤›› በማለት ሁኔታውን ያብራራሉ፡፡
ከነዳጅ ዋጋ ጋር በተያያዘም አንድ ሊትር ነዳጅ በ16 ብር ከ61 ሳንቲም እንደሚቀዱ፣ መኪናው ደግሞ በሊትር ከአሥር ኪሎ ሜትር የበለጠ እንደማይጓዝ፣ የትራፊክ መጨናነቅ በሚፈጠርባቸው ጊዜያት መኪና ለማቆም እንደሚገደዱ፣ ተሽከርካሪ በቆመ ቁጥር ደግሞ የነዳጅ ፍጆታው ከፍ እንደሚል፣ ታሪፉ ግን እነዚህን ጉዳዮች ያላገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ማኅበራቸው በኪሎ ሜትር ለማስከፈል አስቦ የነበረው 21 ብር ከ46 ሳንቲም ነበር፡፡ ወደ ገበያው ከተገባ በኋላም ሁኔታውን እያዩ በኪሎ ሜትር እስከ 16 ብር ዝቅ አድርገው ለመሥራት አቅደው ነበር፡፡
‹‹እኛ ሕዝቡን ለመዝረፍ ብለን አይደለም፡፡ ብዙ ዕዳዎች አሉብን፡፡ የወጣው ታሪፍ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ እንኳንስ ዕዳ እየከፈልን የምንከፍለው ዕዳ ባይኖርብንም የሚያዋጣ አይደለም፤›› የሚሉት አቶ ረታ፣ የወጣው ታሪፍ ያከስረናል ብለው ያሰቡ ብዙዎች የአክሲዮን ድርሻቸውን ለመሸጥ የውልና ማስረጃ ጽሕፈት ቤቶችን እያጨናነቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የዛይራይድ መሥራች ከሆነው ሀብታሙ ታደሰ ለማወቅ የተቻለውም ይህንኑ ነው፡፡ ከድርጅቱ ጋር አብረው ከሚሠሩት 536 ታክሲዎች መካከል 300 የሚሆኑት ሰማያዊ በነጭ የተቀቡ ላዳ ታክሲዎች ሲሆኑ፣ የተቀሩት አዲሶቹ ሊፋን ታክሲዎች ናቸው፡፡ ከእነሱ መካከል አሥር ሰዎች የአክሲዮን ድርሻቸውን ሸጠዋል፡፡ ገዥ በማፈላለግ ላይ ያሉም አሉ፡፡
ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አያሌው ግርማ (ስማቸው ተቀይሯል)፣ የነበራቸውን ላዳ ታክሲ ሸጠው የአክሲዮን ድርሻ ከገዙት አንዱ ናቸው፡፡ በአዲሱ ሊፋን 530 መኪና በፊት ከሚያገኙት የተሻለ እንደሚሠሩ ጠብቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ሁኔታዎች ከጠበቁት በተቃራኒ መሆኑን ‹‹እጠቀምበታለሁ ብዬ የገዛሁት ነገር ጉዳት ሆነብኝ፡፡ የወጣው ታሪፍ በቂ ጥናት አልተደረገበትም፡፡ በዚህ ከምሠራ ሌላ ብሠራ ያዋጣኛል›› ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡ መኪናውን ለመሸጥ እየተደራደሩ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አያሌው፣ ከቻሉ አትርፈው ካልቻሉ ደግሞ በቅናሽ ሸጠው በሚያኙት በሌላ ሥራ ለመሰማራት መወሰናቸውን ይናገራሉ፡፡
ሌላው የአክሲዮን ድርሻቸውን ለመሸጥ በድርድር ላይ የሚገኙት የመኪና ዕቃ መለዋወጫ ነጋዴው አቶ ሲራጅ ተማም ናቸው፡፡ አቶ ሲራጅ የአክሲዮን ባለድርሻ የሆኑት ዕዳውን ለመክፈል ከተቸገረ ሰው በመግዛት ነው፡፡ ‹‹ልጁ መኪኖቹ እንደመጡ ነው የሸጠልኝ፡፡ በወቅቱ እሱ ዕዳውን መክፈል ስላልቻለ እኔ ደግሞ መኪናውን ስለወደድኩኝ ነበር የገዛሁት፡፡ ድርሻውን የሸጠልኝም 40,000 ብር አትርፎብኝ ነው፡፡ ሆኖም ደስተኛ ነበርኩኝ›› የሚሉት አቶ ሲራጅ፣ ሥራቸውን ትተው ከላዳው በሚያገኙት ለመተዳደር ወስነው እንደነበር፣ ነገር ግን በወጣው ታሪፍ ማትረፉ የሚቻል መስሎ ስላልታያቸው ሐሳባቸውን ለውጠው ገዥ እያፈላለጉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የሚገዛ ከተገኘ ድርሻቸውን እስከ 22,000 ብር እንደሚሸጡ ካልተገኘም ‹‹ከዚያ በታች ቢሸጥም ምንም አይደለም›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ሲራጅና አቶ አያሌው ድርሻቸውን ለመሸጥ ድርድር ያልጀመሩትም ቢሆኑ፣ ታሪፉ ካልተስተካከለ ኪሳራቸው እንደሚበዛና ዕዳቸውን ለመክፈል እንደሚቸገሩ በመግለጽ ‹‹መኪኖቹን ለባንክ ማስረከብ ነው፡፡ ሌላ አማራጭ የለንም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የታሪፉ ነገር የመጨረሻ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የራሳቸውን ታሪፍ አውጥተው በመሥራት ላይ የሚገኙ ማኅበራትም አሉ፡፡ ከዛይራይድ ጋር አብረው የሚሠሩት 536 ታክሲዎች በኪሎ ሜትር 12 ብር መነሻውን ደግሞ 20 ብር በማድረግ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ታክሲው በደንበኛው ፍላጎት እንዲቆም ሲደረግም፣ በደቂቃ 20 ሳንቲም ይቆጥራል፡፡ ‹‹ይህንን ያደረግነው በጥናት ተመስርተን ነው›› የሚለው ሀብታሙ፣ ታሪፉ በቀን ከሚገኘው ገቢ 20 በመቶ የሚሆነው ለነዳጅ የሚውልበትን ሁኔታ አገናዝቦ፣ እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ወጪዎችን ታሳቢ አድርጎ መውጣቱን ይናገራሉ፡፡
ሌሎች በኪሎ ሜትር ከ24 እስከ 26 ብር የሚያስከፍሉ ሜትር ታክሲዎች መኖራቸውን፣ ነገር ግን እነሱ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያላገናዘቡ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በኪሎ ሜትር አሥር ብር ተብሎ የወጣውን ታሪፍ በተመለከተ ‹‹እንደተባለው አክሳሪ አይደለም፡፡ አዋጭ ነው ማለትም አይቻልም›› ብሏል፡፡
ለዚህም ታሪፉ ሲወጣ በከተማው ውስጥ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ከግምት ሳያስገባ በቀን 160 ኪሎ ሜትር እንደሚሄዱ መታሰቡ፣ የመነሻ ዋጋ አለመካተቱ፣ እንዲሁም ተሽከርካሪዎቹ በቀን ከሚያገኙት ገንዘብ ላይ 250 ብር ለባንክ ዕዳ እንደሚከፍሉ፣ 20 በመቶ ለነዳጅ እንደሚውል ከግምት አልገባም በሚል ነው፡፡
በተጨማሪም ‹‹አንድን ተሳፋሪ የሚፈልገው ቦታ ካደረሱ በኋላ ወደነበሩበት ለመመለስ መታጠፊያ መንገድ እስኪያገኙ ቢያንስ አንድ ኪሎ ሜትር ይጓዛል፡፡ በታሪፉ መሠረት ደንበኛው የሚከፍለው እስከወረደበት ርቀት ላለው ብቻ ነው፡፡ ይህም ተጨማሪ ነዳጅ በነፃ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው›› ይላል፡፡
‹‹እኛ መንግሥት በሚያወጣው ታሪፍ ላይ ችግር የለብንም እንሠራለን›› የሚለው ሀብታሙ፣ አያዋጣንም ብለው የሚከራከሩት አብዛኛዎቹም ስለ ገባያው ሁኔታ በግልጽ የተረዱ አለመሆናቸውን ይናገራል፡፡ በኪሎ ሜትር የሚከፈለው ዋጋ በቀነሰ መጠን ተፈላጊነታቸው ይጨምራል፡፡ ከብዛትም ያተርፋሉ ብሏል፡፡ ከእነሱ ጋር ዋጋ ቀንሰው በመሥራት ላይ የሚገኙትም በተመሳሳይ አማካይ የቀን ገቢያቸው 1,200 ብር ደርሷል፡፡
በትክክል እየሠሩበት ያለው ሒሳብ ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ሳያገናዝቡ ታሪፉ አክሳሪ እንደሆነ የሚናገሩም ያጋጥማሉ፡፡ በዚህ ረገድ ሀብታሙ በቅርቡ የገጠመውን እንዲህ ያስታውሳል፡፡
ቦሌ ጫፍ ያገኘውን ላዳ ታክሲ በ80 ብር ሳሪስ እንዲያደርሰው ተደራድረው መንገድ ጀመሩ፡፡ ከዚያም አዲስ ስለወጣው የታክሲ ታሪፍ ማውራት ጀመሩ፡፡ ሾፌሩም ታሪፉ አክሳሪ እንደሆነ እያማረረ ተናገረ፡፡ ሁኔታው የገረመው ሀብታሙም ‹‹አሁን እኔን በኪሎ ሜትር ምን ያህል ያስከፈልከኝ መሰለህ›› ሲል ጠየቀው፡፡ ሾፌሩም ‹‹18 ብር አካባቢ›› ብሎ መለሰለት፡፡ ነገር ግን ሂሳቡን ተሳስቶ ነበረና ሀብታሙ ትክክለኛውን አስልቶ በኪሎ ሜትር በ9 ብር እየወሰደው እንደሆነ አስረዳው፡፡
የወጣው ታሪፍ ፍትሃዊ አይደለም በሚል ማስተካያ እንዲደረግበት የቀረበው አቤቱታ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሃሙስ ኅዳር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሽ አልተሰጠዉም፡፡ ነገር ግን ሪፖርተር ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም ጋር ባደረገው ቆይታ፣ ‹‹ለሜትር ታክሲዎች የተመደበላቸው ታሪፍ ሲበዛ ነው›› በማለት የወጣው ታሪፍ አንሷል ሲሉ ያነሱት መከራከሪያ ተቀባይነት እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡
ተሽከርካሪዎቹ ሲገቡ መንግሥት 165 በመቶ የሚሆነውን የመኪኖቹን ዋጋ ትቷል፡፡ ይህንንም ያደረገው በፊት በድርድር ሲሠራበት የነበረውን ሕዝቡን ለብዝበዛ ሲያጋልጥ የነበረውን አሠራር በአዲስ ለመቀየር ታስቦ ነው፡፡ በኪሎ ሜትር ታሪፍ ወጥቶለት የሚሠራበት አሠራር በሌሎችም አገሮች የሚሠራበት ነውም ብለዋል፡፡
‹‹አገልግሎቱ አዲስ ስለሆነ በተቻለ መጠን እንዲበረታቱ ስለፈለግን ብዙ ነገሮችን ትተናል፡፡ ለምሳሌ መኪና ማሳጠብ አለብን ተብሎ መኪና ማሳጠቢያ አሥራ አንድ ሺሕ ብር ይያዝልን ብለው አድርገናል፡፡ ለመኪና ማሳደሪያ ስድስት ሺሕ ብርም ወጪ ይያዝልን ተብሎ እሺ አልን፡፡ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ሁሉ ይዘን ነው ታሪፍ ያወጣነው፤›› ብለዋል፡፡
የወጣው ታሪፍም በሚኒባስ አራት ብር ከ50 ሳንቲም የሚከፈልበትን ከ100 እስከ 120 ብር እንዲያገኙበት ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን፣ ይህ ሕዝቡ ካለው የመክፈል አቅም ጋር ሲተያይ እንኳን ሊጨመርበት ውድ መሆኑን፣ አንዳንዶች የሚከራከሩት ዋጋው አንሷቸው ሳይሆን የአመለካከት ችርግ ኖሮባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አንዳንዶች በኪሎ ሜትር የሚከፈለውን ታሪፍ የመወሰን ሥልጣን ያላቸው አክሲዮን ማኅበራቱ ናቸው፡፡ መንግሥትን አይመለከትም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ የወጣው ታሪፍ ሚዛናዊ መሆኑን፣ መንግሥት ጣልቃ ባይገባበት ኖሮ ዳግመኛ ሕዝቡ ከፍተኛ ለሆነ ብዝበዛ ይጋለጥ እንደነበር አስተያየት ይሰጣሉ፡፡
ከሰሞኑ ‹‹የውበት እስረኞች›› የሚል ቅፅል የተሰጣቸው እነዚህ አዳዲስ ታክሲዎች ወደ ገበያ በመግባታቸው በኮንትራት ታክሲ ዋጋ ላይ መጠነኛ የሆነ መረጋጋት እንዲታይ አድርገዋል፡፡ የክፍያው ሁኔታ በሰው አሥር ብር እንዲሆን የጠየቁ እየሠሩበት ያሉም አሉ፡፡
አዳዲሶቹ ታክሲዎች በመስቀል አደባባይ