Wednesday, October 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማግሥት ለሚመጣው ሁሉ መዘጋጀት ብልኅነት ነው!

የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ አወዛጋቢው ዶናልድ ጆን ትራምፕ የአሜሪካ 45ኛው ተመራጭ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ የእሳቸው አሸናፊነት ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ በዋና ዋና የአሜሪካ ከተሞች በሁከት የታጀቡ ተቃውሞዎች ተቀስቅሰዋል፡፡ የትራምፕ መመረጥ አሜሪካን ሁለት ቦታ ከፍሎ ዓለምን ግራ ባጋባበት በዚህ ወቅት፣ ከአሜሪካ ጋር እ.ኤ.አ. ከ1903 ጀምሮ ግንኙነት ያላት ኢትዮጵያም የሚያሳስቧት ጉዳዮች ይኖሩዋታል፡፡ ለ113 ዓመታት የዘለቀው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በትራምፕ ፕሬዚዳንትነት ዘመን ሳንካ ሊያጋጥመው ይችላል ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ አወዛጋቢው ትራምፕ በንግድ ግንኙነቶች፣ በወታደራዊ ትብብሮች፣ ከአገሮች ጋር በሚኖሯቸው ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችና በመሳሰሉት በውጭ ፖሊሲያቸው ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ስምምነቶችንም ሊሽሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የተቃኘ ዝግጅት ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ ብልኅነት ነው፡፡

በአሜሪካዊ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማግሥት ኢትዮጵያን የሚያሳስቧት ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የመጀመሪያው አሜሪካ ለኢትዮጵያ ጠቀም ያለ ሰብዓዊ ዕርዳታ በመስጠት ግንባር ቀደም ናት፡፡ የልማት ዕርዳታም በመስጠት ትታወቃለች፡፡ አሜሪካ ለአፍሪካ በሰጠችው የታሪፍና የኮታ ነፃ ዕድል ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ናት፡፡ በፓወር አፍሪካ ኢኒሼቲቭ አማካይነት ለመደገፍ ከታሰበው የታዳሽ ኃይል ምንጭ ልማት ፈንድ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ፣ በቀዳሚነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተመረጡ አምስት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ከአሜሪካ ጋር በንግድ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በባህልና በፀረ ሽብርተኝነት ትግል ትልቅ ግንኙነት ያላት ኢትዮጵያ፣ በአወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ ዘመን ያልተጠበቀ ክስተት ሊያጋጥማት ይችላል፡፡ ዘመን ተሻጋሪው የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ግንኙነት ላይ ሳንካ ሊያጋጥም ይችላል በሚል እሳቤ ለዚህም መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በመጪዎቹ 100 ቀናት ውስጥ ቅድሚያ በሚሰጧቸው ዋና ዋና የውስጥና የውጭ ጉዳዮች ላይ ከመጠመዳቸው በተጨማሪ፣ መጪዎቹን አራት ዓመታት ከተለመደው የአሜሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ባህል ወጣ ብለው የሚያተራምሷቸው በርካታ ጉዳዮች ይኖሩዋቸዋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ‹‹የአሜሪካን ታላቅነት ለማስመለስ›› በሚለው ዘመቻቸው የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ያደረጉዋቸውን ስምምነቶችና ዘመናት የተሻገሩ ትብብሮችን ‹‹ለአሜሪካዊያን ጥቅም›› ሲሉ እንደሚሰርዙዋቸው ወይም ዋጋ አልባ እንደሚያደርጓቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጊዜ ያለፈበት ነው ሲሉ ማጣጣላቸው፣ በአውሮፓም ሆነ በተለያዩ አኅጉሮች ያሉ የአሜሪካ ሸሪኮችን አስደንግጧል፡፡ አሜሪካ ከዓለም አቀፍ የፀጥታና የደኅንነት ሚናዋ የሚገታትን ዕርምጃ ሊወስዱም ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለ፡፡ እሳቸው ቅድሚያ ለአሜሪካ ጥቅም ሰጥተው ሲንቀሳቀሱ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ጤናማ ይባሉ የነበሩ ግንኙነቶችን አጣጥለዋል፡፡ በተለይ ለአፍሪካና ለሌሎች ታዳጊ አገሮች የሚደረጉ ድጋፎችን የሙስና ምንጭ ሲሉም አውግዘዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ቢያንስ የመጪዎቹ አራት ዓመታት የአሜሪካ ሁኔታ አያስተማምንም ማለት ነው፡፡ መፍትሔው በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ የተቃኘ ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡

የነጮች የበላይነትን የማስፈን ዓላማ አላቸው ተብለው የሚታሙት ትራምፕ ገና ከአሁኑ ከአውሮፓ የቀኝ ክንፍ አክራሪ ፓርቲ መሪዎች ሙገሳ እየተዜመላቸው ነው፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ ፖሊሲያቸው ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ የተባሉት ትራምፕ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘብ ቢሉም ለታዳጊው ዓለም ያላቸው አመለካከት ጥሩ አይደለም፡፡ የአሜሪካን ጥቅም የሚያስከብሩት በትክክለኛ ወዳጅነትና በፍትሐዊነት ነው ቢሉም፣ ከታዳጊው ዓለም ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በጣም ቀዝቃዛ እንደሚሆን ሥጋት አለ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ ግንኙነት መሥርተው አብረው ቢዘልቁም፣ ድሮም ቢሆን አመርቂ ያልነበረው የልማት ድጋፍ ጭራሽ ሊዳፈን ይችላል፡፡ ካልሆነም ሌላ ገጽታ ይዞ ይመጣ ይሆናል፡፡ ከትብብር ይልቅ አስገዳጅነት፣ ከወዳጅነት ይልቅ ጠላትነት የመሳሰሉት ሁሉ ይታሰባሉ፡፡ ለሚመጣው ሁሉ መዘጋጀት ብልኅነት ነው፡፡

ከመንግሥታት ግንኙነት በተጨማሪ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይም የተደቀነ ሥጋት አለ፡፡ የዶናልድ ትራምፕ አደገኛ ዕርምጃዎች ከሚባሉት አንዱ በኢሚግሬሽን ፖሊሲው ላይ የሚያሳርፉት ምት ነው፡፡ በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ የተለያዩ አገሮች ዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለው ከአገር የማስወጣት ዘመቻ ትልቁ ራስ ምታት ነው፡፡ ከእነዚህ ሰነድ አልባ ባይተዋሮች መካከል ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይም በጣም ያሳስባል፡፡ እነዚህ ለዓመታት የነዋሪነት ወይም የዜግነት ሰነድ የሌላቸው ወገኖች ላይ ሊወሰድ ይችላል የተባለው ዕርምጃ ተግባራዊ ሲሆን፣ እንደ አገር ከፍተኛ ጫና ያስከትላል፡፡ በአገር ውስጥ ባሉ ዘመዶቻቸው ላይ ደግሞ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ይፈጥራል፡፡ እነዚህ ከአሜሪካ ሊፈናቀሉ ይችላሉ በሚባሉ ወገኖች ላይም ይህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ይህ የዶናልድ ትራምፕ ዕርምጃ የማይገታ ከሆነ እንደ አገርም እንደ ሕዝብም የተለየ ዝግጅት ማድረግ የግድ ይሆናል፡፡

ለአሜሪካ ፖለቲካ እንግዳ የሆኑት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ መላውን ዓለም የሚያሳስቡ ዕቅዶችን ይዘው ባልታሰበ ሁኔታ ሲመረጡ፣ በእሳቸው መመረጥ ያልተደሰቱ አሜሪካዊያን ደግሞ በበርካታ ከተሞች ተከታታይ ተቃውሞዎች አድርገዋል፡፡ ለአሜሪካ የምርጫ ፖለቲካ እንደ አዲስ የታየው ክስተት አገሪቷን እየናጠ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የአስፈሪ ፖሊሲዎቻቸው ትሩፋቶች ደግሞ በተለይ አፍሪካን ሊጎዱ የሚችሉ እንደሚሆኑ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ሰውየው ከተለመደው የአሜሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ባህል አፈንግጠው የሚፈጥሩት ትርምስ የማይሽር ጠባሳ ሊፈጥር ይችላል፡፡ አሜሪካኖች የሚፈልጉን ለጥቅማቸው አስፈላጊ እስከሆንን ድረስ መሆኑ የታወቀ ሀቅ ቢሆንም፣ በአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዘመን የአስፈላጊነት ደረጃው መለኪያ ምን እንደሆነ ለጊዜው ላይታወቅ ይችላል፡፡ እሳቸው በሥልጣን ዘመናቸው ለአገራቸው ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡት ከተለመደው መንገድ ወጣ ያለ ከሆነ፣ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት እንደ ተራ ነገር ቢቆጠር ሊገርም አይገባም፡፡ ይልቁንም የሚበጀው በዚህ መንፈስ የተቃኘ ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማግሥት ለሚመጣው ሁሉ መዘጋጀት ብልኅነት ነው የሚባለው!

    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...

የመከፋት ስሜት!

ከቤላ ወደ ጊዮርጊስ ልንጓዝ ነው፡፡ መውሊድና መስቀልን በተከታታይ ቀናት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግጭቶች በሙሉ ሁሉን አሳታፊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተገቶ የተስፋ ጭላንጭል መታየት ሲጀምር፣ በአማራ ክልል ሌላ ዙር ዕልቂትና ውድመት ሊያደርስ የሚችል ግጭት መነሳቱ ብዙዎችን ያሳስባቸዋል፡፡ በአማራ...

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...