Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሰው ፊት ያሳየ ሙያ

የሰው ፊት ያሳየ ሙያ

ቀን:

ሙዚቃ አቀናባሪ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ ሙሉጌታ አባተ ለባህላዊ እንዲሁም ለዘመናዊ የሙዚቃ ዘርፍ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ሙዚቀኞች መሀከል ይጠቀሳል፡፡ በመልካሙ ተበጀ፣ ታምራት ሞላ፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ማንአልሞሽ ዲቦ፣ ፍቅረአዲስ ነቃጥበብ፣ ታደሰ ዓለሙ፣ አምሳል ምትኬ፣ ጎሳዬ ተስፋዬና በሌሎችም ድምጻውያን አልበሞች ተሳትፏል፡፡ ይህ ሙዚቀኛ በጠና ታሞ ኮሪያ ሆስፒታል እንደሚገኝ የተሰማው በቅርቡ ነበር፡፡ ሙዚቀኛው ለሕክምና የተጠየቀው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ቤተሰቡ ስለተቸገሩ ሕዝብና የሙያ አጋሮቹ እንዲረባረቡም ጥሪ ቀርቧል፡፡

የሙዚቀኛውን ሕይወት ለመታደግ እንቅስቃሴ ያደረጉት የቅርብ የሙያ አጋሮቹና የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አንዳች የጤና እክል ሲገጥማቸው ለዕርዳታ ፊታቸውን ወደ ሕዝብ የሚያዞሩ ሙዚቀኞች እንዲሁም ሌሎችም የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሲታመሙ ብቻ ሳይሆን ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ተቸግረው በሕዝብና በተለያዩ ተቋሞች ዕርዳታ ሲደረግላቸው መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡

በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች አንድ ባለሙያ የጤና እክል ሲገጥመው አልያም ሲቸገር ብቻ የመደጎም ነገር ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ጉዳዩን የሚመለከቱት አንድም የኪነጥበብ ባለሙያዎች ስለምን ዘወትር ይለመንላቸዋል ከሚል ሐሳብ በመነሳት ነው፡፡ በሌላ በኩል ዘርፉ ባለሙያዎቹ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በአግባቡ የሚያስተዳድሩበት ከመሆን ምን አገደው? የሚል ጥያቄ ይሰነዘራል፡፡ ባለፈው ሳምንት መባቻ በርካታ አንጋፋና ወጣት ሙዚቀኞች የተሰባሰቡበት አንድ መርሐ ግብር ነበር፡፡ ዝግጅቱ የተሰናዳው አዲስ የሙዚቃ መገበያያ ሥርዓት ለማስተዋወቅ ሲሆን፣ ሥርዓቱ በሙዚቃው ያሉ ባለሙያዎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዝግጅቱ አዲሱን የመገበያያ ሥርዓት በመደገፍ ደስታቸውን የገለጹ ባለሙያዎች፣ የሙዚቀኞች ልመና የሚቀርበት ቀን ሩቅ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ መገበያያው ድምጻውያን፣ ግጥምና ዜማ ደራሲዎች፣ አቀናባሪዎችና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች ከአልበም ሽያጭ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ነው፡፡ በዕለቱ ተገኝተው አስተያየታቸውን ከሰጡ ሙዚቀኞች መሀከል ኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ) ሙዚቀኞች የኮፒራይት መብታቸው ተጠብቆ በሥራቸው ተገቢውን ጥቅም ስለማያገኙ በድህነት ለመኖር መገደዳቸውን ተናግሯል፡፡ ‹‹የሙዚቃ ሙያ መተዳደሪያ መሆን አልቻለም፡፡ አርቲስቶች በድንገት ሲታመሙ ባለሀብትና ሕዝቡ ይለመናል፤›› ሲል ነበር ሁኔታውን የገለፀው፡፡ በሌሎች አገሮች በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሚተርፉ ሲሆን፣ በኛ አገር ግን ሙያቸው የሰው ፊት እንዲያዩ ያስገደዳቸው ባለሙያዎች ቁጥር ያመዝናል፡፡

ሌላው ሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ፣ ባለሙያዎች በድህነት ተዘፍቀው ሲኖሩ፣ የኪነጥበብ ሥራዎቻቸው ግን በሕዝቡ ተወዳጅነት አግኝተው ዘመናት ይሻገራሉ ይላል፡፡ ለዚህ ችግር የዳረጋቸው ደግሞ በሕጉ መሠረት ከሥራዎቻቸው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ስለማይሆኑ ነው፡፡ በዝግጅቱ የተገኙ ሌሎችም በሙዚቃው ያሉ ስመጥር ባለሙያዎች ሐሳቡን ተጋርተዋል፡፡ ሙዚቀኞቹ ሙሉጌታ አባተ በሚገኝበት ሁኔታ እንዳዘኑና የሌሎች ሙያተኞች እጣ ፈንታም ተመሳሳይ እንዳይሆን ሥጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሙዚቀኞች ሲታመሙ መታከሚያ አጥተው ከመለመናቸውም በላይ ሲሞቱ እንኳን መቅበሪያ ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነበት እንደነበር በሐዘኔታ የተናገሩ ባለሙያዎችም ነበሩ፡፡

ይህ ችግር የሙዚቀኞች ብቻ ሳይሆን የደራስያን፣ ሰዓሊያን፣ የቴአትር ባለሙያዎች እንዲሁም የፊልሙን ዘርፍ የሚነካ ነው፡፡ ሕዝብ በሥራዎቻቸው ለዘመናት የተደሰተባቸው የኪነጥበብ ሰዎች ሲጎሳቆሉ የብዙዎች ልብ ይነካል፡፡ ሥራዎቻቸውን እንደ ማሳያ ይዘው ጎዳና ዳር የሚለምኑ ባለሙያዎች አልያም በመኪና ላይ ፖስተራቸው ተለጥፎ የሚለመንላቸው ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በየዐውደ ዓመቱ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከተለያዩ ተቋሞች የተሰጣቸውን ዕርዳታ ሲቀበሉ የሚያሳዩ መርሐ ግብሮች የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ያጨናንቃሉ፡፡

በእርግጥ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሁም ከዜጎች ኑሮ አንጻር ዕርዳታ የሚያስፈልግባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች አንድ ሰው ለሕክምና የሚጠየቀው ወጪ ከአቅሙ በላይ ሆኖ ለዕርዳታ እጁን ሊዘረጋም ይችላል፡፡ በተለያየ ሙያ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች በስተእርጅና ደጋፊ አጥተው የኅብረተሰቡን ዕርዳታ ሊሹም ይችላሉ፡፡ በነዚህ ሁኔታዎች ታዲያ ‹‹ለሰው መድኃኒቱ ሰው ነው›› እንዲሉ ኅብረተሰቡ እርስ በእርስ ቢረዳዳ ክፋት የለውም፡፡ ጥያቄው የኪነጥበብ ባለሙያዎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ዘለቄታዊ መፍትሔ መስጠት የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው ነው፡፡

ለኪነጥበብ ባለሙያዎች የገንዘብ ወይም የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ችግሮቻቸው በዘለቄታ የሚፈታ መፍትሔ ነውን? ሲሉ የሚጠይቁ አይታጡም፡፡ ባለሙያዎቹን መርዳት ሕዝቡ የሰጣችሁትን ስለማይዘነጋ በችግራችሁ ጊዜ አለኝታ ይሆናችኋል የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ ተግባር ነው ሲሉ ሁኔታውን የሚገልፁም አሉ፡፡ ያነጋገርናቸው የኪነጥበብ ባለሙያዎች በችግር ጊዜ ብቻ ዕርዳታ ከማድረግ ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚበጅባቸው መንገዶች ቢሰፉ መልካም ነው የሚል አስተያየት ይሰነዘራሉ፡፡ የኪነጥበብ ዘርፎች ለባለሙያዎች ቢያንስ ጥሩ የሚባል ኑሮ የሚያስገኙ በማድረግ ረገድ መሠራት እንዳለበትም ያምናሉ፡፡

የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ፣ የሙያ ማኅበራት የኪነጥበብ ባለሙያዎች የጤና እክል ሲገጥማቸው ጥላ ከለላ ለማበጀት ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን ያወሳሉ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የደራስያን፣ ሙዚቀኞች፣ ሠዓሊያን፣ ፊልም ሥራዎችና ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበራት ከጥቁር አንበሳ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡ ስምምነቱ ባለሙያዎቹ የነጻ ሕክምና የሚያገኙበት አግባብ ቢፈጠርም፣ ባለሙያዎች በስፋት እየተጠቀሙበት ነው ለማለት አይቻልም ይላሉ ፕሬዚዳንቱ፡፡

በዋነኛነት የጠቀሱት ችግር ባለሙያዎች ሕክምና ለማግኘት የሪፈራል ወረቀት እንዲያመጡ መጠየቃቸው ነው፡፡ ‹‹ባለሙያዎቹ በቀጥታ ሄደው መታከምን ይመርጣሉ፡፡ ሥርዓቱ የተዘረጋው ባለሙያዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ቢሆንም በዚህ ሁኔታ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ባለሙያዎች ተመካክረውና መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ አንዳች ፈንድ ሊቋቋም ይገባል፤›› ይላሉ፡፡

አሁን የሚታየው የባለሙያዎችን ክብር በሚነካ መልኩ ሲታመሙ ወይም ሲቸገሩ የመለመን አካሄድ ተገቢ አለመሆኑን ያምናሉ፡፡ በተለይም ቀደምት ባለሙያዎች ያገኙት የነበረው ክፍያ አነስተኛ ከመሆኑ አንጻር የችግሩ ዋነኛ ተጠቂ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ከሞላ ጎደል በዚህ ዘመን ያሉ ባለሙያዎች የተሻለ ተከፋይ ስለሆኑ በመጠኑም ቢሆን የችግሩ ስፋት ሊቀንስ ይችላል፡፡ ‹‹ዘመናቸውን በሙሉ ከነጻ ባልተናነሰ መልኩ ያገለገሉ ባለሙያዎች ዕድሜያቸው ሲገፋ ይደጎማሉ፡፡ ይህ ተስተካሎ የጥበቡ ሰዎች ለራሳቸው የተሻለ መፍትሔ ማምጣት አለባቸው፤›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ጠንካራና አቅም ያለው ፈንድ ማቋቋም ውጣ ውረዱን እንደሚያቃልልም ያክላሉ፡፡ ባለሙያዎች በሥራቸው ከሚያገኙት ገቢ ጥቂቱን እየቆጠቡ በሚያስፈልገው ጊዜ የሚገለገሉበት መንገድ መፍጠር ሌላ አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡

የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ እንደሚለው፣ ጥበባዊ ሥራዎች ባለሙያዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉበትን አሠራር መፍጠር ቀዳሚው ዕርምጃ መሆን አለበት፡፡ ‹‹አሁን ያለው ሁኔታ ኪነጥበብ እንደ መተዳደሪያ አስተማማኝ አይደለም ከሚል ድምዳሜ ያደርሳል፡፡ የኪነጥበብ ባለሙያ ማለት ሁሌ የሚቸገርና ተረጂ ነው የሚል የተሳሳተ ገፅታም እየተላበሰ ነው፤›› ይላል፡፡ አንጋፋ ባለሙያዎች ዘወትር በድጎማ ሲኖሩ ማየት፣ ወጣት ባለሙያዎች ለሙያው የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል ብሎም ያምናል፡፡ ወደ ሙያው የመግባት ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች ሙያውን ከተቀላቀሉ ችግረኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሊገምቱ ይችላሉ፡፡

ባለሙያው እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጠው ሁሉም የኪነጥበብ ዘርፎች ባለሙያዎች ተገቢ ጥቅም የሚያገኙባቸው መሆን እንዳለባቸው ነው፡፡ እንደምሳሌ የሙዚቃና ፊልሙን ዘርፍ መውሰድ ይቻላል፡፡ ሙዚቀኞች የኮፒራይት መብታቸው ተጠብቆላቸው የሮያሊቲ ክፍያ ቢያገኙ፣ እንዲሁም ፊልሞች በተገቢው መንገድ ለተመልካች ቀርበው ባለሙያዎቹ ቢከፈላቸው ችግሩን ማቃለል ይቻላል፡፡ አሁን ያለው አካሄድ ግን ሙዚቃዎችና ፊልሞች በፍላሽና በሚሞሪ በሕገ ወጥ መንገድ የሚቸበቸቡበት ነው፡፡ ደራስያንም ከልፋታቸው ጋር የሚመጣጠን ገቢ ያገኛሉ  ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡

ያሬድ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሲቸገሩ መረዳት የለባቸውም የሚል አቋም የለውም፡፡ ያለው አማራጭ ከሕዝብ ወይም ከተቋሞች ገንዘብ አሰባስቦ መርዳት ከሆነ፣ ከምንም ነገር በፊት የሰው ሕይወት ስለሚቀድም ይደጎሙ ይላል፡፡ በሕዝብ ርብርብ ሕይወታቸው ከሞት አፋፍ የዳኑ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መኖራቸው በተቃራኒው ዕርዳታ በማጣት ያለፉም እንዳሉ መዘንጋት እንደሌለበት ይገልጻል፡፡ ለመተባበርና መደጋገፍ እውቅና ባይነፍግም፣ ዘለቄታዊ ለውጥ ማምጣት ላይ ማተኮር የተሻለ ነው ይላል፡፡ ባለሙያዎች የመደጎም ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ራሳቸውን የሚችሉባቸው አማራጮችን መከተልን ይደግፋል፡፡

ባለሙያዎች እርስ በርስ የሚደጋገፉበት መንገድ መኖር እንዳለበት ያምናል፡፡ ባለሙያዎች በዕድሜ ሲገፉ ከሙያው የማስወጣት ነገር አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለውም ይናገራል፡፡ ለብዙ ዓመታት መሥራት የሚችሉ ባለሙያዎች ያለጊዜያቸው ከዘርፉ ሲገለሉ ይታያል፡፡ ለአዳዲስ ባለሙያዎች እድል መስጠት ተገቢ ቢሆንም፣ ቀደምት ባለሙያዎችን ከጨዋታ ውጪ በሚያደርግ መንገድ መሆን የለበትም፡፡ ‹‹ኪነጥበብ እስከ ሞት ድረስ ይሠራል፡፡ ባለሙያዎቹ አቅም እስካላቸው ድረስ እየሠሩ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ እንዲሁ ዕርዳታ ማድረጉ ግን ሙያውን የሚያስንቅም ነው፤›› ይላል፡፡ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ገመና በአደባባይ በማውጣት ክብረ ነክ በሆነ መልክ ዕርዳታ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነም ይገልጻል፡፡

በያሬድ ገለጻ፣ የሙያ ማኅበራት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ካላቸው ሕጋዊ ፈቃድ አንጻር ለባለሙያዎች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል አይደለም፡፡ ስለዚህም የተራድኦ ድርጅት ተቋቁሞ እስከወዲያኛው ችግሩን መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ግን ሙያውን የተረጂዎች በሚያስመስል መንገድ ሳይሆን፣ አሁን ያለውን አንገብጋቢ ችግር ከመቅረፍ አንጻር መሆን አለበት፡፡ የሙያተኞችን መብት የሚያስከብሩ ሕግጋትን መተግበርና ሲጣሱም ተገቢው ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበትም በአጽንኦት ይናገራል፡፡

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዘዳንት ዳዊት ይፍሩ ችግሩን ለመቅረፍ በ2006 ዓ.ም.  የኪነጥበብ ባለሙያዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ተቋቁሞ፣ ገንዘብ በማሰባሰብ የተቸገሩ ሙያተኞችን ለመርዳት እንደተሞከረ ያስታውሳሉ፡፡ ባገር ውስጥና ውጪ ካሉ ባለሙያዎች ገንዘብ ለማሰባሰብም ተሞክሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ በታቀደው መጠን ሊንቀሳቀስ አልቻለም፡፡ ‹‹ድርጅቱ እየሠራ ባለመሆኑ አምና የማኅበራት ኤጀንሲ ፈቃዱን ነጠቀን፡፡ ኤጀንሲውን ተለማምጠን ፈቃዱ ቢመለስልንም ያሉን አባላት ውስን ናቸው፡፡ የገንዘብ አቅምም የለንም፤›› ይላሉ፡፡

ባለሙያዎች የሰው እጅ ከሚያዩ በሚል የሚጀመሩ እንቅስቃሴዎች በኪነጥበቡ ባለሙያዎች እንዳልተደገፉ ይናገራሉ፡፡ ሙያተኞችን በሥራዎቻቸው ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ በማድረግ ችግሩ እንዳይከሰት በማድረግ ሐሳብ ከሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ጋር ይስማሙበታል፡፡ ሆኖም አሁን የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ካለው ችግር አንጻር መሆን እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ በቅድሚያ የኪነጥበብ ባለሙያዎች አንዳቸው ሌላቸውን መደገፍ አለባቸው ይላሉ፡፡ እክል ሲገጥም የሚረዱ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ዘላቂ መፍትሔን ያማከሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡

አንዳንዴ ዕርዳታ የሚያደርጉ ተቋሞች የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ሽፋን በመርዳት ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ‹‹ለሞት አንድ ሐሙስ የቀረው ባለሙያ ገንዘብ ተሰባስቦለት ሳይጠቀምበት ያልፋል፡፡ የሚረዱት ባለሙያ ያለውን እውቅና ከግምት በማስገባት ያን ሰው በመርዳታቸው ታዋቂ ለመሆን የሚሞክሩም አሉ፤›› ይላሉ ሙዚቀኛው ዳዊት፡፡ እስከ አሁን ኪነጥበብን በማክበር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚንቀሳቀስ አካል እንዳላዩም ያስረዳሉ፡፡ ወጣት ባለሙያዎች ይህን ሁኔታ ለመቀየር ኃላፊነት እንዳለባቸውም ይጠቁማሉ፡፡

‹‹ባለሙያዎችና ቤተሰቦቻቸው በሥራዎቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደ የሕይወት ዘመን ሲደመር 50 ዓመት ያሉ ድንጋጌዎች መከበር አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ሙያው ክብር አጥቶ ሙያተኛውም ተንቆ ይኖራል፤›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ባለሙያዎችና መንግሥትም የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው የኪነጥበብ ወዳጇ ስመኝ አምሳሉ ትገልጻለች፡፡ በሌሎች አገሮች ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ሕይወት ዝቅተኛ መሆኑ ያሳዝናል ትላለች፡፡ የኪነጥበብ ሥራዎች ከአገር ውጪ ያላቸውን ተደራሽነት በማስፋት ባለሙያዎቹ ተጠቃሚነታቸውን ቢያሳድጉ መልካም እንደሆነ ታምናለች፡፡

በእሷ አስተያየት፣ ባለሙያዎች የተለያዩ ዘመን አመጣሽ መንገዶችን በመጠቀም ሥራዎቻቸውን ለገበያ ቢያቀርቡም ይመረጣል፡፡ ባለሙያዎቹ አቅማቸውን ለማጠንከር ሥራዎቻቸው ገበያ ላይ ሲቀርቡ በሕገወጥ መንገድ መሰራጨት እንደሌለባቸውም ትገልጻለች፡፡ ‹‹ባለሙያዎቹ ለለውጥ ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ሁሌ ተረጂ የማድረግ ነገርም መቀየር አለበት፤›› ትላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...