Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹በኢትዮጵያ ንግድ አካባቢ ያለው ሁኔታ አስፈሪ ነው ብዬ አስባለሁ››

  አቶ ክቡር ገና፣ የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተርና የኢኒሼቲቭ አፍሪካ መሥራች

  አቶ ክቡር ገና በኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቅ ስም ካላቸውና በብዙ ምክንያቶች ጎልተው ከሚጠቀሱ ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውስጥ የነበራቸው አስተዋጽኦ፣ ምክር ቤቱ ከንግድ ነክ ጉዳዮች ባሻገር በማኅበራዊና ፖለቲካዊ አገር ጉዳዮች ውስጥ ሳይቀር ንቁ ሆኖ እንዲሳተፍ ማስቻላቸው ከሚነገርላቸው መካከል አቶ ክቡር ሰፊ ቦታ አላቸው፡፡ ምክር ቤቱ በሁለት አገር አቀፍ ምርጫዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ፣ መራጮች ድምፅ እንዲሰጡና የምርጫ ክርክሮች እንዲካሄዱ በማድረግ በኩል በእሳቸው ይመራ የነበረው ንግድ ምክር ቤት አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ እንዲህ ያሉ የንግድ ማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መብቶች የሚያስጠብቁ እንቅስቃሴዎች ግን ቀስ በቀስ እየተዳከሙ መጥተዋል፡፡ ይልቁንም ንግድ ምክር ቤቶቹ እርስ በርሳቸው የሚጋጩበትና የተካረረ ጭቅጭቅ ውስጥ የገቡበት፣ አመራሮች ያለገደብ ሥልጣን ላይ የሚቆዩበት መድረክ እየተፈጠረ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡ አቶ ክቡር እንደሚሉት በአገራዊና በአኅጉራዊ የኢኮኖሚና የንግድ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ እርስ በርስ መናቆር፣ የበላይና የበታች ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ የሚደረጉ ፍትጊያዎች ሰፊውን ቦታ ይዘዋል፡፡ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታም የወደፊቱ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ዕጣ ፈንታ አስፈሪ እንደሆነ ሲገልጹም፣ መንግሥት በንግድ ምክር ቤቶች ላይ ማድረግ የሚገባውን ተሳትፎ አለማድረጉ፣ ጥቅሙ ለራሱም ሆኖ ሳለ ምክር ቤቶቹም ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ ኢንቨስት ሊያደርግባቸው ሲገባ አለማድረጉ የወደፊቱ የአገሪቱ ንግድ ምክር ቤቶች ጉዞ አስፈሪ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ አቶ ክቡር ኢኒሼቲቭ አፍሪካ የተባለውን ተቋም በመመሥረት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዕድገት ቦታ እንዲሰጠውና በመልካም አስተዳደርና በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ዙሪያ ሲንቀሳቀሱ በርካታ ዓመታት አሳልፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአኅጉራዊው የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት በበጎ ፈቃደኝነት በዋና ዳይሬክተርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ ንግድ ምክር ቤቶች ወቅታዊ ጉዳይ፣ በአፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ተቋም ላይ በማተኮር አቶ ክቡር ገና ከብርሃኑ ፈቃደ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንዲህ ተሰናድቷል፡፡

  ሪፖርተር፡- የግሉ ዘርፍ በአገር ውስጥ ያለው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሚና እንዴት ይገለጻል? እንዴትስ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል?

  አቶ ክቡር ገና፡- እንግዲህ በአገር ደረጃ ስንወስደው፣ በአንድ አገር ዕድገትም ሆነ በአንድ አገር የኅብረተሰብ መቻቻልና መኗኗር ውስጥ ሚና ያላቸው የተለያዩ ክፍሎች አሉ፡፡ መንግሥት ከፍተኛ ሚና ቢኖረውም የተለያየ ሚና ያላቸው የኅብረተሰብ አካላት በተለያዩ ጉዳዮች ይሰባሰባሉ፡፡ አንዳንዱ በቤሰተብና በዕድር ይሰባሰባል፣ አንዳንዱም በአካባቢ ጉዳይ ይሰባሰባል፡፡ አንዳንዱም በንግድ ይሰባሰባል፡፡ በሙያውም የሚሰባሰብ ይኖራል፡፡ እነዚህ በሙሉ የአባሎቻቸውን ጥቅም የማስጠበቅና ከአባሎቻቸውና ከኅብረሰተቡ ጋር ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ለማቀራረብ የሚጥሩ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ እንግዲህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተብለው የሚጠሩት በብዙ ይከፋፈላሉ፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡ በሌላ በኩል እንደ አንድ ክፍል ይታያል፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡም በራሱ ይደራጃል፡፡ አንዳንዱ በንግድ ምክር ቤት አማካይነት ይደረጃል፡፡ ሌላውም በተለያዩ ማኅበራት ይደራጃል፡፡ በዘርፍም ይደራጃል፡፡ እነዚህ ሁሉ አካላት ተሰባብስበው የሚያንቀሳቅሱት ሐሳብና የሚያንሸራሽሩት ውይይት ነው ኅብረተሰቡን ካለበት ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ የሚወስደው፡፡

  ሪፖርተር፡- ይህንን ካነሳን የንግድ ኅብረተሰቡ በጥቅሉ የግሉ ዘርፍ ከሌሎች የሲቪክ ማኅበረሰብ እንቅስቃሴዎች አኳያ የፖለቲካና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በምን መልኩ የተለዩ ናቸው? መገለጫቸውስ ምንድነው?

  አቶ ክቡር ገና፡- የተለየ መገለጫ ያለው አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን የንግድ ኅብረተሰቡ ከሌላው የኅብረሰተብ ክፍሎች ትንሽ ለየት የሚለው በምንድነው ካልን የራሱን ገንዘብ አውጥቶ ለሥራ ማዋሉ ነው፡፡ ሌሎቹ በአብዛኛው ከሌላ የሚመጣውን ገንዘብ የሚያስተዳድሩ ናቸው፡፡ መንግሥት ከሕዝቡ በታክስና በመሳሰሉት መንገዶች የሚሰበስበው፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች፣ ከመንግሥትና ከሌሎች ገንዘብ የሚሰበስቡ ሲሆን፣ የንግድ ኅብረተሰቡ ግን በአብዛኛው ከራሱ ተነስቶ የራሱን ገንዘብ ለማሳደግ ነው ጥረቱ፡፡ ካልሆነለትም ለኪሳራም ሊዳረግ ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነ በቀር ልዩነቱ ብዙም የተለየ እንቅስቃሴ የለውም፡፡

  ሪፖርተር፡- የንግድ ኅብረተሰቡ ተደራጅቶ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አለ፡፡ ይህ እንቅስቃሴው ከዚህች አገር ሁኔታ አኳያ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

  አቶ ክቡር ገና፡- የብዙ አገር ተለምዶ ምንድነው ብለን ካየን ከፖለቲካው ጋር መቀራረብ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሐሳብ ልዩነት እንኳ ቢኖር የንግድ ኅብረተሰቡ ግን ከመንግሥት ውጪ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ከመንግሥት ጋር እንኪያ ሰላንቲያ ውስጥ መግባትም አያዋጣውም፡፡ ነገር ግን በራሱ የንግድ ሥራውን ሊያስፋፋ የሚችል ሐሳብ ቢኖረውና ያ ሐሳብም ከመንግሥት ጋር የሚቃረን ሆኖ ከተገኘ፣ እስከ መጨረሻው ድረስ በመከራከር ፖሊሲ እንዲለወጥ የማድረግ ትግል እንበለው ወይም ኃላፊነት አለበት ተብሎ ይታሰባል፡፡ ወደ እኛ አገር ስንመጣ በተለያዩ መንገዶች አሁን የምናያቸው ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር ያለው የፖሊሲ ለውጥ ጥያቄ በምን መልኩ መስተካከል አለበት የሚል ጉዳይ ላይ ሐሳብ ሲንሸራሸር አናይም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በተወሰነ ደረጃ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ስብሰባዎች ሲደረጉ እናያለን፡፡ ነገር ግን የንግድ ኅብረተሰቡን የሚያሰባስቡ ድርጅቶች አቅማቸው በጣም ውሱን ከመሆኑ የተነሳ፣ የንግድ ኅብረተሰቡን ለመርዳትና ለማሳደግ የሚችል የሰው ኃይል የላቸውም፡፡

  ሪፖርተር፡- በአንፃራዊነት በዚህ አገር የሚንቀሳቀሱ የንግድ ማኅበረሰቡን የሚወክሉ ማኅበራት ረዘም ያለ ቆይታ አላቸው፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ እንደመሆናቸው የሚጠበቅባቸውንና የሚያስቡትን ያህል አሳክተዋል ማለት ይቻላል? አሊያም በዚያን ዘመን የነበረው የንግድ ማኅበረሰብ አሁን ካለው ይልቅ በእነዚህ ተቋማት ተጠቃሚ ነበር ልንል እንችላለን?

  አቶ ክቡር ገና፡- ለውጥ አምጥተዋል፣ የንግድ ኅብረተሰቡን ተረድተዋል፣ አሳድገዋል ለማለት እኮ  ያላቸው አባል ቁጥር ያሳያል፡፡ የማኅበራቱ አባላት ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ ብዙም ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው ስለማይታሰቡም ሊሆን ይችላል፡፡ አሊያም ደግሞ አባላትን ለመሳብ የሚደረገው ጥረትና ከገቡ በኋላ ደግሞ የእነሱን ችግር ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ አጥጋቢ ሆኖ ስላልታየ ነው፡፡ ይህንን ለማየት በአዲስ አበባ ከተማ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራውን አይቶ ስንቱ ነው በምክር ቤትም ሆነ በተለያዩ ዘርፍ ማኅበራት በኩል አባል የሆነው? ገንዘቡን አዋጥቶ በእነዚህ ድርጅቶች ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሥራና ሐሳብ የሚጠብቀው ስንቱ ነው ሲባል በጣም አነሳ ቁጥር ነው፡፡ ስለዚህ ለጥያቄው የሚያረካ ሆኖ የተገኘ አይመስለኝም፡፡

  ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አመራር ነበሩ፡፡ በወቅቱ ንግድ ምክር ቤቱ ንቁ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉት ውስጥ የሚጠቀስ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ በዚህ አባባል ይስማማሉ? ይህ የሚያስማማ ከሆነም እርስዎ በነበሩ ጊዜ የነበረውን እንቅስቃሴ እንዴት ይገልጹታል?

  አቶ ክቡር ገና፡- እኔ የማየው እንዴት መሰለህ? እኔ ብቻ ሳልሆን እመራው የነበረው ቦርድ ከዛሬ 20 ዓመት በላይ ማለት ነው ሥራ ሲጀምር፣ ከደርግ መንግሥት ወደ ኢሕአዴግ መንግሥት ሥርዓት የተገባበት ወቅት ስለነበር አብዛኛው ነገር ታች ወርዶ ነበር፡፡ ምንም ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ከምንም ነገር ተነስተህ ትንሽ ቀና ስትል የብዙዎችን ዕይታ ትስባለህ፡፡ በዚያ መንገድ ነው የማየው፡፡ ትልቅ ነገር ሠርተናል ለማለት ሳይሆን በወቅቱ ታች ከነበረው ንግድ ምክር ቤት አኳያ ትንሽ እንዲነቃ አድርገነው ካልሆነ በቀር፣ ያን ያህል የሚወራለት ሥራ ሠርተናል ማለት አልችልም፡፡

  ሪፖርተር፡- ሌላው ቢቀር ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ሁለት የፖለቲካ ምርጫዎች ላይ ንግድ ምክር ቤት ንቁ ተሳትፎ ነበረው፡፡ ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥ፣ ክርክሮችና ውይይቶች እንዲኖሩና እንዲስፋፉ የተደረገበት ጊዜ ይታወሳል፡፡ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች በምክር ቤቱ እንዲካሄዱ ያስቻለው ምክንያት ምን ነበር?

  አቶ ክቡር ገና፡- ንግድ ምክር ቤትንም ሆነ ሌላውን የዘርፍ ማኅበር ስናይ የሚጠበቅበትን ጥቅም መንግሥት ማየት ይፈልጋል፡፡ በወቅቱ ‹‹ምረጥ አዲስ›› የሚል የምርጫ ቅስቀሳ ተጀምሮ ነበር፡፡ ይህ ወገንተኛ አልነበረም፡፡ የዴሞክራሲ መጀመሪያ አካባቢ ስለነበርም የመምረጥና የመመረጥ ትምህርት ለማስተማር የተደረገ ነበር እንጂ፣ የታወቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚያደርጉት አደንኛው ንግድን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የፖሊሲ ሐሳቦችን አስቀምጦና ታይቶለት፣ ሌላኛው በወዲህ በኩል ንግድን ሳይሆን ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት አስቦ በመሀሉ የትኛው ያስፈልገናል ተብሎ ውይይት የተካሄደበት አልነበረም፡፡ በመሠረቱ የሲቪክ ትምህርት ነበር ማለት እንችላለን፡፡ እንግዲህ ከዚያ ነው ወደ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት የሚጀመረው፡፡ ያ ባህል ቢስፋፋ ኑሮ አሁን ያልኩት ደረጃ ለመድረስ ይቻል ነበር፡፡ ጥቅሜን የሚያስጠብቅልኝ ይህ መንግሥት እስከሆነ ድረስ ይህንን መንግሥት እደግፋለሁ፣ እንዲቆይ አደርጋለሁ የሚለው በአንድ በኩል ይሆናል፡፡ የለም ጥቅሜን የሚያስጠብቅ ሆኖ አላገኘሁትም የሚመጣው መንግሥት ይዞ የመጣው ሐሳብና አስተያየት እንዲሁም ፖሊሲ እኔን የሚያረካኝ ስለሆነ ይኼኛው ይሻለኛል ብሎ ለማለት የሚችልበት መንገድ ነው፡፡ ሠለጠኑ በምንላቸው አገሮች እንዲህ ያለው ነገር ይካሄዳል፡፡ እኔ ሁልጊዜም የምለው ምንድነው ለፖለቲካም ይሁን ለሌላው ለውጥ የአሥር ዓመት ጊዜ በጣም ትንሽ ነው፡፡ በመቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው ሒደቱ የሚታየው፡፡ ተጀምሮ ስኬታማ ስላልሆነ መተው የለበትም፣ መቀጠል አለበት፡፡

  ሪፖርተር፡- እርስዎ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ አሁንም ባለው ሁኔታ በአንፃራዊነት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ከሌሎች አቻዎቹ ይልቁንም ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሳይቀር የተሻለ ተሳትፎና እንቅስቃሴ ያደርጋል እየተባለ ይነገርለታል፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ የታየባቸው መድረኮች እንደነበሩትም ይጠቅስለታል፡፡ ይህ ምክር ቤት ከሌሎቹ በተለየ ለመንቀሳቀስ ምን የለተየ ዕድል ስላለው ነው እንዲህ የተንቀሳቀሰው?

  አቶ ክቡር ገና፡- ሁለት ነገሮችን መለየት አለብን፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በማተኮር መሥራት አለበት፡፡ የአዲስ አበባውም በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ እንጂ ከዚያ ውጪ እየወጣ እንዲሠራ አይጠበቅም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የኃላፊነት ግልጽነት በመጥፋቱ አንዱ የአንዱን ሥራ ወሰድክብኝ የሚል ግጭት በመካከላቸው አለ፡፡ ሥራው ጠፍቶ ሳይሆን የኃላፊዎቹ ችግር ነው ይህንን የሚያመጣው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ትልቁ ድክመት በእኔ አስተያየት የንግድ ምክር ቤቶች ወይም ማኅበራት ለመንግሥት ሀብት መሆናቸው አለመታየቱ ነው፡፡ ምክንያቱም የእነሱ መጠናከር ለመንግሥት የሚቀርቡ የፖሊሲ ሐሳቦችና አቅጣጫዎች የጠነከሩ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ አጀማመሩ ደካማ ከሆኑ እነሱን ለማጠናከር መንግሥትም ኃላፊነት አለበት፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለበት፡፡ ወደ ፖለቲካውና ወደ ራሱ አቅጣጫ እንዲስባቸው ሳይሆን፣ ዓላማቸውን ፈልጎና አምኖባቸው በቻርተር ስላቋቋማቸው ሥራቸውን በትክክል እንዲሠሩ መንገዱን ማመቻቸት አለበት፡፡ ይህንን መንግሥት አላደረገውም፡፡ እዚህ ብቻም ሳይሆን በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥም ስናይ ይህ አልተደረገም፡፡ የሚታሰበው ምንድነው ራሱ በራሱ ተነቃንቆ እንዲሻሻል ነው፡፡ ሲጀምር ደካማ ከሆነ ግን ይህንን ለውጦ ወደ ላይ ለመሄድ ብዙ ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ ላይደርስበትም ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያትም ነጋዴውንም፣ መንግሥትንና ሕዝቡንም ላይረዳ ይችላል፡፡ 

  ሪፖርተር፡- የንግድ ምክር ቤቶች የግሉ ዘርፍ ጥቅም እንዲከበር ወይም በአገር ውስጥ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ የሚጫወቱት ሚና ምንድነው? ምን እንዲያደርጉስ ይጠበቅባቸው ነበር ብለው ያምናሉ?

  አቶ ክቡር ገና፡- በመሠረቱ የአዲስ አበባንና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ስንወስድ፣ ዛሬ በንግድ ጉዳዮች ላይ የሚነጋገሩ፣ ሐሳብ የሚሰጡና የሚፋጩ ነጋዴዎች ናቸው አባላቱ? ወይስ በንግድ ዓለም ውስጥ ምንም ዓይነት የሚረባ ሚና የማይጫወቱ ናቸው? ብለን ስናይ በአብዛኛው በዚህ ውስጥ የሚገኙ ሆነው ይታያሉ፡፡ ምክር ቤት አካባቢ ያሉና ምክር ቤቱን የሚመሩ ሰዎች የትልልቅ ኢንዱስትሪ ኃላፊዎች፣ ባለቤቶች፣ ገንዘብ አንቀሳቃሾች አይደሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ በሌሉበት ቦታ ላይ ስለእነሱ ሆኖ መናገር ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ይህ መለወጥ አለበት፡፡ መንግሥትም የንግድ ምክር ቤቶችን ማዳመጥ ይኖርበታል፡፡ የዶሮዋና የእንቁላሉ ነገር ይሆናል፡፡ ለመደመጥ ደግሞ ምክር ቤቶቹ ጠንክረው መውጣት አለባቸው፡፡ የእኛ ንግድ ምክር ቤቶች በአብዛኛው ዓውደ ርዕይ ማዘጋጀት፣ ዳይሬክተሪ ማውጣት ላይ የተጠመዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥሩ አይደሉም እያልኩ ሳይሆን ከዚህ የባሱ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እየተለወጠ ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ እርስ በርሱ እየተቀራረበ፣ አገሮችም ድንበሮቻቸውን እያነሱ ንግድ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ሕዝብ ገበያ ያለበት ማኅበረሰብ ማቋቋም ችለዋል፡፡ እኛስ መቼ ነው የምንገባው? መሠረተ ልማታችን ምን ይመስላል? የፋይናንስ ጉዳያችንስ እንዴት ይታያል? ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ዕቃዎችን ለማጓጓዝ ያለው የትራንስፖርት፣ የጉምሩክ፣ የኬላ፣ እንዲሁም የደኅንነት ጉዳዎች በሙሉ የንግድ ምክር ቤቶች ሥራዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ እነዚህን ለመሥራት ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ ይህ ዕውቀት ደግሞ ዛሬ በንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ አይታይም፡፡ 

  ሪፖርተር፡- እንዲህ ባሉት ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ የእርስ በርስ አለመግባባቶችና መካረሮች በንግድ ምክር ቤቶች አካባቢ እየታዩ ነው፡፡ በእነዚህ ተቋማት አመራሮች አካባቢ ሽኩቻዎች አሉ፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ከብሔራዊው ምክር ቤት ጋር ተስማምቶ የመሥራት፣ የክልል ምክር ቤቶችም ከብሔራዊው ምክር ቤት ጋር አይወክለንም ይወክለናል የሚል እሰጥ አገባ ውስጥ እየገቡ ይታያሉ፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ወዴት እየወሰዳቸው ነው?

  አቶ ክቡር ገና፡- ንግድ ምክር ቤቱ እንዳልኩት ከነጋዴዎች እጅ እየወጣ ይመስለኛል፡፡ በተወሰኑ ንግድ ምክር ቤቶች አካባቢ ያሉት አመራሮች ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ የንግድ ምክር ቤት ፍቅርም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በውይይት ነገሮችን ማሻሻል እንችላለን ብለው የሚያምኑም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአብዛኛው ግን የግለሰቦች ችግር መፍቻ ሆኗል፡፡ መንግሥት በአንድ በኩል እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ውስጥ ገብቶ ጫና ለማምጣት አለመፈለጉ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን በርካታ የማስተካከያ ዘዴዎች አሉት፡፡ በእነዚህ ዘዴዎች ተጠቅሞ እውነተኛ ንግድ ላይ የሚሳተፉትን ችግራቸውን ለማዳመጥ፣ለችግራቸውም መፍትሔ ለመስጠት መንገድ ካመቻቸ ብዙ ሰው ወደዚህ ቦታ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- በምክር ቤቶች መካከል ያለው አለመግባባት እየተባባሰ መጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና የሌሎቹ ንግድ ምክር ቤቶች ግንኙነት እየሻከረ ይመስላል፡፡ ይህንን አለመግባባት ሊፈታ የሚችለው መፍትሔ ምንድነው? መንግሥትስ እንዴት ይፈታዋል?

  አቶ ክቡር ገና፡- እኔ የሚመስለኝ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የበላይ ሆኖ የአዲስ አበባ፣ የሐዋሳ፣ የድሬዳዋና የሌላውም ንግድ ምክር ቤቶች የበታች ሆነው የሚታዩበት ሥዕል ፈጽሞ የተሳሳተና ተቀባይነትም ሊኖረው የማይገባ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የተቋቋመው የአዲስ አበባን ችግር ለመፍታት ነው፡፡ የድሬዳዋው ወይም የሌላውም እንደዚሁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ደግሞ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች ላይ ማተኮር አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ምን ላይ ነው? የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ሊያድግ የቻለው ምን የተለየ ነገር ቢያገኝ ነው? ለምንድነው ሴቶች እዚህ ዘርፍ ውስጥ የማይገቡት? ፋይናንስ አንድ ቦታ ላይ ብቻ አተኩሮ የሚሔደው ለምንድነው? የሚሉ አጠቃላይ የአገሪቱ ፖሊሲዎች ላይ የሚያጠና ተቋም ቲንክ ታንክ መሆን ሲገባው፣ ጭቅጭቁ ግን አንተ እኔን አልሰማኸኝም፣ አንተ እኔን አታዘኝም የሚሉ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ሥራቸው ግን በጣም የተለያየ ሆኖ ሳለ ትኩረታቸው ግን ድርጅታዊ አወቃቀር ላይ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ከሌሎቹ ጋር ያለው የሥራ ግንኙነት ይህም ማለት ከሥልጣንና ከኃላፊነት ወሰናቸው ውጪ ሆኖ በሚያገናኟቸው መስኮች ላይ ብቻ ማተኮር ይገባው ነበር፡፡ በየዓመቱ የኢትዮጵያ ስታትስቲካዊ መረጃዎችን እያወጣ የቢዝነስ አቅጣጫ ምን ይመስላል ብሎ በማዘጋጀት እነዚያ ላይ መነጋገር መቻል ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ግን ይህንን መሥራት አይፈልግም፡፡ ይልቁንም ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት ይፈልጋል፡፡ ይህንን ለአዲስ አበባና ለሌሎቹ መተው ይችላል፡፡ የሚጠብቁት ትልልቅ ኃላፊነቶች ስላሉ በእነዚህ ላይ ማተኮሩ የሚሻለው ይመስለኛል፡፡

  ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከሆነ የወደፊት ተስፋቸው ምንድን ነው?

  አቶ ክቡር ገና፡- እኛ አገር ያለው ችግር በብዙ ሥራዎች ላይ የመንግሥትን እጅ መጠበቅ ነው፡፡ መንግሥት ገብቶ እንዲያስተካክልና ነገሮችን እንዲለውጥ ነው የሚፈለገው፡፡ ሰውም የሚደሰተው በዚያ ዓይነት አቅጣጫ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ መንግሥትም ቢሆን ለእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ መፍትሔ ላይኖረው ይችላል፡፡ ሥራውም ስላልሆነ እዚያ ውስጥ ገብቶ ሌላ ችግር መፍጠር ላይፈልግ ይችላል፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡ ካመነበት፣ መንግሥትም ለችግሩ መፍቻነት በእናንተ ድርጅቶች በኩል ብቻ ጉዳዩ ሲመጣ ነው የማዳምጣችሁ ካለ፣ ሊገናኛቸው የሚችልባቸው ብዙ መንገዶች ይኖራሉ፡፡

  ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት እንዲሁ በንግድ ምክር ቤቶች ጉዳይ ላይ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ሲገልጹ፣ እነዚህ ተቋማት በዚህ ዓይነት አካሄዳቸው ወደፊት ተስፋ አይኖራቸውም የሚል ሐሳብ አንስተዋል፡፡ አሁንም በዚህ እንደፀኑ ነው?

  አቶ ክቡር ገና፡- ለውጥ ካላመጡ፣ ዕድገት ካላመጡ፣ መሻሻል ካላመጡ የሉም፡፡ አሁንም እኮ የሉም፡፡ እኔ አሉ ብዬ አልናገርም፡፡ የሚጫወቱትን ሚና ብንመለከት ለስሙ ካልሆነ በቀር መንግሥትም ቢሆን ከእነሱ የምጠብቀው ነገር አለ እስቲ እነሱን ላማክር ብሎ የሚሄድበትን ወቅት አላይም፡፡ አንዳንዴ ግድ ይሆንና የፖለቲካው ሁኔታም የሚያስገድድ ይሆንና መንግሥት የንግድ ምክር ቤቱን ሐሳብ መስማት ሊፈልግ ይችላል፡፡ አሁን ባሉት አመራሮች ግን የንግድ ምክር ቤቱ ሐሳብ በመንግሥት እንደማይታይ እገምታለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ይህንን ያህል ስለአገር ውስጥ ንግድ ምክር ቤቶች ካልን ስለፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤትና ኢንዱስትሪ እንምጣ፡፡ እርስዎ ሲመሠረትም ጀምሮ ሚና ነበረዎት፡፡ አሁንም በኃላፊነት ይሳተፋሉ፡፡ የዚህ ተቋም ዋና ዓላማ ምንድነው? ምን ለማከናወን የተቋቋመ ነው?

  አቶ ክቡር ገና፡- ይህ ድርጅት ሲቋቋም እኔ ከደጋፊዎቹ መካከል አልነበርኩም፡፡ በእኔ በኩል የነበረው ክርክር የድርጅቱ አስፈላጊነት ወይም አላስፈላጊነት ሳይሆን፣ ድርጅቱ ሥራውን ለመሥራት የሚችልበት በቂ አቅም የለንም የሚል አቋም ስለነበረኝ ነው፡፡  በአፍሪካ ደረጃ ድርጅት ስትመሠርት የተወሰነ የመንቀሳቀሻ አቅም ሊኖረው ይገባል፡፡ በመንግሥታት ደረጃ የአፍሪካ ኅብረትን እንኳ ብናይ ብዙዎቹ አገሮች መዋጮ አይከፍሉም፡፡ ስለዚህ በእኔ አስተያየት ይህ ተቋም በሌሎች ድርጅቶችና መንግሥታት የሚመራ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ እንደ ንግድ ምክር ቤት ያሉ ተቋማትን በአፍሪካ ደረጃ ስንመለከትም ተመሳሳይ አዝማሚያ ስለሚታይ ይህ ነገር የምንችለው አይደለም የሚል ነበር የእኔ ክርክር፡፡ እውነትም አልነበረም፡፡ የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት ሁኔታ የተለየ ነገር የለውም፡፡ የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤትን ያቋቋሙት የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ስለሆኑና አብዛኞቹም ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ያልተናነሰ፣ እንዲያውም የባሰ ችግር ያለባቸው ስለሆኑ ይህንን ድርጅት በጥሩ ሁኔታ ሊያንቀሳቅሱት አይችሉም፡፡ ለዚህ ተቋም እኔ በነፃ ነው የምሠራው፡፡ ሥራው ግን በነፃ የሚሠራ አይደለም፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ብዙ ይጠበቅብናል፡፡ መለወጥ ከመፈለግን ከገንዘብ ውጪ በበጎ ፈቃድ፣ በራስ አነሳሽነትና ሌሎች የምናውቃቸውን ሰዎች በማምጣት መንቀሳቀስ መቻል አለብን፡፡ አለበለዚያ የትም አንደርስም፡፡ 

  ሪፖርተር፡- የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ከየአገሮቹ ንግድ ምክር ቤቶች ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል? አባላቱስ እነ ማንና ስንት ናቸው?

  አቶ ክቡር ገና፡- ንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ምክር ቤቶች ጉዳይ ላይ ብቻ የሚነጋገር ሳይሆን የአፍሪካ የቢዝነስ ጉዳይ ላይ የሚነጋገር ነው፡፡ የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት የበላይ ሆኖ በሥሩ የየአገሮቹ ንግድ ምክር ቤቶች የሚገናኙበት ዓይነት አይደለም፡፡ የበታችና የበላይነት ግንኙነት የለውም፡፡ በአጠቃላይ እንደ አኅጉር አቀፍ የነፃ ገበያ ስምምነቶች ላይ፣ ወይም በቀጣና ደረጃ የኢኮኖሚ ኮሚሽኖች የሚያደርጉት የሥራ እንቅስቃሴ ወይም አኅጉራዊ የንግድ ኅብረተሰቡን ጥቅም የሚነኩ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡ አባላቱ ንግድ ምክር ቤቶች ብቻም ሳይሆኑ ሌሎች ማኅበራትና የግል ድርጅቶችም ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጋር በመወያት የአሠራርና የተለያዩ ጥናቶችን በመሥራት ለአፍሪካ ኅብረት ያቀርባል፡፡ ጠንካራ የንግድ ምክር ቤቶች ቢኖሩ የበለጠ ጠንካራ እንሆናለን፡፡ ነገር ግን ያለእነሱም መንቀሳቀስ የሚችል ድርጅት ነው፡፡ የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤትን ከተቀላቀልኩ አራት ዓመት ሆኖኛል፡፡ በአራት ዓመት ውስጥ ቀስ በቀስ የአፍሪካ ንግድ ኅብረተሰብ ድምፅ እየሆነ ነው የምንልበትን ምልክት እያየን ነው፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የቅርርብ ወይም የትብብር ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ ከበርካታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ግን እያደገ ያለ ድርጅት እንደመሆኑ ገና ብዙ መጓዝ ይኖርበታል፡፡  

  ሪፖርተር፡- በኢንቨስትመንትና በንግድ መስክ ላይ ያተኮረ የግልግል ተቋም እንዲቋቋም እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ስለዚህ ቢያብራሩልን?

  አቶ ክቡር ገና፡- የግልግል ተቋሙ በአፍሪካ ደረጃ ሳይሆን በኢትዮጵያ የግልግል ተቋምነት የተቋቋመው የንግድ ምክር ቤት የቦርድ ፕሬዚዳንት በነበርኩበት ወቅት ነው፡፡ የተቋቋመበት ዓላማም የንግድ ኅብረተሰቡ በተቻለ መጠን መፍትሔ ማግኘት ያለበት በአጭር ጊዜ ውስጥና ብዙ የገንዘብ ወጪ በማይጠይቅ አግባብ ስለሆነ ያንን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል በማለት ነው፡፡ የግልግል ተቋሙን ለማቋቋም የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ውሳኔዎችን መንግሥት ደግፏቸው ወደ ሥራ የሚገቡበት የማስገገድ ኃይል እንዲኖራቸው ያስፈልግ ስለነበር ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ይህ የሚነግሩን ተቋም ከአዲስ አበባ የግልግል ተቋም የተለየ ነው?

  አቶ ክቡር ገና፡- አይደለም፡፡ ራሱ ይኼው ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም ከተመሠረተ 20 ዓመታት ሊሆነው ነው፡፡ ምን ያህል የንግድ ኅብረተሰቡን አርክቷል የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ለምሳሌ የኮንስትራክሽን ዘርፉን እንውሰድ፡፡ የዚህ መስክ አለመግባባቶች በአብዛኛው እንዲፈቱ የሚፈለገው በግልግል ነው፡፡ ነገር ግን ገላጋይ ተብለው የሚጠሩ ኃላፊዎች የሚጠይቁት ገንዘብ ከመጠን በላይ የናረ ነው፡፡ መንግሥት በነፃ ነው እንዲህ ያሉ ነገሮችን አይቶልህ መፍትሔ የሚሰጥህ፡፡ ችግሩ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ገንዘብ ጥያቄ አይደለም፡፡ ወደ ግልግሉ ስትመጣ ግን የጊዜውን ጉዳይ ያሳንሰዋል፡፡ ገንዘቡም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ ማደግ ሲኖርበት ይህ ባለመሆኑ ብዙ እንቅፋት አለበት፡፡ በኮንስትራክሽን ዕድገት ላይ የገላጋዮች ከሕግ ውጪ መሥራት ሁለቱን ባለጉዳዮች ከማቀራረብ ይልቅ የሚያራርቅ ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ሙከራዎች አሉ፡፡ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ሁለቱ ተከራካሪዎች የሚስማሙበትን ሕግ ይመርጣሉ፡፡ በመረጡት አገር ሕግ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው መከራከር ይችላሉ፡፡ በቂ የሰው ኃይል ያለው፣ በቂ ተቋማዊ አቅም ያለው ተቋም ለመመሥረት በአፍሪካ ደረጃ እየተሞከረ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- መንግሥት በአኅጉራዊው ነፃ የንግድ ስምምነት ውስጥ ለመሳተፍና የአገሪቱን ድንበሮች ለመክፈት እያቅማማና ውድድሩ እንደሚያስፈራው እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

  አቶ ክቡር ገና፡- የኢትዮጵያ መንግሥት የአኅጉራዊው የነፃ ገበያ ስምምነት ያስፈልጋል ብሎ ፈርሟል፡፡ የቀጣና ነክ ስምምነቶችንም ፈርሟል፡፡ ስለዚህ ያምንበታል ብዬ ነው ሐሳቤን ለመስጠት የምነሳው፡፡ በመሠረቱ ይህ ጥያቄ መምጣት የነበረበት ከመንግሥት ሳይሆን ከግሉ ዘርፍ ነበር፡፡ ከቁጥር አኳያም ባይሆን ከገንዘብ አንፃር የኢትዮጵያ ገበያ ያንሰናል፡፡ ስለዚህ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ንግድ ቀጣና ውስጥ መግባት አለብን ብለው መንግሥትን መገፋፋት መቻል፣ የመንግሥት ጥያቄ እንኳ ቢኖር አብሮ መፍታት መቻል አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍርኃት ግልጽ ነው፡፡ ልንቋቋማቸው የማንችላቸው ዘርፎች ስላሉ እነዚያን ለውድድር ብንከፍት የጀመርናቸው በሙሉ ሊጠፉ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለው፡፡ ነገር ግን ያንን ለማረምና ለማተከካል አሁን ካልተነሳን መቼም አናደርገውም፡፡ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ያህንን ለመሥራት ከንግድ ኅብረተሰቡ ጋር መሥራት ያስፈልጋል፡፡  

  ሪፖርተር፡- ከፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤትም ሆነ ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አኳያ የወደፊቱ ሁኔታ ምን ይመስላል?

  አቶ ክቡር ገና፡- ስለወደፊቱ ጥሩ ስሜት አለኝ፡፡ አንድ ነገር ከተበላሸ በኋላም የሚስተካከልበት መንገድ አለ፡፡ የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤትን ስናነሳ አራት ዓመት የቆየሁት ስላመንኩበት ነው፡፡ አቅጣጫው ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ በርካታ ደጋፊዎች አሉን፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለት መለስተኛ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ገንዘብ አግኘተናል፡፡ ተስፋ አለን፡፡ ከተስፋ አልፈን ዋናውን ሥራ ለመሥራት እየጣርን ስለሆነ የሌሎችን ድጋፍ እናገኛለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በተለይ ንግድ አካባቢ ያለው ሁኔታ አስፈሪ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አስፈሪ ነው የምለውም የመንግሥት ኢንቨስትመንት በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ባለመኖሩ ነው፡፡ መንግሥት አሁን ካለው የበለጠ ተሳትፎ ጠጋ ብሎ መፍትሔ መፈለግና መፍትሔዎቹም ከመስመር እንዳይወጡ ማድረግ አለበት፡፡ አልተሞከረም አልልም፡፡ ነገር ግን በበቂ መጠን አልተሞከረም፡፡ 

  ሪፖርተር፡- በመጨረሻም ስለኢኒሼቲቭ አፍሪካ ጥቂት እናንሳ፡፡ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

  አቶ ክቡር ገና፡- ስንጀምር በመልካም አስተዳደርና በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ዙሪያ ለመሥራት ነበር፡፡ አሁንም በአስተሳሰብ ደረጃ ከዚያ የተለየ ነገር የለኝም፡፡ የአንድ አገር ዕድገት በኢኮኖሚው ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ የፖቲካውም ዕድገት አብሮ መምጣት መቻል አለበት በማለት ነው ወደዚያ ያተኮርነው፡፡ ይሁንና የ2009 አዲሱ ዓመት ሲመጣ የገንዘብ አቅማችን ደካማና ከአገር ውስጥም ገንዘብ የማግኘት ዕድሉ በጣም ጠባብ ስለነበረ፣ ከመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ከሚለው ወጥተን ትምህርት ላይ አተኩረናል፡፡ በሒሳብና በሳይንስ ትምህርቶችን የበለጠ ለማሳደግ ነው የተነሳነው፡፡ የመንግሥት አቅጣጫ ወደዚያ ነው፣ የዓለም ትኩረትም እንዲሁ፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ ተማሪዎችና አስተማሪዎች በሚሳዝን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት፡፡ ብዙ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች